በኢትዮጵያ ላይ የተለሳለሰው የስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት

ዲፓርትመንት ሪፖርት
Wednesday, 13 April 2011 06:38
     በስፋት ‹‹ስቴት ዲፓርትመንት›› በመባል የሚታወቀው የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በየዓመቱ ይፋ ያደርጋል፡፡ ይህ የአሜሪካ መንግሥት የአገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝን ጨምሮ የፖለቲካና የሲቪል ነፃነትን በስፋት የሚገመግምበት ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ ላይ በተከታታይ ባወጣቸው መረጃዎች ከመንግሥት ጋር ንትርክ ሲፈጥርበት ቆይቷል፡፡ ለአንዳንድ አገሮች ግንኙነት መበላሸትም እንደ መንስዔ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ስቴት ዲፓርትመንቱ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ ይፋ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱ ከቀደሙት ጋር ሲነፃፀር መለሳለስ የታየበት ቢሆንም፣ አሁንም የመንግሥት ምላሽ መልካም አይደለም፡፡ “የቀደሙት ሪፖርቶች ቅጥያ ነው” በሚል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ እንደ ሌሎቹ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ እጅግ የጨከነ ባይሆንም፣ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለይ በተቃዋሚ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ሕገወጥ ግድያዎች፣ ማሰቃየት፣ ግርፋትና እጅግ የከፋ የእስረኞ አያያዝ መፈጸማቸውን ያመላክታል፡፡ በዜጎች ላይ የግለሰብ ነፃነትን የሚጋፉ የተለያዩ ድርጊቶች መፈጸም፣ የተቃዋሚዎች አባላትና ደጋፊዎች ናቸው ተብሎ የታመነባቸውን ግለሰቦች ያለአንዳች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ማሰር፣ ለፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ቤት እንዲማቅቁ ማድረግ፣ ጋዜጠኞችን ማሰርና ድብደባን ጨምሮ በፕሬስና በመናገር ነፃነት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር፣ በምርጫ ወቅት ገዥው ፓርቲ በተቃዋሚዎች ላይ ፈጸማቸው ያላቸውን ወከባዎች፣ ዛቻዎችና ጥሰቶችን አስፍሯል፡፡ እንዲሁም ደግሞ፣ ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚሠሩ ግለሰቦች ላይ ድብደባና ወከባ ተፈጽሟል ያለ ሲሆን፤ በፖሊስ፣ ባለሥልጣናትና በዳኞች ተፈጽሟል ያለውን የሙስና ቅሌቶችም ስቴት ዲፓርትመንቱ በሪፖርቱ አካቷል፡፡ አግባብ ያለው የሕግ ሒደት እንደማይከናወንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች በተለይም ማዕከላዊ ተብሎ በሚታወቀው የፖለቲካ እስረኞች ለተለያዩ ግርፋትና ሰቆቃዎች መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የዓማፂ ቡድኖች አባላት የሆኑ የፖለቲካ እስረኞች በምህረት መፈታታቸውን ያደነቀ ቢሆንም፣ በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው ብቻ ለእስር ተዳርገው በእስር ቤት እየማቀቁ አሉ ያላቸውን ሌሎችንም የመረጃ ምንጮች ዋቢ በማድረግ ከ200 እስከ 300 ዜጎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ያስረዳል፡፡

የፕሬስ ነፃነትን በሚመለከት የሪፖርቱ ክፍል የአውራ አምባ ጋዜጣ የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ጋዜጦኛ ውብሸት ታዬ ላይ የደረሰው ጫና፣ ቀደም ሲል በሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊና በጋዜጠኛ ተሾመ ንቁ የተፈጸመው ጥቃትና እስራት፣ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መዘጋትና በጋዜጠኛ አብርሃም በጊዜው ላይ የደረሰ አካላዊ ጥቃት፣ በሌሎች አዘጋጆች ላይ የደረሱ ማስፈራራቶች፣ በቪኦኤ ጋዜጠኞች ላይ ደረሰ ያለውን ወከባና የፍቃድ ክልከላን ጨምሮ ቀደም ሲል የፀደቀው የፕሬስ ሕግ በጋዜጠኞች ላይ የጣለው ራስን በራስ ሳንሱር የሚያስደርግ ጫናን ተመልክቷል፡፡

ሪፖርቱ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመግባት፣ የሥራ ዕድገት ለማግኘት፣ ሥራ ቅጥርና ለሌሎች የመንግሥት ጥቅማ ጥቅሞች የኢሕአዴግ አባልነት ‹‹ካርድ›› ያስፈልጋልም ብሏል፡፡ ዜጎች በነፃነት የመደራጀትና ሠልፍ የመውጣት መብቶች በተለያዩ መንገዶች መከልከላቸውን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ የአረና ትግራይ ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረው የአቶ አረጋዊ ገብረ ዮሐንስና ሌላው የተቃዋሚ አባል የነበረው የአቶ ቢያንሳ ዳባ ግድያዎችም በምርጫ ወቅት ተፈጸሙ ካላቸው የፖለቲካ ጫናዎች መካከል ተካተዋል፡፡ ከትግራይ እስከ ኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ የመድረክ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ሪፖርቱ አትቷል፡፡

የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሲቪክ ድርጅቶች በወጣው አዲሱ የሲቪል ማኅበራት ሕግ ምክንያት ተግባራቸውን በአግባቡ ማከናወን አለመቻላቸውን የሚገልጸው ስቴት ዲፓርትመንቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የሚሰጡዋቸውን ትችቶች ክፉኛ የሚጠላ፣ የሚነቅፍና ፍፁም የማይቀበል ብሎታል፡፡ ስቴት ዲፓርትመንትን፣ ሂውማን ራይትስ ዎችንና ሌሎችን ለመንቀፍ በመንግሥት ሚድያ የተሠሩ ዶክመንተሪ ፊልሞችንም የዚሁ ማሳያ አድርጎ አቅርቦታል፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሪፖርቱን “የቀደሙት ግልባጭ” ያሉት ሲሆን፣ በስሚ ስሚ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ብዙም የሚያስጨንቅ አይደለም በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከቀደሙት በምንም ነገር የማይለይ ያሉት አምባሳደር ዲና፣ በቅርቡ ሰፋ ያለ ምላሽ ለመስጠት መንግሥት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ግን የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ይላሉ፡፡

ስቴት ዲፓርትመንቱ በ56 ገጽ ሪፖርቱ በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት በኢትዮጵያ ተፈጸሙ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የሲቪል፣ የፖለቲካና የእስር ቤት ሁኔታዎችን ያካተተ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ቀደም ባሉ ዓመታት ሪፖርቱ ባወጣቸው መረጃዎች ላይም ትኩረት አድርጓል፡፡

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በተካሄደው 4ኛ ዙር ምርጫ ባልተለመደ ሁኔታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን 99 በመቶ የተቆጣጠረው ገዢው ፓርቲ በተቃዋሚዎች፣ በሂውማን ራይትስ ዎችና በሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በእጅጉ መነቀፉ ይታወሳል፡፡ ስቴት ዲፓርትመንቱ በዚህ ሪፖርቱ ያካተታቸው ነገሮች በአብዛኛው እነዚህ ወገኖች አሉ፣ ሪፖርት አድርገዋልና አሳውቀውም ነበር ከሚል ሁለተኛ የመረጃ ምንጭ በብዛት ከመጠቀም ውጪ ራሱ የሠራው የመስክ ሥራ መኖሩን የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡

ስቴት ዲፓርትመንቱ ቀደም ባሉት ሪፖርቶቹ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2008 እና በ2009 ያወጣቸው መረጃዎች በመንግሥት እጅግ የተነቀፉ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ በማስረጃ ያልተደገፉና በስሚ ስሚ የተመሠረቱ መኖራቸውን አምባሳደር ዲና ያስረዳሉ፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ ከሚያወጡዋቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሪፖርት በማውጣት የሚታወቀው ስቴት ዲፓርትመንቱ፤ በተለይ ደግሞ ዓማፂ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱባቸው እንደ ኦጋዴንና ኦሮሚያ በመሳሰሉ አካባቢዎች የኦብነግና ኦነግ አባላት ተብለው የሚታሠሩ ዜጎች፣ የሚደርስባቸው ግድያ፣ የፖለቲካ ጫና፣ ግርፋትና ማሰቃየት የግለሰቦች ስም እየጠቀሰ እስከማውጣት የደረሰበት ሁኔታ ነበር፡፡ መንግሥትም በበኩሉ ሙሉ በሙሉ ውሸት መሆኑን በመጠቆም፣ ድርጅቶቹ የራሳቸው ሌላ ድብቅ አጀንዳ እንደነበራቸውም ይገልጻል፡፡

ስቴት ዲፓርትመንቱ በአሁኑ ሪፖርቱም ቢሆን በአብዛኛው ብዙ ሽፋን የሰጠው ኦብነግ በሚንቀሳቀስበት የኦጋዴን አካባቢ ተፈጸሙ ባላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ውንጀላዎች ሲሆን፣ በተቃዋሚዎች ላይ ደረሱ የተባሉት ወከባዎች፣ ግድያዎች፣ እስራቶችና ሌሎችንም ጠቃቅሷል፡፡

ምርጫ 97 እና አወዛጋቢው ውጤቱን ተከትሎ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ቀጥለው በተካሄዱ ምርጫዎች በተለይ ደግሞ በግንቦት 2002 በተካሄደው አራተኛ ዙር አገራዊ ምርጫ ላይ ያሳደረውን የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ ስቴት ዲፓርትመንቱ ለመተንተን ሞክሯል፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት በአብዛኛው በብሔር ደረጃ እየሆነ መምጣቱን፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ እጅግ በተበታተነና በተከፋፈለ መንገድ መቀጠላቸውና 97ን ተከትሎ የፀደቁ አንዳንድ አዋጆች በቅድመ ምርጫ 2002 ምቹና ነፃ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዳይኖር ማድረጋቸውን፣ ኢሕአዴግም ከእነዚህ ሁኔታዎች ትልቅ የፖለቲካ ጠቀሜታ ማግኘቱን ያትታል፤ የምርጫ ውጤቱን ለማሳያነት በመጠቀም፡፡

