‹‹አራት ኪሎ ከገቡ በኋላ ሥልጣን ይለቀቃል ማለት የማይታሰብ ነው›› አቶ ልደቱ አያሌው

– ለመማር፣ ትዳር ለመመስረትና ልጅ ለመውለድ አቅደዋል

– አቶ ሙሼ ሰሙ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ሆኑ
Reporter:የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ተቃዋሚ ሆነው ሳሉ ከሥልጣን መውረድና መውጣትን ካልተለማመዱ በስተቀር አራት ኪሎ ከገቡ በኋላ ሥልጣን ይለቃሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት መሆኑን፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው ከትናንት በስቲያ ገለጹ፡፡

አቶ ልደቱ ይህንን የገለጹት ላለፉት አራት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ከቆዩበት ሥልጣን ሲሰናበቱ አዲስ ለተሾሙት የፓርቲው አመራሮች ባደረጉት ንግግር ሲሆን፣ ለንግግራቸው መነሻ የሆናቸው፣ የእሳቸው ፓርቲ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሪዎችን የሥልጣን ጊዜ የሚገድብ ሕገ ደንብ ያለውና በተግባርም እያሳየ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ሳይወዱ በግድ በሕዝብ ተቃውሞ እንኳን ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ሲጠየቁ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚጀምሩ የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ ቱኒዚያን፣ ግብፅን፣ ሊቢያን፣ የመንንና ሌሎችንም የዓረብ አገሮችን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተረጋጋ፣ የሠለጠነና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር የእርሳቸውም ሆነ የፓርቲያቸው አባላት ፍላጐት መሆኑን፣ ሥርዓቱ የአገርም አሠራር እንዲሆን እንደሚመኙ የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ የእርሳቸው ፓርቲ አገርን የማስተዳደር ሥልጣን ቢይዝ፣ የመጀመሪያ ሥራ የሚያደርገው የአገሪቱን መሪ ሥልጣን የሚገድብ አንቀጽ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ማካተት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ካላቸው ዕድሜ ጋር ሲሰላ ሦስት አራተኛውን በፖለቲካ ትግል ውስጥ ማሳለፋቸውን፣ ከ18 ዓመታት የፖለቲካ ትግል በኋላ አሁን የደረሱበትንና ያሉበትን የፖለቲካ ብቃት ሲመዝኑት ‹‹ተለውጫለሁ›› የሚለው ቃል እንደማይገልጸው አቶ ልደቱ ተናግረዋል፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ከመማር በላይ ጥሩ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበርኩኝ፤ እያጠፋሁም፣ እያለማሁም ለሕዝብም ለመንግሥትም ጥሩ አስተዋጽኦ አድረጌያለሁ፤›› ያሉት አቶ ልደቱ፣ ባለፉበት የፖለቲካ ትግል ሒደት ተሳስተውና አጥፋተው ሊሆን እንደሚችል በመናገር፣ ‹‹በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ሒደት ውስጥ አላጠፋሁም ወይም አልተሳሳትኩም የሚል ካለ እውነተኛ ፖለቲከኛ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ኢዴፓን ከጓደኞቻቸው ጋር መሥርተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ ትግል የሥርዓት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በማሳየት በጐ ነገሮችን ማበርከታቸውን የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ሥርዓቱን ዴሞክራት ከማስመሰል ያለፈ ፋይዳ የለውም፤›› ለሚሉት በተግባር ማሳየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀሪያ ጊዜ በ1997 ዓ.ም. ሕዝብ በምርጫ መብቱን እንዲያስከብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ልደቱ፣ ያለ መታደል ሆኖ ተገኝቶ የነበረውን አጋጣሚ ጤናማ በሆነ መንገድ መጠቀም አለመቻሉን፣ ሕዝቡ በድምፁ የሰጠውን ውጤት በተሳሳተ አቅጣጫ በመሄድ ሜዳ ላይ እንዲበተን መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ድምፅ ሜዳ ላይ በመበተኑም በ2002 በምርጫ ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ሰዎች ስለፖለቲካ ጥፋት ሲያስቡ የእሳቸውን ጥፋት ከቅንጅት ጋር እንደሚያያይዙት የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ ‹‹በእርግጠኛነት የምናገረው ከቅንጅት ጋር በነበረን ግንኙነት እኔም ሆንኩ ሌሎች የፓርቲው አባላት አልተሳሳትንም፤ ይልቁንም እንደ ስህተት መቆጠር የነበረበት ከዚያ በፊት የሠራነው ስህተት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፖለቲካን ለጥላቻ መጠቀም ሳይሆን የሐሳብ ልዩነት ሆኖ መታየት እንዳለበት የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነጭና ጥቁር ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ወገኖች ቢኖሩም፣ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጐን ለጐን ሆነው እንዲከራከሩ፣ እንዲወያዩና እነዲነጋገሩ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በፖለቲካ ትግል ውስጥ ትልቅ ውጤት ሆኖ መመዝገብ ያለበት ገዢው ወገን አሸንፎ መንግሥት መሆን ሳይሆን፣ ኅብረተሰቡ ፖለቲካን የሚያይበትን መንገድ ለውጦ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ልደቱ፣ ፓርቲያቸው ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ አንድም ጊዜ ሳያቋርጥ በየሁለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔውን በማካሄድ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ በመቻሉ፣ በአባላቱ ላይ ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲዳብር ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

