ይድረስ ለኢሕአዴግ መሪዎች (በሊቢያ በኩል የተላከ)

(እስክንድር ነጋ ከኢትዮጵያ)

ፓሪስ፤ ቅዳሜ፣ ምሣ ሰዓት፣ መጋቢት 1ዐ/2ዐዐ3 የሳርኮዚ የታላቅነት ህልም እየሆነ ነው… ምሳ ግብዣቸው ላይ የዓለም ዋና ዋና መሪዎች በአድናቆት ታድመዋል… «በመሪዎች መሪነት» አድምቀዋቸዋል…. ትንሽ የማይባሉ ፈረንሣዮች እንባ እየተናነቃቸው ነው፤ በታላቁ ንጉሣቸው ሊዊ 16ኛው ዘመን የነበረው ኃያልነታቸውን እየታወሳቸው…. ዛሬ ፈረንሳይ የዓለም መዘውር ሆናለች…. ሳርኮዚም በሊዊ 16ኛው ተመስለዋል፡፡

ኦባማ ብቻ የውሃ ሽታ ሆነዋል…. የመሪነቱን አክሊል ለአውሮፓዊያን አቀብለው ወደ ብራዚል ነጉደዋል፡፡

ግራ አያጋባም ጃል?

ኃያሏ አሜሪካ ምን ነካት? …. የናዚ ጀርመንን የፈረጠመ ጡንቻ እንደጨው ያሟሟችው የትላንት በስቲያዋ አሜሪካ የት ገባች?…. ከሩሲያ ተነስቶ ዓለምን ላናጋው የሶሻሊስት ማዕበል ዝንፍ ያላለችው ብርቱዋ አሜሪካ ምን ዋጣት?…. እውን በኢራቅ የጨረፋት እንቅፋት ወኔዋን ሰልቦት ቀረ እንዴ? ….

ይሄ ሆነ መጨረሻዋ?

ቤንጋዚ፤ ማለዳ ቅዳሜ፣ መጋቢት 1ዐ/ 2ዐዐ3

የሞአመር ጋዳፊ ቅጥረኛ ጦር ወደቤንጋዚ እየገሰገሰ ነው…. ታንኩ፣ ብረት ለበሱ፣ መድፉና ሞርታሩ የከተማዋን በር እያንኳኩ ነው…. የጦር አውሮፕላኖቻቸው ከላይ የቦምብ ናዳ ያዘንባሉ…. ከባድ መሣሪያዎቸቸው ከርቀት ሆነው ያጓራሉ….

ቀላል መሣሪያዎች የታጠቁት ተቃዋሚዎቻቸው፣ በከተማዋ ህንፃዎች ውስጥ መሽገዋል…. እያንዳንዷን መንገድ የጦርነት አውድማ ለማድረግ ምለዋል….ቤንጋዚ በደም ጐርፍ ለመታጠብ ትንሽ ሰዓታት ብቻ ቀርተዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ወደፊጣሪያቸው ይጮኻሉ…. አቅም ያለው ምግብ ገዝቶ አከማችቷል…. መድኃኒት ከጠፋ ሰነባብቷል…. ውሃ ይጠፋል ብሎ ሁሉም ተጨንቋል…. ያለ ምግብ ወር ይኖራል፣ ያለ ውሃ ግን አንድ ሳምንት እንዴት ይዘለቃል?

የቁርጥ ቀን ደርሳለች…. ጭልምልም ብሏል…. ዓለምም ፊቷን አዙራለች፡፡

አዲስ አበባ፤ ቅዳሜ ምሣ ሰዓት፣ መጋቢት 1ዐ/ 2ዐዐ3

የአክራሪዎቹ ኢሕአዴግ መሪዎች ፊት ቦግ ቦግ ብሎ አብርቷል…. ከሊቢያ መልካም ወሬ እየተሰማ ነው…. በዲስፕሊን የታነፀ ጥቂት ወታደር ሚሊዮኖችን መጨፍለቅ እንደሚችል በተግባር እየታየ ነው…. ቱኒዚያ ሲናድ፣ ግብፅ ሲናድ፣ በኢትዮጵያም

ተመሳሳይ ክስተት ሊፈጠር ይችላል ብለው በመጠራጠራቸው እየተቆጩ ነው….

