‹‹ገመና ድራማ ላይ ኢንቨስት ያደረግነው እኛ በመሆናችን አብላጫው የሞራልና የኢኮኖሚ መብቱ የእኛ ነው›› አቶ አብነት ጌታቸው፣ የዶን ፊልሞች ፕሮዳክሽን ማኔጀር

ሪፖርተር ባለፈው ሁለት ሳምን የገመና ድራማን ክፍል አንድ ልዩ የጥያቄና መልስ ዝግጅት አቅርበንላችኋል አሁንም ክፍል ሁለትን ለማንበብ ይሞከሩ እንደ እኛ እምነት ግን የፕሮዳክሽን ባለቤቶች ተብዬዎች የሰው ንብረትን ዘረፋ በቁም እንዝረፍ ባዮችከመሆናቸውም ባሻገር የአንድን ባለንብረት ገንዘብ አለኝ እና እንደልቤ አሽከረክራለሁ በማለት የአእምሮ ፈጠራ ስራን በእራሳቸው ስም ዘርፎ ለማስቀረት የሚጥሩትን በእኛ በኩል አልወደድነውም ገንዘብ ማውጣት እና የሙያ ፈጠራን መፍጠር ፈጽሞ የተለያዩ ናቸው እና አቶ አብነትን እኛ ከመኮነን ወደ፡ኋላ አንልም ስለዚህ አሁንም ለብ ያላችሁ ልብ በሉ ለእርሳቸውም ልቦና ይስጣቸው  ስለዚህ እኛ ጥፋተኛ መሆናቸውን ስለተገነዘብን ከእኛ ይልቅ አንባብያን ያላችሁን አስተያየት በአስተያየት መስጫ ሳጥናችን ውስጥ ብታስቀምጡልን መልካም ነው ።

አቶ አብነት ጌታቸው የዶን ፊልሞች ፕሮዳክሽን ማኔጀር ሲሆኑ፣ ዳ’አማት ፕሮዳክሽንን ከተቀላቀሉ አንድ ወር ሆኗቸዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቴአትር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቻፕተር መኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮ በፕሮጀክት አስተባባሪነት፣ በተዋናይነት፣ በጸሐፊነት ሠርተዋል፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ጋዜጠኛም ነበሩ፡፡ በፊልም ፕሮዲዩሰርነትም ሠርተዋል፡፡ የራሳቸውን የግል ድርጅትም ከፍተው ነበር፡፡ በአንድ ኪነጥበብን የሚመለከት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችም ናቸው፡፡ በቴአትር ጥበብም በዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በገመና ቁጥር ሁለት ድራማ ዙርያ ምሕረት አስቻለው አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ዳ’አማት ከገመና ቁጥር አንድ ደራሲ አቶ አድነው ወንድይራድ ጋር መግባባት ላይ ለመድረስ ምን ያህል ጥረት አድርጓል?

አቶ አብነት፡- ድርጅቱን እንደተቀላቀልኩ ሁኔታዎችን መለስ ብዬ ተመልክቻለሁ፡፡ ክፍል አንድ ካለቀ በኋላ ክፍል ሁለትን በጋራ ለመቀጠል ሐሳብ ነበራቸው፡፡ በገጸ ባሕርያቱ፣ በሐሳብ፣ በሌላም በሌላም በተመሳሳይ ሁኔታ ለመቀጠል ነበር፡፡ በሚዲያ እንደተገለጸው አቶ አድነው 1.5 ሚሊዮን ብር በመጠየቃቸው መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡ እስከማውቀው ድረስ ድርጅቱ ይህን ለመክፈል አቅም የለውም፡፡ የተጠየቀው ክፍያም ከቀድሞ ጋር ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ ድርጅቱ የኪነጥበብ ሰዎችን ፕሮሞት በሚያደርጉ ሰዎች የተቋቋመና የሚመራ በመሆኑ አቅም ቢኖረውና የተባለውን ክፍያ መክፈል ቢችል ኩራቱ ነበር፡፡ በቀደመው ክፍልም የታየው አርቲስቶች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ የተደረገበት ሁኔታ ነው፡፡ ሽልማት መሰጠቱም ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ አቶ አድነው የተጠየቁት ገንዘብ ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነም አሳውቀው ስለነበር ሌሎች አማራጮችን መጠቀም አልተቻለም፡፡  የተጠየቀው ገንዘብ የአገሪቱ ኢንዱስትሪም የድርጅቱም አቅም የሚፈቅደው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የቁጥር ሁለት አምስት ክፍሎችን ስክሪፕት ለድርጅታችሁ ሰጥተዋል?

