ጋዳፊና የጓዶቻቸው ዝምታ

ላለፉት 42 ዓመታት ሊቢያን በአምባገነንነት የገዙት ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ የሥልጣናቸው መጨረሻ የተቃረበ ይመስላል፡፡ የቱኒዚያንና የግብፅን ፕሬዚዳንቶች ቤን አሊንና ሙባረክን ያባረረው የሰሜን አፍሪካ አመፅ በተለይ ለአፍሪካ አምባገነን መሪዎች አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ የሚሉትንና ቀደም ሲል ዓረብ አገሮችን አንድነት፣ በቅርቡ ደግሞ የአፍሪካን አንድ ወጥ መንግሥት ለመመስረት ሞክረው ሳይሳካላቸው የቀረው ጋዳፊ፣ የሊቢያ ፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባው አመፅና የሰጡት የኃይል ምላሽ ዓለምን አስገርሟል፡፡

 በንፁኅን ሠልፈኞች ላይ በአየር ድብደባ ሳይቀር ኢሰብዓዊ ዕርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኙት ጋዳፊ፣ በተመድ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በዓረብ ሊግ እንዲሁም ደግሞ በተለያዩ አገሮች እየተወገዙ ቢሆንም፣ ጉዳዩ በቀዳሚነት የሚመለከተው የአፍሪካ ኅብረት መለሳለስ ግን ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ አጋጣሚውን ኅብረቱ ምንም ተስፋ የማይጣልበት ተቋም መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉም ትችታቸውን የሚሰነዝሩ መሪዎችና የፖለቲካ ተንታኞችም በዝተዋል፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን በሰሜን አፍሪካ የተጀመረው ይኼ ያልተለመደ አብዮት ‹‹የፖለቲካ ሱናሚ›› የሚል ስያሜ የሰጡት ሲሆን፣ የቱኒዚያንና የግብፅን ፕሬዚዳንቶች አሽቀንጥሮ ከሥልጣን ካበረረ በኋላ በሊቢያ፣ በየመን፣ በባህሬንና በአልጄርያ በመሳሰሉ ዓረብ አገሮችም እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ይገኛል፡፡ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችንና የዓለምን ሕዝብ ቀልብ የሳበው ይኼ አመፅ አነሳሱ ድንገተኛ ቢሆንም፣ ለበርካታ ዘመናት የቆየው የሕዝቡ እሮሮና ብሶት የፈነዳበት፣ ሕዝቦች ከአምባገነንነት፣ ከጭቆና፣ ከረሃብና ከድኅነት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ሕዝባዊ ትግል መሆኑን በስፋት እየተነገረ ነው፡፡

ዓለምን ያሸበረው፣ ኅብረቱን ያላሳሰበው አፍሪካዊ ቀውስ

የዩኒቨርሲቲው ምሩቅና ሥራ አጥ ወጣት ቱኒዚያዊው መሐመድ ቡአዚዝ ታኅሳስ 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ራሱን በማቃጠል የለኮሰው አመፅ፣ አሜሪካንና እንግሊዝን እንዲሁም ደግሞ ሌሎች የአውርፓ አገሮችን በተናጠልም ሆነ በኅብረት እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመግለጽ ቀዳሚ የሆኑት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሠልፈኞች ላይ አላግባብ የኃይል ዕርምጃ እንዳይወሰድ ነበር የጠየቁት፤ በቱኒዚያም በግብፅም፡፡ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት እነዚህ መንግሥታት ከሥልጣን እንዲወርዱ በሰላማዊ ሠልፈኞቹ የቀረበላቸውን ሰላማዊ ጥያቄ መጀመሪያ አሻፈረኝ ቢሉም በመጨረሻ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሊቢያ እየፈሰሰ ካለው ደም አንጻር ሲመለከቱት የቱኒዚያና የግብፅ ፕሬዚዳንቶች አወራረድ በብዙዎች የሚደነቅ ነው፡፡

