ግብፆች ሙባረክን እንጂ ናይልን አላጡም!

ግብፆች ሙባረክን እንጂ ናይልን አላጡም!

SUNDAY, 13 MARCH 2011

በመለሰ ዓ.

በሱዳን አምዱርማን አህሊ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር አሊ አብደላ በቅርቡ ለንባብ ባበቁት ጽሑፍ ግብፆች በናይል ውኃ አጠቃቀም ላይ ፍትሐዊና እኩል የሚለውን መርህ መቀበልን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርገው መመልከታቸውን ማቆም እንዳለባቸው በማያወላዳ ቋንቋ ነው የገለጹት፡፡

ይህ አስተያየት በናይል ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች አሸናፊ የሚሆኑበት (win – win) መፍትሔ ይኑር የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት አቋምን የሚደግፍ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ አጐራባች አገሮች በርካታ ወንዞች ይፈሳሉ፡፡ ከሌሎች የአጐራባች አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሱ ወንዞች ብዙም የሉም፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ወንዞቹ ለሁሉም የአካባቢው ሕዝቦች ጠቀሜታ ይዋሉ የሚለው አቋሟ በላይኛው የተፋሰስ አገሮች የተለመደ አይደለም፡፡ ለላይኛው ተፋሰሶች ውኃ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲያዊና የወታደራዊ ጡንቻ ነው፡፡ በናይል ላይ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት አለን የሚሉት አገሮች ይህን ባያጡትም ሃቁ ይኸው ነው፡፡

በገዛ ዳቦዬ…….
የናይልን ውኃ ጥቅም ላይ ለማዋል ከተናጠል ጥረት በዘለለ በተፋሰሱ አገሮች መካከል የጋራ ርብርብ ሲደረግ ማየት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ ተፋሰሱ ከአፍሪካ የቆዳ ስፋት አንድ አስረኛውን የሚሸፍን፣ ከ300 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርበትና በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ ቢሆንም፣ ብዙ ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ የተፋሰሱ አገሮች ይህን ለማድረግ ያልታደሉት የመጀመርያውና ዋነኛው ምክንያት የግብፅና የሱዳን ‹‹ታሪካዊ መብት›› ያስከበረ የቅኝ ገዢዎች ዘመን ሰለባ በመሆናቸው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በተፋሰሱ አሮች ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር በመቆየቱና ኢኮኖሚያቸውም በውኃ ላይ የሚቻልን ልማት መሸፈን ሳይችል በመቆየቱ በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች ይቀርብ የነበረው የፍትሐዊና እኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ይህ ለአንድ ወገን ያደላ ስምምነት እንዲጸና የተለያዩ ወገኖች ለግብፅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ማድረጋቸው ሌላው ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ግብፅ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥና በዓረቡ ዓለም ባላት ተሰሚነት ሳቢያም ሌሎች አገሮች ውኃውን ተጠቅመው እንዳያለሙ፣ ለልማታቸው ብድር እንዳያገኙ በማድረግ  ሰላማቸውን በማወክ ለራሷ የተሳካ ሥራ ሠርታለች፡፡ ግብፅ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ላይ ያላትን ሚና ሳይቀር ለተመሳሳይ ዓላማ ስትጠቀምበት እንደቆየች ይነገራል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የተፋሰሱ አገሮች ለዚህ የሚመጥን የአፀፋ ዕርምጃ ለመውሰድ የነበራቸው አቅም አናሳ በመሆኑ ሁሉም ነገር ለግብፅ ቀና ነበር፡፡ በተለይም አገራችን የግብፅ ተጽእኖ እንዳለ ሆኖ በራሷ ችግር በመተብተቧ ሳቢያ ለናይል ወንዝ የአንበሳውን ድርሻ ውኃ ብታበረክትም ዓባይንና ገባሮቹን ትርጉም ባለው መልኩ ተጠቅማለች ማለት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ የግብፅ መሪዎች ስትራቴጂካዊ የደኅነት ጉዳያችን ነው በሚሉት ናይል ሳቢያ ዛቻና ማስፊራሪያ ከመሰንዘር ቦዝነው አያውቁም፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ተመራማሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ክንፈ አብርሃ የግጭትና የትብብር ታሪክ ባለው የአፍሪካ ቀንድና አካባቢ ናይል ላይ ወደ ትብብር የመቅረብ አዝማሚያ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1967 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት የውኃና የአየር ጠባይ መረጃ በመሰብሰብ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚያ በመቀጠል እ.ኤ.አ በ1993 የናይል ተፋሰስ የልማትና የአካባቢ ጥበቃ ቴክኒክ ትብብር በካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ሲዳ) አማካይነት በ1997 ደግሞ በዓለም ባንክ የተጀመረው የናይል ተፋሰስ አገሮች የትብበር ጥረቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የኩርንችት ዘመን

