ወጣቷ በአሰቃቂ ሁኔታ አንገቷን ታርዳ ሕይወቷ አለፈ

Reporter:በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ወጣት በእንግድነት በሄደችበት በጓደኛዋ ቤት የካቲት 7 ቀን 2003 ዓ.ም. አንገቷን ታርዳ ሕይዋቷ ማለፉን ቤተሰቦቿ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ድርጊቱ እውነት መሆኑን ፖሊስ አረጋግጧል፡፡
ወይዘሪት የሹምነሽ ታደሰ የተባለችው ወጣት የምትኖረው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ አዳራሽ ማሠልጠኛ ፊት ለፊት እንደነበር የገለጹት የሟች

ቤተሰቦች፣ አንገቷ በስለት ተቆርጦ ሕይወቷ ያለፈው ግን በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10 ልዩ ቦታው ገርጂ እንቡጥ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወጣቷን አንገት በማረድ ‹‹ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል›› በሚል የተጠረጠረው ካሳሁን ታደሰ የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የሚናገሩት የሟች ቤተሰቦች፤ በስልክ እንደጠራቻትና ለሕይወቷ መጥፋት ምክንያት እንደሆነች የተጠረጠረችው ጓደኛዋ ወይዘሮ ተዋበች ሃይማኖትም በፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋሏን አስታውቀዋል፡፡

የካቲት 6 ቀን 2003 ዓ.ም. ጓደኛዋ በስልክ ጠርታት መሄዷንና እሷው ዘንድ ማደሯን የሚናገሩት የሟች ቤተሰቦች፤ የካቲት 7 ቀን 2003 ዓ.ም. ተጠርጣሪው ወደ ጓደኛዋ ቤት መጥቶ አብረው ምሳ ከበሉ በኋላ፣ የሟች ጓደኛ ፀጉሯን ልትሠራ ስትወጣ ሌሎቹን በመሰናበት አብሯት መውጣቱንና ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ በመመለስ ድርጊቱን እንደፈጸመ ተናግረዋል፡፡

የሟች ቤተሰቦች ጓደኛዋን በተለያዩ ምክንያቶች ለእህታቸው ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆናለች በሚል እንደተጠራጠሯትና ጥርጣሬያቸውንም ለፖሊስ በመንገር መንግሥት የሟችን ደም እንዲወጣላቸው ጠይቀዋል፡፡

የተፈጠረውን አደጋ በሚመለከት ያነጋገርነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን፤ ድርጊቱ መፈጸሙን በመግለጽ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ የሟች ቤተሰቦች በተጠቀሱት አካባቢና ክፍለ ከተማ የካቲት 7 ቀን 2003 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ድርጊቱ መፈጸሙንም ዲቪዚዮኑ ተናግሯል፡፡

ሟች ወይዘሪት የሹምነሽ ታደሰ ጓደኛዋ ዘንድ ሄዳ በነበረችበት ጊዜ ተጠርጣሪው ካሳሁን ታደሰ በእንግድነት መጥቶ እንደነበርና የሟች ጓደኛ ስትወጣ አብሮ ወጥቶ ከደቂቃዎች በኋላ በሻንጣ ውስጥ ይዞት የነበረውን ስለት፣ ፕላስተር፣ መቀስና አርቲፊሻል ሽጉጥ ይዞ በመመለስ፣ ሟች በጓደኛዋ መኝታ ቤት እንዳለች አንገቷን በስለት አርዶ ሕይወቷ እንዲያልፍ ማድረጉን ዲቪዝዮኑ አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪው ድርጊቱን በሚፈጽምበት ወቅት የወይዘሮ ተዋበች እህት፣ ሠራተኛና ሕፃናት እንደነበሩ የገለጸው ፖሊስ፣ እህትየዋን ግንባሯንና እጇን በስለት በመቁረጥ የእሷንና የሠራተኛዋን አፍ በፕላስተር ሲያሽግ፣ ሕፃናቱ በመጮኻቸው እነሱን ሊያስፈራራ ሲወጣ ጉዳት የደረሰባት የወይዘሮ ተዋበች እህት ሸሽታ በመውጣት የድረሱልኝ ጩኸት በማሰማቷ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር መዋሉን ዲቪዚዮኑ አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪው ራሱን ለማጥፋት ሆዱን በስለት ቢቆርጥም በተደረገለት ሕክምና መዳኑንና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ቀጣይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ዲቪዚዮኑ ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው ለፖሊስ በሰጠው ቃል ከሟች ጋር ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለውና ገንዘብ በመፈለጉ ብቻ መሆኑን መናገሩንም ጠቁሟል፡፡ የሟች ጓደኛንም በቁጥጥር ሥር በማድረግ ከወንጀሉ ጋር ‹‹ግንኙነት አላት ወይስ የላትም›› የሚለውን በማጣራት ላይ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

 

Advertisements

1 thought on “ወጣቷ በአሰቃቂ ሁኔታ አንገቷን ታርዳ ሕይወቷ አለፈ

Comments are closed.

%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close