ኢትዮጵያና አፍሪካ፤ ትንበያ 2050

ከሪፖርተር ፖለቲካ አምድ የተወሰደ በቅኝ ግዛት ስር ያልወደቀችው ኢትዮጵያ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ከቅኝ ግዛት እንዲወጡ ያደረገችው አስተዋጽኦ ሁሌም በምሳሌነት የሚነሳ ነው፡፡

በ1960ዎቹ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት የትኛውንም ወገን አቋም ሳትይዝ የአስታራቂነት ሚና በመጫወት ህብረቱ እንዳይበተንና አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጋለች፡፡ በዘመናዊቱ ኢትዮጵያ የነገሱ ነገስታት ሕዝባቸውን ቢጨቁኑም ለአፍሪካ ሕዝቦች ግን የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በቅርቡ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ የአፍሪካ አጀንዳ ትልቅ ስፍራ እንዲይዝና የዓለምን ሕዝቦች እንዲያነጋግር በማድረግ በኩልም ጠ/ሚኒስትር መለስ የተጫወቱት ሚና የሚጠቀስ ነው፡፡ አፍሪካን በዓለም ለመወከልና ስለአኅጉሪቱ ለመሟገት ከአህጉሪቱ ኃያላን አገራት ኢትዮጵያ ሦስተኛዋ እንደምትሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ አንዳንድ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

የአፍሪካ የፀጥታ ጥናት ተቋም (Institute of Security Studies -ISS) የተባለው ማዕከል ያሳተመውና ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 14 ቀን 2003 ዓ.ም. “African Futures 2050” በሚል በተቋሙ ዳይሬክተር ዶ/ር ጃኪ ሲሊያርስና በሌሎች ሁለት ተባባሪዎች ተዘጋጅቶ ለምርቃት የበቃው መጽሐፍ አፍሪካ በመጪዎቹ 30 እና 40 ዓመታት ምን እንደምትመስል፣ የትኞቹ አገራት የበላይነት ሊኖራቸው እንደሚችል፣ አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሊኖራት የሚችለው ተጽዕኖ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚና ፖለቲካ የትኞቹ የዓለም አገራት ከፍተኛ ስፍራ እንደሚኖራቸው የተተነበየበት ነው፡፡

አፍሪካና ትንበያዎቿ
ጥንታዊ ጽሑፉን በበላይነት ያካሄዱት የአይ.ኤስ.ኤስ ዳይሬክተር ዶ/ር ጃኪ የተቋሙ ዋና ጽሕፈት ቤት በሚገኝበት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ሲሆኑ፣ የአፍሪካ አመባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና አንዳንድ ባለሥልጣናት በብዛት በተገኙበት በዚሁ በመጽሐፋቸው የምርቃት ዕለት ባደረጉት ንግግር “ዓለም እየተቀየረች ናት” በማለት በአሁኑ ወቅት በተለይ በሰሜን አፍሪካ (ቱኒዚያ) የተጀመረው ዓመጽ እንዴት በፍጥነት እየተዛመተ እንደሚገኝ ያብራሩ ሲሆን፣ በመጽሐፋቸው ግኝቶችና በአፍሪካ ውስጥ ያጋጥማሉ ባሏቸው ተግደሮቶች ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የቀድሞው የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ቤን ዓሊና የቀድሞው የግብጽ ፕሬኪዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን መውረድ፣ በግብጽ እየተደረገ ያለው የሕገመንግስት ማሻሻያና ለውጦች፣ በሊቢያ ያለው ቀውስ፣ ዓመፁ በፍጥነት ወደ የመን፣ ሶርያ፣ አልጄርያና ሌሎች ዓረብ አገራት መስፋፋት “ማን አይቶታል?” ሲሉ የጠየቁት ዶ/ር ጃኪ በርካታ ነገሮች ቀድሞ ከታሰበው ወጪ እየሆኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ የአፍሪካ የወደፊቱ ለውጥም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን በማመላከት፡፡

