የጋዳፊ ጀምበር እየጠለቀች ይሆን?

ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ለ42 ዓመታት ቀጥቅጠው ከገዟት አወዛጋቢው ሙአመር አል ጋዳፊ መዳፍ እያፈተለከች ትመስላለች፡፡

በ42 ዓመታት የአገዛዝ ዘመናቸው በነውጠኝነት የሚታወቁት ጋዳፊ ራቁታቸውን ያስቀራቸውን የበቀደሙን አሳፋሪ ንግግራቸውን ተከትሎ ዓለም ውጉዝ ከመአርዮስ እያላቸው ነው፡፡ የገዛ ሕዝባቸውን ለማጨፋጨፍ የእርስ በርስ ጦርነት ያወጁት ጋዳፊ፣ በሊቢያ ሕዝባዊ ተቃዋሚዎች ላይ በአደንዛዥ ዕፅ የሰከሩ፣ አይጦች፣ ቁንጫዎች፣ ቅጥረኞች፣ ወዘተ. በማለት

አፀያፊ ስድቦችን ሰንዝረዋል፡፡ ደጋፊዎቻቸውም እነዚህን ዜጎች የገቡበት ገብተው እንዲገድሏቸው አዘዋል፡፡ ይህን ዓይነቱን አሳፋሪ ተግባር እንዲፈጸም ያዘዙት እኚህ ግለሰብ የተባበረችው አፍሪካን በመመስረት ለመንገሥ ማሰባቸውም የአንድ ሰሞን አስቂኝ ወሬ ነበር፡፡ የጋዳፊን የኋላ ታሪክ ለማወቅ የሰዬውን ስብዕና በጥቂቱ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡

ሙአመር አቡ ሚንያር አል ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ1942 ተወለዱ፡፡ ሰርት በምትባለው አካባቢ ከበደዊን ቤተሰብ የተገኙት ጋዳፊ በወጣትነታቸው የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ጋማል አብደል ናስርና የዓረብ ሶሻሊስት ፓርቲያቸው አድናቂ ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ በ1956 በስዊዝ በተነሳው ቀውስ በፀረ እስራኤል ሰላማዊ ሠልፍ ላይ መሳተፋቸውን የኋላ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በወጣትነታቸው በሴረኝነታቸው የሚታወቁት ጋዳፊ በሊቢያ ወታደራዊ ኮሌጅ በመግባት በውትድርና የሠለጠኑ ሲሆን፣ ተጨማሪ ወታደራዊ ሥልጠናዎችን በግሪክና በእንግሊዝ ወስደዋል፡፡ በዕጩ መኮንነታቸው ዘመን የሊቢያን ንጉሥ ለመገልበጥ ያሴሩ እንደነበርም ይነገራል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ቢጤዎቻቸውን በሚስጢር ያሰባስቡ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 1 ቀን 1969 በጋዳፊ የሚመሩ ጥቂት መስመራዊ መኮንኖች ያለምንም ደም መፋሰስ የንጉሥ መሐመድ ኢድሪስ ቢን ሙሐመድ አል መህዲን መንግሥት ገለበጡ፡፡ ይህ የመንግሥት ግልበጣ ሲከናወን ንጉሡ ለሕክምና ቱርክ ውስጥ ነበሩ፡፡ የዘውዳዊውን አገዛዝ የገረሰሱት ጋዳፊ ወዲያውኑ የሊቢያን ዓረብ ሪፐብሊክ መመስረታቸውን አወጁ፡፡ በወቅቱ

ዕድሜያቸው 27 የነበረው ኮሎኔል ጋዳፊ ትልቁን የፀሐይ መነፅራቸውን ዓይናቸው ላይ ደንቅረው በወታደራዊ ዩኒፎርማቸው ግርማ ሞገስ ተላብሰው ብቅ በማለት ፀረ ኢምፔሪያሊስት አብዮት እንደሚመሩ ለዓለም አስታወቁ፡፡ የቀድሞዋን ቅኝ ገዢ ኢጣሊያ ዜጎችም ከአገራቸው አባረሩ፡፡ ሊቢያም የምትመራው በእሳቸው ፍፁማዊ የበላይነት ሥር መሆኑን በማስታወቅ ራሳቸውን ‹‹የአብዮቱና የሕዝቡ መሪ›› ሲሉ አስተዋወቁ፡፡

