ጀርመን አሥር የፒኤችዲ ትምህርቶችን ለኢትዮጵያውያን አዘጋጀች ሌሎችም አጫጭር ዜናዎች ተካተዋል

የጀርመን የትምህርት ልውውጥ አገልግሎት ጀርመን አገር ሄደው ለሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች አሥር የፒኤችዲ የስኮላርሺፕ ትምህርቶችን መዘጋጀታቸውን፣ በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ተጨማሪ ስኮላርሺፖችን በኢትዮጵያ ለሚማሩ ተማሪዎች ለሦስት ዓመት የሚቆይ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል የ790 ሺሕ ዩሮ በጀርመን የትምህርት ልውውጥ ፕሮግራም መዘጋጀቱ ተመልክቷል፡፡ ይህ የተገለጸው የጀርመን የትምህርት ልውውጥ ፕሮግራም ዋና ፀሐፊ ዶክተር ዶሮቲ ሩላንድ ከመጋቢት 7 እስከ 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

*      *       *
ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ
አገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የ2003 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ከ1.3 ሚሊዮን የሚበልጡ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን እንደሚወስዱ አስታወቀ፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው አገር አቀፍ ፈተናዎች ከግንቦት 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ይሰጣል፡፡ የዘንድሮ የስምንተኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከግንቦት 17 ቀን ጀምሮ የ10ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና፣ ከግንቦት 30 ቀን ጀምሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና፣ ከሰኔ 6 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል ተብሏል፡፡ በዚህ ዓመት በመላ አገሪቱ ባሉ 1,111 ትምህርት ቤቶችና በውጭ አገር በሚገኙ ሦስት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች ከ1,300,000 ለሚበልጡ ተፈታኞች የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም በ414 የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከ144 ሺሕ ለሚበልጡ ተፈታኞች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና እንደሚሰጥም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

*      *       *
የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ኤግዚቢሽን አዘጋጀ
የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክትልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ‹‹ሆርቲፍሎራ ኢትዮጵያ 2011›› በሚል መጋቢት 14 ቀን 2003 ዓ.ም. የሚከፈት ኤግዚቢሽን ማዘጋጀቱን ማስታወቁን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በሚከፈተው በዚህ አራተኛው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ ከ30 አገሮች የመጡ ከ150 በላይ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ፡፡ ከተሳታፊ ኩባንያዎች መካከልም የግብርና ግብዓት፣ የመስኖ መሣሪያዎች፣ የግሪን ሀውስ፣ የዘርና ችግኝ፣ የምርት መሰብሰቢያና ማሸጊያ፣ የእርሻ መሣሪያዎችን፣ ማቀዝቀዣዎችንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የሚያቀርቡ ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ የአበባ፣ አትክትልና ፍራፍሬ ምርቶችን የሚገዙ ኩባንያዎችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

*      *       *

የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ተመረቀ
ባለ 400 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በይፋ መመረቁን ዋልታ ዘግቧል፡፡ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ተመርቋል፡፡ በ2001 ዓ.ም. ሥራው የተጀመረው የበለስ፣ ባህርዳር፣ ደብረ ማርቆስና አዲስ አበባ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት በአገሪቱ እየተገነቡ ከሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ዓላማውም ከበለስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፍ አቅም ባለው መስመር ወደ ተያያዙት ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ወይም ወደ ብሔራዊ ኃይል ጥምረት ማስገባት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከአጠቃላይ ወጪው 85 በመቶ ከቻይና በተገኘ ብድር፣ ቀሪው ደግሞ በመንግሥት ፕሮጀክት በሦስት ዙሮች ተከፋፍሎ የተከናወነ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close