በዓባይ ላይ ጥናት ያካሂድ የነበረ ሔሊኮፕተር ተከሰከሰ

በዓባይ ወንዝ ላይ ሁለት ግድቦችን ለመገንባት የሚያስችል ጥናት በማካሄድ ላይ የነበረ አነስተኛ ሔሊኮፕተር ባለፈው ሰኞ ወድቆ ተከሰከሰ፡፡ሔሊኮፕተሩ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ቆንጮ አካባቢ ተነስቶ መንድያና ቤኮ አቦ በተባሉት ቦታዎች ላይ ለሚካሄዱ ሁለት አዳዲስ ግድቦች ጥናቶችን ሲያካሂድ፣ ድንገት ዓባይ ላይከተወጠረ ገመድ ጋር በደረሰ ግጭት ተከስክሶ ዓባይ ወንዝ ውስጥ ገብቷል፡፡

አብራሪውን ጨምሮ ጥናቱን የሚያካሂዱ አምስት ባለሙያዎች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በዋና ከውኃው ውስጥ መውጣታቸውን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው  ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሔሊኮፕተሩ ለዚህ ጥናትና ለሌሎች ፕሮጀክቶች በኪራይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ነበር፡፡ ሔሊኮፕተሩ አጠቃላይ ዋጋው ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፣ በቀን 1,500 ዶላር እየተከራየ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ንብረትነቱ የአንድ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ሔሊኮፕተሩ የሰኞ ጠዋቱን ሥራ አጠናቆ ከሰዓት ላይ ሥራውን በማከናወን ላይ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ዓባይን ለመሻገር ከወጠሩት ጠንካራ ገመድ ጋር ተጋጭቶ ወድቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ከጀመረው ከታላቁ ሚሌኒየም የኃይል ማመንጫ ግድብ በተጨማሪ ሁለት የኃይል ማመንጫ ግድቦችን በዓባይ ወንዝ ላይ የመገንባት ዕቅድ አለው፡፡

የሁለቱ ግድቦችን የአዋጭነት ጥናት ስምንት የአገር ውስጥና የውጭ አማካሪ ድርጅቶች እንዲያከናውኑ ከአንድ ዓመት በፊት ሥራውን ሰጥቷቸዋል፡፡ ሥራውን የተረከቡት ሁለቱ የአገር ውስጥ አማካሪ ድርጅቶች ትሮፒካል ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስና ሸበሌ ኮንሰልት ናቸው፡፡

የውጮቹ ደግሞ የኖርዌይ ኩባንያዎች የሆኑት ኖርፕላን ኮነሰልትና ኖር ኮንሰልት፣ እንዲሁም የእንግሊዝ ኩባንያ የሆነው ስኮት ዊልሰን ይገኙበታል፡፡ የመንድያ ግድብ 200 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ በአጠቃላይ 2,000 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሚገኘውም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ነው፡፡

የቤኮ አቦ ግድብ ደግሞ 285 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ 2,100 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ግድቡ ይገነባል ተብሎ የታሰበው በአማራ ክልል ጎጃምና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ አዋሳኝ በሆነው ቤኮ አቦ አካባቢ ነው፡፡

ሁለቱ ግድቦች በአጠቃላይ ከሚሌኒየሙ ግድብ በ1,150 ሜጋ ዋት አንሰው 4,100 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጩ ተገምቷል፡፡ በአገሪቱ ቀጣዮቹ ትላልቅ ግድቦች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለጥናቱ የሚሆነውን ገንዘብ የኖርዌይ መንግሥት ለኢትዮጵያ በዕርዳታ የሰጠ ሲሆን፣ ለጥናቱም 290 ሚሊዮን ብር ወጭ ይሆናል፡፡ ኩባንያዎቹ በ27 ወራት ጊዜ ውስጥ ጥናታቸውን ያጠናቅቃሉ ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close