የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት በእስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው .

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የላዕላይ ምክር ቤት አባልና ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታዴዎስ ቦጋለና ሌላው የድርጅቱ አባል አቶ ግርማ ነጋ፣ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመታት ከአራት ወራት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ስድስተኛ ወንጀል ችሎት ትናንት ፈረደባቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በፍርድ ቤትና በምርጫ ቦርድ እግድ የተጣለበትን የመኢአድ ማኅተም መጠቀማቸውን በመጥቀስ የመሠረባቸው ክስ፣ በሰዎችና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ ነው፡፡

ዶ/ር ታዴዎስ በሁለት ዓመት ከአራት ወራት ጽኑ እስራት፣ አቶ ግርማ ደግሞ በአንድ ዓመት ከስምንት ወራት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በማስተላለፉ ሁለቱም ግለሰቦች ወደ ማረሚያ ቤት ተልከዋል፡፡

ዶ/ር ታዴዎስ በፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ብጥብጥ ምክንያት ክስ ተመስርቶባቸውና በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው በምህረት ከተለቀቁት የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሰዎች አንዱ ስለነበሩ፤ በነበረባቸው የወንጀል ሪከርድ ምክንያት ቅጣቱን ሊያከብድባቸው ችሏል፡፡ አቶ ግርማ ቀደም ባሉት ጊዜያት ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ባለመፈጸማቸው ቅጣቱ ቀሎ ሊወሰን ችሏል፡፡

መኢአድ ጠቅላላ ጉባዔውን በታኅሣሥ 2003 ዓ.ም. በማድረግ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልን በፕሬዚዳንትነት መምረጡ ይታወሳል፡፡ ‹‹ጉባዔው ሥልጣን ሰጥቶኛል›› የሚሉት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል አቶ ያዕቆብ ልኬን በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት በመሾማቸው፣ ዶ/ር ታዴዎስና አሥር የሚሆኑ የመኢአድ ከፍተኛ አመራሮች ቅሬታ እንዳነሱ እነ ኢንጂነር ኃይሉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ጉባዔው ሥልጣኑን እስከሰጠኝና መተዳደሪያ ደንቡ እስከፈቀደልኝ ድረስ ይመጥናል፣ ሥራውን በደንብ ያውቃልና ብቃት አለው የምለውን የድርጅቱን አባል መሾም እችላለሁም፤›› ይላሉ ኢንጂነር ኃይሉ፡፡

እነ ዶ/ር ታዴዎስ በበኩላቸው፣ ጠቅላላ ጉባዔው ሥልጣኑን እንዳልሰጣቸውና የድርጅቱ መተዳደሪያ ሕገ ደንብ እንደማይፈቅድ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ እነ ኢንጂነር ኃይሉ ድርጅቱ ቀደም ብሎ ይጠቀምበት የነበረውን ማኅተም እነ ዶ/ር ታዴዎስ እንደከለከሏቸው በመግለጽ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለፖሊስ በማሳወቅ አዲስ ማኅተም ያስቀርጻሉ፡፡ ለድርጅቱ አባላት ታኅሣሥ 15 ቀን 2003 ዓ.ም. በድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ግቢና በር ላይ ማኅተሙ መቀየሩን ያስታውቃሉ፡፡

ከክልል ለጠቅላላ ጉባዔ ለመጡ የድርጅቱ አባላት የትራንስፖርት ገንዘብ ያስፈልግ ስለነበር በቀድሞው ማኅተም ተጠቅመው ገንዘብ ማውጣታቸውን፣ የተለያዩ ደብዳቤዎችን በመጻፍ አሮጌውን ማኅተም ተጠቅመዋል በሚል እነ ኢንጂነር ኃይሉ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ መሠረት፣ መደበኛ ክስ የመሠረተው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እነ ዶ/ር ታዴዎስ ድርጊቱን መፈጸማቸውን በሰዎች ምስክሮችና በሰነድ ማስረጃ በማረጋገጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን አስተላልፎባቸዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close