ገመና ድራማ በቅርቡ ቀጣዩ ክፍል ይቀጥላል ‹‹ገመና ቁጥር ሁለት ብለው ርዕሱን መጠቀም አይችሉም›› አቶ አድነው ወንድይራድ፣ የገመና ድራማ ደራሲ

የሪፖርተር ጋዜጣ ያጠናቀረውን እኛ እንዲህ አቅርበንላችኋል ፣

የአርክቴክቸር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በ1979 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያም ለተወሰኑ ዓመታት ከሠሩ በኋላ ወደ ኪነጥበብ ገብተዋል፡፡ የገመና ድራማ ደራሲ አቶ አድነው ወንድይራድ እውነተኛ ታሪኮችን፣ ቴአትሮችና ፊልሞችን ጽፈዋል፡፡ የአና ማስታወሻ፣ ጣውንቶቹና ክሊዮፓትራ ከጻፏቸውና ተርጉመው ለመድረክ ካበቋቸው ቴአትሮች የሚጠቀሱ ሲሆኑ አንድ ዕድል የተሰኘውን ፊልምም ጽፈው ራሳቸው ዳይሬክት አድርገዋል፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አድነው ምንም እንኳ በርካታ ሥራዎችን ቢያበረክቱም የሚጠቀሙት በብዕር ስማቸው ‹‹አዶኒስ›› በመሆኑ ብዙ አይታወቁም፡፡ በመልክም እንደዚያው፡፡ በዚህ ምክንያት እኛም ምስላቸውን ይዘን መውጣት አልቻልንም፡፡ ቁጥር ሁለት ገመና ድራማ የፊታችን እሁድ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቁጥር አንድ ገመና ድራማ ደራሲ አቶ አድነው በቁጥር ሁለት ላይ አይሳተፉም፡፡ ከገመና ድራማ ጋር በተያያዘ ምሕረት አስቻለው አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ከሜጋ ኪነጥበባት ማዕከል ጋር የነበራችሁ ግንኙነት እንዴት ነበር?

አቶ አድነው፡- ከገመና ድራማ በፊት ከሜጋ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረኝም፡፡ ፍላጎትም እንደዚያው፡፡ ብዙ ሥራ ሠርተዋል ልንገናኝ የምንችልባቸው ዕድሎችም ተፈጥረዋል፡፡ በአንድ አጋጣሚ አርባ ክፍል ያለው ድራማ ኮንትራት ነበራቸው፤ አሥራ አምስቱን መሥራት ችለው ሃያ አምስት ቀርቷቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ያንን ሃያ አምስት ክፍል የሚሠራላቸው ሰው በመፈለግ ላይ ሳሉ ከእነሱ ጋር ይሠራ በነበረ አንድ ጓደኛዬ በኩል ቀረቡኝ፡፡ የሙሉ ጽሑፉን ይዘት አይተውና ገምግመው ሳይሆን ለሃያ አምስት ክፍል የሚያዘጋጀውን ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ ሳያዩ የሚቀበሉኝና የሚከፍሉኝ ከሆነ ፈቃደኛ መሆኔን ገለጽኩ፡፡ እነሱም ተስማሙ፡፡ ተፈራረምን፡፡ ሃያ አምስቱ ክፍል ሳያልቅ ሜጋ ፈረሰ፡፡ ገመና ላይ የተሳተፉት የሜጋ ሠራተኞች ብቻ እዚያ ቢሮ ውስጥ ሥራውን ለመጨረስ ቀሩ፡፡ ይቀጥል ከተባለ ሥራው መቀጠል ያለበት ሜጋ ወደ ዋልታ ስለተቀላቀለ ከዋልታ ጋር ወይም ከሌላ አካል ጋር መሆን ነበረበት፡፡ የሜጋ ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ እቁባይ በርኸ ይኽን ያውቅ ስለነበር ደአማት በሚል ድርጅት ሥር ለሌላ ሃያ አምስት ክፍል ተፈራረምን፡፡ እኔም ለዓመት እንዲሞላ በማሰብ ምንም እንኳ የተፈራረምኩት ለሃያ አምስት ክፍል ቢሆንም ሃያ ሰባት አደረግኩት፡፡

ሪፖርተር፡- የተከፈለዎት በስምምነታችሁ መሠረት አልነበረም?