አቶ አብነት፡- ስለዚህ ነገር አቶ አድነው በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የተለያዩ ነገሮችን በማለታቸው አንዱ መልስ መስጠት የምንፈልግበት ጉዳይ ነው፡፡ ስክሪፕቱን ሊጠቀሙብኝ ይችላሉ ብለው ሲሰጉ ወይም በዚህ ጉዳይ ወደ ሚዲያ መሔድ ሲያስቡ ዶኩመንቱ እኛ እጅ ነበር፡፡ እዚህ መጥተው በወዳጅነት ጠይቀው እኛም ሰጥተናቸዋል፡፡ እጃቸው ላይ ኮፒ ሁሉ የነበረ አልመሰለኝም፡፡ እኛም ኮፒ አድርገን ሳይሆን የሰጡትን ሲጠይቁ እንዳለ ነው አንስተን የሰጠናቸው፡፡ በዚህ ወቅት ድርጅቱ በቀጠራቸው ሁለት ጸሐፊዎች የተጻፈው ገመና ቁጥር ሁለት አምስት ክፍል ቀረፃ ተጀምሮ ነበር፡፡ እሳቸው የሰጡት አምስት ክፍልም ቀደም ብሎ ለማስታወቂያ ተብሎ ቀረፃ ተደርጎበት ነበር፡፡ አለመግባባት ሲፈጠር የእሳቸው ስክሪፕት እዚያ ላይ ቆመ፡፡ ነገር ግን ገና ለገና ስክሪፕቴን ይጠቀማሉ ብሎ ስም ማጥፋት ተገቢ ነገር አይደለም፡፡ ምናልባት የካምፓኒውን ፍላጎት ይጎዳል ብለው ያደረጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከእኔ በላይ ጸሐፊ የለም፤ አዳዲስ ጸሐፊዎች አይወጡም የሚል አንድምታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ስጋታቸው ስጋት ብቻ ነው፡፡ የእሳቸው ተመሳሳይ አክተሮች፣ ተመሳሳይ ታሪክ፣ ተመሳሳይ የሥራ አወቃቀር ተከትሎ የመሔድ ይዘት ያለው ጽሑፍ ነው፡፡ የእኛ ግን በብዙ መልኩ የተለየ ነው፡፡ የእሳቸውን የሚመስል ገጸ ባሕሪ፣ የታሪክ አወቃቀር፣ የታሪክ ፍሰት የለንም፡፡ ይህንን ሳያጣሩ ነው እዘረፋለሁ ብለው መገናኛ ብዙኀን ላይ የወጡት፡፡ ስለዚህ አካሔዳቸው የካምፓኒውን ስም ማጥፋትና የኢኮኖሚ ፍላጎትን መጉዳት ነው፡፡ በፍጹም የተለያዩ ሐሳቦችና አካሔዶች ናቸው በገመና ቁጥር ሁለት የሚንፀባረቁት፡፡

ሪፖርተር፡- ገመና የሚለውን ርዕስ መጠቀም ትችላላችሁ?

