ባንኮች የስምንት ወራት ሰነድ ግዥ ውዝፍ መክፈል ጀምሩ ተባሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ቀደም ሲል በባንኮች ላይ ተጥሎ የነበረውን የብድር ገደብ በማንሳት የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ መመሪያ ካወጣ በኋላ፣ ባንኮቹ ካለፈው ሐምሌ 2002 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ የካቲት 2003 ዓ.ም. ድረስ ለሰጡት ብድር 27 በመቶ ውዝፍ የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እንዲከፍሉ ታዘዋል፡፡ በአዲሱ መመርያ መሠረት ባንኮች ካሁን በኋላ የሚሰጡትን ብድር 27 በመቶውን ያህል የብሔራዊ ባንክን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙ የሚገደዱ ሲሆን፣ ነገር ግን ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ እስካለፈው ወር ድረስ የሰጡትን ብድር 27 በመቶ ወደኋላ ተመልሰው መግዛት እንዳለባቸው ያዛል፡፡

የብድር ገደቡ በተለቀቀ በቀናት ውስጥ ከብሔራዊ ባንክ የተላከው ይህ ትዕዛዝ፣ ባንኮቹ የተጠየቁትን የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ለመፈጸም እንዲችሉ የአሥራ አምስት ቀን ዕድል ሰጥቷል፡፡

ባለፈው ሐሙስ ምሽት የግል ባንኮች ፕሬዚዳንቶችን ሰብስቦ ያነጋገረው ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመሪያ ለማስፈጸም ጠንካራ አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በግል ከሚንቀሳቀሱ ባንኮች መካከል ትላልቅ ናቸው ተብለው የሚታመኑት ባንኮች እስከ 700 ሚሊዮን ብር ውዝፍ የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ለማካሔድ ይገደዳሉ፡፡

የባንክ አገልግሎት ዘርፉን ገና የተቀላቀሉ አዳዲስ ባንኮች በአዲሱ መመርያ በእጅጉ ተጎጂ እንደሚሆኑ ከመናገር አልቦዘኑም፡፡ ወደ ባንክ ዘርፍ ለመግባት ከፍተኛ የመነሻ ካፒታል ወጪ ማድረጋቸውን የሚጠቅሱት እነዚሁ ባንኮች፣ ወጪያቸውን ለመመለስና ለረጅም ጊዜ ዘርፉ ውስጥ ከቆዩት ሌሎች ባንኮች ጋር ተወዳድሮ ለመዝለቅ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

በሌላ በኩል በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ባንኮች በብድር መልክ ከሚሰጡት ገንዘብ 27 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ላይ ማዋል ሲጀምሩ፣ የሦስት በመቶ ወለድ የሚገኝበት የብሔራዊ ባንክ ሰነድ፣ አምስት በመቶ ከሚከፈልበት ተቀማጭ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነትን (ኪሳራን) ሊያመጣባቸው እንደሚችል ባንኮቹ ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም አብዛኛዎቹ የባንክ ባለሙያዎች ባንኮቻቸው በብድር የሚያስከፍሉት የወለድ ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ እንደማይቀር እየገመቱ ነው፡፡ የብድር ገደቡ በሥራ ላይ ከዋለ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በየባንኩ ብድር ጠያቂዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው ይነገራል፡፡ ነገር ግን የብድር ገደቡን መነሻነት ተከትሎ ለብድር የሚከፈለው የወለድ ምጣኔ በተበዳሪው ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ መገመት እንደማይከብድ ባለሙያዎቹ አክለው ይገልጻሉ፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close