አቶ አድነው፡- በእርግጥ በስምምነታችን መሠረት አልነበረም፡፡ በመጀመሪያው ሃያ አምስት ነገሮችን ስላየ በሁለተኛው የተደረገው ምንም ነገር ሳያይ ግማሽ ክፍያ ሊሰጠኝ ነበር፡፡ ሌላውን ግማሽ ደግሞ ቀሪውን ግማሽ ክፍል ሳስረክብ ነበር፡፡ ነገር ግን በስምምነታችን መሠረት አንድ ክፍል ሃያ ደቂቃ ነበር፡፡ ይህ አንሷል በሚል የሕዝብ አስተያየት በሁለተኛ ሃያ አምስቱ ክፍል ሠላሳ ደቂቃ እንዲሆን ተደረገ፡፡ ይህ ተጨማሪ ሥራ ስለሆነ ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልገኝ ግልጽ ነው፡፡ ልወስድ የማይገባኝን ገንዘብ አልወሰድኩም፡፡ ስለዚህ የገንዘቡ መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት ክፍያዬን እወስድ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ገመና ቁጥር አንድ ሲጠናቀቅ የተለያያችሁት በምን ነበር?

አቶ አድነው፡- ገና ወደ አርባ ክፍል ገደማ እያለ እንደምንቀጥለው ስላወቅኩ ቁጥር ሁለትን ጀምሬው ነበር፡፡ እናም የቁጥር ሁለትን አምስት ክፍል (ለአምስት ሳምንታት የሚታይ) ሰጥቻቼዋለሁ፡፡ ከዚያ በመነሳት ድራማው ለአንድ ዓመት እንዴት እንደሚሔድ መመልከት ይቻላል፡፡ ያ የድራማው ፎርማት ነው፡፡ እንዴት እንደሚቀጥል በግልጽ ያሳያል፡፡ ቁጥር አንድ ያለቀው ሃምሳ ሁለተኛ ክፍል ላይ ነው፡፡ የድራማውን ቀጣይ አካሔድ ሃምሳ ሦስት ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ያንን ተከትሎ ማንም ሊሠራው ይችላል አቅጣጫው በእጃቸው ስለሆነ፡፡ ጥሩ አድርገው ሊጽፉት ይችላሉ? ሌላ ጉዳይ ቢሆንም ሊጽፉት ግን ይችላሉ፡፡ እናም ያን የሰጠኋቸውን አምስት ክፍል አይጠቀሙበትም ብዬ አላስብም፤ ስጋቴም ያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመካከላችሁ አለመግባባት የተፈጠረው እንዴት ነው?

አቶ አድነው፡- ከሽልማቱ ጋር በተያያዘ ከእነሱ እንድጠብቅ የተደረግኩት ነገር ነበር፡፡ ቃል የተገባልኝ ነገር ባይኖርም በተዘዋዋሪም ቢሆን በሽልማቱ ላይ እንድጠብቅ የተነገረኝ ነገር ነበር፡፡ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ከመድረሱ በፊት ቁጥር ሁለትን በሚመለከት እንድፈራረም ጠየቁኝ፡፡ ድራማው እንደሚቀጥል አውቃለሁ፡፡ ግን ከመፈራረሜ በፊት የሽልማቱን ቀን ማየት አለብኝ አልኩኝ፡፡ ምን ያህል ለሥራዬ ዋጋ እንደሚሰጡ ማየት ፈለግኩኝ፡፡ ቀኑ ደረሰ የጠበቅኩት ነገር አልሆነም፡፡ ይህ የቅሬታዬ መጀመርያ ነበር፡፡ የጠበቅኩትን ትልቅ ነገር አላገኘሁም ስለዚህ ይገባኛል የምለውን ነገር ማግኘት አለብኝ፡፡ ለገመና ቁጥር ሁለት 1.5 ሚሊዮን ብር ነበር የጠየቅሁት፡፡ ይህ ደግሞ ከእሳቤያቸው ውጭ የሆነ ገንዘብ ነበር፡፡ የቱንም ያህል ክፍያውን ከፍ ባደርገው ከአምስት መቶ ሺሕ ብር በላይ ይሔዳል ብለው አልጠበቁም፡፡ ለሚከፍለኝ አካል ገንዘቡ ቀላል ነው ወይም የመክፈል አቅም አለው የሚለው ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ማንም ይክፈለው ማን፣ ገንዝቡ በስፖንሠር ይሰብሰብ ወይም በሌላ መንገድ የጠየቅኩት ገንዘብ ለሥራዬ ይገባኛል ያልኩትን ነው፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ በገመና ድራማ የአንድ አገርን ሕዝብ ማዝናናት ቀላል ነገር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- 1.5 ሚሊዮን ብር ሲጠይቁ እነሱ ስንት ብለው ነበር?

