ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የንግድ ባንክ ኤቲኤም ማሽኖች ግዢ ጥያቄ አስነሳ

በጋዜጣው ሪፖርተር

ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶባቸዋል የተባሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 50 የአውቶማቲክ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) ግዢ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን አንድ የባንኩ ባለሙያ ገለጹ፡፡ እነዚህ የኤቲኤም ማሽኖች ከሚሠሩበት የማይሠሩበት ጊዜ ስለሚበልጥ ደንበኞች የሚጠይቁትን ገንዘብ ቆርጠው በማስቀረት ይሰጣሉ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ማሽኖቹ ባንኩ ከተዘጋ በኋላ በምሽት እንደሚሠሩ እኚሁ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡

ባንኩ ኤምቱኤም ከተባለ የሞሮኮ ኩባንያ 50 ዊንከር (Wincor) የተባሉ የኤቲኤም ማሽኖችና 250 POS ለማስመጣትና ከባንኩ ኮር ባንኪንግ አገልግሎት ጋር ለማገናኘት የተስማማ ቢሆንም ኩባንያው ጨረታውን ካሸነፈ በኋላ ዊንከር የተባሉ ማሽኖችን አላስመጣም፤ የማስመጣው የኤንሲአር ማሽኖችን ነው በማለቱ የኤንሲአር ማሽኖች እንዲመጡ ተደርጓል፡፡

ኩባንያው ባንኩ የጠየቀውን ዘመናዊ የዊንከር ማሽኖችን ትቶ የሥሪታቸው ጊዜ ያለፈባቸውን የኤንሲአር ማሽኖች መምጣታቸው አጠያያቂ ነው በማለት ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ የኤንሲአር ማሽኖች ዋጋቸው ከዊንከር ማሽኖች ያነሰ ቢሆንም፣ ባንኩ ለዊንከር ባወጣው ዋጋ ኋላቀሮቹን የኤንሲአር ማሽኖች ሊገዛ መቻሉን እኚሁ ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በጨረታው ሕግ መሠረት ማሽኖቹን ያስመጣው ኩባንያ ዕቃዎችን ያስመጣበትን አገር (Origin of Import) እንዲጠቅስ የሚያስገድድ ቢሆንም፣ በኢንቮይሱ ላይ ዕቃው የመጣበት አገር የአውሮፓ ኀብረት የሚልና በአገር ስም ፋንታ የአኀጉር ስም እንደተጠቀሰ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

እንደባለሙያው ገለጻ፣ የኤቲኤም ማሽኖቹ አዲስ አበባ ሳይደርሱ በሥራ ላይ የነበሩና ከበርካታ አገሮች ተሰባስበው የገቡ ሊሆን ይችላል፡፡ ማሽኖቹ የተገዙት በዋናነት የቪዛ ካርድ አገልግሎት ለመስጠት ቢሆንም፣ ዘግይቶ የተጀመረው የቪዛ ካርድ አገልግሎት የሚንቀሳቀሰው በእጅ ነው፡፡ ለእነዚህ ማሽኖች የ77 ሚሊዮን ብር ግዥ ተፈጸመ መባሉ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

እንደባለሙያው፣ ዋነኛው ችግር “MAGIX” የተባለው የኤቲኤም ሶፍትዌር አሁን ባንኩ ከሚጠቀምበት “MYSIS” ከተባለው የኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር ጋር መገናኘት ስለማይችል ነው፡፡ “MAGIX” የተባለው ሶፍትዌር ባንኩ አሁን ከሚጠቀምበትም ሆነ ወደፊት ሊጠቀምበት ካቀደው ኮር ባንኪንግ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ኃላፊዎቹ ያረጋገጡበት ሰነድ ያመላክታል፡፡

ሶፍትዌሮቹ የሚጣጣሙና የሚናበቡ ናቸው ቢባልምና ባንኩ እየተጠቀመበት ያለው “MYSIS” የተባለው ሶፍትዌር ማሽኖቹ ከተገዙ በኋላ ችግር አለው ቢባልም፣ ቀደም ሲል ለባንኩ ሶፍትዌር ያቀረበው የ“MYSIS” ኩባንያ ባለሙያውን በመላክ ችግሩ የት ጋ እንደተፈጠረ ጠይቆ ነበር፡፡ ችግሩን የሚያስረዳ ባለመኖሩ የተላኩት ባለሙያ ያለሥራ በውጭ ምንዛሪ እየተከፈላቸው ከቆዩ በኋላ ወደመጡበት መመለሳቸውን የባንኩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ባለሙያው በበኩላቸው፣ ቀድሞ ይሠራበት የነበረውን ኮር ባንኪንግ በቅርቡ በአዲሱ ለመተካት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ የኤቲኤም ማሽኖቹ ግዢ ከአዲሱ ኮር ባንኪንግ በፊት ቀድሞ መደረጉ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “MAGIX” ሶፍትዌር ጋር ለማገናኘት በተጨማሪ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ወጪ እንደሚጠይቅም አስረድተዋል፡፡

“MAGIX” የተባለው የኤቲኤም ሶፍትዌር ባንኩ ከገዛው ወይም ወደፊት ከሚገዛው ኮር ባንኪንግ ለማገናኘት ይችላል ተብሎ ወጪ ከተደረገ በኋላ፣ አሁን እንደገና አዲስ ከሚገዛው ኮር ባንኪንግ ጋር ለማገናኘት ተጨማሪ ወጪ መጠየቁ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የሚያሳይ ነው ሲሉ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

ይህንን ጥያቄ እያስነሱ ያሉትን የኤቲኤም ማሽኖች በማስመልከት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምላሽ እንዲሰጥበት ከሁለት ሳምንት በፊት ጥያቄዎች ቢላኩለትም ምላሹን ማግኘት ግን አልተቻለም፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close