የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን እጎበኛለሁ አሉ

 

የግብፅ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሳም ሻሪፍ ኢትዮጵያን በቅርቡ እንደሚጎበኙና አዲስ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚመሠርቱ በግብፅ ለኢትዮጵያ አምባሳደር መሐመድ ድሪር ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት በተለይ በዓባይ ጉዳይ ለመደራደር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግብፅ ውስጥ የተከሰተውን ሕዝባዊ አመፅ ተከትሎ የሙባረክ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሳም ሻሪፍ የካቲት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በግብፅ ከፍተኛ ወታደራዊ ምክር ቤት ተሹመዋል፡፡ የ58 ዓመቱ ኢሳም እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2005 የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ አዲስ አበባ በመምጣት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንደሚፈልጉ ቢገልጹም፣ የጉብኝታቸው ጊዜ መቼ እንደሚሆን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ 5,250 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን የታላቁ ሚሌኒየም ግድብን በይፋ ካስታወቀች በኋላ ግብፅ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጫናዎች ለመፍጠር እየጣረች የቆየች ቢሆንም፣ አሁን ከዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር በውኃው ክፍፍል ላይ ለመደራደር እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ የግብፁ የውኃ ሀብት ሚኒስትር ሑሴን አል አትፋይ እንደገለጹት፣ ግብፅ ከላይኛው የተፋሰሱ አገሮች ጋር ያላትን የውኃ ክፍፍል ከግጭት ይልቅ በድርድር መፍታት ብቸኛው አማራጯ እየሆነ ነው፡፡

ስምምነቱ የሁሉም የተፋሰሱ አገሮችን በእኩል በጋራ ተጠቃሚ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ዓለም አቀፋዊ ድርድር የግብፅ የመጨረሻ አማራጭ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ግብፅ የዓባይን ወንዝ የአንበሳ ድርሻ በቅኝ ግዛት ጊዜ በተፈረመ ውል ስትጠቀም የቆየች ቢሆንም፣ በተፋሰሱ አገሮች መካከል የተፈረመው አዲሱ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ውኃውን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አገሮቹ እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡ በስድስቱ የተፋሰሱ አገሮች መካከል የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ ማን ምን ያህል ውኃ ያግኝ የሚለውን ስለማያካትት የግብፅ ታሪካዊ የውኃ ኮታዋን አይነካም ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የትብብር ማዕቀፉ ዋነኛ ዓላማ ማን ምን ያህል ውኃ ያግኝ የሚለውን ለመወሰንና ፍትሐዊ የውኃ  ክፍፍል በተፋሰሱ አገሮች መካከል ለማድረግ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የግብፅ ከፍተኛ ወታደራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሑሴን ታንታዊ ኢትዮጵያና ግብፅ በዓባይ ወንዝ ምክንያት ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነታቸው እንደማይበላሽ፣ በቅርቡ የሹመት ደብዳቤያቸውን ላቀረቡት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መሐመድ ድሪር መግለጻቸው ታውቋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close