በኤርትራ ላይ ሊጨከን ነው ወይስ…?

ኢትዮጵያን ላለፉት 20 ዓመታት የገዛው የኢሕአዴግ መንግሥትና በበላይነት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኤርትራ ላይ በያዙት አቋምና በሚወስዱዋቸው የተለሳለሱ ዕርምጃዎች በብዙዎች ዘንድ ለትችት ዳርጓቸው ቆይቷል፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል ወቅት በኤርትራ ላይ ከያዘው ‹‹የቅኝ ግዛት›› አቋም ጀምሮ፣ መለያየቱንና ከዚያም በኋላ በድንበር ውዝግቡ የሆነውን ሁሉ በመታዘብ፣ የኢትዮጵያ መሪዎችን ማንነት ጥያቄ ውስጥ እስኪገባ ድረስ የተሳሳቱና ሚዛናቸውን ያልጠበቁ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የሚያስታውሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስለ ኤርትራ የሚሰጡዋቸው ጠንከር ያሉ መግለጫዎች ግን ብዙዎችን ግራ ያጋቡ ይመስላሉ፡፡ ተቃዋሚዎች ደግሞ የአገር ውስጥ ችግርን የማስቀየስና አጀንዳ የመፍጠር ጉዳይ አድርገውታል፡፡ ኢሕአዴግ በታሪኩ ሞክሮት የማያውቀውን ወረራ ሊያካሂድ ይሆን? የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽስ ምን ይሆን?

ከመከላከል ወደ ማጥቃት?
የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ የአቋምና የስትራቴጂ ለውጥ ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ በኤርትራ ላይ ለረዥም ጊዜ ይዞት የቆየውን ሽብርን የመከላከል ስትራቴጂ መቀየሩን ግልጽ ያደረገው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ‹‹አሰና›› ከተባለ አንድ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ‹‹ከኋላ ሆነው አይዞህ ሲሉት ከነበሩት መንግሥታት መካከል ሁለት ሦስተኛው ተወግደዋል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ‹‹ለተደፈጠጠው ሕዝብ ተስፋ›› አድርገው የተመለከቱትን የወቅቱ የሰሜን አፍሪካ አመፅም በአዎንታዊ መልኩ አንስተዋል፡፡ ከሥልጣን ከተገለሉት መካከል ዋነኞቹ ሁከት ፈጣሪ መሆናቸውን በማስታወስ፡፡ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የአስመራ መንግሥት የሚከተለው ፖሊሲ ሕግሐኤ (ሻዕቢያ) በሳህል የትጥቅ ትግል ይከተለው ከነበረው የሚለይ እንዳልሆነ በመተቸት፣ ‹‹ኤርትራዊ ለመሆን ብቃት የሌለው ትውልድ ፈርሶ እንደ አዲስ መሠራት አለበት ብለው፣ የወጣት ኤርትራውያንን አጥንት አፍርሰው ለመግጠም እየሞከሩ ነው፤›› በማለት ኃይል የተቀላቀለበት ንግግር አድርገዋል፡፡ አቶ መለስ በዚህ ዓይነቱ በኤርትራ ላይ ጠንካራ ሊባል የሚችል ንግግራቸው፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት ጓደኞቹን በየተራ መወገዳቸውን ሲመለከት በአንገቱ ዙርያ የተጠመጠመው ገመድ እንደሆነ ያያል፤›› ብለዋል፡፡  የእነ ሙባረክንና ጋዳፊን ዕጣ ፈንታን በማስታወስ፡፡

አቶ መለስ መንግሥታቸው እስካሁን በኤርትራ ላይ የተከተለው የመከላከል ስትራቴጂ ጉድለት እንደነበረው የጠቀሱ ሲሆን፣ ‹‹አሁን የኤርትራ መንግሥት ፖሊሲውን እንዲቀይር ወይም ከሥልጣን እንዲወገድ ለመንቀሳቀስ ወስነናል፤›› በማለትም የስትራቴጂያቸው ለውጥ አበስረዋል፡፡ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም፣ የኤርትራን መንግሥት የሽብር ተግባር ከመቆጣጠር በዘለለ ወታደራዊም፣ ፖለቲካውም ዕርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ አሳውቀዋል፡፡

