ደን ምንጠራው፣ ታላቁ ግድብና መሬት ወረራው

ባህር ዳር ከተማ ከመደረሱ በፊት ከእንጅባራ ከተማ በስተግራ 100 ኪሎ ሜትር ላይ የቤኒሻንጉል ክልል ትልቁ ዞን የሆነው መተከል ይገኛል፡፡ ለዘመናት ተረስቶ የቆየው ይህ ዞን አሁን ሁለት ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡የመጀመርያው በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የሚሌኒየም ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ለኢንቨስተሮች የተሰጡት ሰፋፊ መሬቶች የሚታረሱበት ፕሮጀክት ነው፡፡

የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያውያን መነቃቃትን በመፍጠር የቦንድ ሽያጩ እየተፋፋመ ይገኛል፡፡ የግብርና ልማቱ ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚለውን የውድነህ ዘነበ ዘገባ፣ የሁለቱን ፕሮጀክቶች አንድነትና ልዩነት እያመሳከረ ይተነትናል፡፡

በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው ባምቡዲ፣ ዓባይ የሚያዝበት ቀጣና እንዲሆን ተመርጧል፡፡ ይህ ሥፍራ ለአካባቢው ተወላጆች ልዩ ትዝታ አለው፡፡ ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ አካባቢ ሕዝቡ ከጨቋኞችና ቅኝ ገዢዎች ነፃ ለመውጣት ትግል ያደረገበት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

‹‹ቀደም ሲል የነበሩትን ጨቋኝ ገዢዎች የታገልንበት ቦታ ነው፤›› በማለት የአካባቢውን ውለታ የሚያስታውሱት የክልሉ ነባር ፖለቲከኛና ታጋይ  አቶ አልክደር አህመድ ዛይድ ናቸው፡፡

‹‹ትግላችንን ከዚህ ጀምረን ጫፍ አድርሰነዋል፡፡ አሁን ደግሞ ይህ አካባቢ ወደ ታላቅ ልማት መሸጋገሩ ለእኛ ብዙ ትርጉም አለው፤›› ይላሉ አቶ አልከድር ጨምረው ሲገልጹ፡፡ የጉሙዝ አባቶችም የዚህ ቦታ ልዩ ትዝታ አላቸው፡፡ አዛውንቶቹ እንደሚገልጹት፣ በጥንት ዘመን ኦቶማን ቱርኮች በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የመተከል ዞንን ምሥራቅ አፍሪካን ለመቆጣጠር ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው በሚል መርጠውት ነበር፡፡ አካባቢውንም ለመቆጣጠር ትግል ያካሄዱ ቢሆንም ከብዙ ትግል በኋላ ከሽፎባቸዋል፡፡

የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም  እንደገለጹት፣ የጉሙዝ አዛውንቶች መራር ነገርን ለመግለጽ፣ ‹‹ቱርክንም ቢሆን ወርደህ ግጠም›› የሚል አባባል እንዳላቸውና  አካባቢው የትግል መነሻ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ታላቁ ዓባይ ባምቡዲ የሚደርሰው አገር ውስጥ የሚገኙ ገባር ወንዞችን በሙሉ ይዞ ነው፡፡ እዚያው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንኳ የሚያገኛቸውን ዶር፣ ሎርዶ፣ ዶንደር፣ ዴዴሳ፣ ግልገል በለስና አባት በለስ ወንዞችን በሙሉ ካጠቃለለ በኋላ ነው ባምቡዲን አቋርጦ 40 ኪሎ ሜትር ከተጓዘ በኋላ ሱዳን የሚገባው፡፡ ምናልባት ከብዙ ሺሕ ዓመታት በፊት አንድ የነበሩት የባምቡዲ ተራሮችን ደርምሶ ይሆናል  ዓባይ ሱዳን መግባት የጀመረው፡፡ ምክንያቱም ተራሮቹን ከግራና ቀኝ ቆመው ሲመለከቱዋቸው ዓባይ ከማለፉ በፊት የተቃቀፉ ይመስላሉና ነው፡፡

አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት እዚህ ቦታ ላይ ግዙፍ ግድብ በመገንባት ዓባይን ሥራ ሊያሠራው አቅዷል፡፡

ግድቡ
ዓባይን የሚያቆመው ግድብ 145 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል፡፡ ግድቡ በአጠቃላይ  1,680 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የሚኖው ሲሆን፣ በዚህም 63 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህም ከተፈጥሯዊው የጣና ሐይቅ እጥፍ ነው፡፡ ውኃው በአብዛኛው የሚያርፈው መተከል ዞን በተለይም ጉባ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ ሐይቁም ሆነ ግድቡ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ለበረሃማው መተከል ዞን እስትንፋስ ይሆንለታል፡፡

ግድቡ ስንት ብር ያወጣል?