በእርስ በርስ ጦርነት ሲታመሱ የነበሩት የላይኛው የናይል ተፋሰስ አገሮች አንጻራዊ ሰላም በማግኘታቸውና ፊታቸውን ወደ ልማት በማዞራቸው፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ጀምረዋል፡፡ በተለይም ከሕዝብ መጨመር ጋር ተያይዞ ናይልን ለኃይል ምንጭ፣ ለመስኖና ለሌሎች ተዛማጅ ጥቅሞች የማዋል ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ መንፈስ በናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ /Nile Basin Initiative/ ዙሪያ ለአሥር ዓመት ያህል እልህ አስጨራሽ ክርክር በማድረግ የመጨረሻው ስምምነት ግንቦት 6 ቀን 2002 ዓ.ም. ሲደርስ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ኬንያ ሲፈርሙ ግብፅና ሱዳን ተቅውመው ነበር፡፡ ቡሩንዲና ዴሞክራቲክ ኮንጐ በይደር ቆይተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ስምምነቱን ስድስት አገሮች መፈረም ስለነበረባቸው ሁኔታዎች በእንጥልጥል ቢቆዩም፣ ቡሩንዲ ሰሞኑን ስምምነቱን (Comprehensive Framework Agreement) የፈረመች ሲሆን፣ ኮንጐም የቀን መቁረጥ ጉዳይ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ የእነዚህ ሁኔታዎች መለዋወጥ ንዝረት የፈጠረባቸው ከተሞች ካርቱምና ካይሮ ናቸው፡፡ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር የቡሩንዲ ውሳኔን ተቀባይነት የሌለው ነው ያሉት በደቡብ ሱዳን የመገንጠል ውሳኔ መንፈሳቸው ለተጐዱ ሰሜን ሱዳናውያን መጥፎ ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ የግብፅ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ሙና ኦማር ከዚህ የተለየ አቋም አላሳዩም፡፡ አል-አህራም ጋዜጣ ሌላ ራስ ምታት በሚል ርዕስ ሰሞኑን እንደዘገበው፣ ግብፅ ከአዲሱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚመጥን ስትራቴጂ መቅረጽ ይኖርባታል፡፡ ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኅንም ይህ ጊዜ ከወቅቱ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ጋር በማያያዝ ለግብፅ የኩርንችት ዘመን አድርገው ሊያቀርቡት ይዳዳቸዋልና የስምምነቱን ትክክለኛ ትርጉም ማስረዳት ይገባል፡፡ በዚህ ስምምነት አሸናፊዎች እንጂ ተሸናፊዎች አይኖሩምና ‹‹ግብፆችን ሳይታጠቁ ደረስንባቸው›› ዓይነት ስሜትም ማንጸባረቅ ብልህነት አይመስለኝም፡፡ ጉዞው ረጅም ነው፡፡ ግብፅ ውኃውንም መሪዋንም አጣች ለሚለው ሟርትም ምላሹ ናይልን አታጡም የሚል መልዕክት መሆን ይገባዋል፡፡

እዚህ ላይ የቡሩንዲ መፈረም አዎንታዊ ዕርምጃ ነው፡፡ የዴሞክራቲክ ኮንጐ ጉዳይም  ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ በቀጣይም አስፈላጊ ጉዳይ በቅርቡ 54ኛ የአፍሪካ አገር የምትሆነው ደቡብ ሱዳን ውሳኔ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ደቡብ ሱዳን ቀደም ሲል በካርቱም የተፈረመው ስምምነት ተገዢ እንድትሆን አትገደድም፡፡ ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ቆማ ስምምነቱን ብትፈርም የላይኛው ተፋሰስ የተሻለ የኃይል ሚዛን እንዲኖረውና በካይሮና በካርቱም ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ይህ ካልሆነና ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን በእነ ግብፅ ተጽእኖ ሳቢያ ካልፈረመች በናይል ላይ የሚደረገው ድርድር ላይ ሌላ ሦስተኛ አካል ተሳታፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከደቡብ ሱዳን መገንጠል በኋላ የሰሜኖቹ ዕጣ ፈንታ ወዴት አቅጣጫ ይሄዳል የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ ከሱዳን ሆነ ከግብፅ በፊት ከነበረው የተለየ አቋም መጠበቅ አዳጋች ነው፡፡ ስምምነቱን ይፈርማሉ ተብሎ አይጠበቁም፡፡ ግብፅ ውስጥ ማንም ሄደ ማንም መጣ በናይል ጉዳይ አንድ ናቸው፡፡ ፒ. ጐድሬል ኦክት የተባሉ የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪ ግብፃውያን እንደዚህ ዓይነት ስሜት ያላቸው በውኃ እጥረት ስጋት (Water Stress Phobia) ስለሚሰቃዩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም ለግብፆች ናይል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው አካል ነው፡፡
በተለይ ግብፆች እስራኤል ከኢትዮጵያ ጀርባ ነች የሚል ከመላ ምት ያለፈ እምነት አላቸው፡፡ አንድ እስራኤላዊ ባለሥልጣን ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉዞ እጅጉን ያሳስባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ግብፆች የዓረቡ ዓለም ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡

ናይል ውኃ ብቻ አይደለም!
በፕሬዚዳንት ሁሴን ሙባረቅ የመጨረሻ ሳምንት የሥልጣን ዘመን ውስጥ እንደ አሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተቸገረ ሰው አልነበረም፡፡ ባራክ ኦባማ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ. ባይደን እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተ የሰጡት መግለጫ የተሳከረ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ የኦባማ ብቸኛ አማራጭ የሆስኒ ሙባረክን እግር እየተከትሉ መግለጫ መስጠት ነበር፡፡ በግብፅ ፖለቲካ በተዘዋዋሪም ቢሆን ተጽእኖ አለው የሚባለው የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤትማ በይፋ ቃል አልተነፈሰም፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያት ባለቀ ሰዓት የማይገባ መልዕክት ላለማስተላለፍ ሲባል ነው፡፡ ማሀንዱራ ኩማር የተባለ ህንዳዊ ተመራማሪ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ላይ በጻፉት መጽሐፍ እንዳመለከቱት አገሮች በዲፕሎማሲው መስክ የውጭ ጉዳያቸውን ሲያስፈጽሙ ሌላው አገር ስለነሱ ያለውን አመለካከት እንዲያስተካክል አልያም ጥሩ ከሆነ በያዘው እንዲቀጥልና በዚህም ብሔራዊ ጥቅማቸው እንዲጠበቅ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ አሜሪካኖቹ ቀደም ሲል በተጠቀሰው መንገድ የተቸገሩት ዋና ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ ያላቸው ብሔራዊ ጥቅም የሚጐዳ አቋም እንዳይዙ ስለፈለጉ ነው፡፡

ወደ ናይል ጉዳይ በተለይም ቡሩንዲ ስምምነቱን ከፈረመች በኋላ ወደ ነበረው ሁኔታ ስንመለስ፣ የተለያዩ የመንግሥት አካላት መግለጫ መስጠታቸው እሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም፣ ምን ያህል የተናበበ ነበር ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብሎም ኤምባሲዎች ቢጠየቁ ተመሳሳይ መልዕክት ተቀርጾላቸው የጋራ ቋንቋ እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የመገናኛ ብዙኅን ዘገባዎችም ቢሆኑ ቡሩንዲ በግርግር መሀል ፈረመች አልያም፤ ጉድ አደረግናቸው ዓይነት መልዕክት ሲያስተላልፉ ነበር፡፡ ይህ ኃላፊነት የተሞላበት አስተያየት አይደለም፡፡ የመገናኛ ብዙኅንም ሌሎች በመረጡልን ካርድ መጫወት አይኖርባቸውም፡፡

የናይል ጉዳይ የውኃ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የናይል ነገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ሚኒስትር መሥርያ ቤት ሚናው እስከምን ድረስ እንደሆነ ማስቀመጥ ብሎም አንድ የጋራ መድረክ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል፡፡ በግብፅ የናይል ጉዳይ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ፍጹም አይለየውም፡፡ በናይል ጉዳይ የመከላከያና የደህንነት መስሪያ ቤቶች ሳይቀሩ አባል የሆኑበት ብሔራዊ  ምክር ቤት ያላችው ሲሆን ምሁራንን የሚያቅፍ ሌላ የቴክኒክ ቡድን አደራጅተዋል፡፡

በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ እንደተገለጸው፣ ከግብፅ ጋር ላለን ግንኙት ወሳኝ የሚሆነው በውስጣችን የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ሰላም በማግኘቷና ኢኮኖሚዊ እያደገ በመምጣቱ ውኃዎቻችንን መጠቀም ጀምረናል፡፡ በቀጣይ በተያዘው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ እንደተመለከተው፣ በመስኖ በኃይል ማመንጨት ሰፊ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም በዓባይ ጉዳይ ላይ ፍትሐዊ ክፍፍልን የሚደግፍ አካባቢያዊና ዓለማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር መሥራት እንጂ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጦር አውርድ ማለት አይገባም፡፡ በናይል ጉዳይ እኛ ተጠቅመን ሌላ ይጥፋ የሚል ፍላጐት እንደሌለን ወዳጅም ጠላትም እንዲያውቀው ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ውኃ ወለድ ጦርነት?