ለእነዚህ ፕሬዚዳንቶች ከሥልጣን መውረድ ምክንያት የሆነው በእነዚህ አገሮች የተነሳው አመፅ ይዞት የተነሳው ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ መላው ዓለም ያደነቀው ቢሆንም፣ እነዚህ አመፆች በመካሄድ ላይ በነበሩበት ጊዜ 16ኛ ጉባዔውን እዚሁ አዲስ አበባ ሲያካሂድ የነበረው የአፍሪካ ኅብረት ግን ትኩረት ሰጥቶ በአጀንዳ ሊወያይበት ቀርቶ አንድም ቃል ትንፍሽ አላለም፡፡ የግብፁ ሙባረክ የሕዝባቸውን ጥያቄ እንዲያዳምጡና የኃይል ዕርምጃ እንዳይወስዱ ከባራክ ኦባማና ከሌሎች የዓለም መሪዎች ጥያቄ ሲቀርብላቸው የአፍሪካ ጉዳዮችን በቀዳሚነት የሚመለከተው የአፍሪካ ኅብረት ግን አልደገፈምም፣ አልተቃወምም፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት፣ ለሕዝባቸው ሰብዓዊ መብትን የነፈጉና በንፁኅን ዜጎች ላይ ኢሰብዓዊ ወንጀል መፈጸማቸው የሚነገርላቸው አብዛኛዎቹ የኅብረቱ አባል መሪዎች ‹‹ነግ በእኔ›› በሚል ስጋት ተጠምደው ቀደም ሲል በሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር፣ በቅርቡ ደግሞ በኬንያ ሰባት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ በዓለም አቀፉ ወንጀለኛ ፍርድ ቤት የተመሠረተው ክስን በመቃወም ግን ቀዳሚ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ እነዚህን ክሶች በማጣጣልና ኅብረቱ እንዲቃወማቸው በመወትወት ቀዳሚ ነበር፡፡ ኤርትራ በሶማሊያ በምታደርገው ጣልቃ ገብነት ማዕቀብ እንዲጣልባት ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ጥያቄ በማቅረብም ኅብረቱ ቀዳሚ ነበር፡፡

በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት መሪዎች በስተቀር ከ20 ዓመታት በላይ ሥልጣን ላይ የቆዩ መሆናቸው የሚነገርላቸው የአፍሪካ መሪዎች አሁን ከተከሰተው አመፅ እየተማሩ አይመስሉም የሚሉ የፓለቲካ ተንታኞች ይበዛሉ፡፡ ‹‹የአፍሪካ መሪዎች ልጆቻቸውን ወይም ሚስቶቻቸውን የማንገስ ዓላማ አላቸው እንጂ ሥልጣን በቃኝ የሚል ስሜት አሁንም የላቸውም፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ ይደገም በተባለበትና በቅርቡ በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ ማሸነፋቸውን የሚናገሩት የኡጋንዳው መሪ ዩወሪ ሙሴቬኒ፣ አሁንም አምስት ዓመት ጨምረው ለ30 ዓመታት እገዛለሁ ማለታቸው መሪዎች በጎረቤታቸው እየተካሄዱ ካሉት አመፆች አለመማራቸውን ይገልጻሉ፡፡ በፈቃደኝነታቸው ወይም ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ከሥልጣን የወረዱ መሪዎችን በመሸለም በአፍሪካ ዲሞክራሲን የማስፈን ዓላማ ያለው ‹‹ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽንም›› ለሁለተኛ ጊዜ የሚሸለም አፍሪካዊ መሪ ማጣቱም ከዚህ ጋር የሚያያዝ መሆኑ ይታመናል፡፡

