ኢትዮጵያውያንና ዓባይ በዚህ ዘመን

‹እኛ እንብላ እናንተ እለቁ?››

በየማነ ናግሽ፤

የዓባይ ተፋሰስ አባል አገሮች የዓባይን ውኃ በፍትሐዊነትና በጋራ ትብብር ለመጠቀም የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሒደቱ ከተጀመረ ወደ አሥር ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ የተለያዩ የስምምነት ሙከራዎችም ተደርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአሥሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት አገሮች የተፈረመው ስምምነት ለጉዳዩ የመጨረሻ እልባት ያስገኛል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፣ በላይኛውና በታችኛው የተፋሰሱ አባል አገሮች መካከል አወዛጋቢነቱ አልተቋጨም፡፡ ስምምነቱን እንደማይፈርሙ በይፋ ያስታወቁት ግብፅና ሱዳንም ጉዳዩን ለማስተጓጎል እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ይነገራል፡፡

የደቡብ ሱዳን አዲስ አገር ሆኖ የመፈጠር ሒደትና እስካሁን አቋማቸው ግልጽ ባልሆነው በብሩንዲና በኮንጎ ምን እየተደረገ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት የበለጠ ክትትል እንዲያደርግ እየተጠየቀ ሲሆን፣ የዓባይን ጉዳይ የአገር ውስጥ ፖለቲካ ትኩረትን ለማስቀየስ ሥራ ላይ እየዋለ መሆኑን የሚጠቁሙም አሉ፡፡

ህልውናቸው ሙሉ ለሙሉ በዓባይ ውኃ ላይ የተመሠረተው ግብፃውያን የሚሰጡትን ሥፍራ ያን ያህል ባይሆንም፣ ኢትዮጵያውያንም ለዓባይ ውኃ ያላቸው ፍቅር፣ አድናቆት፣ ቁጭትና ንዴት በባህላዊ ዘፈኖቻቸው ሳይቀር ይገልጻሉ፡፡ አሁን አሁን ግን ጉዳዩ ቁጭትም ብቻ ሳይሆን፣ የደበዘዘው የአገሪቱ የውስጥ ፖለቲካን እየተካ መምጣቱን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ጥናቶች እየቀረቡ ውይይቶችም ሲደረጉ ይስተዋላል፡፡

ከእነዚህ መካከል ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ፋኩልቲ (FBE) አዳራሽ የተካሄደው ውይይት ይገኝበታል፡፡ በዚህ አራት ጥናታዊ ጽሑፎች ለውይይት መነሻ ይሆኑ ዘንድ የቀረቡበት መድረክ፣ በአብዛኛው በተፋሰሱ አባል አገሮች እየተካሄደ ያለው የሰላም ስምምነት ይዘትና የቀድሞ ‹‹ውሎች›› እንቅፋትነት፣ በተፋሰሱ ዙርያ ስለሚካሄዱ አንዳንድ ፕሮጀክቶች፣ ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር እያደረገችው ስላለው እንቅስቃሴና የፖሊሲ አማራጮችን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል ‹‹የዓባይ ውኃ ሙግት›› በሚል መጽሐፋቸው የሚታወቁት አምባሳደር ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ‹‹The Legal Challenges of the Nile . . . ›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ቀደም ሲል በቅኝ ገዢዎች ወቅት የተረፈሙ፣ በተለይ ደግሞ የ1929 እና 1959 ስምምነቶች በአሁኑ ወቅት በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ሕጋዊና ፍትሐዊ ማዕቀፍ ላይ እንዳይደረስ ምን ያህል እንቅፋት እንደሆኑ አሳይተዋል፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸውና ግብፅንና ሱዳንን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሕገወጥ ስምምነቶች፣ አሁን በመፈረም ላይ ያለውን ስምምነት በመሳሰሉ ሌሎች አሳታፊ ስምምነቶች ካልተተኩ አስቸጋሪ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በቅኝ ገዢዎች የተደረጉ ስምምነቶች በመሆናቸውም ምንም ዓይነት ሕጋዊ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግብፅና ሱዳን አንፈርምም ያሉትን ስምምነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እነዚህ ሕጎች ምንም ዓይነት ዕውቅና የማይሰጡ መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡ ናይል በተለይ ለግብፆች የብሔራዊ ደኅንነት ዋና አካል መሆኑን ብቻ ሳይሆን በሕይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎችዋና በመሪዎቿ አማካይነት በተደጋጋሚ ከሚናገሩት መረዳት ይቻላል የሚሉት አምባሳደር ኃይሉ፣ ለኢትዮጵያ ደግሞ ዓባይ የለውጥና ድህነትን የማጥፋት ትልቁ ተስፋ መሆኑን ያስረግጣሉ፡፡ ‹‹ናይል በአገራችን ውስጥ ካሉት ያልተጠቀምንባቸው ተፈጥሮአዊ ፀጋዎች ትልቁ ነው፤›› በማለት፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል አቶ ዘነበ ከበደ በበኩላቸው፣ ግብፅ ከዋና የውኃው ሕጋዊ ባለቤትነት ጥያቄ አላስፈላጊ ወደሆኑት ‹‹እንቶ ፈንቶ›› ያሉት ጉዳይ መግባቷን አስረድተው፣ የተፋሰስ አባል አገሮቹንም በተለያዩ ወቅቶች ለመደለል መሞከሯን አክለዋል፡፡ አቶ ዘነበ እንደሚሉት፣ ግብፅ የምትጠቅሳቸው ‹‹ተፈጥሮዊና ታሪካዊ›› ወዘተ የሚሉት የመጠቀም መብቶች በዓለም አቀፍ የውኃ ሕጎች የሚደገፉ አይደሉም፡፡