በዓረብ ብሔረተኝነት ሥር እስላማዊ ሶሻሊዝምን በማወጅ በግል የተያዙ አነስተኛ ይዞታዎችን ለዜጎች በመተው ትላልቅ ኩባንያዎችን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር አዋሉ፡፡ የእስልምናን ሞራላዊ እሴቶች በማስተዋወቅም መጠጥና ቁማርን አገዱ፡፡ ‹‹አረንጓዴው መጽሐፍ›› በሚባለው የፍልስፍናቸው መገለጫም የአገዛዛቸውን የፖለቲካ አቋም አስታወቁ፡፡ ከዚያም ‹‹ጃማህርያ›› የሚባለውን ወይም ‹‹የሕዝብ መንግሥት›› በማለት የመንግሥታቸውን ቅርፅ ለወጡ፡፡ በዚህም አገሪቱ በሕዝቡ ቀጥታ ተሳትፎ የምትተዳደር አገር ናት አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እንደፈለጋቸው መመሪያዎችንና ትዕዛዞችን የሚያወጡት እሳቸው ብቻ ነበሩ፡፡ መንግሥታቸውን ‹‹ሕዝባዊ›› ቢሉትም የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻው እሳቸው ሆነው አረፉት፡፡

ቀስ በቀስ በጋዳፊ ላይ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች መቅረብ ሲጀምሩ የጋዳፊ ምላሽ ኃይል የተቀላቀለበት መሆን ጀመረ፡፡ ‹‹አብዮታዊ ኮሚቴ›› በመባል የሚታወቀው የጋዳፊ ቀኝ እጅ ተቃዋሚዎችን ደብዛቸውን ያጠፋ ጀመር፡፡ በስደት ላይ ያሉትን ሳይቀር ያሉበት ድረስ እየሄደ የሚገድለው ይኼ ኃይል ሊቢያውያንን ፀጥ እረጭ አደረጋቸው፡፡ ጋዳፊንና መንግሥታቸውን የሚቃወም ከተገኘ ‹‹አብዮታዊው ኮሚቴ›› የመጨረሻውን ዕርምጃ በመውሰድ ያስወግዳል፡፡ ይህ ዓይነቱ አስፈሪ ዕርምጃ ከጊዜ ወደጊዜ አድማሱን እያሰፋ በመምጣቱ ጋዳፊ ሊቢያ ውስጥ የተቃዋሚዎቻቸውን እንቅስቃሴ በብቃት አዳፈኑ፡፡

የውጭ ግንኙነታቸውን የግብፁን ጋማል አብዱል ናስር የፓን ዓረቢዝም ፍልስፍና በመከተል የጀመሩት ጋዳፊ፣ ዓረቦችን በአንድ መንግሥት ሥር ለማስተዳደር ሌት ተቀን ይጥሩ ጀመር፡፡ በዚህም የዓረብ ብሔረተኝነትን በመስበክ የእንቅስቃሴው መሪ ለመሆን ቆርጠው ተነሱ፡፡ በዚህ ምኞትም ሊቢያን፣ ግብፅንና ሶሪያን በመቀላቀል ‹‹የዓረብ ሪፐብሊክ ፌዴሬሽን›› መመሥረታቸውን አወጁ፡፡ ይሁንና የጋዳፊ አካሄድ ያልተዋጠላቸው ግብፅና ሶሪያ ውህደቱን ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ ከዚያም ከቱኒዝያዊው የወቅቱ መሪ ሐቢብ ቡርጊባ ጋር በመነጋገር በሊቢያና በቱኒዝያ አማካይነት ፌዴሬሽኑን በመመስረት ውጥናቸውን ለማሳካት ሞከሩ፡፡ ይህም በቡርጊባ እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀረ፡፡ በዚህም ሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ ገቡ፡