እስከ እራት አልጠበቁም…. ብርጭቆቻቸውን ምሣ ሰዓት ላይ አንገጫገጩ…. ቺርስ!… የሁለት ወር ውዥንብር እየጠራ ነው… «It’s about time» አሉ ራሰ በረሃው!… ጭብጨባ!…. ጭብጨባ… በታላቁ ግቢ!…

ቤንጋዚ፤ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ፣ መጋቢት 1ዐ/2ዐዐ3

የቤንጋዚ ነዋሪ ከቤቱ አልወጣም…. ጎዳናዎች ፀጥ ረጭ ብለዋል…. የጋዳፊ ጦር መቀበሪያ ለመሆን ተዘጋጅተዋል፡፡

የሳርኮዚ ምሣ ግብዣ ከተገባደደ 9ዐ ደቂቃዎች አልፈዋል፡፡

እንደድንገት የተዋጊ ጄቶች አስፈሪ ጩኸት አየሩን ሰነጠቀው…. ድፍን ቤንጋዚ መሬት ላይ ተነጠፈ፤ ከሰማዩ ጥፋት ያድነው ይመስል…. አልጋ ስር፣ ጠረጴዛ ስር፣ ወንበር ስር አጥር ስር፣… ነፍስ ናት!

ግን… ግን… ግን… አንድም ጥይት ቤንጋዚ ላይ ሳያርፍ ቀረ…. የጋዳፊ አየር ኃይል ዒላማውን ስቷል ብሎ ከመጠርጠር ሌላ ምን አማራጭ አለ?

በዚያች ቅፅበት ግን፣ ዓለም ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተሸጋገረች…. የአምባገነኖች የ ሉዓላዊነት ምሽግ ተናጋ፤ ገና ባይናድም፡፡

ሰንዓ፤ ሰኞ ከሰዓት፣ መጋቢት 12/ 2ዐዐ3

የየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ድብልቅልቋ ከወጣ ሶስት ቀናት ሆኗታል… ዓርብና ቅዳሜ በሕዝቧ ኡኡታ የተጨነቀው የሰንዓ አየር፣ ዛሬ በእልልታ ቀልጣል፡፡

በ72 ሰዓታት ውስጥ ምን ተፈጠረ?

ለ32 ዓመታት በስልጣን ላይ ተደላድለው የኖሩት የፕሬዝዳንት ዓሊ አብደላ ሳሌ ታማኝ ወታደሮች ዓርብ ዕለት የ4ዐ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ በፍርሐት ይበተናሉ በሚል ተስፋ… ውጤቱ ግን ተቃራኒ ነው የሆነው፤ እንደ ግብፅ… በነጋታው መላ ሰንዓ ከቤቱ ተነቅሎ የወጣ ነው የመሰለው፡፡

ስለሊቢያ ሲዘግብ የዋለው አልጀዚራ፣ ሰኞ ረፋዱ ላይ ትሪፖሊን ጥሎ ሰንዓ የገባ… ለዓለም የሚያበስረው ትኩስ ዜና ይዟል… 3 የየመን ጄኔራሎች ጦራቸውን ይዘው ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ተቀላቀሉ… ሳሌ ከሞላ ጎደል አልቆላቸዋል… የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡

አዲስ አበባ፣ ሰኞ ምሽት፣ መጋቢት 12/2ዐዐ3

ስለ ሊቢያ ገረፍ ገረፍ አድርጎ የዘገበው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ ስለየመን ምንም ሳይተነፍስ ቀረ… በምትኩ፣ ጃፓን ውስጥ ከደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር በተያያዘ ስለአንድ ውሻ ረጅም ዘገባ አቀረበ፡፡

ከምሽቱ 5፡3ዐ ላይ፣ ኢቲቪ 2 ስለ ፕሬዚዳንት ሳሌ ታላቅነት የሚተርክ ዶክመንተሪ አቀረበ… Yemen A Strong President and better future ይላል አርዕስቱ… የመን ልማት በልማት ሆናለች… እንደ ኢቲቪ 2 ዶክመንተሪ ከሆነ!

