የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ፈተናዎች

Reporter– ለመዳን ሁለት ወር ይፈጅ የነበረው ቁስል የመጀመርያ ዕርዳታ ባለማግኘቱ ብቻ አራተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ጥቂት መቶ ብሮችን ብቻ ይጠይቅ የነበረው ሕክምና ዛሬ ላይ በመቶ ሺሕ ብር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲወጣ ግድ ብሏል፡፡

– በተለይ ከተሽከርካሪ አደጋ ጋር በተያያዘ በቀላሉ መትረፍ የሚችሉ ሰዎች በአንድ መፈልቀቂያ ብረት አለመገኘት ምክንያት ብቻ በተደጋጋሚ ተሽከርካሪ ጨፍልቋቸው ሲሞቱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

– በአንድ መዝናኛ ውስጥ በቴሌቪዥን በመተላለፍ ላይ የነበረ እግር ኳስ ይመለከት በነበረ አንድ ወጣት ላይ የለስላሳ ጠርሙስ ይወረወርና እጁ ይጎዳል፡፡ ሆስፒታል የወሰዱት ሰዎች ካርድ አውጥተውለት ሕክምና ሊያገኝ ሲል በፈሰሰው በርካታ ደም ምክንያት የወጣቱ ሕይወት አልፏል፡፡

በኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋዎች ሕክምና ከተመላላሽ ታካሚዎች ሕክምና ባልተሻለ ሁኔታ ይገኝ ስለነበር፣ በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡ ነበር፤ ዛሬም ቢሆን አደጋ የሚደርስባቸው ሰዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ትኩረት ተነፍጎት ለረጅም ዘመን የቆየ በመሆኑ፣ ችግሩም እንዲህ ሆኖ የዘለቀው ለዚህ ተብሎ የተቋቋመ የሕክምና ትምህርት ቤት ባለመኖሩና በቂ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው ነው፡፡ ድንገተኛ አደጋ ደርሶባቸው ከሚሞቱ ሰዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሆስፒታል ሳይደርሱ ይሞታሉ፡፡ በመኪና አደጋ፣ በእሳት ቃጠሎ፣ በሥራ ላይ በሚያጋጥሙ የደኀንነትና የጥንቃቄ ጉድለት በሚከሰቱ አደጋዎች፣ በአውሮፕላን አደጋ፣ በወሊድ ጊዜና በመሳሰሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሕይወት የማዳን ጥሪዎች ይቀርባሉ፡፡ ደም የሚፈሳቸውና በሕይወት ለመቆየት ጭንቅ ውስጥ የሚወድቁ ዜጎች ከሞት ጋር ይፋጠጣሉ፡፡ በጤና ባለሙያዎች ቸልተኝነትና፣ በሕክምና ተቋማት ውስጥ ተገቢ የሆኑ መሣሪያዎች ባለመኖራቸው፣ ለድንገተኛ አደጋ ሕክምና ጠንቅ የሆኑ ችግሮች አሁንም ይጠቀሳሉ፡፡ ምንም እንኳን የድንገተኛ አደጋ ሕክምና በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ ነው ቢባልም፣ ከድንገተኛ ጥሪ የስልክ መስመር ጋር በተያያዘም አሳሳቢ የሆኑ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ችግሮቹንና የተለያዩ አሳዛኝ አጋጣሚዎችን ከባለሙያዎች አስተያየት ጋር ያካተተውን ዘገባ ዝርዝር ይመልከቱ፡፡

በብርቱካን ፈንታና በምሕረት አስቻለው

ከአራት ዓመት በፊት ነበር፣ አንድ የፊቱ ገጽታ ሙሉ ለሙሉ የማይታይ፣ አንድ እጁም ከመበስበሱ ብዛት የተነሳ እየተላ የነበረ ወጣት ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ብቅ ያለው፡፡ እንዲመለከቱት የተጠሩት ሐኪም የሆስፒታሉ አጠቃላይ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስትና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የድንገተኛ ሕክምና ቡድን አባል ዶ/ር አዳነ ኃይሌ ነበሩ፡፡ ፊቱ ሙሉ ለሙሉ የተገሸለጠው ሕመምተኛ የመጣው ገጽታው በማይታይ ሁኔታ ቢሆንም መናገር ይችላል፡፡ ከሳምንት በፊት የመኪና አደጋ ደርሶበት ባሕር ዳር ውስጥ የመጀመርያ ዕርዳታ እንዳገኘ፤ ከዚያም ለቀጣይ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ እንዲሔድ ስለተነገረው የተባለውን እንዳደረገ ይናገራል፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ግን አንድም ሊመለከተው ፈቃደኛ የሆነ ሐኪም ወይም ሆስፒታል ይጠፋል፡፡ ፊቱ ላይ እንደነገሩ ጣል የተደረገው ፋሻም ከበሰበሰው ሥጋው ጋር ተጣብቆ መጥፎ ጠረንን አምጥቶ ነበር፡፡