ባለፈው ዓመት ባወጣቸው በተለይ ሁለት ተከታታይ ሪፖርቶች በኢትዮጵያ መንግሥት ክፉኛ የተወቀሰው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ተገደሉና ታሰሩ ያላቸውን ሰዎችም በመንግሥት ሚድያ በማነጋገር ጭምር ‹‹ውሸት ላይ የተመሠረተ›› መሆኑንም በማሳየት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህ ሪፖርቶችን የሚያብጠለጥላቸው የኒዮ ሊበራሊዝም አክራሪዎችና አራማጆች በማለት ሲሆን፣ መረጃ የሚሰበስቡበትን መንገድም ይተቻል፤ ሳይንሳዊ አይደለም በማለት፡፡

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ቢቢሲ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ዕርዳታን ለጦር መሣሪያ ግዢ አውሎታል›› የሚል ሪፖርቱ  በሰር ቦብ ጌልድ ኦፍና በሌሎችም የተሰነዘረበት ትችትን ተከትሎ፣ ሚዲያው የተሳሳተ ዘገባ ማስተላለፉን አምኖ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ስቴት ዲፓርትመንትንና ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በውሸት ላይ የተመሠረቱ መረጃ የሚነዙ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተመሳሳይ አቋም እንዲወስዱ መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም፣ ከምርጫ 2002 ትንሽ ቀደም ብሎ ‹‹ተፅዕኖ የማድረጊያ አንድ መቶ መንገዶች፤ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ጥሰት በኢትዮጵያ›› በሚል ሪፖርቱ ምርጫው ያለቀለት መሆኑን፣ ተቃዋሚዎች በምርጫው ዝግጅት የሚንቀሳቀሱበት የፖለቲካ ምህዳር እጅግ መጥበቡን የሚያሳይ ባለ 59 የመስክ ሥራ በሪፖርት መልክ አቅርቦ የነበረው ሂውማን ራይትስ ዎች ብዙም ሳይቆይ፣ ‹‹ልማት ዘእንበለ ነፃነት›› በሚለው ቀጣይ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕርዳታን ለፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ እንደ መሣሪያ እየተጠቀመበት መሆኑን ያቀረበው ሪፖርት በመንግሥት በቀላሉ የታለፈ አልነበረም፡፡ ቡድኑ ይህንን አካሄድ ኢሕአዴግ 99 በመቶ ያሸነፈበት ምርጫ 2002 ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅእኖም ለማሳየት የሞከረበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሂውማን ራይትስ ዎች በዚሁ ዘገባው ባቀረባቸው ትንታኔዎች ብዙዎች በተለይ ደግሞ እንደ መድረክ የመሳሰሉ የተቃዋሚዎች ስብስብም ያደነቁት ሪፖርት የነበረ ቢሆንም፣ በለጋሽ አገሮች ግን ድጋፍ የተቸረው አልነበረም፡፡ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ምዕራባውያን አገሮች በተለይ ምርጫ 2002ን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዙን እንዲያሻሽል የሚያደርጉት ጫና እየቀነሰ መምጣታቸው የሚናገሩ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር፣ የአሁኑ የስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርትም የዚሁ የአስተሳሰብ ለውጥ አካል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የስቴት ዲፓርትመንቱ የወቅቱ ሪፖርት የበፊቶቹን ሪፖርቶች መረጃ ያካተተ ቢሆንም፣ በአቀራረቡም ሆነ በይዘቱ መለሳለስ ታይቶበታል፡፡ ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲናም ይህንን አልካዱም፡፡ ሪፖርቱ በውስጡ አካተታቸው ያሉዋቸው አንዳንድ ድምዳሜዎች ግን አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት የማይቀበላቸው መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ “ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በሌሎች ዋና ዋና ጉዳዮች አብረን መሥራታችንን እንቀጥላለን፤” ብለዋል፡፡

‹‹ዲሞክራሲ በሕዝቦች በራስ ተነሳሽነት ይሰፍናል›› የሚል አቋም ያላቸው ባራክ ኦባማ ፕሬዚዳንትነቱን ከቡሽ አስተዳደር ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ታሳድረዋለች ተብሎ ተገምቶ የነበረው ጫና እስከዚህም ሲሆን፣ እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገሮችም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማስፈን የነበራቸው ፍላጎት እየቀነሰ መምጣቱ ወይም ደግሞ ተስፋ መቁረጣቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ስቴት ዲፓርትመንቱ በዚሁ ስድስት ክፍል ያለው ሪፖርቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝን የፕሬስ ነፃነትን ጨምሮ የሲቪል መብቶች መከበርን ዜጎች መንግሥታቸውን በሰላማዊ መንገድ መቀየርን ጨምሮ የፖለቲካ መብቶች መከበርን፣ የሥልጣን መባለግንና የመንግሥት ግልጽነትን፣ መንግሥት ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች የሚሰጠውን ምላሽ፣ ማኅበራዊ ማግለልና ሕገወጥ የዜጎች ዝውውርን በተመለከተ አገኘሁት ያለውን መረጃ አካቷል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close