‹‹በኢትዮጵያ ዓመፅ ቢነሳ ባለቤቱ ሕዝቡ እንጂ ፓርቲዎች አይደሉም››

አንድነት ፓርቲ

– መድረክ ዛሬ በመቀሌ ለጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይቀሰቅስ መከልከሉን ገለጸ

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሰሞኑን ‹‹ሽብርና አመፅን ከሚቀሰቅሱ መካከል›› ያሉዋቸውን የአንድነት የፓርቲ አባላት ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመፅ የሚቀሰቀስ ከሆነ የእንቅስቃሴው ባለቤት ራሱ ሕዝቡ እንጂ ፓርቲዎች አይደሉም አለ፡፡ ከዚህ ይልቅ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማስፈራራት አቁሞ የሕዝቡን ብሶት እንዲያዳምጥ አሳስቧል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ተቃዋሚዎችን ለመምታት የተደረገ ሴራ ነው ሲሉም የፓርቲው አመራሮች ይወቅሳሉ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማስጠንቀቂያ ንግግር እጅግ ማዘናቸውን የሚናገሩት የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ስዬ አብርሃ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ግድብ ሊሠራልህ ስለሆነ ቦንድ ግዛ፣ ለልማት አዋጣ ተብሎ በሚቀሰቀስበት ወቅት፤ ዜጎች አባል የሆኑባቸውን ተቃዋሚዎችን ማስፈራራትና ዛቻ መንዛትን ምን አመጣው?›› በማለት እርስ በርሱ የሚጋጭ ድርጊት ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡

‹‹ዜጎች ለልማት እንዲሰለፉ ጥሪ እያደረግክ፣ ነፃነታችሁን ግን አታገኙም ማለት ሰጥቶ መከልከል ነው፡፡ ዜጐችን ግዴታችሁን ፈጽሙ ስትላቸው መብታቸውንም ልትጠብቅላቸው ይገባል፡፡ አሁን የተደረገው ግን ቦንዱን ግዙ፣ በገዛ ገንዘባችሁ ነፃነታችሁን አሰጣችኋለሁ ዓይነት ነው፡፡ ከነበረው የልማት አጀንዳና መንፈስም እጅግ የሚቃረን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ አንድነት ፓርቲ፣ ‹‹የጭዳ ፍየል ፍለጋ ከመወራጨት ለተገቢ የሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ መስጠት›› በሚል ርዕስ ባወጣው በዚሁ መግለጫው፣ በአሁኑ ወቅት በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለውን አመፅ ‹‹ድንቅ ሕዝባዊ ገድል›› በማለት ያደነቀ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አፈናዎች ሥር እየማቀቁ ላሉት ሕዝቦችም ከፍተኛ የመነቃቃትና የነፃነት ስሜት እየፈጠረ መሆኑን ያትታል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜን አፍሪካ አገሮች ካለው ችግር በእጅጉ የባሰ የኑሮ ብሶትና የፖለቲካ አፈና መኖሩን የሚገልጸው አንድነት፣ በእነዚያ አገሮች እየተፈጠረ ያለው አመፅ እዚህም ሊደገም ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ በመግባቱ ‹‹ኢሕአዴግ ሽብር መንዛቱን እንደ መፍትሔ አድርጎ ወስዶታል›› ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመድረክ በተለይ ደግሞ አባል ፓርቲው በሆነው በአንድነት ፓርቲ ላይ ኢሕአዴግ የሽብር መልዕክት በመንዛት ማነጣጠሩን የሚናገረው ፓርቲው፣ ‹‹እነ አቶ መለስ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ከማጣታቸው የተነሳ ሌሎችንም ከመወንጀል አልተቆጠቡም፤›› በማለት የኤርትራን መንግሥት፣ የግብፅን መንግሥት፣ የንግዱን ማኅበረሰብ፣ ኦነግንና ሌሎችን የዚሁ የኢሕአዴግ የሽብር ሰለባ ካላቸው መካከል ይዘረዝራል፡፡

ሕዝባዊ አመፅ የተቀሰቀሰባቸው አገሮችም መሪዎቻቸው ተመሳሳይ ‹‹የማላከክ ባህሪ ታይቶባቸዋል›› የሚለው አንድነት፣ ‹‹አምባገነን መንግሥታት ሁልጊዜም ወደ ውስጣቸው መመልከትና እውነታውን መጋፈጥ የሞት ያህል ያስፈራቸዋል፡፡ ኢሕአዴግ ባደረበት ስጋት አሊያም ኢትዮጵያና ሕዝቧ ለሚገኙበት እጥፍ ድርብ ጭቆናና ችጋር መንስዔ ኢሕአዴግ ራሱ ነው፤›› በማለት የአቶ መለስን ንግግር ከአምባገነን መሪዎች ባህሪ ጋር አገናኝቶታል፡፡

ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመላ ሊረባረብበት የሚገባ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ስዬ፣ ኢሕአዴግ ይህንን ለፖለቲካ ጥቅም እንደመሣሪያነት የሚያውለው ከሆነ ግን የሕዝቡን የመተባበር መንፈስ ይገድለዋል ይላሉ፡፡ አቶ ስዬ ስለ አገር ልማትና አንድነት የሚጨነቁ ዜጎች ከሻዕቢያና ከመሳሰሉት ጠላቶች ጋር መፈረጅን ‹‹የአስተሳሰብ ቀውስ ነው›› ብለውታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመፅ ከተቀሰቀሰ መንስዔው የኢሕአዴግ አምባገነንነት፣ ለሕዝብ ብሶት ምላሽ አለመስጠትና የፕሬስና የሲቪክ ማኅበራት እንቅስቃሴ አፈና መሆኑን የሚያትተው አንድነት፣ የአቶ መለስ መልዕክት ‹‹በዋናነት ሕዝብ ከፍርኀት ወጥቶ ነፃነቱን እንዳይጠይቅ ለማስፈራራት የታለመ ነው፤›› ይላል፡፡ ሰሞኑን በመንግሥት በኩል የሚነገረው ስለ ሁከት፣ ስለጦርነትና ሲያሻውም ስለልማት መለፈፉ ከጭንቀት የተነሳ መሆኑን አንድነት በመግለጫው ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል፣ መድረክ በዛሬው ዕለት በመቀሌ ለጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይቀሰቀስ መከልከሉን የፓርቲው አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በምርጫ ወቅት ብቻ ነው ሕዝባዊ ቅስቀሳ ማድረግ የምትችሉት፤›› በሚል በከተማው የፀጥታ ኃላፊዎች ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸው የሚናገሩት አቶ አንዱዓለም፣ ቀደም ሲል በአዲስ አበባና በሐዋሳ መድረክ ባካሄዳቸው ስብሰባዎች ቅስቀሳ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው አልተሳካልንም፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close