የአዋሽ ባንክ የቀድሞ አመራሮች በ6.2 ሚሊዮን ዶላር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው

የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበርን ከ13 ዓመታት በላይ በፕሬዚዳንትነት የመሩትን አቶ ለይኩን ብርሃኑን ጨምሮ አሥር የሥራ ኃላፊዎች፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ 6,196,760.88 የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ በመስጠታቸው ባሳለፍነው ሳምንት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው፡፡ ክሱ የተመሠረተባቸው አቶ ለይኩን ብርሃኑ ፕሬዚዳንት የነበሩ፣ አቶ ምትኩ አብሹ የዓለም አቀፍ ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአቶ ለይኩን አማካሪ የነበሩ፣ አቶ ታደሰ አሻግሬ የዓለም አቀፍ ባንኪንግ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ፣ ወይዘሮ ወንጌላዊት ብርሃነ ሥላሴ በዓለም አቀፍ ባንኪንግ መምርያ ኢምፖርት ዋና ክፍል ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ጌታሁን አለማር የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ እንዳለ ቱኒ የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ የውጭ ምንዛሪ ዲፓርትመንት ኃላፊ፣ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ አባት የሀብተ ጊዮርጊስ ቅርንጫፍ የውጭ ምንዛሪ ዲፓርትመንት ኃላፊ፣ አቶ ደረጀ አበበ የለገሀር ቅርንጫፍ የውጭ ምንዛሪ ዲፓርትመንት ኃላፊ፣ አቶ ቸርነት ዋቅጋሪ የመርካቶ ቅርንጫፍ የውጭ ምንዛሪ ዲፓርትመንት ኃላፊና ወይዘሮ ፍቅርተ ሽመልስ በኢንተርናሽናል ባንኪንግ መምሪያ ኦፊሰር ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ በተለያየ የአመራር ኃላፊነት ላይ እ.ኤ.አ ከኦክቶበር 2009 እስከ ዲሴምበር 2009 ድረስ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ በአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንኪንግ ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ በሚሰጥባቸው በለገሀር፣ በአዲስ ከተማ፣ በሀብተ ጊዮርጊስና በመርካቶ ቅርንጫፎች ይሠሩ እንደነበር የክስ ቻርጁ ያመለክታል፡፡ አቶ ለይኩን፣ አቶ ምትኩና የተወሰኑት የአዋሽ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሆነው ሲሠሩ እንደነበርም ይገልጻል፡፡

በመሆኑም ከውጭ ምንዛሪ አጠያየቅ፣ አፈቃቀድ፣ አጠቃቀምና ከግዢ ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሕገወጥ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ክሱ ያትታል፡፡

ተከሳሾቹ አሥር የተለያዩ ጥፋቶችን መፈጸማቸውን የዓቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ያመለክታል፡፡ በአጠቃላይ ከባንኩ የውጭ ምንዛሪ መመርያ ውጭ በሆነ መንገድ በተጭበረበሩ ሰነዶች በድምሩ 6,196.760.88 የአሜሪካን ዶላር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲፈቀድ ማድረጋቸውን የክስ ቻርጁ ይገልጻል፡፡

በተጭበረበረ ሰነድ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የውጭ ምንዛሪ በመሰጠቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰው ሠራሽ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲያጋጥመው በማድረጋቸው፣ አዋጅና መመርያ እንዲጣስ በማድረጋቸው፣ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን፣ በሌላ ሰው ጥቅምና የሥራ አመራር ላይ የተፈጸመ ጉዳት በማድረስ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ የክስ ቻርጅ ይዘረዝራል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ግድፈት ጋር በተያያዘ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮችን ቦርድ አቶ ምትኩ አብሹን ከሥራ ካገደና ካሰናበተ በኋላ፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ለይኩንን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባንኩ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ላይ ያልተገባ ግድፈት ሲፈጸም ዝም በማለታቸው ከሥራ እንዲታገዱና ምርመራ እንዲደረግላቸው ማዘዙ ይታወሳል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close