‹‹በሊቢያ የተጋለጠው ኅብረት››

በቱኒዚያና በግብፅ በተካሄደው አብዮት ምንም ቃል ትንፍሽ ያላለው ኅብረቱ፣ በቅርቡ በሊቢያ ላይ ያወጣው መግለጫ ደግሞ ለባሰ ትችት ዳርጎታል፡፡ ድሮም በብዙዎች በአምባገነንነታቸው የሚታወቁትና ለ42 ዓመታት የገዙት የሊቢያው ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ፣ በምንም ጉዳይ ያልተስማማቸውን አካል ወይም ግለሰብ በኃይልና በጥይት ለመቅጣት ወደኋላ የማይሉ መሪ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በአገራቸው የተነሳባቸውን ሕዝባዊ አመፅም ለመስማት ዝግጁ አይደሉም፡፡ እንደ መሰሎቻቸው የጎረቤት አገሮች ፕሬዚዳንቶች ብዙም ደም መፋሰስ ባልታየበት በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላማዊ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከሥልጣን ለመውረድ አልፈለጉም፡፡ ይልቁንስ በምድርም በአየርም በሠልፈኞቹ ላይ ጥይት እያዘነቡባቸው ይገኛሉ፡፡

የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ጉዳዩን በጀኔቫ የመከረበት ሲሆን፣ ችግሩ ያሳሰበው የድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ግን ያለአንዳች ልዩነት በሙሉ ድምፅ በጋዳፊ ላይ ማዕቀብ ጥሏል፡፡ የሰላማዊ ሠልፈኞች ሕይወትን ለመታደግም፣ ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እያሰበበት መሆኑ ይነገራል፡፡ ለጊዜው የፕሬዚዳንቱና የተባባሪዎቻቸው ገንዘብና ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ያገደ ሲሆን፣ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የጦር ወንጀለኝነት ክስ እንዲመሠረትም ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በሊቢያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው እንደ ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና የመሳሰሉት አባል የሆኑበት የአውሮፓ ኅብረትም ቢሆን ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ የዓረብ ሊግ፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይም ሊወሰዱ የሚገባቸውን አስቸኳይ ዕርምጃዎች አስመልክተው የተለያዩ ሐሳቦችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመፈጸም እያሰቡ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ የአሜሪካ ኮንግሬስ በሊቢያ አየር እንቅስቃሴ ላይ ማዕቀብ ያደረገ ሲሆን፣ በባሕር ጠረፍ አካባቢ የባሕር ኃይል ተዋጊ መርከቦች ማስጠጋቱን ሚዲያዎች እየገለጹ ነው፡፡ እንቅስቃሴውን እንደ ኢራንና አፍጋኒስታን የመሳሰሉት አገሮች እየተቃወሙት ቢሆንም፣ የምዕራባውያን በቅርቡ ጣልቃ መግባት ግን አይቀርም እየተባለ ነው፡፡

ተባይ፣ ማፍያ፣ በሐሺሽ የደነዘዙና የተለያዩ ስያሜዎችን ለተቃዋሚዎቻቸው ሲሰጡ የቆዩት ጋዳፊ አሁን ደግሞ ‹‹አልቃይዳዎች›› በማለት እየተሳደቡ ሲሆን፣ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት አስግቷቸዋል፡፡ ‹‹ምዕራባውያን ወደ አገሬ ከገቡ የሺዎች ደም ይፈሳል፤›› ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

እንደተጠበቀው ባይሆንም፣ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች መሪዎችም በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ስጋት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹም በድፍረት አምባገነኑ ፕሬዚዳንት ጋዳፊ ሥልጣን እንዲለቁና ቀውሱ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ እየጠየቁ ነው፡፡ እንደ ሲኤንኤን ዘገባ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም የወሰዱት አፍሪካዊ መሪ የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ብቻ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ያህያ ጃማ ባለፈው ሐሙስ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ጠይቀው፣ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት ዝምታ ግን ሊቢያ ውስጥ እየሆነ ካለው በላይ አስደንግጦኛል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አስደንጋጩ ነገር የአፍሪካ ኅብረት ዝምታ ነው፡፡ በግንባር ቀደም ሊንቀሳቀስበት ሲገባ በዚህ ጉዳይ ገለልተኛ አካል ሆኖ የሌሎችን መግለጫ እየሰማ ነው፣ ጭራሽም አልተወያየበትም፤›› ብለዋል፡፡