ባለፈው ሰሞን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማምረት ብቃቷን ለሌሎች ተሞክሮዋን እንድታካፍል ተጋብዛ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ስብሰባ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም፣ ተደረገ ስለተባለው የስትራቴጂ ለውጥ ከተመድና ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር በኒው ዮርክ መምከራቸውን ተናግረዋል፡፡ በኤርትራ መንግሥት ላይ የተጣለው የተመድ ማዕቀብ ተግባራዊ ሳይሆን በመጓተቱ ኢትዮጵያ ቅሬታ እንዳላት ማስረዳታቸውን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በአሁኑ ወቅት የተጣለውን ማዕቀብ ተግባራዊ ማድረግን ጨምሮ በኤርትራ ላይ አግባብ ያለው ዕርምጃ ካልተወሰደ የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱን መፍትሔ እንደሚፈልግ አሳስበዋል፡፡ እሳቸው፣ ‹‹በዚህ የስትራቴጂ የመጀመሪያ ዕርምጃ ለውጥ ካልመጣና የኤርትራ መንግሥት አደብ ካልገዛ ግን መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ ለመውሰድ ወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ተመሳሳይ ተግባር እየፈጸመ አልነበረም ወይ? አሁን ምን አዲስ ነገር ስላለ ነው የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ የተገደዳችሁት በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹አዲሱ ነገር የኤርትራ መንግሥት እንቅስቃሴ ሌላ ሥራ ትቶ 24 ሰዓት ኢትዮጵያን እንዴት ላተራምስ ብሎ አቅዶ የሚንቀሳቀስ ሆኗል፡፡ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት ሥራዬ ብሎ እየተንቀሳቀሰበት ይገኛል፡፡ ይህንን ሥራውን እንዲያቆም የስትራቴጂ ለውጥ ለማድረግ ተገደናል፤›› ብለዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ በተባለው በተለይ ተመድንና አሜሪካን ዕርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ ካልተቻለ፣ የምትወስዱት ዕርምጃ ምን ዓይነት ነው? ለሚለው ተከታይ ጥያቄ ግን፣ ‹‹በጊዜው ይገለጻል›› ከማለት ውጪ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር፣ በአሁኑ ወቅት የመድረክ የሥራ አመራር አባልና የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ስዬ አብርሃ ግን ይህንን የኢትዮጵያ መንግሥት የአቋም ለውጥ ‹‹ትርጉም ያለው አይደለም›› ያሉበትን ምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡ ‹‹ይኼ መንግሥት አስመራ ያለው መንግሥት ባህሪ ምን እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማወክ እንደሚፈልግ ይታወቃል፡፡ አንዴ ጦርነቱ ከተከፈተብን ይኼ መንግሥት ሰላም አይሰጠንም ብለን አቋም በመያዛችን የተለያየ ስም ተለጥፎብን ተወግዘናል፡፡ ስለዚህ አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ የአቶ መለስ መንግሥት ይህንን እያወቀ መሬትም ቢሆን ቆርሶ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፤ ሰላም እስከሰጣችሁን ድረስ ብሎ በ1996 ዓ.ም. በፓርላማ አዋጅ አውጥቷል፡፡ ይኼ ግን የኤርትራን መንግሥት እንደማይመልሰው እየታወቀ መሞዳመዱን ስለመረጠ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሁኔታ ቀጥሏል፤›› ብለዋል፡፡

በተግባርም የኤርትራ መንግሥት ባህሪ አለመለወጡን የሚናገሩት አቶ ስዬ፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ግን እንደ መጫወቻ ካርድ ነው የሚጠቀምበት እንጂ፣ አዲስ ነገር ኖሮት አይደለም ወይም ደግሞ ቁምነገር ይሠራል ተብሎ አይጠበቅም፤›› በማለት ጉዳዩን በሌላ መልኩ ይመለከቱታል፡፡

‹‹በአስመራ ሰው ይኑር ዝንጀሮ መቼ ጉዳይ ሆነ?››
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኤርትራን በተመለከተ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሻቸው ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ‹‹እኛ ችግራችን ከኤርትራ ሕዝብ አይደለም፣ አስመራ ካለው የሻዕቢያ ቡድን እንጂ፤›› ከሚለው እሳቤ ተነስተው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር፣ ‹‹አስመራ ቤተ መንግሥት ዝንጀሮም ቢቀመጥ የእኛ ጉዳይ አይደለም የኤርትራ ሕዝብ ጉዳይ እንጂ፤›› በሚልም የሽብር ተግባሮችን መከላከል እንጂ አስመራ በመሄድ የምንቀይረው መንግሥት አይኖርም፣ ኃላፊነታችንም አይደለም ሲሉ ይደመጡ ነበር፡፡ ለዚህም የአንድ አገር ሉዓላዊነትን እንደሚያከብሩ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ የሕዝቡ የራሱ ሥራ መሆኑን የፀና አቋም እንዳላቸው፤ እልባት ሳያገኝ አሥር ዓመት ያለፈበት የድንበር ግጭትም ለብዙዎች ግልጽ ባልነበረው ‹‹የሰጥቶ መቀበል›› ድርድር እንዲፈታ ነበር ደጋግመው የሚናገሩት፡፡

