የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱ ከተጻፈበት ቀለም ዋጋ አንጻር ሲመዘን

አቶ አረጋዊ ገብረ ዮሐንስ በቅርቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው የ2010 የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ውስጥ በፖለቲካ ሳቢያ ተገለዋል ተብለው ከቀረቡ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ በግንቦቱ ምርጫ የዓረና ፓርቲ አባል የነበሩት አቶ አረጋዊ ሆቴላቸው ውስጥ በግል ፀብ ከተጣሉት አቶ ፅጌ በርሄ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ገጽታ እንዳለው ፓርቲያቸው ቢገልጽም፣ አቶ መለስ ዜናዊ ለፓርላማ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ግን ጉዳዩ ከግለሰቦች አምባጓሮ የዘለለ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በሕጋዊ የፍርድ ቤት ሒደት ጥፋተኛ በተባሉት አቶ ፅጌ ላይ የ15 ዓመት እስራት ቢበየንም የውጭ ጉዳይ ሪፖርቱ አሁንም በሰነዱ ላይ አስፍሮታል፡፡ አጥፊው በዚህ ሁኔታ በተቀጣበት ሁኔታ ላይ ይህን ማካተት የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ይጥሳል የሚል ትርጉም አለው፡፡ ጥፋተኛውን በረጅም ጊዜ እስር ከመቅጣት በላይ ምን መደረግ እንደነበረበት ሪፖርቱ አይጠቅስም፡፡ ከሳምንታት በፊት የወጣው 56 ገጽ ያለው ሪፖርት ይህን ዓይነት በርካታ ተመሳሳይ ክሶች አካቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት ይህን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት ከመረጃ አሰባሰቡ ጀምሮ ሳይንሳዊነት ይጐድለዋል ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ይህን በተናገሩበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የነበረው የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የእንግሊዝኛ ዘጋቢ ፒተር ሄይንሄሌሄን ፂሙን እያሻሸ ያቀረበው ጥያቄ፣ ሪፖርቱን ብቻ ነው ወይስ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ነው ውድቅ ያደረጋችሁት? ሲል ጠይቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሪፖርቱ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ይህ ሪፖርት እንዲወጣ ፖለቲካዊ አንድምታውን በተመለከተ ያለውን ትርጉም ለመዳሰስ የሞከሩ ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ የሪፖርተር ጋዜጣም በኢትዮጵያ ላይ የቀረበው ክስ የተለሳለሰ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በትንሽ ተጨባጭ ሁኔታዎችን አያሳይም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሪፖርቱ ያካተታቸው በርካታ አገሮች ግን ይህ የተለመደ ዓመታዊ ሥነ ሥርዓት (Ritual) ብለውታል፡፡ ቻይናን የመሳሰሉ አገሮች በበኩላቸው ‹‹የነፃነት ምድር ናት›› የምትባለውን አሜሪካ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የሰብዓዊ መብት አያያዝ አብጠልጥለዋታል፡፡

ሰብዓዊ መብት እንደፖሊሲ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን በሰሞኑ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አብዮት ሳቢያ ሥራ ስለበዛባቸው ሪፖርቱ ከወትሮው የወጣው ዘግይቶ ነው፡፡ ይህ ሪፖርት በ194 አገሮች (ከአሜሪካ በስተቀር) ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በየዓመቱ ይዳስሳል፡፡ የሪፖርቱ እንከን ከወዲሁ ይጀምራል፡፡ እ.ኤ.አ ኦገስት 28 ቀን 2010 የወጣው የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ እንደሚያሳየው፣ ከአንድ መቶ አሜሪካዊ ወጣት ውስጥ አንዱ እስር ቤት ነው የሚገኘው፡፡ እንደጋዜጣው አስተያየት በአሁኑ ወቅት እስር ቤት የሚገኙት ሁለት ሚሊዮን ሴቶችና ወንዶች አሜሪካውያን በተበላሸ የእስር ቤቶችና የአስተዳደር ሁኔታ ለመኖር ተገደዋል፡፡

