ፕሮፌሰር አንድርያስ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አማካሪ ሆኑ

ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ከየካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ ሆነው ተሾሙ፡፡ፕሮፌሰር አንድርያስ ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመሩት ከነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መልቀቃቸውን ከትናንት በስቲያ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስን ይተኳቸዋል ከተባሉት ግለሰቦች መካከል የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ዋነኛው ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር አንድርያስ መልቀቂያቸውን ያስገቡት ከጥቂት ወራት በፊት ሲሆን፣ ይህንንም ያደረጉት በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የፕሬዚዳንት ሥልጣናቸውን ለወጣት ተተኪዎች ማስረከብ በመፈለጋቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የራሳቸውን ሥራዎች መሥራት በመፈለጋቸው እንደሆነ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ በተለይም የጽሑፍ ሥራዎቻቸውን ለመሥራት በቂ ጊዜ እንደሚፈልጉ ደብዳቤው ይገልጻል፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ከጤናቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ደብዳቤው ያትታል፡፡

ፕሮፌሰር አንድርያስ በደብዳቤያቸው ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የኢትዮጵያን ወጣቶች እንድኮተኩት ይህን ወርቃማ ዕድል ስለሰጡኝ ጥልቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በተጨማሪ ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ለሌሎች የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የፕሮፌሰር አንድርያስ ገጸ ታሪክ (ፕሮፋይል) እንደሚያሳየው፣ በዊሊያም ኮሌጅና በዬል ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ያጠኑ ሲሆን፣ በተለያዩ የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ብራውን ዩኒቨርሲቲ፣ ዩሲኤልኤ (ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ ሎስ አንጀለስ)፣ ዩሲ በርክሌይ (ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ በርክሌይ) እና ፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ የተለያዩ ጽሑፎችን አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አንድርያስ በዩኔስኮ የሰብዓዊ መብቶችና ዲሞክራሲ ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ በተለያዩ ሕዝባዊ ድርጅቶችም ሊቀመንበር ናቸው፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close