የሊቢያና የየመን አስተምህሮት ለኢሕአዴግ

የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በጋዳፊ ላይ የተባበረ ክንዱን ያነሳው የካቲት 15/2ዐዐ3 ዓ.ም. ነበር፡፡ የጋዳፊ ተቃዋሚዎች ትሪፖሊን ለማጥቃት እየተዘጋጁ በነበረበት መባቻ ላይ ኒውዮርክ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ፀጥታ ምክር ቤት፣ የገዛ ዜጎቻቸውን በጦር አውሮፕላን በደበደቡት ጋዳፊ ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ከመጣል ያለፈ እርምጃ መወሰድ አስፈላጊ መስሎት አልታየውም፡፡

በ15 ቀናት ልዩነት ግን፣ ጋዳፊ ከሞት መንጋጋ አፈትልከው ተቃዋሚዎቻቸው እምብርት ድረስ ለመዝለቅ በቁ፡፡

የጋዳፊ ማንሰራራት ምዕራባውያንን በጥቅሉ ቢያበግንም፣ የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰደችው ግን ፈረንሳይ ብቻ ነበረች፡፡ ቤንጋዚን ማዕከል ያደረጉትን የጋዳፊ ተቃዋሚዎች የመንግሥትነት እውቅና በመስጠት፣ ጋዳፊ ወደ ስልጣን ሲመለሱ ፈረንሳይ በገለልተኝነት ላለመመልከት አቋም ወሰደች፡፡ 27 የአውሮፓ አገራት በሚያስደንቅ ፍጥነት በነጋታው ፈለጓን ተከተሉ፡፡ እንደወትሮው የአሜሪካንን አመራር አልጠበቁም፡፡ አሜሪካ ኩርፊያ ቢጤ ከጀላት፡፡

ከሁለት ቀናት በኋላ፣ ለአውሮፓውያኑ ካልተጠበቀ አቅጣጫ ታላቅ ድጋፍ ተቸረ፤ ከአረብ ሊግ፡፡ 22 የዓረብ ሃገራት ስብስብ የሆነው ይህ ተቋም፣ ምዕራባዊያን በሊቢያ ላይ የበረራ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጠየቀ፡፡ ይህም፣ ለወታደራዊ እርምጃ ጥርጊያ መንገድ ከመክፈቱም ባሻገር፣ አሜሪካ ወደ አውሮፓውያኑ ስብስብ እንድትቀላቀል አስገደዳት፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ፀጥታ ምክር ቤት በበኩሉ፣ ከአምስት ቀናት በኋላ ለበረራው ማዕቀብ በብርሃን ፍጥነት ቡራኬውን ሰጠ፡፡ ማዕቀቡን ለማስከበር «አስፈላጊ እርምጃ» እንዲወሰድ የሚፈቅድ አንቀፅም አውሮፓውያኑ ላይ ሮጣ ለመድረስ የረፈደ እንቅስቃሴ በጀመረችው አሜሪካ ውትወታ ተካተተ፡፡ ይህ አንቀፅ ነው ቅዳሜ ለተወነጨፉት ሚሳኤሎች እና የፈረንሳይ ተዋጊ ጀቶች ምክንያት የሆነው፡፡

