ትውልደ ኢትዮጵያዊው የሕክምና ባለሙያ ከኬንታኪ ገዢ የክብር ሽልማት አገኙ

ትውልደ ኢትዮጵያዊውና የ‹‹ሰዎች ለ ሰዎች›› መሥራች ዶክተር እናውጋው ማሐሪ ስላደረጉት ሰብዓዊ አገልግሎት ከኬንታኪው ገዢ ስቲቨን ኤል በሸሂር የክብር ሽልማት አገኙ፡፡

ገዢው በሽሂር በቅርቡ ለዶክተር እናውጋው የሰጡት ሽልማት፤ በአሜሪካ ኬንታኪ ግዛትና በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሙያና በገንዘብ እያስተባበሩ በሚያንቀሳቅሱት ‹‹ፒፕል ቱ ፒፕል ኔትወርክ›› አማካይነት በዓለም በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ለሚገኙና በኤችአይቪ/ኤድስ በጣም ለተጐዱ ሕዝቦች ለሚሰጡት የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ክብር መገለጫ ነው፡፡

በኔትወርኩ ሥር በበጐ ፈቃደኝነት የታቀፉት ባለሙያዎች ክህሎታቸውን፣ ሀብታቸውንና ጊዜያቸውን በማቀናጀት በዓለም የተጐዱ ሕዝቦችን ሕይወት በመታደግና ተስፋ በመስጠት የበኩላቸውን አየተወጡ እንደሚገኙም ገዢው ጠቅሰዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዶክተር እናውጋው የመሠረቱት ‹‹ፒፕል ቱ ፒፕል››ን ወደ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅትነት በማስፋት በኤድስ ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት ድጋፍና እንክብካቤ በመስጠት፣ የጤና ትምህርት፣ ስኮላርሺፕና ተደራሽ ላልሆኑ ሥፍራዎች የቴሌ ሜድስን ሕክምናን በማድረስ የአገልግሎት አድማሱን እንዲያሰፋ ላደረጉት አስተዋጽኦም ሽልማቱ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ዶ/ር እናውጋው ለአሜሪካዋ ኬንታኪ ግዛት ነዋሪዎችም ቢሆን ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የበጐ ፈቃድ አገልግሎታቸውን መቸራቸው አስመስግኗቸዋል፤ አሸልሟቸዋል፡፡

በኬንታኪ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች የጤና ኢንሹራንስ የላቸውም፡፡ ዶ/ር እናውጋውና ፒፕል ቱ ፒፕል እነዚህ ሕዝቦች የተሻለ የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማስቻል በሮዋን አካባቢ የፒፕል ቱ ፒፕል ክሊኒክ አቋቁመዋል፡፡

በክሊኒኩ የጤና ኢንሹራንስ መክፈል ያልቻሉ አሜሪካውያን ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት በመሆኑ ዶ/ር እናውጋውንና ፒፕል ቱ ፒፕል ለዓለም ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ፤ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙ መሆኑም ተነግሯል፡፡

‹‹የሰዎች ችግር በሰዎች ይፈታል›› ከሚል ዓላማ በመነሣት ኔትወርኩ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፕሮግራሙ፣ ከሙያውና እርስ በርሳቸው በግንባር እያገናኘ የሚሠራ የሰብዓዊ አገልግሎት ተቋም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከጤና ባሻገር በትምህርት፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች የሚሠራ ሲሆን፣ የፌስቱላ ሆስፒታልን ለመርዳት ከሚንቀሳቀሰው በተጨማሪ በድንገተኛ ሕክምና፣ በወጣቶች ትምህርት፣ በሙያ ሥልጠናና በኤችአይቪ ዙርያ ይሠራል፡፡

የሕክምና ትምህርታቸውን በመጀመሪያ በቼኮዝላቫኪያ ቀጥሎም በካናዳና በአሜካ የተከታተሉት ዶ/ር እናውጋው በኦክላንድ መሠረቱን ካደረገው ለትርፍ ያልተቋቅመ ‹‹ዘ አፍሪካን አሜሪካን አትሌቲክስ ስፖርትስ ኦፍ ፌም›› በ2000 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ የሰብዓዊ አገልግሎት ሽልማት እንዲሁም ከአሜሪካ አካዴሚ ኦፍ ኒውሮሎጂ በ2002 ዓ.ም. አጋማሽ በኢትዮጵያ የኤድስ ሕሙማንና የነርቭ ሕክምናን ለማሻሻል ባደረጉት ሥራ ‹‹ፔሸንት አድቮኬት ኦፍ ዘ ይር አዋርድ›› ካገኙዋቸው ሽልማቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ፒፕል ቱ ፒፕል ለትርፍ ያልተቋቋመና መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትውልደ ኢትዮጵያዊውንና ኢትዮጵያዊውን እንደ ድልድይ ሆኖ በማገናኘትና ዲያስፖራው ለትውልድ አገሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ ይሠራል፡፡ ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ይኸው ድርጅት በኢትዮጵያም ቢሮ ያለው ሲሆን፣ በካናዳ፣ በስዊድንና በፊንላንድም እየሠራ ይገኛል፡፡

ዶ/ር እናውጋው መሐሪ ኒውሮሎጂስት ሲሆኑ፣ ከ10 ዓመታት በፊት ለመሠረቱት ‹‹ፒፕል ቱ ፒፕል ግሎባል ኔትወርክ›› ፕሬዚዳንት ናቸው፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close