ጋዳፊ ነዳጅና ደም

ለወንድም ሙአመር ጋዳፊ ዘንድሮ ቀናቸው አይደለም፡፡ ከውጭም ከውስጥም የስንግ ተይዘዋል፡፡ አመፅ፣ ማዕቀብ፣ ተቃውሞ አልተለያቸውም፡፡

አሜሪካ በቃዎት ብላለች፡፡ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የጉዞና የሀብት ማዕቀብ ጥሎባቸዋል፡፡ በርካታ የአውሮፓ አገሮችም ፊት ነስተዋቸዋል፡፡ የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሊስኮኒ ለምን ደውለው አንድ ነገር አይሏቸውም ሲባሉ “ልረብሻቸው አልፈልግም”  ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡ የጣልያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮቤርቶ ማሮኒም ቢሆን ጋዳፊ የማይረሱ መሪ ናቸው ያሉዋቸው፡፡ ለ42 ዓመት ሊቢያን የመሩት ጋዳፊ በሕዝባዊ ቁጣ ተዳክመዋል፡፡ መጪውን ጊዜ እሳቸውም ልጆቻቸውም አያውቁትም፡፡ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ባለፈው ዓርብ ሁለቴ ደውለው ሥልጣን ልቀቁ ቢሏቸውም ጋዳፊ አሻፊረኝ ነው ያሉት፡፡ ለነገሩ ሥልጣን ለቀው የት ይሄዳሉ? ጋዳፊን ተቀብሎ ማን አሳር ያያል?

አንድ ጥይት አንድ ሰው
አሁን ባለው ሁኔታ ጋዳፊ ዋና ከተማዋ ትሪፖሊ አልዚዝያ ይሁኑ እንጂ በየምሽቱ ቤት እየቀየሩ እንደሚያድሩ ይነገራል፡፡ ከጎናቸው የማትለየው ነርሳቸውና ነፍሳቸው ናት የምትባለው ዩክሬናዊት ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡ ሊቢያውያን ብቻ ሳይሆኑ የሥርዓቱ የቅርብ ሰው የሆኑ ሚኒስትሮችና ጄኔራሎች የከዷቸው ጋዳፊ ህልውናቸው የተንጠለጠለው በአገሪቱ ጦር ኃይል ላይ አይደለም፡፡ ከግብፅና ከቱኒዚያ በተቃራኒ የኃይል ሚዛኑ (Balance of Power) ያለው በጦር ኃይሉ ላይ አይደለም፡፡ ጋዳፊ የመፈንቅለ መንግሥት እንዳይካሄድባቸው በመስጋት የመከላከያ ኃይሉን ደካማ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ተቋማዊ ቅርፁም የተልፈሰፈሰ ነው፡፡ ቁጥሩም 40 ሺሕ ያህል እንደሆነ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ ፍራንክ ጋርድነር የተባለ የቢቢሲ የፀጥታ ጉዳይ ጋዜጠኛ የጋዳፊ ሕይወት ታማኞቻቸውን ባቀፈው አብዮታዊ ብርጌድ፣ በራሳቸው ጋዳፊ ጎሳ አፍሪካውያን መሪዎችና ቅጥረኞች መዳፍ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዙሪያቸው ያሉት አንድም በጋዳፊ የቅርብ ሰዎች እንዳያመልጡ ጥበቃ የሚደረግባቸው አልያም እንደመሪያቸው ዙሪያው የጨለመባቸው ናቸው፡፡