አቶ አድነው፡- የጠየቅኩት ገንዘብ ከጠበቁት በላይ ስለሆነባቸው የምንችለው ይኼን ያህል ነው ብለው ያስቀመጡት ነገር አልነበረም፡፡ በእርግጥም እኔም የጠየቅኩት ገንዘብ ለድርድር እንደማይቀርብ በወቅቱ አሳውቄ ነበር፡፡ ግን ዓይነት አለው እኮ፡፡ ነገሮች ሲቀዘቅዙ መግባባት ላይ መድረስ የምንችልበትን መንገድ መፍጠር እንችል ነበር፡፡ ግን እኔ በራሴ መንገድ የፈለግኩትን አደርጋለሁ ሲባል ነው ችግር የተፈጠረው፡፡

ሪፖርተር፡- ገመና ቁጥር ሁለት ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች ነው እየተጻፈ ያለው?

አቶ አድነው፡- በእነዚህ ሰዎች የሚጻፈው ስክሪፕት ምን ሊመስል ይችላል ለሚለው የራሴ ግምት አለኝ፡፡ እዚህ ጋ የምፈራው ግን ጸሐፊዎቹ እኔ ቀደም ሲል ስለሰጠሁት አምስት ክፍል ምንም የሚያውቁት ነገር ስለሌለ፣ የሚያጽፋቸው አካል እንደ አዲስ የራሱ ሐሳብ እያስመሰለ የእኔን ሐሳብ እንዳይሰጣቸውና እነሱም በዚያ መልኩ እንዳይጽፉና እንዳይሳሳቱ ነው፡፡ እኔ በኋላ ለመከራከሪያ እንዲሆነኝ ለእነ እቁባይ የሰጠሁትን አምስት ክፍል ለመገናኛ ብዙኀን በትኛለሁ (ሪፖርተር ጋዜጣም ኮፒው ደርሶታል)፡፡ ስለ ጉዳዩ ፀሐይ ላይ ወጥቼ መጮህ አልችልም፡፡ መገናኛ ብዙኀን የሥራዬ ጠባቂ እንዲሆኑልኝ በማሰብ ነው የበተንኩት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በገመና ቁጥር ሁለት ላይ ጥያቄዎት ምንድን ነው?

አቶ አድነው፡- ለጊዜው እያልኩ ያለሁት ገመና ቁጥር ሁለት ብለው ርዕሱን መጠቀም አይችሉም ነው፡፡ በስክሪፕቱ ላይ ለጊዜው ምንም ማለት አልችልም፡፡ የተወሰኑት ሥራዎችን እስክመለከት ድረስ፡፡ ነገር ግን የሰጠሁት አምስት ተከታታይ ክፍል ጽሑፍ ሌላው ጥያቄዬ ነው፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ይዤ የተነሳሁት የርዕሱን ጉዳይ ነው፡፡ በተመሳሳይ ስለ አምስቱ ክፍል ስክሪፕት ደግሞ ለሚዲያ አሳወቄያለሁ፡፡ ይኼን ያህል ጊዜ ሥሠራ ሚዲያ ላይ ወጥቼ አላውቅም፡፡ አሁን ግን ግዴታ አለብኝ፡፡ ምንም ነገር ቢፈጠር ሚዲያ ላይ አይወጣም፤ እኛም የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን የሚል እሳቤም ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ አንድም ይኼ አስተሳሰባቸው ትክክል እንዳልሆነ ማሳየት ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ሚዲያ በተጨማሪ በዚህ ጉዳይ ከጀርመን ሬዲዮ ጣቢያ ጋርም ቃለ መጠይቅ አድርጌያለሁ፡፡ የመጀመሪያ ዕርምጃ ያደረግኩት ሚዲያ ላይ መውጣትና በእኔ በኩል ያለውን ነገር ማሳወቅ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ወደ ክስና ወደ ማሳገዱ እሄዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ገመና ቁጥር ሁለት በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በቅርቡ እንደሚጀምር ማስታወቂያ እየታየ ነው፡፡