ወጣቱ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ሆስፒታሎች ከተንከራተተ በኋላ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል የሔደው ከአንድ ዘመዱና ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተወከሉ አንዲት ሴት ጋር ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በግለሰቡ ጉዳይ ጣልቃ የገባው ‹‹አንድ ዜጋ በአገሩ ላይ ሕክምና ለማግኘት እንዴት ሳምንት ሙሉ ይንከራተታል?›› በሚል ነበር፡፡ ወጣቱ ሕክምና ማግኘት ብቻም ሳይሆን ሕክምና የሚያገኝበት ፍጥነት ለእስትንፋሱ መቀጠል ወሳኝ ነበር፡፡

ዶ/ር አዳነ እንዳሉት፣ ፊቱን ማጠብ ሲጀምሩ በአሸዋ ተሞልቶ ነበር፤ ቆዳው ሙሉ ለሙሉ እንደተነሣና የግንባሩ አካባቢ ሙሉ በሙሉ በመበስበሱ አጥንቱ ገጥጦ ነበር፡፡ አንድ እጁም ሙሉ በሙሉ በስብሶ ስለነበር እንዲቆረጥ ተደርጓል፡፡ ይኼ ሁሉ የሆነው የድንገተኛ አደጋ ሕክምና የሚሰጥ ተቋም ስላልነበረ ብቻ እንደነበር ዶ/ር አዳነ ነግረውናል፡፡

ለመጀመርያ ዕርዳታ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ሲሄድ በጣም በቀላሉ በንጹሕ ውኃ እንኳን ቢያጥቡት ኖሮ ጉዳቱ እዚህ ደረጃ ባልደረሰ ነበር ይላሉ፡፡ ወጣቱ ዛሬም በሆስፒታሉ ሕክምናውን በመከታተል ላይ ነው፡፡ ለመዳን ሁለት ወር ይፈጅ የነበረው ቁስል የመጀመርያ ዕርዳታ ባለማግኘቱ ብቻ አራተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ጥቂት መቶ ብሮችን ብቻ ይጠይቅ የነበረው ሕክምና ዛሬ ላይ በመቶ ሺሕ ብር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲወጣ ግድ ብሏል፡፡

በአገሪቱ ከ2000 ዓ.ም. በፊት የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ይሰጥ የነበረው እንደማንኛውም ዓይነት ተመላላሽ ሕመምተኛ ሁሉ ካርድ እንዲወጣ ተደርጐና የሪፈራል ወረቀትም ተጠይቆ ነበር፡፡ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ቦታ ያልተሰጠው የሕክምና ዘርፍ እንደነበረም ይነገራል፡፡ ለማሕጸንና ጽንስ፣ ለቀዶ ሕክምናና ለሌሎችም የየራሳቸው ክፍል አላቸው፡፡ ለድንገተኛ ሕክምና ግን ራሱን የቻለ ክፍልና የሠለጠነ ባለሙያ አልነበረም፡፡ የድንገተኛ ሕክምና አለመኖር ችግር ከትምህርት ቤቶች እንደሚጀምር ዶ/ር አዳነ ይናገራሉ፡፡ የድንገተኛ ሕክምና ትምህርት በሰርጂካልና በሜዲካል ትምህርት ውስጥ እንደ አንድ ትምህርት ይሰጣል እንጂ ለብቻው ወጥቶ ሥልጠና የሚሰጥበት ሁኔታ አልነበረም፡፡

‹‹ድንገተኛውን ማከም ቢቻልም እንዴት እናክመው? የሚለው ትልቅ ፈተና ነበር፤›› በማለት ሥርዓቱ የተደራጀ አለመሆኑ ጉዳቱን እንዳባባሰውም አክለው ይገልጻሉ፡፡

‹‹የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ቀደም ባለውና አሁን ያለበትን ደረጃ ስንመለከት፣ ከዚህ ቀደም አንድ ሰው ድንገተኛ አደጋ መንገድ ላይ ቢገጥመው ከቀናውና የሚያውቁት ሰዎች ካጋጠሙት አፋፍሰው ወደ ጤና ድርጅት ይወስዱታል፡፡ ካልሆነም በትንሽ አደጋ ሕይወቱ እዚያው መንገድ ላይ ታልፋለች፡፡ ወደ ጤና ድርጅት የሚወሰዱትም ቢሆኑ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ራሱን ችሎ የሚሰጥበት ሁኔታ ስላልነበር በሌላ ሕክምና ውስጥ ነበር የሚስተናገዱት፤›› ያሉን ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና በዳይሬክቶሬቱ ሥር የሚገኘውና የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ላይ የሚሠራው ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ቢሻው ናቸው፡፡ ድንገተኛ አደጋው ከተከሠተበት ቦታ ጀምሮ እስከ ጤና ተቋሙ ድረስ ያለው ሁኔታ በችግሮች የተሞላ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት አዳዲስ አሠራሮች ከመዘርጋታቸው በፊት በነበረው ሁኔታ ድንገተኛ ሕክምና በአገሪቱ ነበር ለማለት ያስችል ነበር? ብለን ለዶ/ር አብርሃም ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡ በትምህርት ቤት፣ በተለያዩ ድርጅቶች፣ በቀይ መስቀልና በሌሎች በጎ ፈቃደኞች እዚህም እዚያም የተነጣጠሉ ሥራዎች ከመኖራቸው ባሻገር፣ ይህ ነው ሊባል በሚያስችል ደረጃና ወጥ በሆነ መልኩ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና በአገሪቱ ይሰጥ ነበር ለማለት የሚያስደፍር ምንም ዓይነት ነገር እንዳልነበር፣ ይልቁንም ይሰጥ የነበረው የመጀመርያ ዕርዳታ እንደነበር ነግረውናል፡፡

