የጥብቅና አገልግሎት ከሙያው አካላት ጋር ያለው ግንኙነት የወረደ መሆኑ ተነገረ

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የጥብቅና አገልግሎት አሠጣጥ ከዳኝነት አካሉ፣ ከሕግ ትምህርት ተቋማትና ጠበቃው ራሱ ከሙያ አጋሩ ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት በማናቸውም ሚዛን ቢለካ የወረደ መሆኑን ዶ/ር ዘውድነህ በየነ የተባሉ ጠበቃና የሕግ አማካሪ አስታወቁ፡፡

ዶ/ር ዘውድነህ ይህንን የገለጹት የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መጋቢት 29 ቀን 2003 ዓ.ም በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የጥብቅና ሥነ ምግባርን በሚመለከት ከጠበቆችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ የፓናል ውይይት ላይ ነው፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ በሆኑት አቶ አበበ አሳመረ፣ ‹‹የጠበቆች የሥነ ምግባር ችግሮች›› በሚል በቀረበው የመነሻ ጽሑፍ ላይ በተደረገ ውይይት፤ ዶ/ር ዘውድነህ በሰጡት አስተያየት፣ ጥብቅና የሙያ ዘርፍ ተብለው ከተለዩ የሙያ ዘርፎችና በተለዩ ሕጎች ከሚገዙ የሙያ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን፣ ኢትዮጵያም ዘርፉን የሚገዛ ሕግ ማውጣቷንና የሚቆጣጠረው መሥርያ ቤትም መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዘውድነህ ገለጻ፤ ከሕግ አወጣጥ፣ ከማስፈጸም፣ ሕጉንም በጠበቃው በኩል ከመተግበር አኳያ በተለምዶ በመሥራትና ሕጎቹም ዝም በማለት በተፈጠረ ክፍተት አላስፈላጊ የሆነ የፖለቲካ ትርጉም እየተሰጣቸው ነው፡፡ ሙያውን እንደ ሙያ ባለማየት በአገሪቱ ጠቅላላ የፍትሕ ሥርዓት ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥል ችግር ይታያል፡፡

የጥብቅና ሙያ በራሱ በኅብረት የመወያየት፣ የመነጋገር ውጤት የሚገለጽበት፣ ሥነ ምግባርን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ተክኖ በተግባር እንዲተረጎም የሚጠይቅ የሙያ ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዘውድነህ፣ ሙያው በትክክል ሳይተገበር ሲቀር በራሱ በባለሙው ቁጥጥር እንዲደረግበት የሚደረግና ብዙ አገሮች እየተገዙበት ያለ የተግባር ሙያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በዳኝነት አካሉና በጥብቅና አገልግሎት ሰጪው መካከል ያለውን ልዩነትና አለመግባባት ሕዝቡ የሚመለከትበት ሁኔታ የሚያሳዝን መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዘውድነህ፣ ዳኛው ጠበቃውን፣ ጠበቃው ዳኛውን ለሕዝቡ የሚያማበትን አስነዋሪ ነገር በመተው ወደ አዲስና ተግባብቶና ተባብሮ የሚሠራበት ምዕራፍ መሸጋገር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በብዙ አገሮች የጥብቅና አገልግሎት አሰጣጥን ለመግዢያነት የተለያዩ ማለትም የጠበቆች ማኅበርን በልዩ አዋጅ በማቋቋም ራሱን እንዲገዛ፣ ቁጥጥሩንም ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል የሚያቀርብበት ስልቶች መኖቸውን የጠቀሱት የሕግ አማካሪው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ተቆጣጣሪው አካል በውክልና እንዲሠራ በመደረጉ የጠነከረ የጥብቅና አሠራር ወይም ማኅበር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ ሁለት ጐራ ተፈጥሮ የኢትዮጵያ ጠበቆችና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በመባባል፣ በአንድ ዓይነት ሙያ ላይ ሁለት ማኅበራት መፈጠራቸው አግባብ አለመሆኑንና መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ጤናማ የሆነ የጥብቅና፣ የዳኝነት ውይይትና ግንኙነት መድረክ በሌለበት፣ ተቆጣጣሪውና የጥብቅና አገልግሎት ሰጪው አካል፣ መልካም ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ አንድ የጋራ የሆነና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት፣ ጥሩ የፍትሕ ሥርዓት ሊተገበርባት የምትችል ኢትዮጵያን ማየት እንደማይቻል ዶ/ር ዘውድነህ አስረድተዋል፡፡

‹‹80 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ ያሉት የጠበቆች ብዛት ሁለት ሺሕ መሙላታቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ጎረቤታችን ኬንያ ግን 30 ሺሕ ጠበቆች አሏት፤›› ያሉት ዶ/ር ዘውድነህ፤ እነዚህ እንኳን ተመካክረው ‹‹ለአገር ምን እንሥራ?›› ማለት ያልቻሉበት አገር ላይ መሆናችንን ተናግረዋል፡፡

ተከፋፍሎና ማኅበር አቋቁሞ ከሚንቀሳቀሰው ጠበቃ ሌላ በውጭ ሆኖ የሚታዘበው ብዙ በመሆኑ የሚሠራው በደል የበዛ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዘውድነህ፤ ችግሮቹን ለማስወገድና ያለውን ልዩነት ለማጥፋት አዋጁን መፈተሸ (አዋጅ ቁጥር 199/1992) ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ካልተቻለ የተጠያቂነትንና የአሠራር ነፃነትን በኢትዮጵያ ማምጣት እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡

ሌላው አቶ አበበ አስማረ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ ላይ ‹‹95 በመቶ የሚሆነው ጠበቃ ሕገወጥ ሥራ የሚሠራና ደላላ ነው፤›› በሚል ከፍትሕ ሚኒስቴር ተወካይ የቀረበው አስተያየት ሲሆን፣ ቅሬታን አስነስቷል፡፡

ተወካዩ አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት የቀረበው የዳሰሳ ጽሑፍ ጠበቃ ለሙያው ምን ማድረግ እንዳለበት አለመጥቀሱን በመጠቆም ሲሆን፣ ‹‹እኔ ጠበቆችን ጠበቆች ናቸው ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ 95 በመቶ የሚሆነው ጠበቃ ደላላ የሆነበት አገር ነው፤›› ካሉ በኋላ ለንግግራቸውም ምሳሌ ጠቅሰዋል፡፡

አንዳንድ ጠበቆች ፍርድ ቤት ይዘው የሔዱትን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ‹‹የሕግ መሠረት የለውም›› ብሎ ሲመልሳቸው፣ ሌላ ጠበቃ ፎርጅድ ሰነድ በማዘጋጀት ተመሳሳዩን ጉዳይ ይዞ በመቅረብ ተከራክሮ እንደሚያሸንፍ ተወካዩ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ተወካዩ እርግጠኛ ሆነው የገለጹት፣ ራሱን በመደበቅ ባለጉዳዩን እየመከረ እንዲከራከር የሚያደርግ ጠበቃ መኖሩን በመግለጽ፣ ‹‹ጠበቃው ራፖር ፀሐፊ ሆኗል›› ብለዋል፡፡ ራፖር ፀሐፊ ሆነው ያገለገሉና ከቀበሌ ልምድ አጽፈው ጠበቃ ሆነው የተገኙም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጠበቆች ሁላችንም አንድ ዓይነት ሥነ ምግባር ሊኖረን አይችልም፡፡ አክብረን የምንሠራ አለን፡፡ የሥነ ምግባርም ጉድለት ያለብንም አለን፡፡ ጠበቃ ችግር አለበት ማለት ያስኬዳል፤ ነገር ግን 95 ከመቶ ነው ብሎ በደፈናው መወንጀል ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ውንጀላ ነው፡፡ አግባብም አይደለም፡፡ አይጧ ከሌለች ጉድጓዱ ከየት መጣ? የሚለውን ብሂልም ልብ ይሏል፤›› በማለት የፍትሕ ሚኒስቴር ተወካዩ የሠሰጡትን አስተያየት የተቃወሙት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ስለሺ ቀጸላ ናቸው፡፡

ሌላው የፍትሕ ሚኒስቴር ተወካይና የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መረሳ ገብረ ዮሐንስ በሰጡት አስተያየት፤ የመሥሪያ ቤታቸው ባልደረባ 95 በመቶ በሚል ጠበቆችን የወቀሱበትን አስተያየት ‹‹የራሳቸው ጥናት ይሆናል እንጂ እንደ ፍትሕ ሚኒስቴር ግን የተጠና ነገር የለም፡፡ ጠበቆች ጠንካራና ደካማ ጎን ግን አላቸው፤›› በማለት፣ ‹‹ጠበቆችን በመክሰስና በማስቀጣት ለውጥ ይመጣል ብለን አናስብም፡፡ ጠበቆች ብዙውን ጊዜ የሚቀጡት በሥነ ምግባር ጉድለት ችግር በመሆኑ በእሱ ላይ ተባብረን ልንሠራበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አበበ አሳመረ፣ ‹‹የጠበቆች የሥነ ምግባር ችግሮች›› በሚል ባዘጋጁት ባለ 12 ገጽ የዳሰሳ ጽሑፍ ዙርያ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ሊካተትበት ይገባ እንደነበር ተወካዮቹ ጠቁመው፣ ጥናቱ ሙሉ አለመሆኑን በመግለጽ ጠበቆች ለሥነ ምግባር ተገዢ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በትብብር የመሥራት ጉዳይ ገና ብዙ እንደሚያነጋግር፣ አንዱ አንዱን የመውቀስ እንጂ ‹‹ችግሩ ምንድነው? እንዴትስ እንፍታው?›› የሚል ጥያቄ እንደማይነሳ የገሉጹት አቶ አበበ፣ ‹‹በዳሰሳ ጽሑፋቸው ጠበቃ ችግር የለበትም›› አለማለታቸውን ጠቁመው፣ ከተሰማራበት ዲሲፕሊን ውጭ ከሄደ በወንጀለኛ ሕጉ ሊጠየቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዓቃቤ ሕግን በወንጀል ጉዳይ ተከራክሮ ማሸነፍ አይቻልም፤›› በሚል ‹‹ጠበቆች የወንጀል ሕግ አንይዝም›› እያሉ መሆኑንም አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽኑ ያዘጋጀውን የአንድ ቀን ፓናል ውይይት የሥነ ምግባር አውታሮች አስተባባሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበሩትና በቅርቡ ጡረታ የወጡት አቶ ኃይሉ በርሄ መርተውታል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close