ይህ ጥረታቸው ያልተሳካላቸው ጋዳፊ ፊታቸውን ወደ ፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ግንባር በማዞር ጠንካራ ድጋፋቸውን ማሳየት ጀመሩ፡፡ ይህ ውሳኔያቸው ከግብፅ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንደጎዳባቸው ይነገራል፡፡ ምክንያቱም እ.ኤ.አ በ1979 ግብፅ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ለማድረግ እየጣረች ስለነበረች ነው፡፡ ሊቢያ ከግብፅ ጋር የነበራት ግንኙነት ሲበላሽ ጋዳፊ ፊታቸውን ወደ ቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት አዞሩ፡፡ ከሶቪዬት ብሎክ ውጪ ሚግ 25 ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖችን በማግኘት ሊቢያ የመጀመሪያዋ አገር ሆነች፡፡ ከነዳጅ የሚገኘውን ገንዘቧን ይዛ ከሶቪዬት የጦር መሣሪያ ብታጋብስም፣ እንዲህም ሆኖ የሊቢያና የሶቪዬት ኅብረት ግንኙነት ያን ያህል አልነበረም፡፡ ጋዳፊ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እያሉ የሊቢያን የተፅዕኖ አድማስ ለማስፋት ‹‹የሰሐራ እስላማዊ መንግሥት›› ለመመሥረት ከሰሐራ በታች ያሉ የመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎችን መርዳት ጀመሩ፡፡ በዚህም በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በርካታ አማፂያንን በመርዳት ፊታቸውን ወደ አፍሪካ አዞሩ፡፡ ይህ አደገኛ እንቅስቃሴያቸው ያልተዋጠላቸው የአፍሪካና የምዕራብ መንግሥታት ጋዳፊን በጥንቃቄ ማየት በመጀመራቸው ጋዳፊ ከበርካታ መንግሥታት ጋር መጣላት ሥራቸው ሆነ፡፡

በተለይ በ1970ዎቹ ውስጥ ጋዳፊ ሊቢያን በተለያዩ የሽብር ተግባሮች ተሳታፊ ከማድረጋቸውም በላይ፣ በዓረቡ ዓለምና በተቀረው ዓለም ውስጥ በተካሄዱ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ይነሳ ጀመር፡፡ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ አጋማሽም ምዕራባውያኑ በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ያሉት የሽብር ጥቃቶች ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ጋዳፊ መሆናቸውን፣ እሳቸውም ዓለም አቀፍ አሸባሪ መሆናቸውን በይፋ አስታወቁ፡፡ ጋዳፊ ‹‹ብላክ ሴፕተምበር›› በመባል የሚታወቀውና በሙኒክ ኦሊምፒክ ጭፍጨፋ ለፈጸመው አሸባሪ ቡድን የገንዘብ ምንጭ መሆናቸውን አሜሪካ አስታወቀች፡፡ በበርካታ መንግሥታት ዘንድ ቁጣንም ቀሰቀሰባቸው፡፡ በተለያዩ የሽብር ድርጊቶች ውስጥ በእሳቸው የነዳጅ ገንዘብ የሚደገፉ ኃይሎች እንዳሉበት በዓለም ተነዛ፡፡ በዚህም ጋዳፊ በምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙኀን አሸባሪ ሆነው ተፈረጁ፡፡ በወቅቱ ከእያንዳንዱ የሽብር ጥቃት በስተጀርባ የጋዳፊ እጅ እንዳለበት በሰፊው ተወራ፡፡

በፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ዘመን የሊቢያና የምዕራቡ ዓለም ፍጥጫ ተካሮ ጫፍ ደረሰ፡፡ በተለይ ሬገን ጋዳፊ በዓለም ላይ እየደረሱ ላሉ ብጥብጦች፣ ለኢራን የአያ ቶላህ መንግሥት ድጋፍ በመስጠታቸውና በፀረ ምዕራባውያን አቋማቸው ‹‹የመካከለኛው ምሥራቅ ያበደ ውሻ›› አሏቸው፡፡ ከዚያም እ.ኤ.አ በ1986 በሬገን ትዕዛዝ የሊቢያ ከተሞች ትሪፖሊና ቤንጋዚ በአሜሪካ አየር ኃይል ተደበደቡ፡፡ በሁለቱ ከተሞች ላይ በተካሄደው ጥቃት 45 የሊቢያ ወታደሮችና ሲቪሎች ተገደሉ፡፡ ሬገን ይህንን ጥቃት ያዘዙት የሊቢያ መንግሥት በምዕራብ በርሊን ዳንስ ቤት ውስጥ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት እጃቸው እንዳለበት በመረጋገጡ መሆኑን በወቅቱ ተነግሯል፡፡ በዚያ የቦምብ ጥቃት የአሜሪካ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ጋዳፊ ከተለያዩ የሽብር ድርጊቶች ጋር በተገናኘ ስማቸው በሰፊው ከመነሳቱም በላይ፣ እጅግ ዘግናኝ በተባለው የሎከርቢ አውሮፕላን አደጋ ባለቁት መንገደኞች ጥቃት የሊቢያ እጅ መኖሩ ተረጋገጠ፡፡ ያንን አሳዛኝ የፍንዳታ አደጋ ካደረሱት ሽብርተኞች ውስጥ የሊቢያ ዜጎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ በቅርቡ አንዱ ተፈቶ መለቀቁ ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ለሎከርቢውና ለበርሊኑ ተጎጂ ቤተሰቦች 1.5 ቢሊዮን ዶላር ካሣ በመክፈል ዳግመኛ በሽብር ተግባር ላይ እንደማይገኙ በመስማማት ራሳቸውን ከዚህ ድርጊት ማራቃቸውን አስታወቁ፡፡ ይህን ሁሉ ሽብር መርተው በወንጀለኝነት አለመከሰሳቸው ብዙዎችን ያስደነቀ ነገር ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር ጋዳፊ ከዓረቡ ዓለም ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ በማዞር የተባበረች አፍሪካን የመመስረት ውጥን ይዘው የቀረቡት፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አገሮችን የጎሳ መሪዎችና ባህላዊ መሪዎች በማደራጀት ራሳቸውን ንጉሠ ነገሥት ለማድረግ ሲቋምጡ የነበሩት አወዛጋቢው ጋዳፊ፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች የቀረበላቸው አቀባበል ቀዝቃዛ ነበር፡፡ ከነዳጅ የሚያጋብሱትን ገንዘብ ተገን በማድረግ የተለያዩ የመደለያ ስጦታዎችን ይዘው መቅረብ ልማድ ያደረጉት ጋዳፊ፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ዜጎች በሊቢያ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን አፍሪካን አንድ መንግሥት ለማድረግ ከጋናው ክዋሜ ንክሩማህ በመኮረጅ የጀመሩት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴውን ያገኘው ምላሽ ግን ቀዝቃዛ ነበር፡፡ ከሁለት መቶ በላይ ባህላዊ መሪዎችን በመሰብሰብ እ.ኤ.አ በ2009 ራሳቸውን ‹‹ንጉሠ ነገሥት›› በማለት አዲስ አበባ ውስጥ ሥርዓተ ንግሥ መፈጸማቸው በብዙዎች ዘንድ መሳቂያ አድርጓቸዋል፡፡ ጋዳፊ በእነዚህ ባህላዊ መሪዎች አማካይነት ራሳቸውን ሲያነግሡ ተቀባይነት አላገኙም ነበር፡፡ ብዙዎችም ለየላቸው እስከማለት ደርሰዋል፡፡

ጋዳፊ ይህ አዲሱ ውጥናቸው አልሠራ ብሎ ተቀባይነት ሲያጡ ቲያትራቸውን በመቀጠል በዓረብ ሊግ ስብሰባ ላይ በመገኘት ‹‹ንጉሠ ነገሥት›› መሆናቸውን በመተው ‹‹የዓረብ መሪዎች የበላይ›› እና ‹‹የሙስሊሞች ኢማም›› ነኝ አሉ፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥንም ተቹዋቸው፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው በህንድ ውቅያኖስና በየመን ባህረ ሰላጤ የተሰማሩትን የሶማሊያን የባህር ላይ ወንበዴዎች ተግባር አደነቁ፡፡ ድርጊታቸውም የስስታሞቹን ምዕራባውያን ወረራ ለመመከት የተደረገ ራስን የመከላከል ዕርምጃ እንጂ የባህር ላይ ውንብድና አይደለም አሉ፡፡ ‹‹ምዕራባውያን በገዛ ፕላኔታችን አብረውን በሰላም መኖር ካልፈለጉ ወደሌላ ፕላኔት መሄድ ይችላሉ፤›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ በራሳቸው የቅዠት ዓለም ውስጥ እንደሚኖሩ የሚነገርላቸው ጋዳፊ እንደገና ከምዕራቡ ዓለም ጋር መተነኳኮሳቸውን ቀጠሉ፡፡