‹‹በአገራችን የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ባለመኖሩ የደረሰው ጉዳት በቀላል የማይገመትና በጣም ከባድ ነው፡፡ ጉዳቱም በድንገተኛ አደጋ ሕክምና ክፍል ውስጥ የማያበቃና ታካሚዎቹ አልጋ ይዘው ቀጣይ ሕክምና የሚያደርጉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ብዙዎቹ ቀዶ ሕክምና ስለሚፈልጉም የድንገተኛ አደጋ ሕክምናን በሚመለከት የሚደረጉ የአሠራር ለውጦች በጤና ተቋማቱ ላይ አጠቃላይ ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋሉ፤›› በማለት እንኳን ሕክምናው ሳይኖር ሕክምናው እየተሰጠ ያለው ኪሳራም ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡ አገልግሎቱ የሆስፒታሎችን ግብዓት በጉልህ ቢወስድም እያንዳንዱ የጤና ተቋም ይነስም ይብዛም ራሱን የቻለ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና የሚሰጥ ክፍል ሊኖረው ይገባል የሚል አቋም እንደ መርሕ ተይዞ እየተሠራበት ይገኛል፡፡

ምንም እንኳ ሕክምናው ቀደም ባሉት ጊዜያት ባለመኖሩ የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ይህ ነው ብሎ ለማስቀመጥ ጥናት ቢያስፈልግም፣ ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ለመሆኑ ዶ/ር አብርሃም ምንም ጥርጣሬ የላቸውም፡፡

የሕክምና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር
የሕክምና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ጉዳይ በተደጋጋሚ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚነሣ ቅሬታ ነው፡፡ ‹‹ተቃጥዬ የሚረዳኝ አጣሁ፤ ደም እየፈሰሰኝ የሚመለከተኝ የሕክምና ባለሙያ አልነበረም፤ ምጥ ይዞኝ ስጮህ ነርሷ አትጩሂብኝ አለችኝ፤ ልጄ ጣር ውስጥ ሆኖ የሕክምና ባለሙያዋ ስልክ ታወራ ነበር፤ የተሳሳተ መድኃኒት ሰጥተው ገደሉብኝ፤ ሐኪሙ ስብሰባ ውስጥ ናቸው በመባሉ የአባቴ ሕይወት አለፈ፤›› የሚሉ እሮሮዎች ይደመጣሉ፡፡ ኅብረተሰቡንም በሕክምና ባለሙያዎች ላይ እምነት እንዲያጣ ያደረጉ ጉዳዮችም ናቸው፡፡

በሪፖርተር ጋዜጣም በተደጋጋሚ በሕክምናው ዘርፍ ስለሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ግድፈቶችን ዳስሰናል፡፡ የችግሩ መነሻ ምንድን ነው? የባለሙያው ግዴታስ? ዶ/ር አዳነ መልስ አላቸው፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻ የሚያደርጉት ኅብረተሰቡ ስለባለሙያዎች ያለውን አመለካከት ነው፡፡ ‹‹ኅብረተሰቡ እንደ ሰው የሚርበንና የሚጠማን፣ የሚደክመንና የምንሳሳት አይመስለውም፤›› በማለት፣ ሌላው ምክንያት ደግሞ የነበረው ሥርዓት እንደነበር ይጠቁማሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፣ ሥርዓቱ አንድ አደጋ የደረሰበት ሰው ካርድ እንዲያወጣ ስለሚያዝ ባለሙያውም ይህ እንዲደረግ ያስገድዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ኅብረተሰቡ ባለሙያውን እንደ ክፉና ጨካኝ አድርጎ ይወስደዋል፡፡

በሕክምና ሙያ ውስጥ ስህተት መፈጸም እንደሌለበት ሐኪሙ ቢያምኑም ነገር ግን ባለሙያው እንደማንኛውም ሰው በመሆኑ ስህተት ሲፈጥር ይታያል፡፡ ሌሎች ሙያዎች ላይ ስህተት ሲፈጠር ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም፣ በሕክምና ላይ ለሚፈጠሩ ስህተቶች ግን መጨረሻው ሞት ወይም ጉዳት በመሆኑ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ማንኛውም ባለሙያ እንደሚረዳው ይገልጻሉ፡፡ በተቃራኒው ስህተቶች ሲፈጠሩ ባለሙያው ግድ እንደሌለው ተደርጎ መቆጠሩ ትክክል እንዳልሆነም ይጠቁማሉ፡፡ ኅብረተሰቡም ለባለሙያው በሰጠው ትልቅ ቦታ ምክንያት ትንሹ ስህተት እንዲጎላበት ማድረጉንም ያክላሉ፡፡