‹‹አፍሪካ እየተለወጠች ነው” በሚል መነሻቸውም፣ በጥናታቸው የተጠቀሙባቸው ማናቸውም መስፈርቶች የአፍሪካ ዓመታዊ ገቢ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስችልም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹አፍሪካ ባላት ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት መጠን ምክንያት ዕድገቱ እየታየን ላይሆናል ይችላል›› ያሉት ጸሐፊው፣ በአሁኑ ሰዓት 900 ዶላር የሆነው የአንድ አፍሪካዊ አማካይ ዓመታዊ ገቢ በመጪዎቹ 20 ዓመታት (2030) ወደ 1760 ዶላር ከፍ በማለት በእጥፍ እንደሚያድግ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም፣ በአሁኑ ወቅት ያለው ወደ አንድ ቢሊዮን ገደማ የሆነው የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር በ50 በመቶ ጨምሮ 1.55 ቢሊዮን በሚደርስበት ወቅት የአሕጉሪቱ ኢኮኖሚ በዕጥፍ እንደሚያድግ አመላክተዋል፡፡

እነዚህን ለውጦች ለመተንበይ መሰረታዊ ያሉዋቸውን ነጠቦችንም ዶ/ር ጃኪ አስቀምጠዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የከተማነት ከፍተኛ መስፋፋት ይገኙባቸዋል፡፡ በዓለም ለታየው ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው ያሏቸው እነዚህ ሁኔታዎች ‹‹በአፍሪካም ወሳኝነታቸው ይቀጥላል›› ይላሉ፡፡

‹‹አፍሪካ በ2032 ከቻይና የበለጠ፣ በ2036 ደግሞ ከህንድ የበለጠ አምራች ኃይል ይኖራታል›› የሚል ትንበያቸውን አስቀምጠዋል፡፡ የኢኮኖሚ ፓሊሲና ማሻሻያ በአፍሪካ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ዶ/ር ጃኪ፣ አፍሪካ እንደህንድ ሁሉ ‹‹የእርሻ መሬት አረንጓዴ አብዮት ተጠቅማ ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር ትችላለች›› የሚለውንም ትንበያ አስፍረዋል፡፡ የቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ማብቃት ተከትሎ አፍሪካ ውስጥ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን የሚመጡ መሪዎች ቁጥር እጅግ መቀነስ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና በአፍሪካ አገሮች መካከል ይካሄዱ የነበሩ ግጭቶችም መቀነስ፤ የኢኮኖሚ አብዮት ለማካሄድ የተረጋጋ የፓለቲካ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እንድምታ አስቀምጠዋል፡፡ አጥኚው፤ የአፍሪካ ዕድገትን ለማፋጠን ይረዳል በማለት ትልቅ ስፍራ የሰጡት ሌላው ምክንያት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቭስትመንትና የዳያስፖራ ገቢ (ሐዋላ) ነው፡፡ ይህ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስተመንት እና የዳያስፖራ ገቢ ለህንድ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ያደረገ ትልቅ ምሳሌ ተደርጐም ተጠቅሷል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ ፍላጎትን በተመለከተም፣ ቻይናና ሕንድ በዋናነት BRICS (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድና ቻይና) ደግሞ በአጠቃላይ የአፍሪካን ዕድገት የሚያፋጥኑ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ያሉ አገሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም ‹‹የአፍሪካ እድገት ከሌሎች ይልቅ የሕንድ የዕድገት መንገድ የተከተለ ይሆናል›› የሚል ግምታቸው› አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹እ.ኤ.አ. በ2050 በአፍሪካ ውስጥ አንድ የበላይነት ያለው አገር አይፈጠርም›› ያሉት አጥኚው፣ ትልቅ ሀብት ያካብታሉ ያሏቸውና A4 የሚል ስያሜ የሰጧቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያና ግብጽ የአኅጉሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ አገሮች እንደሚሆኑ ተንብየዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የዓለም ኢኮኖሚ በእጥፍ በሚያድግበት በ2030ም፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ የአየር ለውጥን እንቅፋት በመቋቋም ዕድገቱን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ጃኪ አፍሪካ ይገጥማታል በማለት ካስቀመጡት ተግዳሮት መካከል፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ሕዝብ ቁጥር ማስተናገድ አለመቻልና የከተማ አስተዳደር ጉድለት ለፓለቲካ አለመረጋጋት እንደመነሻ ይሆናል የሚል ነው፡፡ዶ/ር ጃኪ ለሪፖርተር እንደገለፁት፣ የከተማ መስፋፋት፣ የወጣት ቁጥር መጨመርና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው መፈናቀል ለአፍሪካ የወደፊት መሪዎች ዕድልም ፈተናም ይሆናል፡፡