አቶ አብነት፡- ከጠበቆቻችን ጋር እንደተነጋገርነው እኛም እንዳየነው የቅጅና የተዛማጅ መብት ላይ የኮፒ ራይት ሕጉንም እንደተመለከትነው ርዕስ ጥበቃ አልተደረገለትም፤ የቅጅና የተዛማጅ መብት 410/96 ላይ፡፡ ርዕስን በሚመለከት ከስም ጋር በተያያዘ የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ላይ ነው በተለየ መልኩ የሚመለከተው፡፡ የኪነጥበባትና የኪነጥበብ ሥራዎች ላይ የቅጂና ተዛማጅ መብትን በተመለከተ ርዕስ ላይ የሚያስቀምጠው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ታሳቢ የተደረገው የሚመስለኝ የኦዲዮ ቪዥዋል ሥራ የኢኮኖሚ መብት በማያሻማ መልኩ የካሜራ ባለሙያዎች፣ የድምፅ ሰዎችንና አክተሮችን ቀጥሮ ጽሑፉን ወደ ሕዝብ እንዲደርስ ያደረገው ፕሮዲውሰሩ በመሆኑ ለፕሮዲዩሰሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጸሐፊውም የሞራልና የኢኮኖሚ መብት አለው፡፡ ተከፍሎት ይጽፋል፣ ሥራው የእርሱ ለመሆኑ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ እነዚህ መብቶች ሁሉ ተጠብቀውለት ነው የሚሠራው፡፡ በሌላ በኩል ፕሮዲዩሰሩ በርካታ ነገሮችን ጨምሮ ወደ ሕዝብና ወደ ገበያ ስለሚያደርሰው ሰፊ የኢኮኖሚ መብቱን ይወስዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ርዕሱን ያወጣው ማን ነው?

አቶ አብነት፡- እሳቸው የሰጡት ርዕስ ሰርጎ ገብ የሚል ነበር፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ለሪፖርተር ጋዜጣም እንዳሉት ሳይሆን ገመና የሚለው ርዕስ አማራጭ ብለው ከሰጧቸው ርዕሶች ውስጥ ያልነበረ ነው፡፡ ገመና የሚለውን ርዕስ ያወጣው የድርጅቱ ሠራተኛ (ዳይሬክተር) የነበረ ሰው ነው፡፡ እሳቸውም መጀመርያ አካባቢ ገመና የሚለውን ርዕስ የእኔ ነው ሲሉ አልተደመጡም፡፡ ይህ በተለያዩ መንገዶች መረጋገጥ የሚችል ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማንም ያውጣው ማንም ርዕሱ ለእሳቸው ሥራ የተሰጠ በመሆኑ በርዕሱ ላይ መብት ያላቸው እሳቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

አቶ አብነት፡- ርዕሱን መቀየር እንችላለን ርዕሱም የእኛ ብቻ ነው ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም ስምና ርዕስ በኮፒ ራይት የተጠበቀ አይደለም፡፡ በንግድ ምልክት፣ ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ 501/98 ጥበቃ የሚደረግለት ንግድ ምልክት ነው፡፡ ይህ የተደረገው አገልግሎትና ምርት የሚሰጡ ነጋዴዎችንና ተጠቃሚዎችን ለመጠበቅ ብዥታዎችን ለማጥራት ነው፡፡ እኛም ገመና የእኛ ነው ብለን አናምንም፡፡ ሌላ ሰው ገመና ብሎ ሊሠራ ይችላል፡፡ የድራማውን ተፈጥሮ፣ የሴራ አወቃቀርና አጠቃላይ የታሪኩ አካሔድ እስካልተመሳሰለ ድረስ፡፡ የእሳቸው ስክሪፕት አንድ ነገር ሲሆን ፕሮዲዩሰሩ የጨማመራቸው በርካታ ነገሮች ናቸው ገመናን ገመና ያደረጉትና ዋጋ የሰጡት፡፡ ስለዚህ የንግድ ፍላጎት እንዳለው ኩባንያ ገመና የሚለው ርዕስ ላይ ፍላጎት አለን፤ ስለዚህም ነው ርዕሱን መጠቀም የመረጥነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የሰው ሥራ የመዝረፍ ነገር አይደለም፡፡ ከእሳቸው በፊትም መስኮት በሚል ፕሮግራም ገመና የሚል አጭር ድራማ ተላልፏል፡፡ የኢኮኖሚ መብት የፕሮዲዩሰሩ ነው፡፡ ይህ የሆነው ነገሩን ያገዘፈውና ለሕዝብ ያደረስነው እኛ ስለሆንን ነው፡፡ እንደ ተመለከትኩት የኦዲዮ ቪዥዋል፣ የቅጂ መብትና ትሬድ ኔምን በሚመለከት በተለያየ ሚዲያ የተቀላቀለ ነገር ተናግረዋል፡፡ የተመዘገበ ምልክርትና ዓርማ አለን፣ የዶን ፊልሞች ነን፡፡ እሳቸው ገመናን እንደ ንግድ ስም አላስመዘገቡትም፣ ትሬደርም አይደሉም፣ ካምፓኒው የገዛው የአንድ አርት ሥራ ስም ነው ገመና፡፡ የይዘት ጥያቄ እስካልተነሳ ድረስ ማንም ሰው ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ገመና የሚለው ሥራ ገዝፎ ሕዝብ ዘንድ እንዲቀርብ ብዙ ነገሮችን ኢንቨስት ያደረገው ግን ፕሮዳክሽን ካምፓኒው ነው፡፡ እሳቸው ስክሪፕቱን ጽፈው ቢያስቀምጡት ይህ አይመጣም ነበር፡፡ ስለዚህ ርዕሱ ከእሳቸው ጋር ሳይሆን ይበልጥ ተያያዥነት ያለው ከፕሮዳክሽን ካምፓኒው ጋር ነው፡፡ እሳቸው በሔዱበት ሎጂክም ለልጃቸው ፓንዶራ ብሎ ያወጣ ሰው አባት መሆን እንደማይችል ሁሉ ለእሳቸው ልጅ የወጣው ፓንዶራ የሚለው ስም ለሌላ ልጅስ መውጣት አይችልም ወይ?