የዓለም ሕዝብ ያወገዘው የጋዳፊ አሰቃቂ ዕርምጃ በአፍሪካ ኅብረት አልተወገዘም፡፡ የአፍሪካውያን ሰብዓዊ መብቶች እንዲጠብቁ፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ መልካም አስተዳዳር ለማምጣት፣ የአኅጉሪቱ ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር መሪ ቃሉ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የአፍሪካ ኅብረት፣ የሊቢያን ጉዳይ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ በብዙዎች ዘንድ ተተችቷል፡፡ የመግለጫው ይዘትም፣ የሊቢያ መንግሥት ‹‹ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅማል›› የሚል ነው፡፡

ዶ/ር ማይክል ጃይ ኬይ ቦከር የተባሉ አፍሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ፣ የኅብረቱን አቋም አሳፋሪ በማለት ተችተው፣ የኅብረቱ ዝምታ ‹‹አፍሪካ የነጮች ሸክም›› (The White Men’s Burden) መሆኗን ያረጋገጠ መሆኑን፣ ኅብረቱ አቅም ቢኖረውም መሪዎቹ ባላቸው አምባገነናዊ ባህሪ ምክንያት የአፍሪካ ችግሮችን ሊፈታ የማይችል መሆኑን ጠቋሚ ነው ብለዋል፡፡ የኅብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበርን ጨምሮ ኅብረቱ ውስጥ ያሉት መሪዎችም በተመሳሳይ ‹‹ነግ በእኔ›› የሚሉ ናቸው በማለትም ተችቷቸዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በሰሜን አፍሪካ በተፈጠሩ ሁኔታዎች በተለይ ደግሞ በሊቢያ ሁኔታ ጠንከር ያለ ዕርምጃ ለመውሰድ አቅም ባይኖራቸውም፣ ጠንካራ መግለጫ አለማውጣታቸው የሚኮንኗቸው የፖለቲካ ተንታኞች ብቻም አይደሉም፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ የሚሠሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ኤክስፐርት፣ በአፍሪካ ኅብረትና በአፍሪካ መሪዎች ሁኔታ እጅግ ማዘናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በኅብረቱ ውስጥ ተሰሚነት አላቸው ያሉዋቸው መሪዎችም የጋዳፊ ዕጣ ፈንታን በዝምታ መመልከት እንደመረጡ ይናገራሉ፡፡ ከሥልጣን ካልወረዱ ዓማፂዎቻቸውን በመደገፍ እንዳይበቀሉዋቸው በመስጋት፡፡ ይህንን ዝምታ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ አንቀጾችን የሚጥስ መሆኑንም እኚሁ ኤክስፐርት ይናገራሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው 15ኛው የኅብረቱ ስብሰባ፣ የአፍሪካ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲመሠረት ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት ያላገኘላቸው ሙአመር ጋዳፊ፣ ከጋናና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ የአካባቢ ባህላዊ ንጉሦችን ሰብስበው ‹‹የአፍሪካ ንጉሠ ነገሥት›› የሚል ስያሜ ለራሳቸው መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡

መረጃ ያልተነበየው የቴክኖሎጂ አብዮት

በመጪዎቹ ወራት፣ ዓመታትና ዘመናት ምን ሊያጋጥም እንደሚችል በተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች እየተተነተነ መፍትሔም ቀድሞ የሚፈለግበት የሉላዊነት (ግሎባል) ዘመን ተብሎ የሚገለጽ ቢሆንም፣ በቱኒዚያ የተከሰተው ግን በየትኛውም ምሁርና የፖለቲካ ተንታኝ ያልታሰበና ያልተገመተ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ በመሆን ቀዳሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