አቶ አድነው፡- አዎ ለሃምሳ ሁለት ሳምንታት ሲያዝናናችሁ የቆየው ገመና ቁጥር ሁለት ይቀጥላል ነው የሚለው ማስታወቂያው፡፡ ርዕሱን መጠቀማቸው ብቻ ሳይሆን ችግሩ ከመጀመሪያው ጋር ሁለተኛውን ሊያለያዩት አለመፈለጋቸው ነው፡፡ ታይታኒክ ብሎ ፊልም መሥራት ይቻላል፣ ሃሪፖተር ብሎ ግን ፊልም መሥራት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሃሪፖተር እንደ ንግድ ስያሜ (ትሬድ ኔም) ሆኗል፡፡ ገመና እንደ አንድ ነጠላ ድራማ ርዕስ አይደለም፡፡ ትሬድ ኔም ሆኗል፡፡ ስፖንሰር የሚመጣው ለዚያ ነው፡፡ የተከታታይ ድራማ ርዕስ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ትሬድ ኔም ያደርገዋል፡፡ እነሱም ስሙን መጠቀም የፈለጉት ለዚያ ነው፡፡ በዚያ ላይ ከመጀመሪያው ጋር ላለማነጣጠል እየሞከሩ፡፡ ይኼ ሕጋዊ አካሔድ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ሁኔታውን በሚመለከት የሕግ ባለሙያዎችንና በኪነ ጥበብ ውስጥ ያሉ ሰዎችን አማክረዋል?

አቶ አድነው፡- ለጉዳዩ በጊዜ ምላሽ እንድሰጥ መሔድ ባለብኝ መንገድ መሔድ እንዳለብኝ ብዙዎች ነግረውኛል፡፡ አንተ ምንም የማትል ከሆነ እኛ በሕግ ነገሩን እንያዘው ያሉኝም አሉ፡፡ እኔ ግን ቆም ብሎ ነገሮችን ማየት በመምረጤ ነው እስካሁንም የቆየሁት፡፡ ስለዚህ በሕጉ አግባብ ረገድ ያማከሩኝና ሊረዱኝም ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹልኝ አሉ፡፡ (ኮፒ ራይት) ላይ ደግሞ ራሴ በቂ ዕውቀት አለኝ፡፡ እየተንቀሳቀስኩ ያለሁትም በዚያ መሠረት ነው፡፡ የግድ ቃል በቃል የእኔን ስክሪፕት መውሰድ የለባቸውም፡፡ ሐሳቤን ከያዙት ያ በቂ ነገር ነው፡፡ የሰጠኋቸው የቁጥር ሁለት አምስት ክፍል ደግሞ ለዚያ ይሆናል፡፡ እሱን በሚመለከት ደግሞ ድራማው ሳይጠናቀቅ በፊት በተደጋጋሚ የቁጥር ሁለቱ የተወሰነ ክፍል መጻፍ መጀመሩን ሲያስተዋውቁ ነበር፡፡ ራሳቸው ሽልማቱን በሚመለከት አዘጋጅተው በነበረው መጽሔት ላይም ስለ ቁጥር ሁለቱ አምስት ክፍል መጻፍ ብዙ ብለዋል፡፡ አሁን አሁን ስለዚህ ነገር መናገር ቢያቆሙም ሊክዱት የሚችሉት እውነት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ገመና የሚለው ርዕስ እርስዎ የሰጡት አይደለም የሚባለውስ?

አቶ አድነው፡- ማንም ያውጣው ማንም ገመና የዚያ ድራማ መጠርያ ነው፡፡ ስለዚህ ማን ያውጣው ማን አይደለም ጥያቄው፤ ይልቁንም ለአንድ ሥራ የተሰጠ ስም መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ስምንት ርዕሶች ሰጥቻቸው ገመናን መርጠዋል፡፡ እኔ መጀመርያ ሰርጎ ገብ የሚል ርዕስ ሰጥቼ እንደ አማራጭ ካቀረብኳቸው ሌሎች ገመና ተመረጠ፡፡ የተመረጠውም ሁላችንም በተሰበሰብንበት ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን ማን ይስጠው ማን ሳይሆን ገመና ርዕስ ሆኖ ለአንድ ሥራ መዋሉ ነው፡፡ ለልጄ ፓንዶራ የሚል ስም አንድ ሰው ቢያወጣላት ስሙ ደስ ካለኝ እቀበለዋለሁ፡፡ ያ ግን የእኔ ልጅ መሆኗን የሚለውጥ ነገር አይደለም፡፡ ስሙን ያወጣው ሰውም ልጄ ነች በማለት ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም፡፡ የርዕሱ ጉዳይ በቀላሉ ይህን ይመስላል፡፡ ማንም ያውጣው  ርዕሱ ከሥራው ጋር ተቆራኝቷል፡፡ ያ ነው መታየት ያለበት፡፡ እነሱ እያሉ ያሉት ገመና ርዕስ ነው ነው፡፡ እኔ ደግሞ ርዕስ ብቻም ሳይሆን ከዚያ ዘሎ ትሬድ ኔም ሆኗል ነው የምለው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ነገሩን ለመፍታት የሞከሩበት መንገድ አለ?