አቶ ዘነበ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የሆነ የውኃ ሕግ እንዲኖር የምትፈልገው ለሁሉም አገሮች ጥቅም ጭምር መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ ግብፅና ሱዳን አሁን በያዙት አቋም የሚቀጥሉ ከሆነ፣ ‹‹ውኃው በእጃችን መሬቱም የራሳችን›› በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነቱ ተፈረመም አልተፈረመም ውኃውን ከመጠቀም ወደኋላ እንደማትል አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ኢትዮጵያ ውኃውን መጠቀም ያልቻለችው በአንድ በኩል በገንዘብ እጥረት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር እንዳታገኝ በግብፃውያን በተንኮል የሚሠሩ ሥራዎች ምክንያት መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ‹‹እኛ እንብላ እናንተ እለቁ›› የሚለውን የማንንም ትዕዛዝ ለመቀበል ዝግጁ አይደለንም ያሉት ኃላፊው፣ ወደፊት የሚያዋጣን ግን ፍጥጫ ሳይሆን ትብብር ነው ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች ተፋሰስ አባል አገሮች ለመነጠልም ሆነ ለመደበል የተደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡

ግብፃውያን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚፈልጉ መንግሥትን ማነጋገራቸውን አስታውሰው፣ ‹‹ኢንቨስትመንቱ ግን የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፤›› በማለት ዋናው ዓላማ ኢንቨስትመንትን የማካሄድ ዓላማ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹Policy Options and Outlook for Cooperation in the Nile Basin›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ደግሞ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ናቸው፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ በዚሁ ጽሑፋቸው የዓባይ ውኃ በስምምነትና በመነጋገር መጠቀም ካልተቻለ፣ የሚተነውም ውኃ ብዙ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹የግብፅ የውኃ አጠቃቀም በዓለም ኋላቀር የሚባል ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዓባይን ማስጮህ ወይስ. . .?
ጥናቶችን ተከትሎ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከጽሑፍ አቅራቢዎችም ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የመጀመርያው አስተያየት ሰጪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ ወጣቱን በእንደዚህ ዓይነት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማነጋገርና ማማከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር በጠበበት ሁኔታ ውስጥ የማይታሰብ መሆኑን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ተማሪው በማከልም አገሪቱ ችግር ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት የዓባይን ጉዳይ ማስጮህስ ምን ይሉታል? ሲል የጠየቀ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርቡ ዓባይን አስመልክተው ለሮይተርስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ‹‹ግብፅ ኢትዮጵያን ለመውረር ታስባለች፡፡ ከወረረችን ግን . . . ›› በሚል ያቀረቡት ኃይለ ቃል የአገሪቱን ፖለቲካ የማስቀየስ ስትራቴጂ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዓባይ ምክንያት ከግብፅ ጋር መጋጨት አስፈላጊ አይደለም በሚል ሐሳቡን ያቀረበው ይኼው ወጣት፣ ከዓባይ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ወንዞችን ማልማትና ሽንኩርት መትከል እየቻልን ለምን ከግብፆች ጋር አላስፈላጊ እልህ ውስጥ እንገባለን በማለት ሐሳቡን አቅርቧል፡፡