የሊቢያ የደኅንነት መዋቅር ከቀድሞው ምሥራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅት ስታሲና የሮማኒያው ሴኩሩታቴ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ከፍተኛ በጀት የሚመደብለት የደኅንነት መዋቅር ከመከላከያ ሠራዊቱ ጠንካራ ነው፡፡ በደኅንነት መዋቅሩ ውስጥ የጋዳፊ ልጆች ሰፊ ሚና ቢኖራቸውም የውስጥና የውጭ ደኅንነት ቁልፍ ቦታዎችን የያዙት አማቻቸው አብዱላ ሳኑሲ ናቸው፡፡ አክራሪና ጨካኝ ናቸው የሚባሉት ሳኑሲ አሁን በአማፅያን እጅ በወደቀችው ቤንጋዚ ጭፍጨፋ እጃቸው አለበት፡፡ ሕዝባዊው ተቃውሞ ምንም ቢያይል ጋዳፊን በርቱ እንጂ እንደ ቱኒዚያና ግብፅ ጄኔራሎች ጋዳፊን በቃዎት ይሏቸዋል ተብለው አይጠበቁም፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት 22 ሺሕ ፕሬዚዳንታዊ ልዩ ጦር እንደነበራቸው ይነገር እንጂ ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን ከማባረር (ዱባይ ውስጥ ሕክምና ላይ እንደሆኑ ይታማል) አላዳናቸውም፡፡ የጋዳፊ ልዩ ቅልብ ጦር ግን በቀላሉ አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ልዩ ጦር ተጠሪነቱ ለአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ሳይሆን ለአብዮታዊ ኮሚቴ ነው፡፡ የእዚህ ኮሚቴ አዛዦች ደግሞ የጋዳፊ ልጆች ሃኒባልና ከሚስ ናቸው፡፡ እንደ ሳዳም ሁሴን ልጆች ኡዴና ቁሰይ እንደማለት ነው፡፡ ጋዳፊን በቅርብ ርቀት የሚጠብቋቸውም በአብዛኛው አህል አል-ከህምን (የድንኳን ሰዎች ማለት ነው) የሚባሉት ቆንጆዎቹ ናቸው፡፡ ስለሆነም የጋዳፊ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚወድቀው ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የቆረጠ አጥፍቶ ጠፊ አልያም ካለቀለት መንግሥት ጋር አንሞትም በሚል ጎራቸውን ለውጠው አሰላለፋቸውን ከአማፂያኑ ጋር ካደረጉ ብቻ ነው፡፡ ከሚሰጥም መርከብ ጋር ማን ይሰጥማል?

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቲም ኒብሎክ እንደሚሉት ጋዳፊ ገንዘባቸውን በተለያየ መልክ ስለሚያስቀምጡ ምን ያህል አላቸው የሚለውን  በእርግጠኛነት መናገር አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር የእሳቸውና የቤተሰባቸው ነው፡፡ ጋዳፊ በሥልጣን ዘመናቸው በርካታ አማፅያንን መልምለዋል፣ አሠልጥነዋል፤ አሁን ደግሞ ቅጥረኞች ለመንበራቸው መድኅን እንዲሆኑ እየተጠቀሙባቸው ናቸው፡፡ ከማሊ፣ ከቻድ፣ ከዚምባብዌ፣ ከጊኒና ከሌሎች አገሮች ያሰባሰቧቸው ቅጥረኞች ከጎናቸው ናቸው፡፡ የኤርትራ መንግሥትም ታጣቂዎችን እንዳሰማራ የኤርትራ ድረ ገጾች እየጠቀሱ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዶላር ከተላከልኝ ምን ገዶኝ ቢሉ አይገርምም፡፡ አሳዛኙ ነገር ጋዳፊ የሌላ አገር ዜጎችን እየተጠቀሙ በመሆኑ ፀጉረ ልውጦች  የተቃዋሚዎች ዒላማ እየሆኑ ናቸው፡፡ ይህም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

