‹የኤርትራ መንግሥት ከሽብር ተግባር አለመታቀቡን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቀናል›› አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ  በኒው ዮርክ ያደረጉትን ጉብኝት በማስመልከት ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የኤርትራ መንግሥት ከሽብር ተግባሩ ለመታቀብ ባለመቻሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቁን ገለጹ፡፡ የኤርትራ መንግሥት ከዚህ እንቅስቃሴ ካልታቀበ  ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱን ደኅንነትና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሲል በኤርትራ ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ አዲስ ስትራቴጂ መንደፉን  አቶ ኃይለ ማርያም አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ይህንን ለማድረግ የተገደደው የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ ስለመዘጋጀቱ መረጃ ስላለው ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት የሚወስደውን ዕርምጃ ጊዜው ሲደርስ ይፋ እንደሚያደርገውም አቶ ኃይለ ማርያም አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኤርትራ ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀናል፤›› ብለዋል፡፡ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆንና አሜሪካም እንድትተባበር ለሚመለከታቸው ሁሉ ማሳሰባቸውን አቶ ኃይለ ማርያም አስረድተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ ከአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጡዋቸው የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ የመረጃ አሰባሰብ ላይ የተመረኮዙ መሆናቸውን መተማመን ላይ መድረሳቸውን አቶ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ ለወደፊቱም በእነዚህና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ሦስት የጋራ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡ የመጀመሪያው በሰብዓዊ መብት፣ በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳር ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ሁለተኛው በኢኮኖሚና በንግድ ትብብር ላይ ይሠራል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በደኅንነትና በመከላከያ ጉዳዮች ላይ የሚሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close