ኢትዮጵያ በኤርትራ መንግሥት ላይ ያላትን ስጋት አሜሪካ እጋራለሁ አለችበአስራት ሥዩም

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ መንግሥትን በተመለከተ የሚከተለውን ፖሊሲ መቀየሩንና ከእሳት ማጥፋት ወደ ዘላቂ መፍትሔ መሸጋገሩን መግለጹን ተከትሎ፣ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያለውን የፀጥታ ስጋት የአሜሪካ መንግሥትም እንደሚጋራው አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ዶናልድ ኢ.  ቡዝ እንዳሉት፣ መንግሥታቸው በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ፀጥታን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚጋራቸው ነጥቦች በርካታ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ በኤርትራ የሚገኘው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት የሚለኩሰውን እሳት መንግሥታቸው ማጥፋት ሰልችቶታል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የኤርትራ መንግሥት በሶማሊያ ከሚያደርገው የታጠቁ አሸባሪዎችን ከማሰማራት  በተጨማሪ፣ “አዲስ አበባን ወደ ባግዳድ” ለመቀየር የብጥብጥ አጀንዳ ይዞ እየሠራ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በግጭትና በብጥብጥ በታጠረው የአፍሪካ ቀንድ ክልል ውስጥ የምትገኝ መረጋጋት የሰፈነባት ደሴት ናት ሲሉ የጠቀሱት አምባሳደር ቡዝ፣ በተለይ የክልሉን ሰላም የማደፍረስ ሚና የሚጫወቱ አገሮችን በተመለከተ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ትሠራለች ብለዋል፡፡ “በተለይ አሸባሪነትንና ጽንፈኝነትን በተመለከተ አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ካሏት አጋሮች መካከል ዋነኛዋ ኢትዮጵያ ነች፤” ያሉት አምባሳደሩ፣ ‹‹በሶማሊያና በሱዳን ጉዳይ እንደተደረገው ሁሉ በኤርትራ ላይም  ተቀራርበን እንሠራለን፤›› ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያና በአርትራ መካከል ግጭት መነሳቱ ለማንም አይጠቅም ያሉት አምባሳደር ቡዝ፣ ነገር ግን አገራቸው አሜሪካ አገሮች የፀጥታ ስጋታቸውን የማስወገድና ራሳቸውን የመከላከል መብታቸውን አትቃወምም ብለዋል፡፡ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ወደ ግጭት የመግባት ፍላጐት እንደሌለው አውቃለሁ፤ ከዚህ በፊቱ ግጭት ከ100 ሺሕ  ያላነሰ የሕይወት ዋጋ በመከፈሉ በድጋሚ ወደዚያ የመመለስ ፍላጐት አይኖርም፡፡ ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን፣ “ራስን የመከላከል መብትን እናከብራለን፤እንደግፋለን፤” በማለት አክለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኤርትራ መንግሥት ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለት ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡ “ይህ መሆን ከልቻለ ግን ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል ትገደዳለች፤” ነበር ያሉት፡፡ ይህ የመንግሥት አቋም ይፋ ከመደረጉ በፊት አቶ ኃይለ ማርያም ወደ አሜሪካ ተጉዘው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ ከአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close