የጋዜጣ ማሳተሚያ ዋጋ በ45 በመቶ ጨመረ

Reporter- ለአዟሪዎች በአራት ብር የሚቀርበው ጋዜጣ በ20 ብር ይታተማል

በየጊዜው የሚጨምረው የጋዜጣ የማሳተሚያ ዋጋ ከነገ መጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን ተመን የሚስተካከል አይደለም፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለሪፖርተር የላከው የሕትመት ዋጋ ተመን 45 በመቶ መጨመሩን ያመለክታል፡፡

የማሳተሚያ ጭማሪውን በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የድርጅቱ የንግድ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳሙ ኃይሌ፣ ‹‹ዋጋው የጨመረው በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የማሳተሚያ ዋጋው የጨመረው በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ብቻ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብርሃንና ሰላም የዋጋ ለውጥ ያደረገው ከውጭ አገር በቅርቡ የሕትመት ወረቀት ማስገባቱን ተከትሎ ነው፡፡ አቶ አዳሙ እንደገለጹት፣ ከዶላር አኳያ የብር የመግዛት አቅም በማዳከሙ ምክንያት፣ የመርከብ ትራንስፖርት ወጪና የጉምሩክ ቀረጥ ተደማምረው ከፍተኛ ጭማሪ አስከትለዋል፡፡ ‹‹አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ተመን ዋጋውን በብር እየለወጡ በዚያ መሠረት ስለሚያስከፍሉን ትልቁን ጭማሪ አምጥቷል፤›› ይላሉ፡፡

የጭማሪው ከፍተኛነት የጋዜጣ አሳታሚዎችንና አዘጋጆችን ክፉኛ እንዳሳሰባቸው የገለጹ ሲሆን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ አዘጋጆች እንደተናገሩት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣው የሕትመት ዋጋ ምክንያት ጋዜጦች እስካሁን ሲሸጡ የቆዩበትን ዋጋ በራሱ ውድ አድርጐት ቆይቷል፡፡ በዚህ ዋጋ ላይ ተጨማሪ ዋጋ መጫን ካለው የኅብረተሰቡ አጠቃላይ የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ለጋዜጦች ህልውና ስጋት መሆኑን አመልክተው፣ ‹‹የግሉ ፕሬስ ራሱን በራሱ እንዲገድል እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፤›› በማለት አዝማሚያውን ይገልጹታል፡፡

መንግሥት ለጉዳዩ ቶሎ እልባት በመስጠት ሊያስተካክለው ካልቻለ የግሉ ፕሬስ ከመጥፋቱም በላይ፣ በተዘዋዋሪ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትንም የሚጋፋ መሆኑን የተናገሩም አሉ፡፡

ተመሳሳይ አስተያየት የሰነዘሩት የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲተር አቶ ዳዊት ከበደ ናቸው፡፡ በእሳቸው እምነት ጉዳዩ የብርሃንና ሰላም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ለሚዲያው እየሰጠ ያለው ዝቅተኛ ትኩረት መገለጫም ነው፡፡

‹‹በሳምንት 50,000 ኮፒ በማይታተምበት አገር ውስጥ እንዲህ ያለው ጭማሪ በመንግሥት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው የሚመስለኝ፤›› ብለዋል፡፡

ለአንዳንድ ሸቀጦች የሚደረገው ድጐማም ለሚዲያ ኢንዱስትሪው መደረግ እንደነበረበትና በብዙ አገሮችም ለሚዲያ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አቶ ዳዊት ገልጸው፣ ‹‹የኢኮኖሚ ጫና በማድረግና ስልታዊ በሆነ መንገድ እንድናቆም ከሆነ የሚፈለገው የሕዝቡን መረጃ የማግኘት መብትም ችግር ውስጥ ይከተዋል፤›› ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ ኢዮብ ካሣም የጉዳዩን አሳሳቢነት ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ጭማሪው ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ቢሆንም፣ ተመኑን የሰሙት ባለፈው ዓርብ ባነጋግርናቸው ወቅት እንደሆነ በመግለጽ፣ የፕሬሱን ጉዞ አስቸጋሪ የሚያደርግ አስደንጋጭ ጉዳይ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡ በሕትመት ስርጭት ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ ሲገልጹም፣ አንባቢያን በዋጋ ጭማሪው ምክንያት የሚጠየቁትን ዋጋ ለመክፈል ስለሚከብዳቸው የጋዜጣ ሥራን አስቸጋሪና ከባድ ያደርገዋል፡፡

ባለፈው ጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም የሪፖርተር ባለቀለም ጋዜጣ ለማሳተም ይከፈል በነበረው ዋጋ ላይ ከ15 በመቶ ያላነሰ ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡

ከዚህ ቀደም የእሑዱን ባለ96 ገጽ የቀለም ጋዜጣ ለማሳተም 148,428.85 ብር ይጠይቅ የነበረው የሕትመት ዋጋ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው ተመን መሠረት ወደ 214,167.40 ብር ያሻቅባል፡፡ ልዩነቱ 65,742.55 ብር በመሆኑም ጭማሪውን 44.40 በመቶ ያደርሰዋል፡፡ በዚህ መሠረት የአንድ ነጠላ ጋዜጣ ማሳተሚያ ዋጋ 20 ብር ይደርሳል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣ ማርኬቲንግ ማኔጀር አቶ እንዳልካቸው ይማም እንደሚገልጹት፣ በብርሃንና ሰላም ተመን መሠረት ለ108 ገጽ ባለቀለም የእሑድ ጋዜጣን ለማሳተም ከዚህ ቀደም 168,516.50 ብር ይጠይቅ የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ ተመን መሠረት ግን 242,521.80 ብር የሚከፈል በመሆኑ፣ ልዩነቱን 73,960.30 ብር ያደርሰዋል፡፡ በመሆኑም ከ44 በመቶ በላይ ጭማሪ አስከትሏል፡፡

ከዚህ ቀደም የሚታተመው የእሑድ ጋዜጣ ዋጋ በነጠላ 14.05 ብር ነበረ፡፡ ለአከፋፋይ በ4.15 ብር ተሽጦ ለአንባቢያን በአምስት ብር ይደርሳቸው እንደነበር አቶ እንዳልካቸው ያስረዳሉ፡፡ በዚህም መሠረት 10 ብር ያህል ለአንድ ነጠላ ጋዜጣ ሪፖርተር ይደጉም ነበረ፡፡ በአዲሱ ዋጋ ደግሞ አንዱ የእሑድ ጋዜጣ ከ20 ብር በላይ የሚታተም በመሆኑ የጋዜጣውን ህልውና አደጋ ላይ እንደጣለው ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ በሳምንት ሁለት ጊዜ ለሚያሳትማቸው የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጦችና በሳምንት አንድ ጊዜ ለሚያሳትመው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋዜጣ በሰንጠረዥ ውስጥ የሚታየውን የሕትመት ዋጋ እንዲከፍል ይጠበቅበታል፡፡

የገጽ ብዛት የባለቀለም ገጾች ብዛት አዲሱ የሕትመት ዋጋ የቀድሞው ሕትመት ዋጋ ልዩነቱ በመቶኛ 

(%)

ማብራሪያ
32 4 27,572.65 18,946.00 8,626.65 45.50 ለእንግሊዝኛው ሕትመት
32 4 64,378.70 44,768.00 19,610.70 43.80 የረቡዕ አማርኛ ሕትመት
36 4 72,824.00 50,761.95 22,062.05 43.49 የረቡዕ አማርኛ ሕትመት
96 12 214,167.40 148,424.85 65,742.55 44.40 የእለተ ሰንበት ሕትመት
108 16 242,521.80 168,561.50 73,960.30 43.00 የእለተ ሰንበት ሕትመት

የሕትመት ዕቃዎችና ግብዓቶች በስፋት ከሚመጡባቸው አገሮች መካከል ህንድ አንዷ ስትሆን፣ የአገሪቱ የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ቢሮ በዚህ ወር ያወጣው የጅምላ ዋጋና የዋጋ ግሽበት መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ የጋዜጣ ሕትመት ዋጋና የማሰራጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ ታይቷል፡፡

ያነጋገርናቸው የጋዜጣ አሳታሚዎች በነገው ዕለት የማተሚያ ቤቱን ኃላፊዎች የማሳተሚያ ዋጋ ጭማሪውን በተመለከተ ለማነጋገር ቀጠሮ መያዛቸውን ገልጸውልናል፡፡

የአሁኑ ከፍተኛ የሕትመት ዋጋ ጭማሪ የጋዜጣ አሳታሚ ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን የጋዜጣን አንባቢያንን ጭምር የሚጐዳ መሆኑን ያነጋገርናቸው አሳታሚዎች ያስረዳሉ፡፡ እንዲህ ያለው ጭማሪ ሲደረግና በተለያዩ ሸቀጦች ላይም ተደራራቢ የዋጋ ጭማሪ ሲፈጠር፣ ዜጐች ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑና መረጃ የማግኘት መብታቸውን ጭምር የሚጋፋ ስለሆነ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻው አስታውቀዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close