ሪፖርተር፡- ገመና ርዕስ ነው ወይስ ትሬድ ኔም?

አቶ አብነት፡- ትሬድ ኔም አይደለም፡፡ ትሬድ ኔም መሆን የሚችለው እንደ ካምፓኒ ሲመዘገብ ካልሆነም ቀድሞ ጥቅም ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩን ቀድሞ ከማንም በፊት የተጠቀመ አካል ከሆነ ሕጉም ያን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ያለ አግባብ የተነሳ ነው፡፡ ይልቁንም ገመና ድራማ ላይ ብዙ ኢንቨስት ያደረግነው እኛ በመሆናችን አብላጫው የሞራልና የኢኮኖሚ መብቱ የእኛ ነው፡፡ ከኮፒ ራይት አንፃርም ብንመለከት የቅጅና የተዛማጅ መብት 410/96 በኦዲዮ ቪዥዋል ሕግ ሥር ጥበቃ ይደረግላቸዋል ተብሎ ከተዘረዘሩት ውስጥ ርዕስ የሚባል ነገር የለም፡፡ ርዕስ አጭር እንደመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለት ይከብዳል፡፡ ከሕግ አንጻር ሐሳብን እንኳን መጠበቅ አይቻልም፡፡ ሰው የሚያስበው ነገር የእኔ ነው ብሎ ጥያቄ ማንሳት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ርዕሱ የማንም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የአቶ አድነው አካሔድ በድርጅታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ብላችኋል?

አቶ አብነት፡- ስክሪፕቴን ይጠቀማሉ የሚለው ስጋታቸው ከስጋት አልፎ እኛን መወንጀል ላይ ደርሷል፡፡ ርዕሴን ተጠቅመዋል እያሉም ለመወንጀል እየሞከሩ ነው፡፡ ምንም ዓይነት የሕግ ጭብጥ ሳይዙ ድራማው አይቀጥልም እናስቆመዋለን ዓይነት አካሔድ ነው የሔዱት፡፡ በዚህ የድርጅቱ ሠራተኞች ላይ የሞራል ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በጠራራ ፀሐይ የሰውን ሥራ ሰርቀን ለመሥራት የተሰባሰብን ሳይሆን በሙያው ልምድ ያላቸው ጥሩ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ጥሩ ጸሐፊዎች ይዘን በመሥራት ላይ ያለን ነን፡፡ አካሔዳቸው የድርጅቱን ስም፣ የኢኮኖሚ ፍላጎትና በደንበኞቻችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ስለዚህም ቀደም ሲል የድርጅቱን ፍላጎት በሚጎዳ መልኩ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ያስተላለፏቸውን መግለጫዎችና መግለጫ መሰል ቃለ ምልልሶችን ካላስተባበሉ እኛም እሳቸውን በፍርድ ቤት ከሰን መብታችንን እንደምናስረክብ በጠበቃቸው በኩል ማስጠንቀቂያ ልከንላቸዋል፤ ይህም ደርሷቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዲያስተባብሉ የምንፈልገው በሁለት ግልጽ ምክንያቶች ነው፡፡ በርካታ ሠራተኞችን ይዘን ከመንግሥትና ከሌሎችም አካላት ጋር እየሠራን ነው፡፡ በሌላ በኩል ለአርቲስቱ የኮፒ ራይትም ሆነ ለኢንዱስትሪው ማደግ የሚሠሩ ባለቤት ባሉበት ሁኔታ ስለምንሠራ አካሔዳቸው ሆን ብሎ የድርጅቱን ፍላጎት መግደልና ስም ማጥፋት ነው፡፡ ስለዚህ ባልነው ሁኔታ ካስተባበሉ ወደ ሕግ ለመሄድ ዝግጅታችንን ጨርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- እሳቸውም ወደ ሕግ እንደሚሔዱ አሳውቀዋል፡፡