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 60,000 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አላት፡፡ ከዚህ ውስጥ 45,000 ሜጋ ዋት ከውኃ ኃይል ሊመነጭ የሚችል ነው፡፡ የተቀረው ከንፋስና ከጂኦተርማል ይገኛል ይላል የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ፡፡

በአብዛኛው ከውኃ የሚገኘውን ኢነርጂ ለማመንጨት የሚችለው የዓባይ ወንዝ ሲሆን፣ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በዚህ ውኃ ላይ የተመሠረተ ግዙፍ ግድብ ለመገንባት የሚያስችል የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተገኙበት በቅርቡ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በወቅቱ የአርበኝነትና የዲፕሎማሲ ቋንቋዎችን በመጠቀም ልብ የሚነካ ንግግር አድርገው ነበር፡፡

‹‹የፕሮጀክቱ ወጭ 3.3 ቢሊዮን ዩሮ ይደርሳል፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት ወጭ በተጨማሪ በራሳችን ወጭ ሊሸፈኑ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት በመኖራቸው ይህን ወጭ መሸፈን በእጅጉ ይከብደናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ ኢትዮጵያ ሸክሙን ለማቃለል ከግርጌ አገሮች (ሱዳንና ግብፅ) ጋር ወጭ መጋራትን በተመለከተ የተካሄደው ውይይት ፍሬ ባለማፍራቱ፣ የ50 ዓመቱ የአገሪቱ ታሪክም ይኼንን የሚያስረዳ በመሆኑ ይህንን ግድብ የመገንባቱ ኃላፊነት በዋነኛነት በኢትዮጵያውያን ላይ የተጣለ ኃላፊነት ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከኪሳቸው አውጥተው በታላቁ ዓባይ ላይ የሚገነቡት ታላቁ የሚሌኒሊየም ግድብ ሥራ እነሆ ተጀምሯል፡፡

ሳሊኒ ማነው?
በ1997 ዓ.ም. በተለይ በአማራ ክልል ወሎ ውስጥ ድርቅ መከሰቱ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ በወቅቱ የነበረው ወታደራዊው መንግሥት ለጀመረው የሰፈራ ፕሮግራም የጣሊያን መንግሥት ዋነኛ አጋሩ ነበር፡፡ የጣሊያን መንግሥት በወቅቱ ከ500 ሚሊዮን ሊራ በላይ ዕርዳታ የሰጠ ሲሆን፣ የሰፈራውን ፕሮግራም የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ተረክቦት ነበር፡፡

በዚሁ ዞን ውስጥ በተለይ ፓዌ  አካባቢ የሰፈራ ፕሮግራም ሲጀመር፣ ዕቅዱ የበለስን ውኃ በመጠቀም ተፈናቃዮቹ በመስኖ  ልማት ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ነበር፡፡ መኖሪያ ቤቶች፣ መንገዶች፣ ቢሮዎችና የግብርና ምርምር ማዕከላት በአካባቢው ቢገነቡም መስኖው ግን ህልም ሆኖ ቀርቷል፡፡

ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ይህ ፕሮጀክት የሚፈልገው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ እንዲቋረጥና የገቡት መሣርያዎችም ሁሉም ክልሎች እንዲከፋፈሉት ተደርጓል፡፡ ከ50 ዓመት በፊትም ይህ ኩባንያ በባምቡዲ ላይ ግድብ እንዲገነባ የቦታ መረጣ አድርጎ ነበር፡፡ ዲዛይኑንም ከስምንት ዓመት በፊት ያዘጋጀው መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በመንደር ምሥረታ፣ በመንገድ ግንባታና በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ውስጥ በስፋት የሚታወቀው ሳሊኒ፣ ይህንን ሥራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ተረክቧል፡፡ ጥናቱንም በራሱ ወጭ በመምራት ለመንግሥት ማቅረቡን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበ  እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም የሚጠኑት የኃይል ማመንጫዎች ከ1,600 ሜጋ ዋት ያልበለጠ አነስተኛ ኃይል  ለማመንጨት የሚያስችሉ ነበሩ፡፡ በዚህ ደረጃ በ5,250 ሜጋ ዋት ግንባታ ለማካሄድ ታስቦ አያውቅም ይላሉ የሚሌኒየሙን ግድብ ፕሮጀክት ግዙፍነት ሲያስረዱ፡፡ 5,250 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችለውን የሚሌኒየም ግድብ ለመገንባት የሚያስፈልገውን ከ78 ቢሊዮን እስከ 80 ቢሊዮን ብር ኢትዮጵያውያን ለማውጣት የቦንድ ግዢ ላይ እየተረባረቡ ነው፡፡ ግድቡ መገንባቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ምልክቶችም እየታዩ ነው፡፡

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና መሬት
የቤንሻንጉል ጉሙዝ በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ይገኛል፡፡ የክልሉ ጠቅላላ ስፋት 5 ሚሊዮን 100 ሺሕ ሔክታር ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ መረጃ መሠረት የሕዝቡ ቁጥር 670,847 ነው፡፡ በዚህ የሕዝብ ብዛት በነፍስ ወከፍ 7.6 ሔክታር መሬት የሚደርስ ቢሆንም፣ አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ በድህነት፣ ኋላቀር በሆነ አስተራረስና ማዕድን በማውጣት የሚተዳደር ነው፡፡

ይህ አጋጣሚ ክልሉን የሰፊ መሬት ባለቤት በማድረጉ የበርካታ ኢንቨስተሮችን ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ በመቶ ሺሕ ሔክታር የሚቆጠር መሬት ለኢንቨስተሮች እየሰጠ ሲሆን፣ የክልሎችን መሬት በውክልና እየተረከበ ለአልሚዎች መስጠት የጀመረው የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ 1,149,052 ሔክታር መሬት ለአልሚዎች ለመስጠት አዘጋጅቷል፡፡ የተወሰነውንም ሰጥቷል፡፡

በእርግጥ የግብርና ሚኒስቴር እየሰጠ ያለው ከጋምቤላ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልል የተረከበውን መሬት ጨምሮ ነው፡፡ በእስካሁኑ ሒደትም 3,636,415 ሔክታር መሬት የተረከበ ሲሆን፣ 300,012 ሔክታር መሬት ለኢንቨስተሮች አከፋፍሏል፡፡

ከቤኒሻጉል ጉሙዝ የእርሻ መሬት ከወሰዱ ኩባንያዎች መካከል ኤስ ኤንድ ፒ ኢነርጂ ሶሉሽን፣ ሆራይዘን ኢትዮጵያ፣ አርደንት ኢነርጂ፣ ዘለቀ እርሻ ሜክናይዜሽንና አምባሰል ንግድ ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተለይ ከክልሉ የመሬት አሰጣጡ በትክክለኛ ልኬት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡  በግምት ወይም በሞተር ሳይከል ተለክቶ ነው ለአልሚዎች የተሰጣቸው፡፡

አቶ ያረጋል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በክልሉ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት በመኖሩ መሬት ለአልሚዎች ሲሰጥ የቆየው ከዚያ ጋራ እስከዚህ ወንዝ፣ ከዚህ ወንዝ እስከዚያ ማዶ እየተባለ ነው፡፡ በዚህም 100 ሔክታር የጠየቀ ኢንቨስተር ከዚያ በላይ ይዞ ቆይቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢንቨስተመንት ቢሮው ባለሙያ ሞተር ሳይክል መቶ ኪሎ ሜትር በማሽከርከር ችካል ይተክልለታል፡፡ ወደ ውስጥ ግን ሞተር ሳይክሉ መግባት ስለማይችል መሬት የመያዝ መብቱ በአልሚው የሚወሰን ይሆናል፡፡

