ኢትዮ ቴሌኮም በሠራተኛው ግፊት የስንብት ክፍያን ሊያስቀድም ነው

በአዲሱ ኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ለማይመደቡ ሠራተኞች ይቋቋማሉ የተባሉ ኩባንያዎች በሠራተኞች ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑና በቅድሚያ የስንብት ክፍያ እንዲከፈላቸው ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የእስካሁኑ ምደባ ክፍተት እንዳለው በመታመኑ አዲስ ፕሮፖዛል ሊቀርብ ነው፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምደባው ለማይመለከታቸው ሠራተኞች እንዲቋቋም ይፈለግ የነበረው የአክሲዮን ማኅበር በአብዛኛዎቹ ሠራተኞች ሊደገፍ ባለመቻሉ፣ መንግሥት ለሠራተኞች አስፈላጊውን ክፍያ በቅድሚያ ለመክፈል እየተዘጋጀ ነው፡፡

ሆኖም ቀደም ብሎ በታሰበው መሠረት ይቋቋማሉ በተባሉት የአክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ እንደራጃለን የሚሉ ሠራተኞች ካሉ፣ ክፍያው ከተከፈላቸው በኋላ እዚያው አክሲዮን እንዲገዙ የሚያስችል አሠራር ለመከተል መወሰኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥት ወደዚህ ሐሳብ እንዲሸጋገር ያደረገው በርካታ ሠራተኞች በአክሲዮን ኩባንያው ላይ እምነት ማጣታቸውን በይፋ በመናገራቸውና በሕግ የሚፈቀድላቸውን የአገልግሎት ክፍያ ይሰጠን የሚለው አቋም በመበራከቱ ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አቶ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እንደገለጹት፣ ሠራተኞች በራሳቸው ገንዘብ በግድ አክሲዮን ካልገባችሁ አይባሉም፡፡ የአብዛኞቹ ሠራተኞች ፍላጎትም ገንዘቡ ይከፈለን የሚል ስለሆነ በዚሁ መሠረት ቀደም ብሎ የነበረውን ሐሳብ ለመለወጥ ተችሏል ብለዋል፡፡ በመንግሥት ደረጃ ታስቦ የነበረው ግን አክሲዮን ኩባንያው ተቋቁሞ አትራፊ እስኪሆን ድረስ ደመወዝ እየተከፈለ ማቆየት እንደነበር መገለጹ ይታወሳል፡፡

መንግሥት ለሚሰናበቱ ሠራተኞች በሠራተኛና አሠሪ ሕግ መሠረት አጠቃላይ የምደባ ሥራውና ከምደባ ሥራው ጋር ተያይዘው ለቀረቡ ቅሬታዎች የሚሰጠው መልስ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ክፍያው ይፈጸማል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ደብረ ጽዮን አስረድተዋል፡፡

ለተሰናባች ሠራተኞች የሚሰጠው ክፍያም እንደ አገልግሎት ዘመናቸው የሚሰላ ነው፡፡ አጠቃላይ ክፍያው ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ከአዲሱ የሠራተኞች ምደባ ጋር ተያይዞ እየታየ ያለውን ክፍተት ለመሙላትና ተጨማሪ ሠራተኞችን ለመመደብ የሚያስችል አዲስ ፕሮፖዛል ሊቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ የሠራተኞች አመዳደብ አካሄድ ተመዝኖ ጉድለት የታየበትን ቦታ ለመድፈን ምደባውን የሚያካሄደው አካል የማሻሻያ ፕሮፖዛል እንዲያቀርብ ታዟል፡፡ ይህም ፕሮፖዛል ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲመደቡ ያስችላል ተብሎ የሚጠበቅ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

አዲሱን ፕሮፖዛልም ሆነ አጠቃላይ የምደባውን ሒደት ለማጠናቀቅ አሁን ባለው ሁኔታ ማወቅ ባይቻልም፣ አጠቃላይ ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ሲቀየር በምደባው ይካታተታሉ ተበለው የሚጠበቁት ሠራተኞች፣ ከአራት ሺሕ በታች እንደሚሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ አብዛኛው ወይም ስምንት ሺሕ የሚሆኑት ሠራተኞች እንደሚቀነሱ ይጠበቃል ተብሎ ነበር፡፡

አሁን እየተደመጡ ያሉት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ምደባው ጉድለት እንደነበረበት ግንዛቤ መያዙን፣ ተጨማሪ በምደባው ወቅት የተፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን ተጨማሪ ምደባ ሊደረግ መሆኑን ነው፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close