አቶ አብነት፡- ርዕስ ላይ እኛ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለብንም፡፡ እሳቸው በየትኛውም መልኩ ርዕስን በሚመለከት ቢመጡ ለመመለስ ዝግጁ ነን፡፡ ስለዚህ ርዕሱን፣ የድርጅታችንን ስምና የንግድ ፍላጎት በሚመለከት የሕግ አግባብን ተከትለን መብታችንን ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን፡፡ ደንበኛ፣ አድማጭ፣ ተመልካች ተጨባጭ ባልሆነ መንገድ እኛ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረውና ጥርጣሬውም እንዲሰፋ አድርገዋል፡፡ የሠራተኞቻችን ሞራል ተነክቷል፤ የተለያዩ ሰዎችም ስልክ እየደወሉ ምንድነው በማለት ጠይቀውናል፤ የተወሰኑ ስፖንሰሮችም ነገሩ እስኪጣራ በማለት ለጊዜውም ቢሆን ራሳቸውን ከድጋፍ አግልለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጉዳዩን በሚመለከት በሚዲያ ምላሽ ለመስጠት ለምን ዘገያችሁ?

አቶ አብነት፡- ዝምታን የመረጥነው ለጉዳዩ የማይገባውን ትኩረት ላለመስጠትና ነገር ላለማራገብ ነው፡፡ በተገቢው ጊዜ ላይ ነገሩን በሕግ አግባብ እንሄድበታለን ብለን በማሰብም ነው፡፡ ለዚያ ደግሞ ሰዓቱ አሁን ነው፡፡ ስም ወደ ማጥፋትና የድርጅቱን ፍላጎት ወደመጉዳት በመሄዳቸው፡፡ ርዕሱን አስመልክተው ወደ ሕግ ሄዱም አልሄዱም ለደረሰብን ጥፋት በሕግ አግባብ እንጠይቃቸዋለን፡፡ ምንም እንኳ እስካሁን መዘግየታችን ቢጎዳንም አሁን ወደኋላ በማንመለስበት ሁኔታ ተነስተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በገመና ቁጥር ሁለት ከሕዝብ የምትጠብቁት  ምላሽ ምንድ ነው?