‹‹አያናግሩም፤ ችላ ይላሉ፤›› የሚባለውም ምናልባትም አንድ የሕክምና ባለሙያ በቀን እስከ 80 የሚደርሱ ሕሙማንን የሚያይ በመሆኑ እያንዳንዱን ሰው ማናገር ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የሕክምና ተቋሙ አደረጃጀት ከፍተኛ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል፡፡

ዶ/ር አዳነ ኦክስጂንን በተመለከተ ስለነበረው ሥርዓት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ‹‹ኦክስጂን ቀን ሲሠራበት ይውልና ማታ ይቆለፋል፡፡ ምክንያቱም መመርያው ከጠፋ ትከፍላላችሁ ስለሚል ነው፡፡››

በየጊዜው ባለሙያው ስህተት እንደሠራ ተደርጎ የሚቀርቡ ክሶች ባለሙያው በነፃነት እንዳይሠራ እንዳስጨነቀው የሚናገሩት ዶክተሩ፤ ‹‹ብዙዎቹ የሚቀርቡት ቅሬታዎች ካለመግባባት ጋር የተገናኙ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ማደንዘዣ የተሰጠው ሰው አንድ በመቶ የመሞት ዕድል እንዳለው ጠቁመው፣ ሕክምና እየተደረገለት ባለበት ወቅት ሕይወቱ ቢያልፍ የባለሙያው ግድየለሽነት ተደርጎ የሚወሰድበት ጊዜ መኖሩን ዶ/ር አዳነ ያመለክታሉ፡፡

በተቋማቱ የተሟሉ መሣርያዎች አለመኖር
ቦታው ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም መውጫ መንገድ ላይ በሚገኘው ጫንጮ አካባቢ ነው፡፡ በአንድ ባለ ተሳቢ የጭነት መኪና ላይ በደረሰ አደጋ የተሽከርካሪው ረዳት ከወገቡ በታች በመኪናውና በተጐታቹ መካከል ይጣበቃል፡፡ ከተጨፈለቀው መኪና ውስጥ ከወገቡ በታች ተጣብቆ የሚገኘውን ሰው ለማውጣት ብዙ ተሞክሮ ግን አልተቻለም፡፡ በመካከል በድንገት በአካባቢው ያልፉ የነበሩ የሕክምና ባለሙያ የተፈጠረውን ነገር ለማየት ወረዱ፡፡ ሰውየው ከወገቡ በላይ ውጭ ነው፣ ከወገቡ በታች ደግሞ ውስጥ ገብቶ ተጣብቋል፡፡ ግለሰቡን ለማትረፍ መፈልቀቂያ ብረት ያስፈልጋል፤ ግን ከየት ይምጣ? ረዳቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከቆየ ሁለት ቀን እንደሞላውና በአካባቢው ያሉት ሰዎች ምግብና መጠጥ እየሰጡት እንደሆነ ተነገራቸው፡፡ ሌላው የነበረው አማራጭ መቁረጥ ነበር፡፡ ነገር ግን የተጣበቀው ከወገቡ ጀምሮ በመሆኑ መቆረጥ ያለበት ከወገቡ ላይ ነው፡፡ ይህንንም ማድረግም አልተቻለም፤ ምክንያቱም ወገቡ ላይ ተቆረጠ ማለት ሕይወቱ አይተርፍምና፡፡

ባለሙያው ብዙ ቢያውጠነጥኑም ሊሳካላቸው ባለመቻሉ ወደ ቤታቸው አቀኑ፡፡ በሁለተኛው ቀን ግን ስላላስቻላቸው ሊያዩት ሲሔዱ ሕይወቱ ማለፉን ተረዱ፡፡ አንድ ቀላል፣ ነገር ግን እስካሁን ያልታሰበበት መፈልቀቂያ ብረት በመጥፋቱ ሦስት ቀን ከወገቡ በላይ ውጭ፣ ከወገቡ በታች ደግሞ ውስጥ ተጣብቆ የቆየው ረዳት ሕይወት ሊያልፍ ቻለ፡፡

በአሁኑ ወቅት አደጋዎች ከቴክኖሎጂው ጋር በመጨመር ላይ እንደሚገኙ ይጠቆማል፡፡ ባደጉት አገሮች የሕክምና መሣርያዎች ከቴክኖሎጂው ጋር እኩል እያደጉ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ቀላል የሚመስሉ መሣርያዎችን እንኳን ማግኘት አዳጋች ነው፡፡

በተለይ ከተሽከርካሪ አደጋ ጋር በተያያዘ በቀላሉ መትረፍ የሚችሉ ሰዎች በአንድ መፈልቀቂያ ብረት አለመገኘት ምክንያት ብቻ በተደጋጋሚ ተሽከርካሪ ጨፍልቋቸው ሲሞቱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