መንግሥታቸው ከአምስት ዓመት በፊት በሶማሊያ ጣልቃ ገብቶ በተለያዩ የኢትዮጵያ ጠላት አገሮች የሚደገፈውና በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ አውጆ የነበረው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን (ICU)፣ በኋላ ደግሞ በአክራሪነቱ የሚታወቀውን የአልሸባብ ቡድንን ለመበታተን ከፍተኛ የሰውና የንብረት ኪሳራ ያስከተለው፣ በዋናነት የኤርትራ መንግሥት ሴራ እንደነበር የተረጋገጠ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ የሁለት ዓመት ቆይታቸው በርካታ የኤርትራ ቅጥረኛ ወታደሮችና ሰላዮችም እንዳጋጠሙዋቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በዘለለ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በመክፈት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃራኒ ከሆኑ እንደ ግብፅ ከመሳሰሉ ወገኖችም ጋር ሲያሴር እንደቆየ ይገለጻል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ የአርበኞች ግንባር፣ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (TPDM) እና የመሳሰሉ ዓማፂ ቡድኖችንም በማደራጀትና በማስታጠቅ ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው ገብተው የሽብር ተግባር እንዲፈጽሙ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአስመራ ዝንጀሮም ይሁን ሰው ቢቀመጥ ጉዳያችን አይደለም ሲሉት የነበሩት ነገር አሁን ለምን ጉዳይ ሆነ?›› በማለት የሚጠይቁት የቀድሞ ጓዳቸው አቶ ስዬ፣ ‹‹በአገር ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ችግር ሊያስከትል የሚችለው ፖለቲካዊ መዘዝ ይኖራል ብሎ የኢሕአዴግ መንግሥት ይሰጋል፡፡ ስለዚህ ይህቺን የሻዕቢያ ካርድ እየመዘዘ ሕዝቡን ለማስፈራራትና ፀጥ ለማድረግ ስለሌላ ስጋት እንዲያስብ ያደርጋል፤›› በማለት የአጀንዳ ማስቀየስ ስትራቴጂ አድርገው ተመልክተውታል፡፡ ‹‹ሕዝቡ ኢሕአዴግ ራሱ የሚፈጥርበትን ችግር እንዳይመለከት ለማድረግ እንጂ የኤርትራ መንግሥት ባህሪ አዲስ ነገር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አዲሱ ነገር ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ውስጥ ውጥረት አለ፡፡ የኢኮኖሚ ችግር አለ፤ ሕዝቡ ተማሯል፡፡ በሌሎች የአካባቢያችን አገሮች እየሆነ ያለውንም ያየዋል፡፡ ስለዚህ ይኼ ነገር ወደ ኢትዮጵያ ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ስጋት የለንም ሲሉ የሚታመን ነገር አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

አዲስ አበባን ባግዳድ የማድረግ ስትራቴጂ?
ኤርትራን ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) እንድትገለል ከማስገደድ ጀምሮ፣ በኢሳያስ ፕሬዚዳንትነት የሚመራው መንግሥት በአፍሪካ ኅብረትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህ ነው የሚባል ቦታ እንዳያገኝ በማድረግ ከዓለም ፖለቲካ እንዲነጠል ከፍተኛ ሥራ መሠራቱ ይነገራል፡፡ ይህንን በማድረግ የተሳካ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራታቸው የሚነገርላቸው የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአሁኑ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሥዩም መስፍን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ መንግሥትን በአሁኑ ወቅት ከዚህ ከዲፕሎማሲና ከፖለቲካ የመነጠል ሥራና የመከላከል ስትራቴጂ ወጣ ብሎ የቀደመ ዕርምጃ (Pro-active Measure) እወስዳለሁ ያለበት ምክንያት፣ አዲስ አበባን ባግዳድ አደርጋታለሁ በሚል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ስለደረሰበት መሆኑን ይናገራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሰሜን አፍሪካዋ ቱኒዝያ የተጀመረው ሕዝባዊ ዓመፅ በሌሎች አገሮች በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ እየተዛመተ ባለበት፣ በምርጫና ተዛማጅ ጉዳዮች አፍሪካ እየታመሰች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ በማነጣጠሩ ጥያቄ የሚያነሱ እየበዙ ናቸው፡፡

