ቃለ መጠይቅ – አቶ መለስ ዜናዊ ከአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት መልስ

-የአፈጻጸም ድክመትን ለማሻሻል መድረኮች ባሉበት ኹኔታ ሕዝቡ ወደ ነውጥ ይገባል ማለት የተዛባ አመለካከት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ሊኾን የሚችልበት ኹኔታ የለም።

– የግብፅ መረጋጋት የሚጠቅመው ለእነሱም ለእኛም ነው። የዐባይ ውኃን በተመለከተ አሁን የተከሰተው ኹኔታ የመንግሥት አስተሳሰብ ለውጥ ይፈጥራል ብዬ አላስብም። የግብፅ ፖለቲከኞች የዐባይ ውኃን እንደ አደንዛዥ ዕፅ ነው የሚጠቀሙበት። የውጭ ጠላት ፈጥረው ሕዝቡን ወደ ገዢው መደብ የሚያሰባስቡበት ነው።

-የኤርትራ መንግሥት ፕሮግራሙን እንዲቀይር ካልኾነ መንግሥቱ እንዲቀየር ኹኔታዎችን በዲፕሎማሲ በማመቻቸት ጥረት ማድረግ አለብን ብለን ስትራቴጂ ነድፈናል።

-ወርኀዊ ደሞዜን በተመለከተ ፀረ ሙስና የሁሉንም ባለሥልጣናትን ደመወዝ ያወጣ ይመስለኛል። ካልኾነ ግን የእኔ ደሞዝ ስድስት ሺሕ አራት መቶ ብር (6400) ነው። የደሞዝ ጭማሪው ገና እኔ ጋራ ስላልደረሰ የተጨመረልኝን አላውቀውም::

በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያም ሊከሰት ይችላል ወይ? የሰሜን አፍሪካ ነውጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰት ይችላል በሚል ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያራምዱት ነው። የእኛ ሕገ መንግሥት ትግሎች በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄዱ ሰፊ ጎዳና የከፈተ ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ የሥልጣን ለውጥ ሕገ ወጥ መኾኑን አስቀምጧል። እያንዳንዱ ዜጋም ሕገ መንግሥቱን ማክበር እና ማስከበር እንዳለበት አስቀምጧል። በዚህም ላይ ከዐሥር ወር በፊት ምርጫ ተካሂዶ ኅብረተሰቡም የነበረው መንግሥት እንዲቀጥል በካርዱ ብይን ሰጥቷል። ኅብረተሰቡ ከዚያ በፊት የነበረውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ዐይቶ በምርጫው እንቅስቃሴ ላይ ሐሳቡን ገልጧል። በተነጻጻሪ ከእናንተ በተሻለ የልማት ሥራ የሚሠራ የለንም ብሎ የአምስት ዓመት ኮንትራት ለኢሕአዴግ ሰጥቷል። ሕዝቡ ኢሕአዴግን እንዲሠራ ብቻ አይደለም ዕድል የሰጠው፤ ስኅተት ስላለም እርሱንም አሻሽሉ ብሎ ነው ወጥሮ ይዞ ድምፁን የሰጠን። ኢሕአዴግ የለውጥ እና የቀጣይነት አጀንዳ ይዞ ነው የቀረበው። ሕዝቡም ለዚህ የአምስት ዓመት ኮንትራት ሰጥቶታል። ኢሕአዴግ ይኼን ካልፈጸመ ሕዝቡ በሚቀጥለው ምርጫ ሊዘርረው እና ሊያባርረው እንደሚችል ኢሕአዴግም ሕዝቡም ያውቃል። ይህ በኾነ በዐሥር ወር ውስጥ መንግሥትን በነውጥ የሚያስወግድበት ምንም ሎጂክ የለም። ለዚህ ነው ሰሜን አፍሪካ እንዳለው ኹኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም የምንለው። በአሁኑ ሰዓት ኢሕአዴግ ኮንትራቱን ለመፈጸም ነው ሌት ተቀን የሚሠራው። ሕዝቡም መንግሥትን ሊገመግም በቂ መድረክ አለው። የአፈጻጸም ድክመትን ለማሻሻል መድረኮች ባሉበት ኹኔታ ሕዝቡ ወደ ነውጥ ይገባል ማለት የተዛባ አመለካከት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ሊኾን የሚችልበት ኹኔታ የለም። እኔን እንቅልፍ እንዳልተኛ የሚያስጨንቀኝ የአምስት ዓመት ፕሮግራማችንን ማስፈጸም መቻላችን ነው። ይህ ማለት ግን ነውጥ ለመቀስቀስ የሚሞክሩ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም። በዚህ ላይ የማያሻማ አቋም የወሰደው ሻዕቢያ ነው። አዲስ አበባን ባግዳድ አደርጋታለሁ ብሎ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን ሁሉ ሰብስቦ መሣርያ እና ፈንጅ እያስታጠቀ እየላከ ነው። በቅርቡም በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ አስታጥቆ ሲልክብን ነበር፤ በሽብር መልኩ እስከ አሁን አልተሳካላቸውም። ከጥቂት ደኅንነቶች እና ከጥቂት ፖሊሶች ሊያመልጡ ቢችሉም ከ 80 ሚልዮን ሕዝብ ግን ሊያመልጡ አይችሉም። ይህ ካልተሳካ በጎዳና ነውጥ ለማተራመስ ሻዕቢያ በተላላኪዎቹ በኩል እየሠራ ነው። አዲስ አበባ ላይ በቂ መዋቅር የሌለውን ኦብነግን ሳይቀር መመሪያ ሰጥቶ እየሠሩ መኾናቸው ይታወቃል። ሌሎቹ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ኹኔታዎች ሲያመቻቸው ሸርተት እያሉ መሄዳቸው እና መታሰር፤ ይቅርታ ጠይቆ መፈታት፤ ተመልሶ መታሰር መንግሥትን እንደሰለቸው ሁሉ እነርሱንም ይሰለቻቸዋል ብለን እናስባለን። በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ስላሉ አገራት ወቅታዊ ኹኔታዎች በሰሜን አፍሪካ እና በአንዳንድ የዐረብ አገራት ያለውን ኹኔታ ሰፋ ባለ መልኩ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ያሉት በሰሜን አፍሪካ ግብፅ፣ ቱኒዚያ እና የመን ነው። ትልቁ ስጋትም የመን ላይ ነው ያለው። ምናልባት ትልቅ የፖለቲካ ስጋት ፈጥሮ የመን የምትበታተንበትን እና የመን ውስጥም የመሸጉት አሸባሪዎች ቀዳዳ እንዳያገኙ ስጋት አለ። የመን ለእኛም የቅርብ ጎረቤት ስለኾነች እናም በቅርብ እየተከታተልነው ነው። ሌላው የግብፅ ጉዳይ ነው። የግብፅ መረጋጋት የሚጠቅመው ለእነሱም ለእኛም ነው። የዐባይ ውኃን በተመለከተ አሁን የተከሰተው ኹኔታ የመንግሥት አስተሳሰብ ለውጥ ይፈጥራል ብዬ አላስብም። የግብፅ ፖለቲከኞች የዐባይ ውኃን እንደ አደንዛዥ ዕፅ ነው የሚጠቀሙበት። የውጭ ጠላት ፈጥረው ሕዝቡን ወደ ገዢው መደብ የሚያሰባስቡበት ነው። አሁን ያለው የግብፅ ለውጥ የሕዝቡን ጥያቄ፣ የፖለቲካ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ በዐባይ ውኃ ጉዳይ አሁን ያለው መንግሥትም፣ በኋላ በምርጫ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀውም መንግሥት በዐባይ ውኃ ላይ የተለየ አቋም ያራምዳል ብዬ አልገምትም። የሊቢያ ጉዳይ በቀጥታ እኛን አይመለከትም፤ ግን በተዘዋዋሪ ይመለከተናል። ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እየጎዳን ነው። የእኛ ተስፋ አሁን ያለው አስከፊ አካሄድ ቆሞ ጉዳዩ በሰከነ እና በሠለጠነ ኹኔታ ይፈታል የሚል አመለካከት አለኝ። ከጸጥታ አኳያ በቀጥታ የሚነካን የየመን ጉዳይ ነው። ሌላው በተዘዋዋሪም ቢኾን እንዳሻቸው አንልም። የሕዝብ መብት ተጠብቆ እንዲኖር እንመኛለን። በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ መንግሥት በአግባቡ እየሠራ አይደለም ስለመባሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊቢያ ውስጥ ኤምባሲ የለውም። ሱዳን ያለው ኤምባሲ ነው ይኼን ደርቦ የሚሠራው። ችግሩ ኢትዮጵያውያኑ በሕጋዊ መንገድ የገቡ አለመኾናቸው ነው። ይኹን እንጂ እርስ በእርስ ስለሚተዋወቁ እና አንድ አካባቢ ስለሚቀመጡ የመረዳዳት እና አብሮ የመኖሩ ባህልም ስላለ በአካባቢው ታዋቂ ሰዎችን በማነጋገር በዚህ መንገድ በማሰባሰብ በብዙ መቶ ሰዎች ሊስት አድርገናል። በሊቢያ ተጨባጭ ኹኔታ መንግሥታቸው ቅጥረኛ የአፍሪካ ወታደሮችን በመቅጠሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ይዞ መሄድ አደጋ ስላለው ሱዳኖቹ የእነርሱን ሰዎች ሲያወጡ አንድ ላይ የእኛን ሰዎችም እንዲያወጡ ስምምነት ላይ ደርሰናል። እንዲያውም የሱዳን መንግሥት የእርሱ ሰዎች ብዙ ስለኾኑ እና ኢትዮጵያውያኖቹ ጥቂት በመኾናቸው ቅድሚያ የእናንተን ሰዎች እናወጣለን ብሎናል። እንደምታውቁት አብዛኛዎቹ በእግር ወደዚያ የሄዱ እንደመኾናቸው አውሮፕላንም መርከብም ሳይጠብቁ በእግርም እየመጡ ያሉ አሉ። ችግሩ ግን የከፋ ነው። ሌሎችን ደግሞ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ በአውሮፕላን እና በመርከብ ለማውጣት እየተነጋገርን ነው። የኤርትራ መንግሥትን ከሥልጣን ለማውረድ የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ ስለነደፈው ስትራቴጂ የኤርትራ መንግሥት የያዘው ስትራቴጂ አካባቢውን ማተራመስ ነው። ሰሞኑን ደግሞ በጅቡቲ ምርጫ ስላለ ይህን ለማተራመስ የሚያስገባው ፈንጂ የትየለሌ ነው። በሶማልያ የሚሠራው ይታወቃል። ይህ መንግሥት የጥፋት ቡድን ነው። 24 ሰዓት ስለ ሰላም እና ልማት ሳይኾን ስለ ሽብር ነው የሚሠራው። ይህ ሥርዐት ለኢትዮጵያ እና ለጅቡቲ ብቻ ሳይኾን ለኤርትራም ጭምር አደጋ ነው። ኤርትራ ወጣት የሌለባት አገር እየኾነች ነው። ወጣቱ እየተተኮሰበት ነው ከአገሩ የሚሸሸው። ስለዚህ ሁልጊዜ አካባቢው ላይ እሳት የሚጭር መንግሥትን እሳቱን እያጠፉ መቀጠል አይቻልም፡፡ ስለዚህ ወይ ፕሮግራሙን እንዲቀይር ካልኾነ መንግሥቱ እንዲቀየር ኹኔታዎችን በዲፕሎማሲ በማመቻቸት ጥረት ማድረግ አለብን ብለን ስትራቴጂ ነድፈናል። የደርግ ባለሥልጣናት በምኅረት የመለቀቅ ኹኔታ በተመለከተ የደርግ ባለሥልጣናት ወንጀል ጉዳይ ክርክር የሚያስነሳ አይመስለኝም። ሥርዐቱም የከፋ የወንጀል ሥርዐት ነው። የሐይማኖት አባቶችም ይህን ገፈት የሚያውቁት ይመስለኛል። አሁን እየተደረገ ያለው የሥርዐቱን ወንጀለኝነት ለጥያቄ ማቅረብ አይደለም። ይህ ድሮም ይታወቃል በሕግም ተረጋግጧል። የምኅረት ጥያቄው በሐይማኖት አባቶችም መነሳቱ ስኅተት አይደለም። እንደተባለውም ሰዎቹ ዕድሜያቸው እየገፋ ነው። ሕገ መንግሥቱም የሞት ፍርድ የተፈረደበት ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ይቀነሳል እንጂ መፍታትን አይፈቅድም። ይኹን እንጂ በሕገ መንግሥቱ ሥር ኾኖ የተወሰነ ጊዜ ከታሰሩ በኋላ የአመክሮ ጉዳይ አለ። እዚህ ላይ ዋናው ነገር ሕገ መንግሥቱ አይጣስም። የሐይማኖት ሰዎችም ይኼን በማንሳታቸው ስኅተት አልሠሩም። ጉዳዩ መንግሥት ጋራ ሲቀርብም በአግባቡ ያስብበታል። ጥያቄውንም ያደምጣል። እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልተደረሰም። መሬት ዘርፈዋል ስለተባሉት ባለ ሀብት እና የመንግሥት ሐላፊዎች መሬት ከዘረፉት ባለ ሀብቶች ጥቂቶቹ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱ አሉ። አብዛኛዎቹ ጥፋተኝነታቸውን አምነው በመጸጸታቸው በይቅርታ ታልፈዋል። የመንግሥት ሐላፊዎች ግን ይባረራሉ፣ በሕግም ይጠየቃሉ። ስለ ወር ደሞዛቸው ወርኀዊ ደሞዜን በተመለከተ ፀረ ሙስና የሁሉንም ባለሥልጣናትን ደመወዝ ያወጣ ይመስለኛል። ካልኾነ ግን የእኔ ደሞዝ ስድስት ሺሕ አራት መቶ ብር (6400) ነው። የደሞዝ ጭማሪው ገና እኔ ጋራ ስላልደረሰ የተጨመረልኝን አላውቀውም።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close