ዶ/ር አዳነ በቅርቡ በአንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኛ ላይ የደረሰውን አደጋ እንደ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ ‹‹ግለሰቡ ሥጋ በመፍጨት ላይ እንዳሉ ከመፍጫው ማሽን የቀረውን ሥጋ ለማውጣት እጃቸውን ሲያስገቡ ይስባቸውና እጃቸው ይፈጭ ጀመረ፡፡ ጣቶቻቸው እየተፈጩ በመውረድ ላይ እንዳሉ አንድ የሥራ ባልደረባቸው ሶኬቱን በመንቀል ቢያስቆሙትም እጃቸውን ከሥጋ መፍጫ ማሽኑ ማላቀቅ ግን ትልቁ ፈተና ሆነ፡፡ የሥጋ መፍጫው የግለሰቡ ክንድ ድረስ እንደዘለቀ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ይዘዋቸው መጡ፡፡ ማላቀቂያ ብረት ግን ጠፋ፡፡ እጃቸው ከክንዳቸው ጀምሮ ሳይቆረጥ መፍጫውን ለማውጣት የተደረገው ሙከራ አድካሚ ሆነ፡፡ መፈልቀቂያ ብረት ለማግኘት ብቻ አምስት ሰዓታትን ፈጀ፡፡ የተገኘውም ብረት ቢሆንም ሳይፈለቅቀው ተቆረጠ፡፡ እንደገና ሌላ መቁረጫ ብረት መፈለግ ተጀምሮ በመጨረሻ ላይ ከስምንት ሰዓታት በኋላ ተሳካ፡፡ ጣቶቻቸውን ብቻ በመቁረጥም ሌላውን አካላቸውን ለማትረፍ ተቻለ፡፡›› በሕክምና ተቋማቱ ውስጥ የእነዚህ መሣርያዎች አለመኖር ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል፡፡

ለአንዳንድ አደጋዎች ደግሞ አገልግሎቱን የሚሰጡ የሕክምና ተቋማት ማነስም ሌላው ችግር እንደሆነ ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ለቃጠሎ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው ሆስፒታል የካቲት 12 ብቻ ነው፡፡ በውስጡ የሚገኙት አልጋዎችም 19 ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎች ሆስፒታሎች የቃጠሎ ሕክምና መስጠት ቢጀምሩ ሕክምናውን በማጣት (ወረፋ ሳይደርሳቸው በመቅረት) የሚሞቱትን ቁጥር እንደሚቀንስ ይገልጻሉ፡፡

የአገሪቱን ገጽታ ከመቀየር አንጻር
የድንገተኛ አደጋ ሕክምና አለመኖሩ ከዜጎችም አልፎ አጠቃላይ የአገሪቱን ገጽታ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ እንዳደረገው፤ በተለይ ደግሞ ለኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ አገር ዜጎች ዋስትና እንዲያጡ ማድረጉ ይነገራል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚከተለውን የውጭ አገር ዜጋ ገጠመኝ እንመልከት፡፡

በመጋቢት 1999 ዓ.ም. ላይ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ነዳጅ ሲያፈላልግ የነበረው የፔትሮናስ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሚስተር መሐመድ ቢን ሞህድ አሪስ ወደ ጋምቤላ ለሥራ ሔደው በቻርተር አውሮፕላን በመመለስ ላይ ሳሉ፣ በአውሮፕላኑ ሞተር ላይ በተፈጠረ ችግር አውሮፕላኑ በድንገት ቱሉ ቦሎ ገጠር ውስጥ እርሻ ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡ ያረፈበት ቦታ ከከተማ ውጭ በመሆኑ ኩባንያው በወቅቱ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ስምምነት አድርጐ ወደነበረው አንድ የታወቀ የግል ሆስፒታል የድንገተኛ አደጋ የስልክ ጥሪ ቢያደርግም፤ ‹‹አምቡላንስ የለንም፤ የሰው ኃይል እጥረትም አለብን፤›› በሚልና በሌላ በሌላም ምክንያት ኩባንያው ላደረገው የድንገተኛ አደጋ ጥሪ ምላሽ መስጠት እንደማይችል አሳወቀ፡፡

የድርጅቱን ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ሌሎች ሁለት ሰዎች ምንም ዓይነት ድንገተኛ ዕርዳታ ሳያገኙ ቆዩ፡፡ በመጨረሻ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት ሥራ አስኪያጁ በገበሬዎች ዕርዳታ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ከተማ በቃሬዛ ተወስደው በአይሱዙ የጭነት መኪና ወሊሶ ከተማ ይደርሳሉ፡፡ የድንገተኛ አደጋ ዕርዳታ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ከወሊሶ አዲስ አበባ በላንድክሩዘር ቢገቡም የድንገተኛ ሕክምና ዕርዳታ ችግራቸው ሊፈታ አልቻለም፡፡ ወደ ማሌዢያ ሔደው ሕክምና ለማድረግ በማሰብ የድንገተኛ የሕክምና ዕርዳታ ያለው ቻርተር አውሮፕላን .ቢያፈላልጉም በአገሪቱ ማግኘት አልቻሉም፡፡ በመጨረሻ የተፈለገው የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ያለው አውሮፕላን ከኬንያ አዲስ አበባ ለማስመጣት ቢችሉም፣ በድንገተኛ አደጋ ሕክምና አለመኖር ለአራት ቀናት በጉዳት የቆዩት ሥራ አስኪያጁ ወደ ማሌዢያ ሊጓዙ ሲሉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