አቶ ልደቱ እንዳብራሩት፣ በርካታ ፓርቲዎች ይመሠረቱና አንድ ጊዜ እንኳን ጉባዔ ሳያካሂዱ ይጠፋሉ፡፡ ቢቆዩም ጊዜውን የጠበቀ ጉባዔ አያደርጉም፡፡ ከፖለቲካ ድርጅትነት ወደ ግለሰብ መጠሪያነት ይቀየራሉ፡፡ የሕዝብና የአገር አጀንዳ ማራመጃ መሆናቸው ቀርቶ የግለሰቦች መታያና የስም መጠሪያ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ኢዴፓ ግን የሚመኘው እንደዚህ ያለ እንቅስቃሴና አሠራር ቀርቶ በየሁለት ዓመቱ ሕገ ደንቡን የጠበቀ ጉባዔ እንዲካሄድና የለውጥ ፓርቲ መሆንን ነው፡፡

አቶ ልደቱ የእሳቸውን ሥልጣን መልቀቅ ተከትሎ ሰዎች በሁለት መልኩ ሊመለከቱት እንደሚችሉ ሲገምቱ፣ አንደኛው ደስታ የሚሰጣቸው መሆናቸውንና ‹‹ተገላገልን፣ የታባቱ›› የሚሉ እንደሚኖሩና በተግባርም ያዩት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ያሉት ደግሞ የሚደነግጡና ‹‹ልደቱ ተስፋ ቆረጠ ማለት ነው?›› የሚሉም እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹በተለይ እሰየው ላሉ አይምሰላቸው፡፡ እኔ በምንም ታሪክ ፖለቲካ በቃኝ አልልም፤ የሕይወት ጥሪዬ በመሆኑ እየጣመኝ ነው የሚሄደው፤ እኖርበታለሁ፤›› ያሉት አቶ ልደቱ፣ ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ግን፣ ‹‹ስለእኔ አሉባልታ የሚያወሩትም ሰዎች፣ እኔ የምሰጣቸውን መጣጥፍ የሚያትሙና እኔን በማናገር ዜና የሚሠሩትም ሚዲያዎች ትንሽ እረፍት ያድርጉ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ልደቱ በሚቀጥሉት የእረፍት ጊዜያቸው ምን ለመሥራት እንዳሰቡ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ጉድለት አሉብኝ የምላቸው ጉዳዮች ስላሉ መማር እፈልጋለሁ፤ ትዳር የለኝም ትዳርም እመሠርታለሁ፤ ልጅም ስለሌለኝ መውለድ አለብኝ፤›› ካሉ በኋላ ኑሯቸው በፖለቲካ ጣጣ ስለተጐዳ በግላቸው የሚተዳደሩበት አስተማማኝ ሥራ ስለሌላቸው ኑሮአቸውን መስመር ለማስያዝ እንደሚሞክሩ ገልጸዋል፡፡

ኢዴፓ መጋቢት 11 እና 12 ቀን 2003 ዓ.ም. ባደረገው 5ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ የማዕከላዊ ምክር ቤት የሥራ ክንውን ሪፖርትና የኦዲትና የኢንስፔክሽን ኮሚቴ ሪፖርት አዳምጦ ከማፅደቁም በተጨማሪ፣ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቋም ወስዷል፡፡

ፓርቲው የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ17 ወደ 25፣ የፓርቲው ሥራ አመራር አባላት ቁጥር ከሰባት ወደ ዘጠኝ ከፍ እንዲሉ አድርጓል፡፡ አቶ ልደቱን በመተካት አቶ ሙሼ ሰሙን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የመረጠ ሲሆን፣ ወይዘሮ ሶፊያ ይልማን ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ መስፍን መንግሥቱን ዋና ፀሐፊ፣ አቶ ሳህሉ ወዳጄን የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፣ ወይዘሪት ሳራ ይስሃቅን የሕዝብ ግንኙነት፣ አቶ ነፃነት ደመላሽን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ በማድረግና ሌሎችንም በመሾም ጉባዔውን አጠናቋል፡፡

 

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close