አዳማን በተኩስ ያሸበሩት የጥበቃ ሠራተኛ ሁለት ሰዎች ገድለው ሞቱ

Reporter:አዳማ በሚገኘው በኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ቅርንጫፍ መሥርያ ቤት ያገለግሉ የነበሩት አቶ ጄሉ ሁሌ የተባሉ የጥበቃ ሠራተኛ፣ ከትናንት በስቲያ ከንጋቱ 12፡30 ጀምሮ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የአዳማ ከተማን በመሣርያ ተኩስ ካሸበሩ በኋላ ሁለት ሰዎችን ገድለው እሳቸውም መገደላቸው ተገለጸ፡፡ የጥበቃ ሠራተኛው በያዙት መሣርያ ሁለት ሰዎች ከገደሉና አንድ የፖሊስ አባልን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን ካቆሰሉ በኋላ፣ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የአዳማ ከተማ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ሻለቃ ብዙነህ ቦደና ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

በጥበቃ ሠራተኝነት ከተሰማሩበት የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ አዳማ ቅርንጫፍ ከሥራ ወጥተው ወረዳ አንድ አካባቢ ወደሚገኘው የባለቤታቸው መኖርያ ቤት ሲደርሱ፣ በተለያየ ጊዜ ሲጋጩዋቸው የነበሩትን ባለቤታቸውን ያጡዋቸዋል፡፡ ከዚያም በባለቤታቸው መኖርያ ቤት ላይ ለደቂቃዎች ሲተኩሱ ከቆዩ በኋላ ወደ መሃል ከተማ እየተኮሱ ሲመለሱ፣  በታጣቂዎች ላይ ተኩስ ከፍተው እንደነበር ሻለቃ ብዙነህ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ድርጊታቸው ሁለት ሰላማዊ ዜጎችን ለሕልፈተ ሕይወት ማብቃታቸውንና አንድ የፖሊስ አባልን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን ማቁሰላቸውን የወንጀል መከላከል ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ተኩስ በማቆም እጃቸውን እንዲሰጡ ከታጣቂዎችና ከፖሊስ አባላት የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ባለመቀበል መተኮሳቸውን ሲቀጥሉ፣ በፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የእሳቸውም ሕይወት ለሕልፈት  መብቃቱን ሻለቃ ብዙነህ አክለው ገልጸዋል፡፡

የጥበቃ ሠራተኛው ወደ ሰማይ እየተኮሱ ስለቆዩ በተባራሪ ጥይት ከሞቱትና ከቆሰሉት ሰዎች በተጨማሪ በሌሎች ግለሰቦች ላይ አደጋ ደርሶ እንደሆነ ፖሊስ ሲያጣራ የቆየ ቢሆንም፣ ተጨማሪ አደጋ አለመድረሱ መረጋገጡን ሻለቃ ብዙነህ አብራርተዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close