‹‹ምንድን ነው ዓላማቸው ቢባሉስ መልስ አላቸው ወይ?›› በማለት የሚጠይቁት አቶ ስዬ፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥትን አስወግደውስ ምን ሊያደርጉ ነው?›› ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ዝንጀሮ ቢቀመጥበትም ጉዳያችን አይደለም አላሉም ወይ በማለት አስተያየታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ‹‹ዝንጀሮ ሳይሆን በአስመራ ሰው መኖር አለበት ብሎ ካልተነሳ ከዚህ በመለስ ምን ዕርምጃ ነው የሚሆነው? ዝም ብሎ ደም መፋሰስ? በሰው ሕይወት መቀለድ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራን ወታደር አሸንፈው አስመራ ያለውን ዝንጀሮ በሰው የመቀየር ዓላማ የላቸውምና፡፡ ከዝንጀሮ ጋር ተጎራብቶ ለመኖር ከተፈለገ ምን ለማድረግ ነው ዕርምጃ የሚወሰደው?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ እንደሚሉትም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ካሰፈረው ‹‹የማንንም አገር ሉዓላዊነትን የማክበር መርህ›› የሚጥስ ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት በሶማሊያና በጂቡቲ በሚያደርጋቸው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶችና አካባቢውን የማተራመስ እንቅስቃሴ ምክንያት በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የተጣለበት ማዕቀብ ተግባራዊ ባለመሆን ያልተደሰተው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የማስፈራሪያ ስትራቴጂ አሁን ማውጣቱ ለምን አስፈለገ? በማለት የሚጠይቁት እኚህ ምሁር፣ እንደ አቶ ስዬ ሁሉ የሕዝብ ትኩረትን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለማስቀየስ ይሆናል የሚል ጥርጣሬም አላቸው፡፡ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን ጉዳዩን በተመለከተ ከተመድና ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር በሰሞኑ የኒው ዮርክ ጉብኝታቸው እንደመከሩበት ይናገራሉ፡፡ መንግሥት በአስመራው ቡድን እንቅስቃሴ ላይ አገኘሁት ያለውን አዲስ መረጃም ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ማሳወቃቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አዲስ አበባን ባግዳድ ለማድረግ ስትራቴጂ ቀርጸው ከሌሎች የኢትዮጵያ ዓማፂዎች ጋር መንቀሳቀስ መጀመራቸውን የሚመለከት ነው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን ፈንጂ በማፈንዳት ለመበጥበጥ ሻዕቢያ ሙከራ አድርጓል የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከወዲሁ በመከላከል ላይ ያተኮረው ስትራቴጂውም ሊከሽፍበት እንደሚችል ስጋቱን ይገልጻል፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ወዳጆች የሆኑት መሪዎች አጣብቂኝ ውስጥ በገቡበት በአሁኑ ወቅት፣ ማስጨነቅ ትክክለኛ ስትራቴጂ ነው ቢሉም፣ ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባን ባግዳድ እናደርጋታለን ያሉት በየትኛው ሚዲያ ይሆን? በማለት ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡

ይኼ የሚባለው የዲሞክራሲን መርህ እንደማይከተል በስፋት የሚነገርለት የኢሳያስ መንግሥት፣ በርካታ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችንና ዜጎችን ለእስርና ለስደት ዳርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት አምባገነን መንግሥታትን እያቃጠለ ያለው የሰሜን አፍሪካ ዓመፅ ዓይነት በኤርትራ ያልተከሰተ ቢሆንም፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎችም በአዲስ አበባ ስብሰባ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ አሥራ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባል የሆኑበት የኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ኪዳን የሚገኝበትና ሌሎች ሲቪክ ማኅበረሰቦች የተካተቱበት የኤርትራ ብሔራዊ ጉባዔ ለማካሄድ የተቋቋመው 56 አባላት ያሉት ኮሚሽን በገነት ሆቴል ስብሰባ እያካሄደ ሲሆን፣ እስካሁን ያደረጋቸውን ተግባራት እየገመገመ በወቅታዊው የኤርትራ ጉዳዮች ላይም እየተነጋገረ ይገኛል፡፡ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተወልደ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ስለቀየሰው አዲስ ስትራቴጂ አስመልክተው፣ ‹‹ድሮም የተሳሳተ ስትራቴጂ ነበር የተከተለው፡፡ ለኤርትራ ሕዝብ የማይጠቅም መንግሥት ለኢትዮጵያ ሊጠቅም አይችልም፡፡ የኤርትራ መዘዝ የኢትዮጵያ መዘዝ መሆኑን ቀድሞ መገንዘብ ነበረበት፤›› ይላሉ፡፡ በመሆኑም፣ የአሁኑን ዓይነት ስትራቴጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀድሞ መከተል የነበረበት መሆኑን በማስገንዘብ፣ ትክክለኛ ስትራቴጂ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close