በፖሊስ ባልደረቦች ላይ አሰቃቂ ግድያና ድብደባ ተፈጸመ

በታምሩ ጽጌ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ በሁለት ፖሊሶች ላይ፣ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች ባደረሱት አሰቃቂ ድብዳባ፣ አንደኛው ሕይወቱ ሲያልፍ ሌላኛው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት በሕክምና ላይ መሆኑን በኮሚሽኑ የሰው መግደልና ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን አስታወቀ ፡፡ሁለቱ የፖሊስ ባልደረቦች የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. የፀጥታ ማስከበር ሥራ ላይ በነበሩበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 11 ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት አካባቢ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ዲቪዚዮኑ አስታውቋል፡፡

ፖሊሶቹ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በስለት መሆኑን የገለጸው ዲቪዚዮኑ፣ በተደጋጋሚ ሰውነታቸውን በመጨፍጨፍ ከባድ ጉዳት ስላደረሱባቸው ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም፣ አንደኛው የፖሊስ ባልደረባ ወዲያውኑ መሞቱን፣ አንደኛው ደግሞ መናገር ባይችልም እስካሁን በፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እንደሚገኝ ዲቪዚዮኑ ጠቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ በአባላቱ ላይ ግድያና ድብደባ ያደረሱትን ተጠርጣሪዎች ማንነት ማወቁን ገልጾ፣ እስካሁን አለመያዛቸውን ግን አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የ40 ዓመት ዕድሜ ያለው ቢኒያም ገረመው ሸዋጥላና የ34 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድሙ ሱራፌል ገረመው ሸዋጥላ መሆናቸውን በፎቶግራፋቸው ጭምር ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close