የዋጋ ግሽበቱ 25 በመቶ ደርሷል

በነጠላ አሀዝ ደረጃ ወርዶ በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት በበጀት ዓመቱ መባቻ ላይ የተደረገውን የምንዛሪ ለውጥ ተከትሎ የጀመረውን የሽቅብ ጉዞ በመቀጠል፣ ባለፈው መጋቢት ወር 25 በመቶ መድረሱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ይፋ አደረገ፡፡ እ.ኤ.አ በ2008/09 ደርሶበት ከነበረው 38 በመቶ እየቀነሰ የመጣው የዋጋ ግሽበት እ.ኤ.አ በ2009/10 ወደ 29 በመቶ መውረዱ ሲገለጽ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተገልጿል፡፡ በየካቲት ወር 16.5 በመቶ የነበረው ይህ ግሽበት አሁን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ 25 በመቶ ማደጉን የኤጀንሲው ሪፖርት ያሳያል፡፡

ለግሽበቱ መጨመር እንደ ዋነኛ ምክንያት የተጠቀሰው የምግብ ዋጋ ማሻቀብ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2008/09 ላይም የምግብና የነዳጅ ዋጋ በዋነኝነት ለግሽበቱ መንስዔ መሆናቸውን መግለጹ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ዋጋም ቢሆን ከፍተኛ ለውጥ ካሳዩ ዋጋዎች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ ኤጀንሲው የዋጋ ግሽበትን ለመገመት የሚጠቀምበት የሸማቾች የዋጋ ማሳያ (ኮንሲውመር ፕራይስ ኢንዴክስ) እንደሚያሳየው ከሆነ፣ የትራንስፖርትና መገናኛ ዋጋ 37.6 በመቶ ማሻቀብ ሲያሳይ፣ የቤት ኪራይ፣ የግንባታ ዋጋ፣ የነዳጅና የውኃ ዋጋዎችም እንዲሁ 23 በመቶ ግሽበት ማሳየታቸውን ተመልክቷል፡፡

በተለይ በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ በአገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋም አብሮ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ነዳጅ ከትራንስፖርት ዋጋና ከማብሰያነት በተጨማሪ ግብዓት በመሆኑ፣ በሌሎች ዘርፎች ላይም ሳይቀር ግሽበትን ሊያባብስ እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ለሪፖርተር እንደለገጹት፣ የነዳጅ ዋጋ መዘዝ ቀላል አይደለም፡፡ በእያንዳንዱ ከውጭ በሚገባ ሸቀጥ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደሚኖረውና ይህም በአገር ውስጥ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳየ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ዘመዴነህ ይህ የአጭር ጊዜ ችግር ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ከውጪ የምናስገባውን ምርት በአገር ውስጥ መተካት ስንጀምር እነዚህ ችግሮች ይቀረፋሉ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል ግን ሰሞኑን የባንኮች የብድር ገደብ ከመለቀቁ ጋርና በመጪው የአምስት ዓመት ዕቅድ ላይ መንግሥት በብዛት ኢንቨስት የሚያደርግበት ከመሆኑ አንጻር፣ የምግብ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ካልቻለ ኢኮኖሚው የግሽበት አደጋ ውስጥ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close