እንደ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሁሉ የአንድ ሊቢያዊ ማንነት ከሚወለድበት የዘር ግንድ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የወንድም ሙአመር አል ጋዳፊም እንደዚሁ በከተሞችና በትምህርት መስፋፋት ሳቢያ በጎሳ ማሰብ የተዳከመ ቢመስልም የጋዳፊ የኃይል ሚዛን በጋዳፊ ጎሳ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በሊቢያ 140 የሚሆኑ ጎሳዎችና ቤተሰቦች (Tribers and family clans) ቢኖሩም በአገሪቱ ፖለቲካ  ተፅዕኖ ያላቸው ጥቂት ናቸው፡፡ የጋሪዮኒስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶክተር አማል አል-አቤይዲ ይህን ቁጥር ወደ ሁለት ያወርዱታል፡፡ ከዓረቡ ዓለም የመጡት ትሪፖሊን ማዕከላቸው ያደረጉት ምዕራቦቹ ቤኒ ሂላልና ምሥራቆቹ ቤኒ ሳሊም ናቸው፡፡ እንደተመራማሪው መደምደሚያ የጋዳፊ ጎሳ 200 ዓመት በሚሆነው የሊቢያ ታሪክ እዚህ ግባ የሚባል ቦታ አልነበረውም፡፡ ሥልጣንም ገንዘብም ያገኙት በጋዳፊ ነው፡፡ ስለሆነም የጎሳው መሪዎች በዚህ ፈታኝ ወቅት ለጋዳፊ ብለው ሳይሆን ለደኅንነታቸው ዋስትና የላቸውምና ጋሻ ሊሆኗቸው ይችላሉ፡፡ በሰርጥ (ፕሬዚዳንቱ ናቸው ከተማ ያደረጓት)፣ ዜልቴን፣ ትሪፖሊ ከተሞች ዙሪያ ያሉ የሰዐድ፣ የዛውያና ዋርፋላ ንዑስ ጎሳዎች እንዲሁም ሙንታሲርና ሱኒ ቤተሰቦች ለጋዳፊ አለኝታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሎከርቢ ፍንዳ ታስሮ በጋዳፊ ጥረት የተፈታው የአብዱልባሲጥ አሊ አልመርጋሃ ጎሳም ጥሎ ላይጥላቸው ይችላል፡፡ ሌሎች ወገኖች ይህን ክርክር አይቀበሉትም፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የሚያቀርቡት ለጋዳፊ አስተዳደር ቅርብ የሆነው ዛውያ ጎሳ በሊቢያውያን ሠልፈኞች የተወሰደውን ዕርምጃ በፅኑ አውግዟል፡፡ ለነገሩ ሳዳምን አሳልፎ የሰጣቸው የራሳቸው ሰው አይደለ? ጋዳፊ የቅርብ ሰዎቻቸው መክዳት የጀመሩት ከስድስት ወራት በፊት ነው፡፡ ለ40 ዓመታት ፕሮቶኮላቸው የነበረው ኑሪ አልሚሰማሪ ተሰዶ በቱኒዚያ አድርጎ ፈረንሳይ ከገባ በኋላ ነው፡፡

የጋዳፊ ገመና
የዊኪሊክስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ጋዳፊ ተጠራጣሪ ናቸው፡፡ ወቅታዊ የዓለም ሁኔታዎችን በሚገባ ይከታተላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተደማጭ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ የፈረስ ውድድር ቀልባቸውን ይሳበው እንጂ በአውሮፕላን መብረር ብቻ ሳይሆን ፎቅ ላይ መውጣት እጅግ ይፈራሉ፡፡ ለጋዳፊ ሰኞና ሐሙስ የፆም ቀናቸው ናቸው፡፡ ጋዳፊ በጭካኔያቸው ይታሙ እንጂ ከሰው ጋር ዓይን ለዓይን እንኳን  መተያየት አይወዱም ነው የሚባለው፡፡ የጋዳፊ የመጀመሪያ ባለቤታቸው ፈቲያ ካሊድ መምህርት የነበሩ ሲሆን፣ መሐመድ የተባለ ልጅ ቢወልዱላቸውም ትዳራቸው ከስድስት ወራት በላይ አልዘለቀም፡፡ ከአሁኗ ባለቤታቸው ፈቲያ ፈርካሽ አምስት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጅ ያፈሩ ሲሆን ሁለት የቤተሰቦቻቸውን ልጆች (ሃና የተባለችው በአሜሪካ ድብደባ ሞታለች) በጉዲፈቻ አሳድገዋል፡፡

