የአንድነት ፓርቲን ንብረት ሰርቆ የተያዘው ግለሰብ በዘጠኝ ዓመታት እስራት ተቀጣ .

የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲን ንብረት ሰርቆ ሊሰወር ሲል እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ የተመሰረተበት ግለሰብ ሚያዚያ 3 ቀን 2003 ዓ.ም. በዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡ የሃምሳ አለቃ ነጋሽ ሀብታሙ የተባለው ግለሰብ ላይ የቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈው የከፍተኛው ፍርድ ቤት የውንብድና ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ግለሰቡ ቅጣቱን ጨርሶ ሲወጣ ለሁለት ዓመታት በመምረጥ፣ በመመረጥና በሌሎችም መብቶቹ ላይ እግድ ተጥሎበታል፡፡

ግለሰቡ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በጥበቃ ሠራተኛነት ተቀጥሮ ለዘጠኝ ወራት ያህል ሲሠራ በቆየባቸው ጊዜያት፣ የድርጅቱ ንብረት የት እንደሚቀመጥና መውጫ መግቢያውን ካጠና በኋላ ካልተያዘው ግብረ አበሩ ጋር በመሆን ታህሳስ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ሌሊት ዝርፊያውን መፈጸሙን ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃ አረጋግጦበታል፡፡

የሃምሳ አለቃ ነጋሽ ከግብረ አበሩ ጋር በመሆን ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ላይ በሁለት ሻንጣ የሞሉትን የድርጅቱን ዕቃ ተሸክመው ወደ ክፍለ አገር የሚሄዱ መንገደኞች በመምሰል በመጓዝ ላይ እያሉ፣ ካዛንቺስ ዮርዳኖስ ሆቴል አካባቢ ሲደርሱ አካባቢውን ይጠብቁ የነበሩ ፖሊሶች ተጠራጥረው ንብረታቸው ስለመሆኑ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ይጠይቋቸዋል፡፡

ያልተያዘው የሃምሳ አለቃው ግብረ አበር አንደኛውን ፖሊስ መትቶ በመጣል ሲያመልጥ ሃምሳ አለቃ ነጋሽ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡

ወንጀለኞቹ ከአንድነት ፓርቲ የዘረፉት ንብረት በፓርቲው ሰዎች 170 ሺሕ ብር የተገመተ ቢሆንም፣ ፖሊስ በሰጠው ግምት የ162 ሺሕ ብር ንብረት ነው፡፡

ወንጀለኞቹ በሻንጣ ይዘው ሊሰወሩ የነበሩት አምስት ኮምፒውተሮች፣ ሁለት ስካነሮች፣ አንድ ቪዲዮ ካሜራ፣ ሁለት ፕሪንተሮችና ሁለት ፕሮጀክተሮች ዋናዎቹ መሆናቸውን፣ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል አቶ አንዱዓለም አራጌ ገልጸዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close