ሂላሪ ክሊንተን ሪፖርቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የሕዝባቸውን መብት የሚያስከብሩ መንግሥታት የመበልጸግ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ታሪክ አሳይቷል፡፡ ሂላሪ አሜሪካ ሪፖርቱን ያወጣችው የኦባማ አስተዳደር የሰብዓዊ መብት ማስከበር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ዋና አጀንዳ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የሁሉም የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንዳንዴ የሚወራረስ ቢሆንም፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝን እንደ አንድ ቁልፍ ተግባር በመያዝ የመጀመሪያውን የሰብዓዊ መብት ሪፖርት በማውጣት የሚታወቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ናቸው፡፡ ከእሳቸው በኋላ ሥልጣን ዴሞክራሲን ማስፈን፣ አሸባሪነትን መዋጋት ወዘተ. የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመአዘን ድንጋይ እንደሆኑ ይግለጹ እንጂ ሪፖርቱ ላለፉት 34 ዓመታት ሲወጣ ቆይቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ፣ አገራቸው የትኛው መደብ እንደምትወድቅ ከመግለጽ ቢታቀቡም 194 አገሮቹን በሦስት መልክ ፈርጀዋቸዋል፡፡ በመጀመሪያው ጐራ የሚመደቡት የሲቪል ተቋማትን የሚጨፈልቁ፣ የዴሞክራሲ አቀንቃኞችን የሚያዋክቡ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚገድቡ አገሮች ናቸው፡፡ በሪፖርቱ መሠረት በሁለተኛው ጐራ የተጠቃለሉት ደግሞ የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ ነፃነት የሚገድቡ 40 አገሮች ናቸው፡፡ ሦስተኛ መደብ የሚያጠቃልለው ውህዳን ሃይማኖቶችን፣ ብሔሮችን የሚያፍኑ እንዲሁም ግብረ ሰዶማውያንን የሚያጠቁ ወገኖችን ነው፡፡

ሚኒስትሯ በሦስቱም መደቦች በተደለደሉት አገሮች ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተለያዩ መነጽሮች በማየት ለመመዘን በመሞከር አገሮች ከአምናው ይልቅ ዘንድሮ ያላቸው የሰብዓዊ መብት አያያዝ የተሻለ እንደሆን ጠቅሰዋል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በተለያየ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የሰብዓዊ መብት ክስ ያቀረበ ሲሆን፣ መንግሥት ቀደም ሲል የነበሩትን የረጅም ጊዜ ጥናት በማድረግ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡

ምርጫ 97/2002
የፖለቲካ ፓርቲዎች አነሰም በዛም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ምርጫ በኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ነው፡፡ ክርስቶፎር ክላፉም የተባለው ጸሐፊ ከምርጫ 97 በኋላ ባቀረበው ጽሑፍ የምርጫ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ቅንጦት ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ ይህ ንቀት ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተደረጉት ምርጫዎች በየወቅቱ የተሻለ ትምህርት እየተቀሰመባቸው ገዢው ፓርቲም ሆነ የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ብርቱ ፉክክር ማሳየት የቻሉበት ሁኔታ እንደነበር አቶ ልደቱ አያሌው ‹‹የአረም እርሻ›› በሚለው መጽሐፋቸው በሚገባ አብራርተውታል፡፡ በተለይም ምርጫ 97 የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው ቅንጅት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የተሻለ የመራጭ ድምፅ ያገኙበት ወቅት አከራካሪ የነበረው እናሸንፋለን የሚለው ሳይሆን በምን ያህል ስፋት የሚለው እንደነበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተስፋ ጐህ ሲቀድ ባሉት መጽሐፋቸው አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርቱ ለሁሉም ፓርቲዎች የሚገባቸውን ሰጥቶ ከመቀመጥ ይልቅ በወቅቱ ሥራ ላይ የዋሉ ሕጐችና አዋጆች ገዢው ፓርቲ የበላይነት እንዲኖረው አድርገውታል ሲል ትችቱን ይጀምራል፡፡ የትኞቹ መመሪያዎችና ሕጐች? ይህ ዓይነት አስተያየት እንደ አጋር አገር አይጠቅምም፡፡ በመቀጠልም ወደ ባለፈው ግንቦት ምርጫ በመምጣት ምርጫው ከቴክኒክ አንጻር ምንም ባይወጣለትም ምርጫውን ለመታዘብ የተፈቀደላቸው ዓለም አቀፍ ባለሥልጣናት ቁጥር አነስተኛ ነው ይላል፡፡ በ2002 ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የሥነ ምግባር ሕግ በማውጣት ለመሥራት ያሳዩት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከምንም በላይ ለኢትዮጵያ የመቻቻል ፖለቲካ ዋጋ ነበረው፡፡ ፖለቲካው ጥቁር ወይም ነጭ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል ውጭ ነበር፡፡ ከአሜሪካዎቹ ኢንተርናሽናል ዴሞክራቲክና ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት በስተቀር የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት በተለይም የጉዳዩ አካላት የሆኑት የኢትዮጵያ ሲቪል ተቋማት ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሪፖርት ከምርጫው አንጻር ያሰፈረው አንቀጽ ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለ ገለልተኛ ያልሆነ ተቋም የ2002 ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ሕዝቡ መስቀል አደባባዩን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ያሰማውን ‹‹የጣልቃ አትግቡብን›› ድምፅ በማሳነስ ‹‹አነስተኛ ሰልፎች ተካሂደዋል›› ሲል ገልጾታል፡፡ ለነገሩ የ2002 ይሁን የ97ቱ ምርጫ ለዘንድሮ 2010 ሪፖርት መነሻ መሆን አልነበረባቸውም፡፡ ሪፖርቱ አንደኛው የሚታማበት ምክንያት ቀደም ሲል የነበሩት ቅጅና ድግግሞሽ (Copy) መሆኑ ነው፡፡ እ.ኤ.አ 2008 በወጣው ሪፖርት የነበረው ከሁለት ዓመት በኋላም እንዳለ ተፈጽሟል ተብሎ ቀርቧል፡፡ አብዛኛው በቆረጥ ለጥፍ (Cut and paste) የተቀመጠ ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት ከሚሰማው አሠራር የውጭ ጉዳይ ከመሰለ አካል አይጠበቅም፡፡