ሙታሲም የፀጥታ ጉዳይ አማካሪያቸው ነው፡፡ ፌሽታ ይወዳል፡፡ አሜሪካኖቹን ቢዮንሴ፣ አሸርና ማሪያ ኬሪን ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሚሊዮኖች ከፍሎ አስደንሷል፡፡ ሃኒባል ተደባዳቢ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ስዊዘርላንድ ውስጥ የቤት ሠራተኛውን ደብድቦ የሁለቱ አገሮችን ግንኙነት አሻክሮ ነበር፡፡ ጣሊያን ውስጥ ለፔሩጂያ ክለብ እግር ኳስ የተጫወተው አል-ሰዓዲ ጠብ የለሽ በዳቦ ነው ይላሉ፡፡ በሊቢያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ጄኔራል ክሬትዝ የሕግ ባለሙያ የሆነችውና የጋዳፊን የአጎት ልጅ ያገባቸው አይሻ (ከሁሉም ለእሷ ፍቅር አላቸው) የተባለች ልጃቸው የሕግ ባለሙያ ስትሆን በአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የሜጀር ጄኔራልነት ሥልጣን አላት፡፡ ከልጆቻቸው ውስጥ ከሚስ የ32ኛ ወታደራዊ ብርጌድ አዛዥ ነው፡፡ ከጋዳፊ ልጆች ውስጥ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ሚና አለው የሚባለው ዶ/ር ሳይፍ አል-ኢስላም ነው፡፡ ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የተመረቀው አል-ኢስላም አባቱ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የነበራቸውን እሰጣገባ እንዲያረግቡ ከእንግሊዝ የስለላ ድርጅት ኦፊሰሮች ጋር ጉልህ ሚና መጫወቱ ይነገራል፡፡ ለውጥ ፈላጊ ነው ይባል ስለነበር የምዕራቡ ዓለም ተስፋ ነበር፡፡

ጋዳፊ የሀብት መጠናቸው ስንት እንደሆነ ባይታወቅም ዛካሪ ሮት የተባለ ፀሐፊ ግን መላው አገሩ የቤተሰቡ ነው ይላል፡፡ አድራጊ ፈጣሪዎች እነሱ ናቸው፡፡ የበኩር ልጃቸው መሐመድን ብናይ የአገሪቱ ቴሌኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የለስላሳ መጠጦች ኩባንያ አዛዥ ናዣዥ ነው፡፡ የአገሪቱ ካዝና የራሳቸው ነው፡፡ ከራሳቸው አልፈው የበርካታ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች የጋዳፊ ተመፅዋች እንደሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ጋዳፊ ከዓመታት በፊት እግራቸውን ተሰብረው ቤት በዋሉ ጊዜ ሊቢያን የውኃ መንገድ ያደረጉ መሪዎች አገራቸው ይቁጠራቸው፡፡