ላለፉት 42 ዓመታት በአወዛጋቢነታቸውና በሴረኝነታቸው የሚታወቁት ጋዳፊ ከሚታወቁባቸው አሳፋፊ ተግባሮቻቸው ዋነኛው ተሳዳቢነታቸው ነው፡፡ ዲፕሎማሲ የሚባለው የዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ስልት የማይዋጥላቸው ጋዳፊ የበርካታ አገሮችን መሪዎችን በመሳደብ፣ በመተቸትና በማንቋሸሽ ይታወቃሉ፡፡ ከእሳቸው እኩይ ዓላማ ጋር የማይተባበር ወይም እሳቸው ያሉትን ሐሳብ የማይቀበል ይሰደባል፣ ይወገዛል፡፡ ራሳቸውን ከማንም በላይ የአምላክ ታዛዥ አድርገው የሚቆጥሩት ጋዳፊ ከእሳቸው በተቃራኒ የተሰለፉ እንደርኩስ ይቆጠራሉ፡፡ በግብዝነት የተሞሉ በመሆናቸውም ከእሳቸው ፍላጎት በተቃራኒ የሚሄድ ማንም ሰው እንደ ኃጢያተኛ ይቆጥሩታል፡፡ ኑሮአቸውን እንደመናኝ ለማስመሰል የሚሞክሩት ጋዳፊ የድንኳን ኑሮ እየኖሩ ለአምላክ ትዕዛዝ ተገዢ ነኝ ቢሉም፣ በዓለም ላይ የሚበትኑት ገንዘብ ለበጎ ተግባር እንደማይውል የአደባባይ ሚስጢር መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በአረንጓዴው አብዮታቸው ያልተጠና ዕቅድና አፈጻጸም በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን ያባከኑት ጋዳፊ፣ በሊቢያ ሕዝብ ስም በርካታ ጥፋቶችን አድርሰዋል፡፡ በእነዚህ ጥፋቶቻቸው ግን አንድም ቀን ተሳስቼ ነበር ሲሉ አይደመጡም፡፡

ጋዳፊ ከሁለት ሚስቶቻቸው ስምንት ልጆች አሏቸው፡፡ ሰባት ወንዶችና አንዲት ሴት፡፡ ልጆቻቸው የሊቢያን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ወታደራዊ ተቋማት ይቆጣጠራሉ፡፡
የሊቢያን የነዳጅ ሀብትና የተለያዩ ኮርፖሬሽኖችንና ኩባንያዎችን በቁጥጥራቸው ሥር በማዋል አብዛኛውን ሕዝብ የበይ ተመልካች አድርገውታል፡፡ ምንም እንኳን 6.4 ሚሊዮን የሚሆነው የሊቢያ ሕዝብ በተነፃፃሪ ሁኔታ ከአካባቢው አገሮች የተሻለ ኑሮ እንደሚኖር ቢነገርም፣ አገሪቱ በጋዳፊ ቤተሰቦች ቁጥጥር ሥር በመሆን ሀብቷ በመመዝበሩ ሊቢያውያን ደስተኞች አይደሉም፡፡ በወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ አጥ መብዛቱ እንቆቅልሽ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ሊቢያን እግር ተወርች ጠፍረው የሚያስተዳድሯት ጋዳፊና ቤተሰባቸው ላለፉት 42 ዓመታት በሕዝቡ ላይ ያደረሱት ሰቆቃ ከዋንጫው ሞልቶ በመትረፍረፉ ካለፈው የካቲት 9 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሊቢያውያን የጋዳፊ አገዛዝ በቃን ብለዋል፡፡ ሕዝባዊው ተቃውሞ ተፋፍሞ በርካታ የሊቢያ ከተሞችም ከጋዳፊ ቁጥጥር ውጪ ሆነዋል፡፡ በቤተሰቦቻቸውና በዘመድ አዝማዶቻቸው የተያዙት የመከላከያና የፀጥታ ኃይሎች ለጊዜው አለሁ ቢሏቸውም የጋዳፊ የሥልጣን ዘመን ሳያበቃ እንዳልቀረ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይስማማሉ፡፡