ለዘርፉ ማንሰራራት የተፈጠረው አጋጣሚ
የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት በጥቂቱም ቢሆን ፈር እየያዘ የመጣው ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ነው፡፡ ከ13 ዓመታት በፊት የድንገተኛ የሕክምና ማዕከል እንዲኖር አንዳንድ ሐኪሞች በራስ ተነሳሽነት የጀመሩት ጥረት ቢኖርም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ለሚሊኒየሙ ዝግጅት ብዙ እንግዶች ከውጭ ይገቡ ስለነበር መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በሁሉም ሆስፒታሎች በአስቸኳይ የድንገተኛ ሕክምና ክፍሎች እንዲከፈቱ ማዘዙ አንድ የታሪክ አጋጣሚን ፈጠረ፡፡ ከውጭ አገር የተውጣጡ የሕክምና ባለሙያዎችም በዘርፉ ሥልጠና መስጠት ጀመሩ፡፡ እናም በዚሁ የሚሊኒየም አጋጣሚ ለድንገተኛ ሕክምና ዘርፉ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡

በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችም የሚሊኒየሙ ዝግጅት ቢጠናቀቅም አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ዳግም ተሰባሰቡ፡፡ ሥልጠናው በውጭ አገር ዜጎች በተሰጠበት ወቅት የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ክፍተት የታየበትና አስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም የተስተዋለበት ወቅት እንደነበር ዶ/ር አዳነ ያስታውሳሉ፡፡

እንደ ዶ/ር አብርሃም ገለጻ ከዓመታት በፊት በአጠቃላይ የአገሪቱን የጤና ዘርፍ በተሻለ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ በወጣው የማሻሻያ ፖሊሲ አማካይነት የድንገተኛ አደጋ ሕክምናም የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት አደጋ በሚደርስበት ቦታ፣ ቅድመ ተቋማት ከሕክምና ተቋማት በፊት የሚስጥር ዕርዳታና በሕክምና ተቋማትም ሊሰጡ የሚገባቸው የሕክምና ዕርዳታዎች ላይ የተለያዩ ሥራዎች መሠራት ጀምረዋል ፡፡

ቅድመ ተቋማት የድንገተኛ አደጋ ሕክምናን በሚመለከት በእያንዳንዱ ወረዳ የአምቡላንስ አገልግሎት እንዲኖር እየተደረገ ሲሆን፣ ለዚህም መሥርያ ቤቱ ከሦስት መቶ በላይ አምቡላንሶችን በመግዛት ላይ ነው፡፡ አምቡላንስ መግዛት ብቻም ሳይሆን በአምቡላንሱ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቷል፡፡

የድንገተኛ አደጋ ሕክምና በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በግሉ ዘርፍም መሰጠት እንዳለበት፤ እንዲሁም በብዙ አገሮች እንደሚታየው የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ማዕከል (ዕዝ) አንድ ሆኖ መልዕክት ወደ ማዕከሉ በማስተላለፍና ከማዕከሉም እየተላለፈ አስፈላጊው አገልግሎት እንዲሰጥ በመደረግ ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ከታሰቡት አምቡላንሶች 51 የሚሆኑት ለተለያዩ ክልሎች መሰጠታቸውንም ከገለጻቸው መረዳት ችለናል፡፡

በድንገተኛ አደጋ ወዲያው ሕክምና ካልተገኘ ለኅልፈት ሕይወት የሚዳርግ ወይም የጤና ሁኔታን ከፍተኛ ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሕክምናው ራሱን ችሎ እንዲሰጥ አሠራር ተዘርግቷል፡፡ በተወሰነ መልኩም ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

‹‹በፊት ማንም ይሁን ማን ሳይታይ ካርድ አውጣ፤ ሪፈራል ይዘህ ና ይባል ነበር፡፡ አሁን ግን ድንገተኛ አደጋ ደርሶብኛል ካለ ወይም ሰው ይዞት ከመጣ ሁኔታው ታይቶ ድንገተኛ መሆኑ ከታወቀ ካርድ አውጣ አታውጣ፤ ገንዘብ ክፈል አትክፈል የሚባል ነገር የለም፡፡ በአዲሱ አሠራር ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች የሚረዱ ልዩ ባለሙያዎችም አሉ፡፡››