እንባና ሳቅ
አብዮቶች ደም አፋሳሽ አሊያም ሰላማዊ፣ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ካልሆነም አጭር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ንጉሥ ሻህን የገለበጠው የኢራን አብዮት 450 ቀናት አካባቢ ነው የፈጀው፡፡ የአልጣህሪሩ የግብፅ አብዮት ደግሞ 18 ቀናት፤ የሊቢያስ? ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም፡፡ ማለት የሚቻለው የበፊቱ ጋዳፊ አይቀጥሉም፡፡ ጋዳፊ 75 ደቂቃ የፈጀ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ይህ መንፀባረቁን ዓለም አይቶታል፡፡ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የመጨረሻ ንግግር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ጋዳፊን ከቆሰለ ነብር ጋር የሚያመሳስሉ ብዙ ናቸው፡፡ ጋዳፊን በውናቸው አይደለም በህልማቸው መቃወም የሚፈሩት ቤንጋዚዎች በትሪፖሊ ላይ ለሚደረግ ዘመቻ እየተዘጋጁ እደሆነ ቢናገሩም ጋዳፊ “ሊቢያን የፈጠርኳትም የማወድማትም” እኔው ነኝ እያሉ ነው፡፡ የሊቢያ እንቲፋዳ (አብዮት) ከሁለቱ የሚለየው ሰላማዊ ባለመሆኑ ነው፡፡ ጦር ኃይሉም ገለልተኛ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ተቃውሞውን የገለጸበት መሪዎቹም ለመመከት የመረጡበት መንገድ ዘግናኝ ነው የሚመስለው፡፡ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆነው ሊቢያዊ ጋዳፊ እንደ ቱኒዝያው ቤን አሊና እንደ ሙባረክ እንደማይሄዱ እርግጠኞች ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሊቢያና የሕዝቧ ጉዳይ አሳስቦታል፡፡ ስለሆነም ጋዳፊን ከሌሎች የመነጠል ስትራቴጂ እየተከተለ ነው፡፡ አሳሳቢው ጉዳይ ጋዳፊ እየፈጸሙት ያለው ጥፋት ብቻ ሳይሆን ከእሳቸው በኋላ ማን ይመጣል የሚለው ነው፡፡ የጦር ኃይሉ አገር የመረከብ አቅም እንደ ተቋም የለውም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሠራተኛ ማኅበራት የሉም፡፡ አገር ሊመሩ የሚችሉ ፖለቲከኞችም አገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ ስለሆነም አገሪቱ ማን እጅ ትወድቅ ይሆን? የሚለው ፈታኝ ጥያቄ ነው፡፡ ለገዘው ተቃዋሚዎች የሽግግር ብሔራዊ ምክር ቤት እያሉ ናቸው፡፡

ከሊቢያ ሕዝብ ውስጥ አብዛኛው የሚገኘው በትሪፖሊና በቤንጋዚ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው በረሃ ነው፡፡ ስለሆነም ለማንኛውም የፖለቲካ መሪ አንዷን ከተማ ማጣት አደጋ ነው፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ሊቢያ ወደከፋ ቀውስ ልትሸጋገር ትችላለች፡፡ አገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት የማትገባበት አሊያም ምዕራብና ምሥራቅ በሚል ለሁለት የማትከፋፈልበት የከፋ ሁኔታ እንደማይከሰት ምንም ዋስትና እንደሌለ ዘ-ኢኮኖሚስት ዘግቧል፡፡ አማፅያኑ ግን ይህ አይደረግም ባይ ናቸው፡፡ የሊቢያው መሪ ተቃዋሚዎቻቸውን በምልጃ፣ በማስፈራራት ብሎም በማጥቃት ለማንበርከክ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ ተቃዋሚዎች የንጉሡን ዘመን ባለ ሦስት ቀለም ባንዲራ ማውለብለብ ብቻም ሳይሆን የመድበለ ፓርቲ ያለባት ሪፐብሊክ እንመሠርታለን እያሉ ነው፡፡