አቶ አብነት፡- ቁጥር ሁለትን እየጻፉ ያሉት ጸሐፊዎች በሙያው ረዥም ልምድ ያላቸውና የዩኒቨርሲቲ ምሩቆች ናቸው፡፡ ከዚያ ባሻገር ፕሮዳክሽን ካምፓኒውም ምንድነው የሚፈልገው? ታሪኩ እንዴት ነው መሔድ ያለበት? የሚለውን የሚያሳይ (synopsis) አምጥተው የተጀመረ፣ የተለየ ታሪክ፣ ፍሰት፣ የሴራ አወቃቀር ያለው ነው፡፡ ቁጥር ሁለቱ የሚያጠነጥነው በአንድ ቤተሰብ ላይ ነው፡፡ በዚያ ቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ውጣ ውረዶች በቤተሰቡም በማኅበረሰቡም ላይ እንዴት ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ የሚያሳይ ነው፡፡ እስካሁን የተሠሩት ሥራዎች አመርቂ ናቸው፡፡ ጥሩ የቴሌቪዥን ድራማ እንደምናቀርብ ጥርጥር የለንም፡፡ ቁጥር ሁለት ብዙ ታዋቂ አክተሮች የተሳተፉበት በፕሮዳክሽንም በቴክኒክም የተሻለ ነገር የሚታይበት ይሆናል፡፡ አገራችን ባለው ሁኔታ በየትኛውም መመዘኛ የተሻለ ሥራ የሚታይበት እንደሚሆንም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የምዕራፍ ሁለት ክፍል አንድ ላይ እንደታየው የተወሰኑ አርቲስቶች እዚያ ላይ የነበሩ እዚህኛውም ላይ አሉ፡፡ የገጸ ባህሪ ተወራራሽነት የለም፣ ተዋናዮቹ ግን የተለያየ ገጸ ባሕሪያት ተላብሰው ይሠራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአቶ አድነው ደብዳቤ ደርሷችኋል?

አቶ አብነት፡- በቴሌቪዥን ገመና ሁለት እያላችሁ ታስተዋውቃላችሁ፣ ገመና ሁለት በሚል ማስተዋወቃችሁን ካላቆማችሁ ክስ እመሰርታለሁ የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ከጥቂት ቀናት በፊት ደርሶናል፡፡ ገመና አንድ እና ገመና ሁለት ይለያያል፣ ነገሩን በደንብ እንየው ካልን፡፡ ገመና አንድ መቶ ወይም አንድ ሺሕ ብንል ገመና የእኔ ነው ሊባል ነው እንዴ? ይህ በፍልስፍናውም በሳይንሱም አያስኬድም፤ በፀጉር ስንጠቃ አካሄድ ከተጓዝን፡፡

ሪፖርተር፡- እንደምትፈልጉት ባያስተባብሉ የክሱ መሠረት ምንድን ነው የሚሆነው?

አቶ አብነት፡- ስም ማጥፋት ይሆናል፡፡ ድርጅታችን የገነባው መልካም ገጽታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ የንግድ አጋሮቻችን ላይ የንግድ ፍላጎታችንን በሚጎዳ መልኩ ተፅዕኖ አድርገዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ምንም ነገር ያለን አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ያለመግባባቱ መጀመርያ የተነሳው በቁጥር አንድ ፍፃሜ ላይ የጠበቁትን ባለማግኘታቸው እንደሆነ አቶ አድነው ተናግረዋል፡፡

አቶ አብነት፡- እኔ በዚያ ወቅት አልነበርኩም፤ ግን ዶኩሜንቶችን አንብቤያለሁ፡፡ ሽልማት ዕውቅና የመስጠት ነገር ነው እንጂ እገሌ መቶ ሺሕ ይጠብቅ እገሌ ደግሞ ሃምሳ ሺሕ የሚባል ነገር የለም፡፡ እሳቸውም የተባሉት ነገር የለም፡፡ ድርጅቱም ሽልማት የሰጠው በድራማው ላይ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን ዕውቅና ለመስጠት ነው፡፡ በግሌ የማምነውም ሽልማት ዕውቅና ነው፤ ሰርተፊኬትም ሊሆን ይችላል፡፡ የአገሪቱ የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ ከፈቀደ በሥራቸውማ አንድ ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ ይገባቸው ይሆናል፡፡ ይህን የሽልማት ዓላማ አቶ አድነው እንዴት መመልከት እንዳልቻሉ ይገርመኛል፡፡ ሽልማቱን የግድ ከገንዘብ ጋር ማያያዛቸው ያሳዝናል፡፡ በመጀመርያው ክፍል በክፍያ ተጎድቻለሁ የሚል ስሜት ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ስቴትመንቱን [የሒሳብ] እንደማየው ቁጥር አንድ በኪሳራ ነው የተሠራው፡፡ ይህን ከተዋናዮች ጀምሮ ሁሉም የሚረዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሽልማቱም ማንንም ይመጥናል ወይም ይክሳል ሳይሆን ዕውቅና ለመስጠትና ለማበረታታት ነው፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close