ከዶ/ር ያዕቆብና ከአቶ ዘነበ፣ ‹‹ችግሩ በዲፕሎማሲ ማለቅ ይኖርበታል›› ከሚል ድምዳሜ አንጻር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አይጋጭም ወይ በሚል አስተያየቱን የቀጠለው ይኸው አስተያየት ሰጪ፣ ወጣቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማሳተፍ አግባብ መሆኑን፣ ወደ አላስፈላጊ ንትርክ በመግባት ግን ግጭቱን ‹‹በአንበሳና በጥንቸል›› ይሆናል በማለት መመሰሉ ከብዙዎች የድጋፍ ጭብጨባ ያገኘ ቢሆንም፣ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች መካከል አንዱ ይህንን አስተያየቱን በመቃወም፣ ስለአገሩ ታሪክና ሁኔታ የማይገነዘብ ትውልድ እየተፈጠረ ያለው በትምህርት ፖሊሲው ምክንያት መሆኑን ተችቷል፡፡

ግብፅ ውስጥ ስለዓባይ የሚያጠኑ በርካታ የምርምር ተቋማት መኖራቸውን የጠቆመው ይኼው አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹በኃይልና በጦርነት ከሆነ ከግብፆች ጋር ሁለት ጊዜ እንተዋወቃለን፡፡ እኛ እያልን ያለነው ግን በዴሞክራሲያዊና በፍትሐዊ መንገድ ውኃውን እንዴት እንጠቀም ነው እንጂ፣ ግብፅ ኢትዮጵያን በኃይል የምታሸንፍበት መንገድ አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለአገሩና ለነፃነቱ ወደኋላ የማይል ኃያል ሕዝብ ነው፤›› በማለት ለተሰጠው አስተያየት አጸፋ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ግብፅ ከዲፕሎማሲያዊ ማስጠንቀቂያ አልፋ የኃይል ዕርምጃ ልትወስድ ትችላለች ለሚለው ግን፣ ኢትዮጵያስ ምን ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅታለች? ሌሎችን ከጐኗ በማሰለፍ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላታል? ኤርትራን መነሻ አድርጋ ኢትዮጵያን ብታጠቃስ? የሚሉ ጥያቄዎች በማንሳት አስቀድሞ የተደረጉ ዝግጅቶች ካሉ እንዲብራሩለትም ጠይቋል፡፡

‹‹ሙያ በልብ ነው››
ጥናታዊ ጽሑፉን በዓባይ ላይ እየሠራ የሚገኘው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪ የሆነ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ፣ ቀደም ሲል የተሰጠውን አስተያየት በመቃወም፣ በየቀኑ የኢትዮጵያ ስም በግብፅ ፓርላማ እየተነሳ የሚውሉብን ግብፆች እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን አስጮሁት መባሉ የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ከዚህ በላይ ስለግብፅ ማውራትና መጻፍ እንደሚገባም በመጠቆም በኢትዮጵያ ተጀምሮ የነበረው የግብፅ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ግን ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ጩኸት ሳይሆን እውነት ነው፡፡ በግብፅ ፓርላማ ላይ መሣሪያ የተተኮሰ ያህል እየተደነፋብን ዝም ማለት የለብንም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ሽንኩርት እንደመትከል አይደለም፤›› በሚል በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ንግግር ላይ የተሰጠው አስተያየት የተሳሳተ መሆኑን ተችቷል፡፡ አድማጩም ለዚሁ አስተያየት ሰጪ ንግግር በጭብጨባ ድጋፉን ገልጿል፡፡