በእስልምና እምነት ተከታይ ዓረብ አገሮች ዘንድ መንግሥትንና ሃይማኖትን ሳይለይ፣ ምዕራባውያን የሚያራምዱትን ዴሞክራሲ በመቀበልና ባለመቀበል የሚደረግ ትግል ‹‹Clash of Civilizations›› በሚል በእነ ሳሙኤል ሃንቲንግተን የቀረቡ የፖለቲካ ትንተናዎች ይገኛሉ፡፡ በምዕራብያውያን ዘንድ ትልቅ ስጋት ሆኖ የቆየው ሽብርተኝነት በአንድ በኩል፣ አሜሪካን ቀዳሚ ያደረገው የፀረ ሽብርተኝነትን ዘመቻ በሌላ በኩል ደግሞ የትንተናው ዋነኛ መገለጫ ተደርጐ ሲታይ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዴሞክራሲ ለማስፈን በተለያዩ አገሮች የምዕራባውያን እጅ ከፍተኛ ሲሆን፣ በዓረብ አገሮች ግን ሃይማኖትንና መንግሥትን ለየብቻ ነጣጥሎ (ሴኩላሪዝም) በምርጫ የሚሞከር ዴሞክራሲ ቀላል አልነበረም፡፡ በኢራን፣ በፓኪስታን፣ በየመን፣ በኢራን፣ በኢራቅ፣ በግብፅ፣ በሱዳን፣ በሳዑዲ ዓረብያ፣ በሊቢያና በመሳሰሉት አገሮች የምዕራባውያንን ትኩረት የሚስበው ከዴሞክራሲ ይልቅ አንድ መሪ ለእነሱ መመቸቱና ሽብርን የሚቃወም ስለመሆኑ ማረጋገጥ ነበር፡፡ ይኼ በብዙዎች ሲተች የቆየው የአሜሪካና የመሰሎቿ ምዕራብ አገሮች የውጭ ፖሊሲ ሌሎች ድሃ አገሮች ከሚከተሉት ፖሊሲ የተለየ መሆኑንና የምዕራባውያንን ጥቅም ብቻ መሠረት ያደረገ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ አገሮቹ ያላቸው የነዳጅና የሌላ ተፈጥሮ ሀብት እንዳይነካ ከአምባገነን መሪዎችም ጋር መሞዳመድ የሚጨምር እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

የምዕራቡን ዓለም አውራ ተደርጋ የምትታየው አሜሪካ ደግሞ፣ በተለይ ዴሞክራሲ የሚሰፍነው በሕዝቦች የራስ ትግል ብቻ ነው የሚሉት ባራክ ኦባማን ወደ ሥልጣን ከመምጣቷ በፊት አንዴ ዴሞክራሲን ለማስፈን ሲባል፣ ሌላ ጊዜ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በምታደርገው ጣልቃ ገብነት፣ አሁን እየታመሱ ባሉት አገሮች አምባገነን መሪዎች በሥልጣን ላይ ለመቆየት መቻላቸውን የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

እነዚህ አገሮች በአሁኑ ወቅት እየተከሰተባቸው ያለው አመፅ፣ የማንም ጣልቃ ገብነት የሌለውና የሕዝቡ ብሶት ያነሳሳው መሆኑንም እየተገለጸ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፣ የአብዮቶቹ ውጤት ሊለያይ ቢችልም መንስዔዎቹ ግን በአብዛኛው ተመሳሳይ መሆናቸውን ነው የሚያስረዳት፡፡ ‹‹የዲሞክራሲን ጥማት›› በአገሪቱ የሚገኙት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተሳስሯቸዋል የሚል እምነት ያላቸው ፕሮፌሰር ገብሩ፣ ‹‹በመስተዋት አዳራሽ ውስጥ የሚኖሩ›› ያሉዋቸው በአፍሪካ ከአንድና ከሁለት አገሮች በስተቀር ሁሉም አመራሮች በሥልጣን ላይ የመቆየት ህልም ያላቸው መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ በነፍጥ የሚደረገው ትግል ዲሞክራሲን እንደማያመጣ የኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮን የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር ገብሩ፣ በአሁኑ ወቅት ለተነሳው አመፅ ትልቅ መሣሪያ ሆኖ ያገለገለው የመረጃ ቴክኖሎጂ መሆኑንም ይናገራሉ፣ ፌስ ቡክንና ትዊተርን በመጠቀም ወጣቱ ያነሳሳው አመፅ መጋጋሉን በመጠቆም፡፡

Advertisements

1 thought on “ጋዳፊና የጓዶቻቸው ዝምታ

Comments are closed.

%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close