የተሰጡት መሬቶች ዕጣ ፈንታ
ሪፖርተር በስፍራው ተገኝቶ ማየት እንደቻለው በኢንቨስተሮቹ መሬት ላይ የሚገኘው የበረሀ ደን ሰደድ እሳት ተለቆበታል፡፡ በቡልዶዘር እየተመነጠረም ነው፡፡ ቃጠሎው ሰደድ እሳት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኤሌክትሪክ እንጨቶችና ሽቦዎችን ጨምሮ እየበላ ነው፡፡ የዱር እንስሳትም ወደ ሱዳኑ ዲንደር ፓርክ እየተሰደዱ ነው፡፡ ቃጠሎው ሁለት ዓላማዎች እንዳሉት ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይገልጻሉ፡፡

የመጀመርያው ከሰል በማክሰል ወደ ሱዳን ወይም ለአገር ውስጥ ገበያ በሰፊው ማቅረብ ሲሆን፣ ሁለተኛው መሬቱን ከተክሎች ነፃ በማድረግ የእርሻ ሥራውን ማካሄድ ነው፡፡ የሚገርመው በመቶ ኪሎ ሜትሮች ሲጓዙ ቃጠሎው ያለማቋረጥ መቀጠሉ ነው፡፡

ደኑ በስፋት ሲቃጠል ነዋሪዎቹ የት ደረሱ?
የቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግሥት የመሬት ችግር እንደሌለበት ይገልጻል፡፡ ክልሉ እንደ ችግር የሚያነሳው ሕዝቡ ተበታትኖ የሚኖር በመሆኑ የመሠረተ ልማት ማሟላት ፈተና እንደሆነበት ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ መፍትሔ አድርጎ የወሰደው ሕዝቡን በማሰባሰብ አንድ ቦታ እንዲከትም ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ዕቅድም ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም በመቅረጽ ተበታትነው ይኖራሉ የተባሉትን ሰዎች በድጋሚ በማስፈር ላይ ይገኛል፡፡

ለምሳሌ ከቻግኒ ከተማ ወደ ጣና በለስ ከተማ በሚወስደው መንገድ ላይ የጉሙዝ ተወላጆች አዳዲስ መንደሮች እየተመሠረተላቸው ነው፡፡ በሥፍራው የሚሠሩት መንደሮች ደን ተመንጥሮ እንደመሆኑ በሁለቱም መንገዶች የክልሉ የደን ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡ ሁኔታው በክልሉ መንግሥት ብዙም ትኩረት የተሰጠው እንደማይመስል ሁኔታዎች በግልጽ ያሳያሉ፡፡

አዲሱ ሐይቅና የአካባቢው ይዞታ

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ግድብ መሠራቱ ለሱዳን ግድብ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ምክንቱም ከኢትዮጵያ የሚሄደው ጎርፍ ደለል በብዛት ይዞ የሚሄድ ስለሆነ ግድቡም ይህንን ስለሚያስቀር ነው፡፡

የግድቡ ተፋሰስ ላይ ያለው ደን በዚሁ መንገድ የሚጠፋ ከሆነ የአካባቢው በረሃማነት ይበልጥ ይባባሳል፡፡ ደኖቹን እንደገና ማልማት ቢያስፈልግ እንኳ ሁኔታው አስቸጋሪ እንደሚሆን የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ ስለዚህ የደኖቹ ዕጣ ፈንታ አስተማማኝ መሆን ለማይቀረው ግድብ ወሳኝ ነው፡፡ የደኖቹ መኖር ለሐይቁ እስትንፋስ በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ይስጠው በማለት ተቆርቋሪዎቹ ይመክራሉ፡፡

አቃጣዮቹና መንጣሪዎቹ

ደን በስፋት እያቃጠሉና እየመነጠሩ ከሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች መሀከል ኤስ ኤንድ ፒ ኢነርጂ ሶሊሽንና ካሩቱሪ የተባሉት የህንድ ኩባንያዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ለኤስ ኤንድ ፒ ኩባንያ መተከል ዞን ውስጥ 50 ሺሕ ሔክታር መሬት ለእርሻ ሥራ ሰጥቶታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደኑን በማስወገድ በቆሎ ለመዝራት በመጣደፍ ላይ ይገኛል፡፡ ካሩቱሪም እንዲሁ ከጋምቤላ ክልል 300 ሺሕ ሔክታር መሬት ከሚኒስቴሩ ተረክቧል፡፡ እሱም እንዲሁ ደኑን እያነደደና እየመነጠረ ይገኛል፡፡ በተለይ ሁለቱ ክልሎች ነበልባል ወሯቸዋል፡፡ ነዋሪዎቹም ምን ጉድ ነው ይላሉ፡፡

የመሬት ሽሚያ ያስብላል?