ጋዳፊ ሁሉም ነገር ከቁጥጥራቸው እየወጣ ሲሄድ ጭካኔያቸው በማየሉ እስካሁን በይፋ እንደተነገረው ቅጥረኞችን ጭምር በማሰማራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያንን አስጨፍጭፈዋል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎዋቸው የኬሚካል ጦር መሣርያ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ስጋት አለ፡፡ በርካታ ባለሥልጣኖቻቸው የከዱዋቸው ጋዳፊ በሕዝባዊው ተቃውሞ ጫና እየበዛባቸው በመምጣቱ ለመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ማድረጋቸውን ቢያውጁም፣ ሰሚ አላገኙም፡፡ የ42 ዓመታቱ የግፍ አገዛዝ በቃን ያሉት ሊቢያውያን ጋዳፊን አሁንም ‹‹በቃ ውረድ›› እያሉ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጋዳፊ በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ በፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ናቸው እያለ ነው፡፡ ጋዳፊ ከጥቂት ደጋፊዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ቀርተዋል፡፡ በርካታ የሠራዊቱ አባላት የሕዝቡን አብዮት እየተቀላቀሉ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አብዛኛውን የሊቢያ ግዛት የተቀሙት ጋዳፊ በዋና ከተማዋ ትሪፖሊም አመፅ ተነስቶባቸዋል፡፡ ጋዳፊ ለጊዜው ‹‹ሥልጣን አለቅም፣ የአብዮቱ ብቸኛ መሪ ነኝ፤›› እያሉ ቢወተውቱም ጀምበሯ እየጠለቀችባቸው ነው፡፡ የሚሳሱለትን ሥልጣናቸውን አሳልፈው ለመስጠት ባለመፈለጋቸው የሊቢያውያን ደም እንደጎርፍ እየፈሰሰ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ለጊዜው ጎልቶ ባይታይም ሊቢያውያን የጋዳፊን ዘመን እንዲያከትም ማድረጋቸው አይቀርም እየተባለ ነው፡፡ የቱኒዝያውያን ቤን አሊንና የግብፁን ሙባረክ ዕጣ ፈንታ መጋራታቸው የማይቀር እንደሆነም በስፋት ይነገራል፡፡ የፈለጉትን ዓይነት ኃይል ይጠቀሙ የሊቢያውያን ጠንካራው ሕዝባዊ አብዮት ጠራርጎ እንደሚወስዳቸው ግን ከወዲሁ የተረጋገጠ ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ካሁን በኋላ ጋዳፊ ታሪክ ለመሆን የቀራቸው ጊዜ በቀናት እየተቆጠረ ነው፡፡ አወዛጋቢውና አነጋጋሪው ኮሎኔል ጋዳፊ ሊቢያን በዓለም ከዋነኞቹ ነዳጅ ላኪ አገሮች ተርታ ያሰለፋት የነዳጅ ሀብት ከፈጠረው የቅንጦት ኑሮ ሊሰናበቱ መቃረባቸው ተገምቷል፡፡ ነውጠኛው ጋዳፊ ሊቢያንና ሕዝቧን ከማጥፋታቸው በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ልዕለ ኃያላን አገሮች ጠንካራ ዕርምጃ ይወስዱ ዘንድ በመላው ዓለም ጥሪ እየቀረበ ነው፡፡ የጋዳፊ ጀምበር በአስቸኳይ ትጠልቅ ዘንድም ጭምር፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close