በተደረገው አጠቃላይ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ የድንገተኛ ሕክምና ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የጤና ተቋማት አስተዳደር፣ የተገልጋዮች አያያዝና የመድኃኒት አስተዳዳር፣ የሆስፒታል ንጽሕናና ሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳዮች ትኩረት ተደርጐባቸው እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፡ አስተዳደርን በሚመለከት አንድ ሐኪም ሕክምና እየሰጠ በሌላ በኩል አስተዳደራዊ ሥራ የሚሠራበት ሁኔታ እንዲቀየር ተደርጓል፡፡ ለእነዚህ መሻሻሎች ተግባራዊነት ታስቦ በአዲስ መልክ የወጣው መመርያ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ ሆስፒታሎችም በሠለጠነ ባለሙያ በቦርድ እንዲመሩ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ ይህ መመርያ አገራዊ እንደመሆኑ ሆስፒታሎች በዚያ መሠረት አቅጣጫ እየያዙ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ጤና ተቋማቱ ዓይነትና ሁኔታ እየታየ ያለው ለውጥ ከሆስፒታል ሆስፒታል ይለያያል፡፡

‹‹በሰነዱ ላይ እንደተቀመጠው በተቻለ አቅም የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ከዋናው መግቢያ ክፍል አቅራቢያ መሆን አለበት፡፡ የተለያዩ ሆስፒታሎች አዲስ ሲገነቡ የተወሰኑት ደግሞ አፍርሰው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ስትሬቸር ወይም ዊልቸር ቀርቦ በቀጥታ ወደ ክፍሉ ተወስዶ የመለየት፣ ከዚያም በትክክል ድንገተኛ አደጋ ከሆነ በአፋጣኝ ሕክምናውን የመስጠት ሁኔታ አለ፡፡ ድንገተኛ አደጋ እንደሌለ ከተረጋገጠ ደግሞ በተመላላሽ ሕክምና እንዲከታተሉ ይደረጋል፤›› በማለት ዶ/ር አብርሃም ይጠቁማሉ፡፡

ኅብረተሰቡ ስለዘርፉ ያለው ግንዛቤ አናሳነት
በድንገተኛ አደጋ ላይ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማጣት ደግሞ እንደ ሌሎቹ ችግሮች በጉልህ የሚታይ ስለመሆኑ ዶክተር አዳነም ሆኑ ዶክተር አብርሃም ይስማሙበታል፡፡ የድንገተኛ አደጋ ሕክምና የሚጀምረው አደጋው የደረሰበት ቦታ ላይ ቢሆንም፣ ኅብረተሰቡ በዘርፉ የጨበጠው ዕውቀት ባለመኖሩ ከፍተኛ ኪሳራን ሲያስከትል መታየቱን በእርግጠኝነት የሚናገሩት ዶ/ር አዳነ ናቸው፡፡

ድንገተኛ አደጋ ደርሶባቸው ሕክምና ሳያገኙ ከሚሞቱት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት ሕይወታቸው የሚያልፍ ናቸው፡፡ ኅብረተሰቡ ስለ ድንገተኛ አደጋ ግንዛቤ ቢኖረውና ሆስፒታል ከመድረሱ በፊት በቀላሉ ማድረግ ያለበትን ነገር ቢያውቅ ለአደጋው መቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆን በአንድ ሆስፒታል ያገኘነውን የድንገተኛ አደጋ ታሪክ እንመልከት፡፡ በአንድ መዝናኛ ውስጥ በቴሌቪዥን በመተላለፍ ላይ የነበረ እግር ኳስ ይመለከት በነበረ አንድ ወጣት ላይ የለስላሳ ጠርሙስ ይወረወርና እጁ ይጎዳል፡፡ ሆስፒታል የወሰዱት ሰዎች ካርድ አውጥተውለት ሕክምና ሊያገኝ ሲል በፈሰሰው በርካታ ደም ምክንያት የወጣቱ ሕይወት አልፏል፡፡ አንድ ሐኪም እንደገለጹልን፣ የተቆረጠበት ቦታ ላይ ቢታሰር ወይም በደህናው እጁ የተቆረጠውን ቦታ እንዲይዘው ቢደረግ ኖሮ የሚፈሰውን ደም በመቀነስ ወጣቱንም ለሕክምና ማብቃትና ሕይወቱን ማትረፍ ይቻል ነበር፡፡ ስለዚህ በእንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች ወዲያው ምን መደረግ እንዳለበት ኅብረተሰቡን መሠረታዊ የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ ዕውቀቶችን ማስጨበጥ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡

ኅብረተሰቡ ስለድንገተኛ አደጋ ግንዛቤ እንዲኖረው በስፋት ሊሠራ እንደሚገባ የተናገሩት ዶ/ር አብርሃም፣ ‹‹ስንቱ ነው የአምቡላንስ ድምፅ ሲሰማ መንገድ የሚለቀው? የድንገተኛ አደጋ የስልክ መስመር ላይስ ስንት ሀሰተኛ ጥሪዎች ይደረጋሉ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች የድንገተኛ አደጋ ጥሪ 939 ላይ በመደወል የሚፈጥሩት ችግር ከግንዛቤ ጉድለት ነው ብለው ቢያምኑም፣ ኪሣራው ግን ይህን ያህል ተብሎ በቀላሉ የማይቀመጥ መሆኑን በእሳት አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኦፊሰር አቶ ከበደ ለገሰ ይናገራሉ፡፡

