ትናንት ማለዳ በደረሰ የመኪና አደጋ 13 ሰዎች ሞቱ

Wednesday, 13 April 2011 06:17
ከአዲስ አበባ 60 ሰዎችን አሳፍሮ ትናንት ወደ መቀሌ ይጓዝ የነበረ የዋልያ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ ይመጣ ከነበረ ቅጥቅጥ አይሱዙ ጋር ተጋጭቶ፣ 13 ሰዎች ሲሞቱ በአሥር ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ትናንት ከጧቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ አውቶቡሱ በኦሮሚያ ክልል በሰንዳፋና በአሌልቱ መካከል ከበኬ ሦስት ኪሎ ሜትር አለፍ ብሎ በሚገኘው ልዩ ስሙ ጮሌ ገበሬ ማኅበር አደጋው በመድረሱ 13 ሰዎች ወዲያውኑ ሞተዋል፡፡ አሥር ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ ቀሪዎቹ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው ጊዜያዊ የሕክምና ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ወደሚሄዱበት ክልል መሸኘታቸውን የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል፡፡የሰሌዳ ቁጥሩ 3-0346256 አንደኛ ደረጃ የሆነው ዋልያ አገር አቋራጭ አውቶብስ ሙሉ መንገደኞችን አሳፍሮ 53 ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዘ፣ ጮሌ ገበሬ ማኅበር ሲደርስ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ ይመጣ ከነበረውና የሰሌዳ ቁጥሩ 3-0320063 ኦሮ ሁለተኛ ደረጃ (30 ሰዎች አሳፍሮ ነበር) ቅጥቅጥ አይሱዙ ጋር ነው የተጋጨው፡፡ አውቶብሱ አንድ መንገድ ሊያቋርጥ የነበረን እረኛ አድናለሁ ብሎ ወደ ጐን ሲወጣ በመጋጨታቸው አደጋው መድረሱን፣ የአሌልቱ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የመረጃ ሠራተኛ ረዳት ሳጅን መሐመድ ሁሴን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ረዳት ሳጅን መሐመድ ገለጻ፣ አደጋው የደረሰው ትናንትና ጧት አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ነው፡፡ የሁለቱም ተሽከርካሪዎች ሹፌሮች ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የሟቾች አስከሬኖችና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ተልከዋል፡፡

የደረሰውን አደጋ በቦታው ተገኝተው የተመለከቱት የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቅጥቅጡ አይሱዙ ውስጥ የነበሩት ተሳፋሪዎች ሙሉ በሙሉ ሳይሞቱ አልቀሩም፡፡ በዋልያ አውቶብስ ውስጥ የነበሩት ደግሞ ሾፌሩን ጨምሮ እስከ አምስት የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል የሚል ግምት አላቸው፡፡ የዓይን እማኞች ይህንን ያህል የሚሆኑት ሳይሞቱ እንዳልቀሩ በጥርጣሬ የተናገሩት ምናልባት አንዳንዶቹ በድንጋጤ ራሳቸውን ስተው ስለነበር ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን የትራፊክ አደጋ ቁጥጥርና ክትትል መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሳጅን አሰፋ መዝገቡን ስለደረሰው አደጋ ጠይቀናቸው፣ በአደጋው አራት ሰዎች ብቻ መሞታቸውን እንጂ ሌላ መረጃ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close