የሚሌኒየም ቦንድ ገበያው ደርቷል ወያኔ በአጭር ጊዜ በቦንድ ግዢ ከበርቴ እንደሚሆን ተጠቆመ

በዓባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባው የሚሌኒየም ግድብ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የተጀመረው የሚሌኒየም ቦንድ ሽያጭ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ትኩረት እየሳበ ሲሆን፣ ግዢውን ለመፈጸም በርካታ ሰዎች የኢትዮጵያ ልማት ባንክንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችን እያጨናነቁ ነው፡፡ ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ለሽያጭ የቀረበውን የሚሌኒየም ቦንድ ለመግዛት የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች፣ ግለሰቦች፣ ማኅበራትና የተለያዩ የኅብረሰቡ ክፍሎች ወደ ባንኮች እየጎረፉ ነው፡፡

በመላ አገሪቱ ያሉ 350 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችና 32 የልማት ባንክ ቅርንጫፎች ይህንን ቦንድ በመሸጥ ሥራ ተጠምደው ሳምንቱን አሳልፈዋል፡፡ እስካሁን የተሸጠው የቦንድ መጠን ግን አልታወቀም፡፡የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቦንድ ሽያጭ መረጃውን ከእነዚህ ቅርንጫፎች በቀላሉ መሰብሰብ ከባድ ነው፡፡ ‹‹መረጃውን በየወሩ ለማጠናቀር ነበር የታሰበው፡፡ ግን ጥያቄው እየገፋ በመምጣቱ በቅርቡ መረጃውን አጠናቅረን ምን ያህል ቦንድ እንደተሸጠ ይፋ እናደርጋለን፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

እስካለፈው ዓርብ ምሽት ድረስ 23 የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የ12 ማሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል፡፡ የቦንዱ ዓይነት እንደ ግለሰቦቹ የሚለያይ ሲሆን፣ በወለድ፣ ያለወለድና በስጦታ ገንዘባቸውን እየሰጡ የሚገኙም አሉ፡፡

ከእነዚህ ነጋዴዎች መካከል የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ባለቤት አቶ ብዙአየሁ ታደለ 500 ሺሕ ብር፣ ያራ የተሰኘው የማዳበሪያ አቅራቢ ድርጅት በኢትዮጵያ ወኪል የሆነው የግሎባል ትረስት ወርዚ ባለቤት ዶ/ር ብሥራትና ቤተሰቦቻቸው አንድ ሚሊዮን ብር፣ የአልሳም ንግድ ሥራዎች ባለቤት አቶ ሳቢር አርጋው አንድ ሚሊዮን ብር፣ የአምባሳደር ልብስ ስፌስ ባለቤት አቶ ሰይድ መሐመድ 100 ሺሕ ብር በስጦታ አበርክተዋል፡፡

በተጨማሪም አራት ባለሀብቶች እያንዳንዳቸው 100 ሺሕ ብር የሚያወጣ ቦንድ ገዝተዋል፡፡ የአዲካ አስጎብኝ ድርጅት ባለቤት አቶ አዋድ መሐመድና የደርጅቱ ሠራተኞች 500,000 ሺሕ ብር ቦንድ ገዝተዋል፡፡ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሠራተኞችም አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ ከመግዛታቸውም በላይ፣ በሙያቸው አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ የናሽናል ኦይል ካምፓኒ (ኖክ) ሠራተኞች የሁለት ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸው ታውቋል፡፡

የግልና የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የቦንድ ግዢና መዋጮ ለማድረግ በውይይት ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቦንድ ግዢ ጥያቄ እየቀረበ ይገኛል፡፡ በርካታ የዳያስፖራው አባላት በቀጥታ፣ በቤተሰቦቻቸውና በወኪሎቻቸው አማካይነት ቦንድ ለመግዛት እየተንቀሳቀሱ መሆኑም እየተነገረ ነው

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close