939
‹‹በጣም የሚገርመው ከጎንደር፣ ከጐጃምና ከሰበታ ከመሳሰሉት ከተሞች በጣም ችግር ውስጥ እንደሆኑ የሚገልጹና ገንዘብ የሚጠይቁ፣ ከፍቅረኞቻቸው እንደተጣሉ፣ ይህም እንደጎዳቸውና ምክር እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልጹ ደዋዮች መስመሩን ያጨናንቁታል፡፡ ደውዬ አምቡላንስ አስመጣለሁ፣ አላስመጣም ዓይነት ውርርድ ውስጥ ሁሉ የሚገቡ አሉ፡፡ በአጠቃላይ ነገሩን በጣም ቀልድ አድርገው የያዙት ጥቂት አይደሉም፤›› ይላሉ፡፡

ለአደጋ በተለይም ለድንገተኛ አደጋ የሚውል ነፃ የስልክ መስመር 939 ላይ በመደወል በሚደረገው ተራ ቀልድና ፌዝ ከጊዜ፣ ከሰው ኃይልና ከንብረት አንጻር የሚደርሰው ኪሳራ ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ዕርዳታ ካላገኙ ሕይወታቸው ማለፉ እርግጥ የሆነ ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች መስመሩ ስለሚያዝባቸው ሕይወታቸው እንደ ዋዛ ያልፋል፡፡

ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያገለግሉ የነፃ የስልክ ጥሪዎች እንደ ድንገተኛ አደጋ የስልክ ጥሪ ሁሉ አላግባብ ለሆኑ የተለያዩ ተግባራት ቢጋለጡም፣ የድንገተኛ አደጋ ጥሪ 939 ግን ከሰው ልጅ እስትንፋስ መቀጠል ያለመቀጠል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ሁኔታውን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸው ወይም ያጋጠማቸው ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ የሚያደርጉት ትግል በሌሎች ያልተገባ ቀልድና ዋዛ ፈዛዛ ይገታል፤ ወይም ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ግለሰቦች የነፃ ስልክ ጥሪውን ጥቅም ተረድተው ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ የማስተማር ሥራ ቢሠራም፣ ውጤቱ አነስተኛ እንደሆነ ከአቶ ከበደ ንግግር ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ኅብረተሰቡን ለማንቃትና ለማስተማር ሞክረናል፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ ባለን የራሳችን የሬዲዮ ፕሮግራምም ተመሳሳይ ሥራ በተደጋጋሚ ሠርተናል፡፡ ነገር ግን ዛሬም ለቀልድና ለፌዝ የስልክ መስመሩን የሚያጨናንቁ ጥቂት አይደሉም፡፡ ወደ ድንገተኛ አደጋ የስልክ ጥሪው የሚደወልባቸው ስልኮች ደግሞ ተደጋጋሚ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም፤›› ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ያስረዳሉ፡፡

ሰዎች የድንገተኛ አደጋ የስልክ ጥሪ ላይ በመደወል ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት የሚፈጽሙት ሙሉ በሙሉ ባለማወቅ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ የስልክ ጥሪ ባይረዝምም፣ ደዋዮቹ መሳሳታቸው ተነግሯቸው ስልኩ ስለሚሰጠው የሕይወት አድን አገልግሎት ይገለጽላቸዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን አንዳንዶች ደጋግመው ከመደወልና መስመሩን ኃላፊነት በጐደለው ድርጊት ከማጨናነቅ አላገዳቸውም፡፡

‹‹ለተመሳሳይ አገልግሎት መዋል የሚችሉ ሌሎች የመስመር ስልኮችን በተደጋጋሚ እናስተዋውቃለን፡፡ አላግባብ የሆኑ የስልክ ጥሪዎች የሚደረጉት ግን በነፃው የድንገተኛ አደጋ የስልክ ጥሪ ላይ ነው፡፡ በዚህ መስመር የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች እንዲሁም የተደወሉባቸው ስልክ ቁጥሮች ይመዘገባሉ፡፡ ተደጋጋሚና ያልተገቡ የስልክ ጥሪዎችን ለማስቆም የሚመለከተው አካል እነዚያን ስልኮች በቀጥታ መዝጋት ስለማይችል ክስ መመሥረትና በዚያ መሠረት በተለያዩ የሕግ ሒደቶች ውስጥ መግባት ያስፈልጋል፤›› በማለት አቶ ከበደ ይናገራሉ፡፡

የድንገተኛ አደጋ ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች የወጣው ወጪ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ደሀ አገር ከፍተኛ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ አይኖረውም፡፡ ለዚህ ዓይነት አገልግሎት የተዘረጋ አሠራር ላይ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት መፈጸም ኪሳራውን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ በገንዘብ የማይተመነውን የሰው ልጆች ሕይወት ለኅልፈት ይዳርጋል፡፡ ስለዚህም ድንገተኛ አደጋን መከላከልና የድንገተኛ አደጋ ሕክምናን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት የሚገባ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close