ዶ/ር ጃኪ በአሁኑ ወቅት በሰሜን አፍሪካ ስላለው ዓመጽ አስመልክተው እንደገለፁት፣ ሁልግዜም ቢሆን የኢኮኖሚ ዕድገት ይቅደም ተብሎ ዲሞክራሲን ወደ ኋላ መጐተት መጨረሻውን ያበላሸዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ለቻይናም ሆነ ለሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት ማስጠንቀቂያ መሆኑን ያመላከቱት ዶ/ር ጃኪ፣  “ሰዎች ኢኮኖሚያቸው እየበለፀገ በመጣ ቁጥር የበለጠ የፓለቲካ ነፃነት ይፈልጋሉ” ብለዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ሚድያና ቴክኖሎጂ መስፋፋት ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች የዓለም ሕዝቦች የሚያነጻጽሩበት እድል መፈጠሩን የገለጹት አጥኚው፣  “ኢኮኖሚና ዴሞክራሲን አንዱን ከሌላው ማስቀድም አይቻልም” በማለት ሁለቱ መሠረታዊ ነገሮች ተነጣጥለው እንደማይሄዱ አስረድተዋል፡፡

አፍሪካ፤ ህንድ፣ ቻይናና አሜሪካ፡-
የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርቱ፣ በቻይና ከ30 ዓመት በፊት በሕንድ ደግሞ ከ20 ዓመት በፊት የሆነው አሁን በአፍሪካ እየተከሰተ መሆኑን ይገልጻል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ አፍሪካ ሕብረትና ኔፓድ የመሳሰሉት ተቋማትም ከዚህ ከዓለም ባንክ ሐሳብ ጋር ይስማማሉ፡፡ ለዚህም እንደመንደርደሪያ የቀረበውም በአፍሪካ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትና የፓለቲካ ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡ አፍሪካ በዓለም ያላት ጠቀሜታ እየጨመረ መምጣቱም እንደ ትልቅ ፋይዳ ተቆጥሯል፡፡ በዓለም ያለውን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት የተቆጣጠሩት ቻይናና አሜሪካ እያንዳንዳቸው 30 እና 22 በመቶ ነዳጅ የሚወስዱት ከአፍሪካ ነው፡፡ አፍሪካ በዓለም ዓቀፍ ጉዳዮችም ወሳኝ ስፍራ እያያዘች መጥታለች፡፡ መጽሐፉ እንደሚለው፣ ማንኛውንም የዓለም ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ ለማስተላለፍ የ192 አገራት ብዙሃን ቁጥር ድጋፍ በሚያስፈልግበት በአሁኑ ወቅት 53 የአፍሪካ አገራት አባላት ተቀባይነትና ድጋፍ ማግኘት እጅግ  ወሳኝ እየሆነ መጥቶዋል፡፡

መጽሐፉ ‹‹ዓለም በ2050 የተለየች ትሆናለች፤›› ይላል፡፡ ቴክኖሎጂና ካርቦን የዓለምን ማህበሪዊ ሁኔታና ተፈጥሮ እንዴት እንደሚቀይሩት መተንበይ አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገረው የዶ/ር ጃኪ ማጽሐፍ፣ ዓለም አቀፋ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነቶች ግን በሦስት አገራት የበላይነት የሚከናወን ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፤ ቻይና፣ ሕንድና አሜሪካ፡፡ ‹‹አፍሪካ በዓለም እስከአሁን ከነበራት ተጽዕኖ በላይ ማሳደር ብትችልም፣ አገሮቹ በሙሉ ተሰብስብው ግን የእነዚህን አገራት (ቻይና፣ ህንድና አሜሪካ) በተናጠል የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ ማሳደር አይችሉም›› የሚል ድምዳሜም ዶ/ር ጃኪ አስፍረዋል፡፡ እንደ አጥኚው ትንበያ፣ ቻይና ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታመጣ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2014 አሜሪካን በመቅደም የዓለማችን የትለቁ ኢኮኖሚ ባለቤት ትሆናለች፡፡ ሕንድም በ2050 የአሜሪካን የኢኮኖሚ መጠን 85 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close