ከሜዲትራኒያን ባሕር ከሚገኙ 15 የአሜሪካና የብሪታኒያ የጦር መርከቦች የተተኮሱ 112 ቶምውሃክ ሚሳኤሎች ለአንድ ሰዓት ተጉዘው ነበር የጋዳፊን አየር ኃይልና ከባድ መሣሪያዎች መርጠው አመድ ያደረጉት፤ እድሜ ለሳተላይት ቴክኖሎጂ፡፡ በዚህ የተገረመ አልነበረም፡፡ የምዕራብያዊያን የቴክኖሎጂ ምጥቀት የወታደራዊ በላይነታቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለጥጦታል፡፡ ያስገረመው ከዓለም መሪዎች የጎረፈው አስተያየት ነበር፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ባን ኪሙ፣ ወታደራዊ እርምጃውን ከማወደሳቸውም ባሻገር፣ ተከታታይ ጥቃቶች እንዲፈፀሙ አብራርተዋል፡፡ «እርምጃው አልረፈደበትም፡፡ የዓረብ ሀገራት፣ አውሮፓውያን፣ አሜሪካዊያን፣ እንደ አንድ ሰው ሆነው የተንቀሳቀሱት፡፡ ሕዝብ ሲጨፈጨፍ የዓለም መንግሥታት የዳር ተመልካች መሆን አይችሉም» ብለዋል ዋና ፀሐፊው፤ ከጋዳፊ ውጭ ያሉትን አምባገነን መንግሥታት ታሳቢ ባደረገ አስተያየታቸው፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ሂላሪ ክሊንተን ግን፣ ካለፈው ይልቅ መፃዒው የሊቢያ ዕድል እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል፡፡ «ጋዳፊ በቀል አርግዘዋል፡፡ ወደ ስልጣን ቢመለሱ ባላንጣዎቻቸውን ለመበቀል ሊቢያን በደም ያጨማልቋታል፡፡ ወደ ስልጣን እንዲመለሱ ሊፈቀድላቸው አይገባም» ብለዋል ክሊንተን፤ ሰፊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰባቸው አምባገነኖች ለምን ከስልጣን የግድ መልቀቅ እንዳለባቸው ሲያብራሩ፡፡

በሊቢያ በኩል መልዕክቱ የተላለፈላቸውን ሀገራት ነቅሶ ለማውጣት ብዙም የሚቸግር አይደለም፡፡ እዚያው መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ከሊቢያ በስተምሥራቅ ከሚገኙት ሞሮኮ፣ አልጄሪያ አንሶቶ፣ በምዕራብ በኩል ያሉትን ሶሪያንና ጆርዳንን ነካክቶ፣ በደቡብ አቅጣጫ እነባሕሬንን፣ ሳውዲንና የመንን የሚያጠቃልል ነው፡፡

ወደ ጥቁር አፍሪካ ሲዘልቅ ደግሞ፣ ቀዳሚዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ እኔ ብቻ አይደለሁም ይህንን የምለው፡፡ ፈረንጆቹ ደጋግመው ሲፅፉበት የሰነባበቱበት ጉዳይ ነው፡፡

ይሄ መልዕክት ለኢሕአዴግ መሪዎች አልደረሳቸውም ብዬ ለመገመት ይቸግረኛል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ይህቺን ሀገር ለ2ዐ ዓመታት እየደቋቆሱ ያገላበጧት የኢሕአዴግ አውራ መሪዎች፣ በፖለቲካ ድህነት እንደማይታሙ አውቃለሁ፡፡ እኔም አላማቸውም፡፡ ስለቆሙለትም፣ ስለሚቃወሙትም ፖለቲካ ጠለቅ ብለው ያውቃሉ፡፡ የዓለም ፖለቲካንም በቅርብ ይከታተላሉ፡፡

ለዚህ ነው በ97 እና በ98 የፈፀሙትን ዓይነት ጭፍጨፋ ለመድገም የሚያስችል ዓለም አቀፍም ሆነ ሃገራዊ ሁኔታ እንደሌለ በጥንቃቄ ያውቃሉ ብዬ በድፍረት የምናገረው፡፡ አስረጂ አይሹም፡፡ እንዲያውም፣ ሾጥ ቢያደርጋቸው፣ አሻሽለውና አብራርተውም ሊያስረዱን የሚያበቃቸው ክህሎት አላቸው ብል አይበዛባቸውም፤ በተለይ መለስ ዜናዊ፡፡

ሆኖም ግን፣ ፈረንጆች For the record እንደሚሉት፣ የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ መልዕክት በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ማስቀመጡ አይከፋምና፣ የኢሕአዴግ መሪዎች ለጥቂት ሴኮንዶች ብቻ እንዲያደምጡኝ በሕዝብ ስም እማፀናቸዋለሁ፤ ለእኛም ለእራሳቸውም ብለው፡፡

ውድ የኢሕአዴግ መሪዎች ሆይ!

ሰላማዊ ሰልፈኞችን የመጨፍጨፊያ ዘመን አብቅቷል፡፡ (በሊቢያ በኩል የተላለፈላችሁ መልዕክት ነው!)

እንዳትሳሳቱ!!!

ፀሐፊውን በ serk27@gmail.com ማግኘት ይቻላል

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close