በ2001 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎች እጥረት መከሰቱ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ ገንዘብ እያላቸው በእህል አለመኖር ብቻ ሕዝባቸውን መመገብ ችግር እንደሚሆንባቸው የተረዱ አገሮች ፊታቸውን ወደ ታዳጊ አገሮች መሬቶች ላይ አዙረዋል፡፡

ከእነዚህ አገሮች መካከል ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ህንድና ጅቡቲ የኢትዮጵያን በር በማንኳኳት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ በሼክ መሐመድ ሑሴን አላሙዲ አማካይነት ሰፊ የእርሻ መሬት አግኝታለች፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሣውያን ቤተሰቦችና ሼክ አላሙዲ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ድርድር 500 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቷል፡፡ በድርድሩ መሠረት ይህንን ሥራ እንዲያከናውን የተቋቋመው ሳዑዲ ስታር የግብርና ልማት ኩባንያ የሥራ አፈጻጸም እየታየ ቃል የተገባው መሬት ይፈቀድለታል ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኩባንያው 10 ሺሕ ሔክታር መሬት ተረክቦ የሩዝ ልማት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ኩባንያው የተረከበው መሬት በጋምቤላ ክልል አሉዌሮ አካባቢ ሲሆን፣ ከተሰጠው መሬት በተጨማሪ በዚሁ ክልል 290 ሺሕ ሔክታር መሬት ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የተቀረውን 200 ሺሕ ሔክታር ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከአማራ ክልሎች እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡

በዚሁ በጋምቤላ ክልል ከሳዑዲ ስታር በተጨማሪ አምስት የህንድ ኩባንያዎች ሰፋፊ መሬት ተረክበዋል፡፡ ካሩቱሪ ግሎባል የተሰኘው የህንድ ኩባንያ ብቻውን ከኢትዮጵያ መንግሥት 311 ሺሕ ሔክታር መሬት የተረከበ ሲሆን፣ 300 ሺሕ ሔክታሩ በጋምቤላ ክልል የተቀረው በኦሮሚያ ክልል ይገኛል፡፡ በዚህ መሬት ላይ ኩባንያው ሩዝ፣ ስንዴ፣ ሸንኮራ አገዳና አበባ እንደሚያመርት የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡ የጅቡቲ መንግሥት በበኩሉ በቀጥታ ስንዴ በማምረት ወደ አገሩ መላክ የሚያስችለው 3,000 ሔክታር መሬት ከኦሮሚያ ክልል አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ይህ መሬት በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ውስጥ ይገኝ እንጂ፣ የመሬቱ ባለይዞታ በመንግሥት ሥር የሚገኘው የባሌ እርሻ ልማት ኢንተርፕራይዝ ነበር፡፡

መንግሥት ለፕራይቬታይዜሽንና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በሰጠው ትዕዛዝ ኢንተርፕራይዙ ካለው መሬት ላይ ተቀንሶ ለጅቡቲ መንግሥት ተሰጥቶታል፡፡ የጅቡቲ መንግሥት በያዝነው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ስንዴ አምርቶ ወደ አገሩ ወስዷል፡፡