በዓለም ላይ ሦስተኛ የዓለም ጦርነት አገሮች በተለያዩ የጋራ ጥቅሞች የተሳሰሩ በመሆናቸው አይከሰትም የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ ከሆነ ግን ብቸኛው መንስኤ ውኃ ነው፡፡ ለዚህም ዋነኞቹ ምክንያቶች የዓለም የውኃ መጠን እየቀነሰ መሄዱና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ናቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (ዩኤንኢፒ) በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ በ2050 2/3ኛ የሚሆኑ የዓለም አገሮች ለውኃ እጥረት ይጋለጣሉ፡፡ ይህም ግጭቶችን ይፈጥራል፡፡ አገሮች በውኃ የተነሳ ዓይን ያወጣ የግለኝነት ስሜት ማንፀባረቃቸው የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ቻይናንን በአብነት ብንወስድ በቲቤት ጉዳይ እሰጣገባ ውስጥ የምትገባው ግዛቲቱ ለቻይና የውኃ ደኅንነት እጅግ አስፈላጊ ስለሆነች ነው፡፡ ቲቤት ያንግቲዝ ወንዝን ጨምሮ የስድስት ትላልቅ ወንዞች ምንጭ በመሆኗ የኤስያ የውኃ ማማ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውኃ ማማ እንደሆነች ሁሉ፡፡

ግብፅ በናይል ጉዳይ የተነሳ ኢትዮጵያን ልትወር እንደምትችል በተደጋጋሚ ተናግራለች፡፡ አንዴ ጋማል አብዱልናስር፣ ሌላ ጊዜ አንዋር ሳዳት እንዲሁም ሙባረክና ቡትሮስ ጋሊ ለታሪክ ድርሳናት የተረፈ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ወረራው ቢቀር ተጋላጭነታችን አስታከው በናይል ጉዳይ እነሱ ብቻ የሚጠቀሙበት የዜሮ ድምር (Zero sum) ሲጫወቱ ነበር፡፡ ግብፆች ይህን የሚያደርጉት 86 በመቶ የሚሆነውን ውኃ ምንጭ ብትሆንም ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ይኑር በምትለው የላይኛው ተፋሰስ አገር ኢትዮጵያ ላይ ነው፡፡ እዚህ ላይ የላይኛው ተፋሰስ ሆኖ በውኃዬ ላይ እንደራደር ማለት የተለመደ እንዳልሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በናይል ጉዳይ ሰፊ ጥናት ያደረጉት ኤርምያስ ፋንታሁን (ስማቸው ተቀይሯል) ይናገራሉ፡፡ ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ ቱርክ ጤግሮስ ወንዝ የላይኛው ተፋሰስ አገር ስትሆን የታችኛው ተፋሰስ ከሆኑት ሶሪያና ኢራቅ ጋር ለመደራደር ብዙም ፍላጐት የላትም፡፡ የቱርክ መንግሥት የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶ የቀጣዩን ትውልድ ደኅንነት በመወሰን በወንዙ ዘላቂነት ላይ አደጋ አላጋልጥም ባይ ነው፡

ኢትዮጵያና ግብፅ ከናይል በላይ ሊተባበሩባቸው የሚችሉ በርካታ አጀንዳ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ያህል ግድብ ብትገነባ የግብፅ የውኃ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ አታሳድርም፡፡ ከዚህ ይልቅ ናይል ሁለቱን ሕዝቦች እትብት ሆኖ ሊያስተሳስራቸው ይችላል፡፡ በዓለም ላይ የተካሄዱ ጦርነቶች ላይ ጥናት ያደረጉት ፒተር ግሊክ በውኃ ጉዳይ የተካሄደ ጦርነት እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ በውኃ ሳቢያ ግጭት ተቀሰቀሰ ከተባለም ከ4500 ዓመት በፊት በጋሽና ኡማ የተባለ የከተማ መንግሥታት ጤግሮስ ወንዝ ላይ ያደረጉት ነው፡፡

በቤይሩት የአሜሪካ ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጆን ዋተርቤሪ ናይል ለግብፅ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው በሚል በጻፉት መጽሐፍ፣ በተፋሰሱ አገሮች መካከል ትብብር ማድረግ ብቸኛው መፍትሔ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ሕዝባቸው በግብርና ላይ የተሠማራ በመሆኑ አገሮቹ ቢያድጉ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ትልቅ አቅም ላላት ግብፅ ገበያ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ግብፅ በወስጥ ጉዳያቸው ገብታ ከማተራመስና የእጅ አዙር ጦርነት (Proxy war) ከማድረግ መቆጠብ ይገባታል የሚለው የእኚሁ ተመራማሪ እምነት ነው፡፡ ግብፆች አገራቸውን የዓባይ ስጦታ ናት ይላሉ፡፡ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዓባይ የኢትዮጵያ ስጦታ ነው፡፡ ስለሆነም በሱዳን የአምዱርማን አህሊ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አሊ አብዲላ እንዳሉት መፍትሔው ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ስምምነት ነው፡፡ ሰላም፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close