የሊቢያ ዳፋ
ዓለም ጠፍጣፋ ናት፡፡ በርህን ዘግተህ የምትቀመጥበት ጊዜ አልፏል፡፡ የአንዱ ጣጣ አለመረጋጋት ለሌላው ይተርፋል፡፡ ለዚህም ነው ዓረቡን ዓለም ባመሰው ትርምስ ጮቤ መርገጥ የማይገባው፡፡ የተከሰተው ሁኔታ ጉዳትም ጠቀሜታም አለው፡፡ እነዚህ አገሮች ውስጥ ሥልጣን ላይ የሚወጡት ኃይሎች ፅንፈኛ ከሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡ ጋዳፊ በአፍሪካ ኅብረት ላይ ያላቸው ፍላጎት፣ ሙባረክም ከዓባይ ወንዝና ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን ይደግፋሉ በሚል ጥርስ ውስጥ የሚያስገባቸው ቅን ዜጋ ባይጠፋም የእነሱ ሰላም ለኢትዮጵያም አስፈላጊ ነው፡፡ የዓረቡ ዓለም ለኢትዮጵያ ምርቶች ትልቅ ገበያ ነው፡፡ እዚያ ከሚገኙት ዜጎቻችንም የውጭ ምንዛሪ እናገኛለን፡፡ የባህረ ሰላጤው አገሮች የኢትዮጵያን የልማት ጥረት በገንዘብ ሊደግፉ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ቀውሱ ቶሎ እልባት ካላገኘ ኢትዮጵያም ደሴት አይደለችምና መጎዳቷ አይቀርም፡፡ አዲስ የዓለም አሰላለፍ ያስከትል ይሆን ያሰኘው አብዮት ቱኒዚያ ውስጥ የተቀሰቀሰው በአንድ የጎዳና ላይ ነጋዴ ነው፡፡ አጠቃላይ የሰሞኑን ትኩሳት ትተን የሊቢያን ቀውስ ብንመለከት ለአፍሪካም፣ ለአውሮፓም የስጋት ምንጭ ሆኗል፡፡ ጎረቤቶቿ ቱኒዚያና ግብፅ ብሎም ሌላዋ አፍሪካዊት አገር አልጄሪያ ቀውሱ ሊቢያን ሊያዳክም የሚችል በመሆኑ የሚደሰቱ ይሁኑ እንጂ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቻቸው የሥራ ዕድል አጥተው ስለሚፈናቀሉ ሐሳብ ገብቷቸዋል፡፡ በሊቢያ አለመረጋጋት የከፋ ነገር የሚገጥማት ሌላዋ አገር ሱዳን ስትሆን በተለይም ከደቡብ መገንጠል በኋላ ብቻዋን የምትቀረው ሰሜን ሱዳን ናት፡፡ ይህ ደግሞ ፀጥታዋ አሳሳቢ ለሆነው ሱዳን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ማለት ነው፡፡ ቻድም ብትሆን የጉዳቱ ሰለባ ከመሆን አትተርፍም፡፡ ሌሎች የአካባቢውና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችም ተጠቂዎች ይሆናሉ፡፡ በእስያ በተለይም በቻይና የዋጋ ግሽበት ጫና (Inflationary pressure)  ያስከትላል፡፡

የነዳጅ ዋጋ ግርግር አይወድም፡፡ የሰሞኑ ትርምስ ዋጋውን ያናረው ሲሆን የሊቢያ ቀውስ ሌላ ጣጣ ያስከትላል/አስከትሏልም፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በአካባቢው ያለው ውጥረት የሚባባስ ይሆናል፡፡ ጋዳፊ እንኳን ከሥልጣን ቢባረሩ የችግሩ መዘዝ ለወራት ይንከባለላል፡፡ ከዓለም ነዳጅ ምርት ሰሜን አፍሪካ 35 በመቶውን ይይዛል፡፡ በዓለም በየዕለቱ ከሚመረተው 88 ሚሊዮን በርሜል ሁለቱ ሚሊዮን የሚመረተው ሊቢያ ውስጥ ነው፡፡ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በሁለት መሠረታዊ ሁኔታ ይለዋወጣል፡፡ አንደኛው በወቅታዊ ሁኔታና ወደፊት ሊከሰት ይችላል ተብሎ በሚኖር ስጋት (Current conditions and future expectations) ስለዚህ በዓለም የነዳጅ መናር ሳቢያ እያገገመ ያለው የዓለም ኢኮኖሚ ሌላ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ለክፉ ጊዜ የተቀመጠ 1.6 ቢሊየን በርሜል የዓለም ስትራቴጅክ የነዳጅ ክምችትስ እስከ መቼ ሊዘልቅ ይችላል? ይህን ችግር ለመቅረፍ የዓለም የነዳጅ ድርጅት በሳዑዲ ዓረቢያ ላይ ተስፋውን ቢጥልም ይህም አስተማማኝ አይደለም፡፡ የሊቢያ ነዳጅ አነስተኛ የሰልፈር መጠን ስላለው ለትራንስፖርት ነዳጅ አገልግሎት የመለወጥ ጠቀሜታ አለው፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ ምን እንደሚከሰት ማወቅ አይቻልም፡፡ በተለይም ከሊቢያ ነዳጅ (10 በመቶ) እና ጋዝ የሚጠቀሙ የአውሮፓ አገሮች ክረምቱ አለፈ እንጂ ምን ይውጣቸው ነበር?