አቶ አድነው፡- ባለኝ ግንኙነትና መቀራረብ በተደጋጋሚ እየተሠራ ያለው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ለአቶ እቁባይ ገልጫለሁ፡፡ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የአምስቱን ክፍል ጽሑፍ ኮፒ የሰጠሁት ነገሩን መለስ ብለው እንዲያጤኑትና ትክክል አለመሆናቸውን እንዲረዱ ያደርጋል ብዬ በማሰብ ነው፡፡ በክፍያ አልተስማማንም፤ በቃ አለቀ አብረን አንሠራም ነው፡፡ ግን የእኔን ሐሳብ ይጠቀማሉ ብዬ በጭራሽ አላሰብኩም ነበር፡፡ ገመና ቁጥር ሁለት ላይ እየሠሩ ካሉ ጭምጭምታ የሰማሁት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ በዚያ ላይ ስለ ኮፒ ራይት የሚያቀነቅን አካል ይህን ይሠራል ብዬ አላስብም፡፡ አሁን ከእነሱ ጋር ጨርሻለሁ፡፡ በገመና ድራማ ምክንያት ወደ ሕግ እንደምሄድ አሳውቄያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን የሠሯቸው ሥራዎችስ?

አቶ አድነው፡- ከጊዜ ወደ ጊዜ የኪነ ጥበብ ስበት ቀስ በቀስ እያየለ መጣ፡፡ እውነተኛ ታሪኮችን፣ የመድረክ ቴአትርና ፊልሞችን መሥራት ጀመርኩ፡፡ ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ያሳተማቸው በብዙ ጋዜጦች ላይም የወጡ እውነተኛ ታሪኮችን ጽፌያለሁ፡፡ በአገሪቱ የተደረገ የሥነ ጽሑፍ ውድድር ነበር፤ የእኔ ሁለት ሥራዎችም አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የአና ማስታወሻ መጽሐፍን አሳትሜአለሁ፡፡ የመድረክ ሥራውን ተርጉሜም ራስ ቴአትርና ማዘጋጃ ቤት ታይቷል፡፡ ከዚያም ጣውንቶቹን ለአገር ፍቅር፣ ክሊዮፓትራ ለብሔራዊ ቴአትር አሁን ደግሞ ቀስተ ደመናን ለአዲስ አበባ ባሕልና ቴአትር አበርክቻለሁ፡፡ ወንድሜ ኃይሉ ፀጋዬ እያዘጋጀው ያለ ሌላ የእኔ ቴአትር ደግሞ አለ፡፡ አንድ ዕድል የሚባል ፊልም ደግሞ ራሴ ጽፌ ዳይሬክት አድርጌያለሁ፡፡ አሁንም እየተሠራ ያለና የተዘጋጀ ፊልም አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ኪነ ጥበብ ውስጥ ያሉት በተሰጥኦ ብቻ ነው?

አቶ አድነው፡- ካልተነበበ እንዴት ይሆናል? የማገኘውን ገንዘብ መጸሐፍት ላይ ስለማውል ትልቅ ላይብረሪ ነው ያለኝ፡፡ ትምህርቴ ከኪነ ጥበብ ጋር ግንኙነት ባይኖረውም ብዙ አንብቤያለሁ፣ አሁንም አነባለሁ፡፡ በኪነ ጥበብ ውስጥ ራሱን እንዳስተማረ ሰው ነው ራሴን የምቆጥረው፡፡ ትምህርት ቤት ላገኝ የምችለውን በማንበብ (ራሴን በማስተማር) አግኝቻለሁ እያገኘሁም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሚዲያ ላይ መውጣት የማይፈልጉት ለምንድን ነው?