ለቀረቡት አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት አቶ ዘነበ ከበደ፣ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የቆየው ግንኙነት መልካም ቢሆንም፣ በውኃው አጠቃቀም ላይ ያላቸው አመለካከት የተለያየ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ አቋም ደግሞ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አቋም በአብዛኛዎቹ የተፋሰሱ አባል አገሮች የሚደገፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በዓባይ ላይ አሁን የያዘውን ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ሒደት ይቀጥልበታል፤›› ብለዋል፡፡

የጋራ ፕሮጀክቶትን በተመለከተ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ሚልዮን ገብረ እየሱስ፣ ኤርትራ የናይል ቢዜን ኢንሼቲቭ (NBI) አባል ያልሆነችበትን ምክንያት በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አምባሳደር ኃይሉ በበኩላቸው፣ ‹‹ችግሩ በዲፕሎማሲ ማለቅ አለበት›› ማለታቸውን አስመልክቶ ለተነሳ አስተያየት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹በትምህርቴም፣ በሙያዬም የሕግና የዲፕማሲ ሰው ነኝ፣ በመሆኑም ጦርነትን አልሰብክም፤›› ብለዋል፡፡ በውኃ ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት አግባብ እንዳልሆነ በማስገንዘብ፡፡

ሆኖም በግብፅ መሪዎች የሚሰጡት አስተያየቶች መልካም ነገር አያመጡም በማለት፣ ‹‹ምናልባትም ኃይልን ለመጠቀም አስበው ከሆነ እኛ ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ ጉዳይ አዲስ አይደለንም፤›› በማለት፣ ‹‹ሙያ በልብ ነው›› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በከፍተኛ ጭብጨባ የታጀቡት አምባሳደሩ፣ ያም ሆኖ ግን ለዲፕሎማሲ ሥራ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ግብፅን ራቁቷን ማስቀረት››
በተለይም የደቡብ ሱዳንን ነፃ መውጣት ተከትሎ፣ የተፋሰስ አባል አገሮቹ አሥራ አንዱ ስለሚሆኑ ዕድልም ፈተናም መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ኃይሉ፣ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት ‹‹ግብፅን ራቁቷን ማስቀረት የመጀመሪያ ዕርምጃችን ይሁን፤›› ብለዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን ነፃ ስትወጣ በቆዩ ሕጎች ለመገዛት የማትገደድ መሆኗንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛውን ደረጃ ይዛለች በማለት አስተያየታቸውን የቀጠሉት ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከግብፅ በልጣ አብዛኞቹን አገሮች ከጎኗ ማሰለፍ መቻሏን አድንቀው፣ ይህንን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት መንግሥትን አሳስበዋል፡፡ ግብፅንና ኢትዮጵያን በአንበሳና በጥንቸል መመሰሉ ግን ታሪክን ያላገናዘበ አስቂኝ አባባል መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹እባካችሁ ግንዛቤያችንን ከፍ እናድርግ›› ሲሉ ቀደም ሲል በቀረበው ሐሳብ ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመጡት አምባሳደር አብዲ ደላል በበኩላቸው፣ ‹‹ግብፅ የምትናገረውን እያሳጣናት ነው፡፡ እንዲያውም ዞሮ ዞሮ ወደዚህ (ወደ ስምምነቱ) መምጣቷ አይቀርም፤›› በማለት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ‹‹ወጣቶች ግራ መጋባት አያስፈልግም፣ ቅጣት መቀበልን አድርገነው አናውቅም፤›› በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ‹‹እቀጣቸዋለሁኝ የሚል አገር ካለ ግን የምንተዋወቅ ይመስለኛል፤›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close