የምግብ ሰብል ከሚያመርቱ ኢንቨስተሮች፣ መንግሥታትና ኩባንያዎች በተጨማሪ የተፈጥሮአዊው ነዳጅ እጥረትና አቅርቦት ያሰጋቸው አካላትም እንዲሁ በመሬት ሽሚያ ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ መሀከል የጀርመን፣ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ፣ የህንድ፣ የብራዚልና የፓኪስታን ኩባንያዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ከእፅዋት የሚገኝ ነዳጅ ከጃትሮፋ፣ ከሸንኮራ አገዳ፣ ከፓልም ዛፍና ከጉሎ ዛፍ ለማምረት መሬት በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ምክንያታቸውም የተፈጥሮ ነዳጅ አላቂ ሀብት በመሆኑና የዚህ ነዳጅ አቅራቢ የሆኑ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የፖለቲካ ሁኔታ መረጋጋት ስለማይታይበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተፈጥሮ ነዳጅ ለዓለም ሙቀት መጨመር የራሱን አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ትኩረታቸውን ከእፅዋት በሚገኝ ነዳጅ ላይ እንዳደረጉ ይገልጻሉ፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ልማት ሰፊ መሬት የሚፈልግ በመሆኑ ትኩረታቸውን የታዳጊ አገሮች ጠፍ መሬት ላይ አድርገዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ባካሄደው የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ እንዲቋቋም ያደረገው የግብርና ኢንቨስትመን ድጋፍ ዳይሬክቶሬት የመሬት ፈላጊ ኩባንያዎችን ጥያቄ በማስተናገድ ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ ከየአገሮቹ በርካታ የባለሀብቶች ልዑካን ቡድኖች ይህንኑ ዳይሬክቶሬት በየቀኑ ሲጎበኝኙ ይውላሉ፡፡

የመሬት ዝርፊያ ያሰኘዋል?

በእርግጥ ኢትዮጵያ 1.2 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ሰፊ አገር ናት፡፡  ከዚህ ውስጥ በመስኖ የሚለማ 75 ሚሊዮን ሔክታር ያላት ሲሆን፣ 15 ሚሊዮን ሔክታር ደግሞ በኋላቀር አስተራረስ ይለማል፡፡ በገበሬዎች በመልማት ላይ የሚገኘው መሬት ተመጣጣኝ ዝናብ በሚያገኙ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ያለ ሲሆን፣ ይህም 40 በመቶ የአገሪቱን መሬት ይሸፍናል፡፡

ዝቅተኛው የአገሪቱ ክልል 60 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን ክፍል የሚሸፍን ሲሆን፣ ነዋሪዎቹም በአብዛኛው በተበታተነ ሁኔታ የሚኖሩና በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ይህ ሥፍራ በአብዛኛው ሞቃት በመሆኑ በወባና በከብቶች በሽታ  ላይ የሚጠቃ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለዘመናት የመሠረተ ልማት ሳይገነባለት ቆይቷል፡፡

ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የተመሠረተው መንግሥት በዚህ አካባቢ ያለውን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ተንቀሳቅሷል፡፡ እነሱም ወባና የከብቶች በሽታዎችን እንዲሁም የመሠረተ ልማት (የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን  አገልግሎቶችና የመስኖ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ የበሽታዎቹም ሆነ የመሠረተ ልማቱ በሚታይ ደረጃ ለውጥ ቢያሳዩም፣ ኢንቨስትመንት  የመሳቡ ነገር ብዙም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይሁንና ባለፉት አራት ዓመታት  ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ እጥረት በመከሰቱና በቀጣይነትም ሊከሰት እንደሚችል የጠረጠሩና የተፈጥሮ ነዳጅ  አስተማማኝ መስሎ ያልታያቸው አገሮችና ኩባንያዎች መጉረፍ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በዋናነት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደመምጣታቸው፣ መንግሥት ምን ያህል ተጠንቅቋል? የሚሉ ወገኖች ጥያቄ ማንሳታቸው አልቀረም፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች ትልቅ ትርፍ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ትርፋቸውን ለማግኘት የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ባለሥልጣናትንም ሙስና ውስጥ ከመዝፈቅ ወደኋላ የሚሉ አይደሉም፡፡ መንግሥት አዋጭነቱን በምን መልኩ አጥንቷል? የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ከግንዛቤ ከቷል ወይ? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚያመርቱት ምርትስ መድረሻው የት ነው? በማለት  ጭንቀታቸውን እነዚህ አካላት በተለያየ መንገድ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የግብርና ኢኮኖሚስት እንደገለጹት፣ ልማቱ ለአገሪቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ግን የሚሰጠው መሬት በምን ዓይነት ይዞታ ላይ ነው ያለው? የግብርና ሚኒስቴር በግልጽ በካርታ ላይ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለበት፡፡ እስካሁን ቦታ እንደተሰጠ እንጂ ቦታው የት እንዳለና በምን እንደተሸፈነ የሚገልጽ ነገር የለም ይላሉ፡፡