ጋዳፊ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ወደ ሊቢያ የተሰደዱ አፍሪካውያንን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ “ሕገወጥ ስደተኞችን በገፍ እንዳለቁባችሁ!” እያሉ ብዙ ገንዘብ ተቀብለዋል፡፡ አሁን ለአውሮፓ አገሮች በተለይም ለጣሊያን ስጋት የሆነው ሊቢያ በገባችበት ቀውስ ምክንያት ከሊቢያ ስደተኞች እንዳይፈልሱ ነው፡፡ አውሮፓዊያን በሊቢያ ያላቸውን ኢንቨስትመንትም ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ ሌላው ጭንቀት የሊቢያ መንግሥት ገንዘብ የፀጥታ ምክር ቤት ላይ እንደቀረበው ቢታገድ ብዙ የአውሮፓ ባንኮች ለኪሳራ ሲዳረጉ በጋዳፊ ቤተሰቦች የሚሠሩ ቢዝነሶችም ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ጋዳፊ አፍሪካ ውስጥ ያሏቸው ቢዝነሶችም ከዚህ አያመልጡም፡፡ ለምሳሌ ኡጋንዳ ውስጥ ያላቸው የቪክቶሪያ፣ የሩዋንዳው ኖቨቴል ኡምባኖ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ዚምባብዌ ውስጥ ያሉ በሊቢያ ፈንድና ኦይል ሊቢያ የተቋቋሙ ሪል ስቴቶች ሊሽመደመዱ ይችላሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ጋዳፊ ከውስጥም ከውጭም ጫና እየበዛባቸውና ሸምቀቆው እየጠበቀ ቢሆንም እንዲሁ በቀናት ውስጥ ላይፈቱ ይችላሉ፡፡ ትሪፖሊ የመጨረሻ ምሽጋቸው ናት፡፡ ፕሮፌሰር ኦማር ቢካዚ በሊቢያ የሚኖሩ ቀጣይ ሁኔታዎችን በተመለከተ ባስቀመጡዋቸው ግምቶች (possible scenarios) ጋዳፊ በመጨረሻዋ ደቂቃ ሳዳም ሁሴን ኩርዶች ላይ እንዳደረጉት ሁሉ የኬሚካል የጦር መሣሪያ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዳፊና በቅርብ ሰዎቻቸው ላይ ከጣለው ማዕቀብ በዘለለ ጣልቃ ሊያስገባው የሚችለው ይህ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዝግጅቱ ውስጥ ውስጡን ተጀምሯል፡፡ ጣሊያን የኔቶ የጦር አውሮፕላኖች ማረፊያዎቿን መጠቀም እንዲችሉ ከሊቢያ ጋር የነበራትን የትብብር ስምምነት ቀዳለች፡፡

ሁለተኛው ሊከሰት የሚችለው ጉዳይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሊካሄድባቸው ይችላል፡፡ የተወሰኑ ጄኔራሎች ይክዱ እንጂ የጦር ኃይሉ አንጃ አልታየበትም፡፡ በተለይም የወታደራዊ ደኅንነቱ አብዱላ አልሳኑሲ የውስጥ ደኅንነት ኃይሉ አዛዥ አል-ቱሃሚ ካሊድና 20 ሺሕ የሚሆነው የጆማህሪያ ፀጥታ ተቋም እንዳለ ነው፡፡ በጋዳፊ የሥልጣን ዘመን ቢደፈጠጥም ለዘመናት በነበረው የእርስ በርስ የውስጥ ጥላቻና ሴራ ሳቢያ የጎሳ ግጭት ስጋት ዝግ ሊሆን አይችልም፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close