አቶ አድነው፡- አዎ ሚዲያ ላይ መውጣት አልፈልግም፡፡ የገመና ድራማ ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ እኔን ወክላ ሽልማት የተቀበለችው ባለቤቴ ነበረች፡፡ እኔ ግን እዚያው ነበርኩኝ፡፡ ካሜራ ማኖች አያገኙኝም ብዬ ካሰብኩት ቦታ ተቀምጬ ነበር፡፡ በእርግጥ አዲሶች ካልሆኑ በስተቀር ነባሮቹ ስለሚያውቁ የእኔን ምስል ለመቅረጽ አይሞክሩም፡፡ ይኼን የማደርገው በቀላሉ በነፃነት መኖር ስለምፈልግ ነው፡፡ የሚታወቁ በኪነጥበብ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ብንመለከት ራሳቸው እንደሚፈልጉት በነፃነት መኖር አይችሉም፡፡ አካሔድ፣ አቀማመጥ በአጠቃላይ እንቅስቃሴዎቻቸው እንደሚፈለገውና እንደሚጠበቀው መሆን አለበት፡፡ ይኼ ለሚያስደስታቸው ሚዲያ ላይ መውጣትና መታወቅ መልካም ነው፡፡ እኔ ግን አልፈልግም፡፡ አሁን ደግሞ አዶኒስ ማነው ከሚለው ጉጉት ጋር አንድ ቀን ሚዲያ ላይ ብወጣ ነገሮች እኔ እንደማልመርጣቸው ይሆናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሚዲያ ላይ ባለመውጣትዎ አጣሁት የሚሉት ነገር አለ?

አቶ አድነው፡- ያጣሁትን ነገር ይኼ ነው ብዬ አላውቀውም፡፡ ግን ብዙ ነገር ላጣ እንደምችል ጥያቄ የለውም፡፡ ብወጣ ብዙ ነገር ላደርግና ላገኝም እንደምችል አውቃለሁ፡፡ በታወቅኩ ቁጥር በሮች ክፍት ይሆናሉ፡፡ እኔን ማንም አያውቀኝም፡፡ ያለመታወቅ ቁጭት ግን የለብኝም፡፡ በዚሁ ነው የምቀጥለው፡፡ ይኼ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ አለመታወቅና በነፃነት መኖርን፤ መታወቅ የሚያስገኘውን ነገር ማጣትን ነው የምመርጠው፡፡

ሪፖርተር፡- በሞባይል ስልክም አይጠቀሙም?

አቶ አድነው፡- ከመጀመሪያውም ስልክ ይዤ አላውቅም፡፡ ገና ወደ አገራችን ሲመጣ ሐሳቡን ነው የጠላሁት፡፡ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ እጽፍ ነበር፡፡ ማተሚያ ቤት ከሚገቡበት ቀን ቀደም ብዬ ጽሑፌን እሰጣቸዋለሁ፡፡ የጋዜጣው ባለቤት አቶ አሰፋ ጎሳዬ በሚፈልገው ጊዜ ሊያገኘኝ አለመቻሉ ደስ ባይለውም ምንም ሊያደርግ አልቻለም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን ሁለት የሞባይል ቀፎዎችን ይዞ ይኼ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ደግሞ ለእኔ ነው አለኝ፡፡ የትም ብትሆን ላገኝህ እችላለሁ አንተም ልታገኘኝ ትችላለህ አለኝ፡፡ እዚህ ጋ አበቃ፤ ይኼ ለእኔ አይሆንም አልኩት፡፡ እግረ ሙቅ የተደረገልኝ ነው የመሰለኝ፡፡ እንዴት ሳልፈልግ እገኛለሁ? የትም ሆኜ ሰው በፈለገው ሰዓት ያገኘኛል? ስለዚህ እስካሁንም በዚህ አቋሜ እንደፀናሁ ነኝ፡፡ ካለ ስልክ መሥራት እንደሚቻል አይቻለሁ፡፡ በዚያ ሲስተም ውስጥ ለገባ ሰው ግን ያስቸግራል፡፡ አንድም ቀን ስልክ መያዝ አልሞከርኩም፤ መደወሉንም በቅርቡ ነው የሞከርኩት፡፡ የሚፈልገኝ ሰው በቤት ስልክ፣ በባለቤቴና በልጄም በኩል ያገኘኛል፡፡ የምገኝበት ሰዓት ይታወቃል፡፡ በዚህ ሰዓት ከተባልኩ እገኛለሁ፤ እኔም እደውላለሁ፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close