ኢኮኖሚስቱ ምክንያታቸውን  ሲያስረዱ፣ ቦታው በደን የተሸፈነ ከሆነ የማር ምርት፣ የዕጣን ምርት፣ የቅመማ ቅመም ምርት ቢካሄድ ይሻላል? ወይስ ስንዴ ማልማት የሚለውን ማስላትና ለአገሪቱ የቱ ይሻላል የሚለውን ማወቅ ይቻላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመሬት ሊዝ ዋጋውን፣ መሬቱ ለምን ያህል ጊዜ በሊዝ እንደተሰጠ? የሚመረተው ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል? ካምፓኒዎቹ ምርቱ የራሳቸው እንደመሆኑ ወደ ውጭ ሲልኩ አገሪቱ ምንድን ነው የምትጠቀመው? የሚለው ጉዳይ በግልጽ መታወቅ አለበት የሚሉ ወገኖች በዝተዋል፡፡

በእርግጥ በእስካሁኑ ሒደት ከተወሰኑት ኩባንያዎች በስተቀር ምርታቸውን ለገበያ ያቀረቡ የሉም፡፡ ወደ ምርት ከገቡት መካከል የጅቡቲ መንግሥት ያመረተው ስንዴና ግሎባል ኢነርጂ የተባለው ኩባንያ ያመረተውን የጃትሮፋ ፍሬ ወደ ውጭ ልከዋል፡፡ ከዚህ ምርት ኢትዮጵያ ምን አገኘች የሚለው ጥያቄም እየተነሳ ነው፡፡

መሬቱን ማነው የሚሰጠው? ስሌቱንስ ማን ሠርቶ?
ክልሎች መሬት ለትላልቅ የእርሻ ኢንቨስትመንት በማቅረብ በኩል የአቅም ውስንነት አለባቸው በሚል፣ የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች  መሬት ተረክቦ  እንዲሰጥ ወስኗል፡፡

የመሬት አሰጣጡ ሒደት ምን መምሰል አለበት የሚለውን ያጠናውና መመርያውን ያዘጋጀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረ አብና የቀድሞ የግብርና  ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር አበራ ዴሬሳ ያሉበት ኮሜቴ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሒደቱን በቅርብ የሚከታተሉት ሲሆን፣ የመሬት አሰጣጡንም እንዲሁ በቅርቡ ሆነው ይከታተሉታል፡፡ ይሁንና ከኩባንያዎቹ ጋር የሚደረገው ውል ግልጽ እንዳልሆነ ጉዳዩን መከታተል የሚፈልጉ ችግር እንደፈጠረባቸው  ይገልጻሉ፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ከበደ እንደሚገልጹት፣ የሊዝ ውል  ግልጽ የማይደረገው ሚስጥራዊነቱ መጠበቅ ስላለበት ነው፡፡ ነገር ግን የመሬት አሰጣጥ  ሒደቱ የሚካሄደው የአገሪቱን ጥቅም ባስጠበቀ መንገድ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ
አገሪቱ በእስካሁኑ ሒደት ወጥ በሆነ የመሬት ፖሊሲ እየተጠቀመች አይደለም፡፡ የትኛው መሬት ለእርሻ፣ የቱ ለማዕድን፣ የቱ ለኢንዱስትሪ፣ የቱ ለደን፣ የቱ ጥብቅ ቦታ እንደሆነ በግልጽ ተለይቶ አልተቀመጠም፡፡ መግባባት ላይም አልተደረሰም፡፡
የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ለትላልቅ ፕሮጀክቶች መካሄድ እንዳለበት በግልጽ ቢታወጅም ተግባር ላይ አልዋለም፡፡

በዘፈቀደ መሬት መስጠት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን የግብርና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ቀደም ሲል ናሽናል ባዮዲዝል የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ በክልሉ 80 ሺሕ ሔክታር መሬት ከተረከበ በኋላ ደኑን መንጥሮት አይሆነኝም ብሎ ወጥቷል፡፡ ፍሎራ ኪኮፓወር የተባለ የጀርመን ኩባንያ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን 11 ሺሕ ሔክታር መሬት በባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ውስጥ ተሰጥቶታል፡፡ ደኑንና ዝሆኖቹን ካተራመሰ በኋላ አካባቢውን ለቆ ወጥቷል፡፡

የሚኒስቴሩ ሚና ለምን?
በአገሪቱ የሚገኘውን ሰፋፊ የእርሻ መሬት ለአልሚዎች እንዲሰጥ ግብርና ሚኒስቴር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ የሚገኙ የደን ሀብቶች እንዲጠበቁና እንዲስፋፉ የማድረግ ኃላፊነትም የሚኒስቴሩ ነው፡፡

የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ አክሊሉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለጋዜጠኞች በሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ላይ እንደገለጹት፣ የደን ጉዳይ ከሚኒስቴሩ መውጣት አለበት፡፡ ምክንያቱም ሚኒስቴሩ ከደን ጥበቃ ይልቅ የግብርና ሥራዎች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ገለልተኛ ወገን ሥራውን ቢያካሂድ ይሻላል፡፡

ሚኒስቴሩ ጥብቅ ቦታዎችንም ሆነ ለወደፊቱ ለአገሪቱ ዘላቂ ልማት ወሳኝ የሆኑ ቦታዎች ከግንዛቤ ሳያስገባ መሬት እየሰጠ ይገኛል ይባላል፡፡ ይህንን ግን ሚኒስቴሩ በፍጹም አያምንም፡፡ በቅርቡ ሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ አካባቢን ባገናዘበ መንገድ የደን ሀብት ሳይነካ መሬት ለልማት እንደሚያቀርብ ይገልጻል፡፡

ጥርስ የሌለው አንበሳ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከስድስት ዓመት በፊት ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማካሄድ እንዳለባቸው በማመኑ አዋጅ አውጥቷል፡፡ ይህንን አዋጅ የማስፈጸም ሥልጣንም ለፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ተሰጥቷል፡፡ ይሁንና በተለይ የግብርና ፕሮጀክቶች ያለምንም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ወደ ሥራ እየገቡ ጥፋት እያደረሱ ነው ተብሎ ወቀሳ ይቀርባል፡፡

የተመረጡና ትላልቅ ፕሮጀክቶች በአዋጁ መሠረት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በራሳቸው አካሂደው ለባለሥልጣኑ ያቀርባሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ደግሞ በባለሙያዎቹ ይህንን ጥናት ካስገመገመ በኋላ እንዲስተካከል ወይም እንዲተገበር ይፈቅዳል፡፡ ፈቃደኛ ሆነው ጥናት ካደረጉ ኩባንያዎች በስተቀር ባለሥልጣኑ በራሱ ክትትል አድርጎ እንደማያውቅ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ብዙኃኑ የአካባቢ ተቆርቋሪዎችን ያስጨነቀው ግን ባለሥልጣኑ በቅርብ ባካሄደው የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የመከታተል ሥልጣኑን  በራሱ ፈቃድ ለዘርፍ መስርያ ቤቶች መስጠቱ ነው፡፡  ይህም ማለት አንድ በግብርና ሥራ መሠማራት የሚፈልግ ኩባንያ ጥናቱን ሠርቶ ለግብርና ሚኒስቴር ያቀርባል፡፡
ሚኒስቴሩ እንዲስተካከል ወይም እንዲተገበር ይፈቅዳል፡፡ በየሩብ ዓመቱም ሚኒስቴሩ ለባለሥልጣኑ ሪፖርት የሚያቀርብበት አሠራር ነው እንዲዘረጋ የተደረገው፡፡

ይህንን አሠራር የአካባቢ ተቆርቋሪዎች በፍፁም አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ የግብርና ሚኒስቴር በዋናነት ተግባሩ ግብርናን  ማስፋፋት ነው፡፡ ፍላጎቱም ይህ በመሆኑ የደን ጥበቃና የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡ ጉዳዮች ናቸው ይላሉ፡፡

የማይቀረው ግድብ የማይቃጠል ደን ይፈልጋል
ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የግድብ ተፋሰስ የተረጋጋ ሥነ ምህዳር ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጎርፍ ምክንያት መሬት እየተሸረሸረ ወደ ግድቡ እንዳይገባ መድረግ አለበት፡፡ አፈር ከገባ የግድቡን ዕድሜ ስለሚያሳጥረው የዛፎች መኖር ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት በአዋጁ መሠረት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሊደረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር አስተያየት እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት ሥልጠና በመግባታቸው አልተሳካም፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close