ፖለቲካዊ ሪፖርት
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪፖርት ኦነግ፣ ኦብነግና ሌሎች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ኃይሎችና ነፍጥ ያነሱ (Violent and opposition groups) ቡድኖች ሲል ነው የሚገልጻቸው፡፡ ይሁን እንጂ የመረጃ ምንጮቹም እነዚህ ለኤርትራ መንግሥት ያደሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው ገጽ ጀምሮ እነዚህን ወገኖች ዋቢ ያደረገው ይህ ሪፖርት የሰጡትን መረጃዎች እንዳለ በጥሬው ነው ያሰፈረው፡፡ ይህ የአብዛኞቹን በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሥነ ልቦና ካለማወቅ የሚመጣ ስህተት ነው፡፡ ከእነዚህ ከዚህ የተሻለ ምን አስተያየት ይጠበቃል? ይህ ለድሃ ዜጋው የሚሰጥን ዕርዳታ ከመቃወም አይበልጥም፡፡ ሪፖርቱ እርስ በርሱ የሚጣረሰው በተመሳሳይ ዓረፍተ ነገር ላይ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ የተፈጸመ ግድያ እንደሌለ ቢገልጽም፣ ተፈጸሙ የሚላቸውን ምንጮች (Crediable sources) ጠቅሶ በተማሪዎች በምዕራብ ኦሮሚያ አርዳይታ ኮሌጅ አለመግባባት ተነስቶ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አንድ ፖሊስ ከሥራ ሲታገድ ሌላው እስር ተበየነበት ሲል ይገልጻል፡፡ የፖሊስ መኮንኖቹ ከሚገባቸው በላይ ኃይል (Excessive force) በመጠቀማቸው መቀጣታቸው እየታወቀ በሪፖርቱ ውስጥ ለምን ማካተት ያስፈልጋል? ይህ ከአቶ አረጋዊ አሟሟት ጋርና በሌሎች ቦታዎች የቀረበው ክስ የፍትሕ ተቋማትን ተዓማኒነት (Integrity) ላይ የተቃጣ አስተያየት ነው፡፡ አጋጣሚው አሳዛኝ ቢሆንም ድርጊቱ የፖሊሱ የተሳሳተ የተናጠል ድርጊት (Isolated case) እንጂ የሥርዓቱን ማንነት አያሳይም፡፡ ከምንጭ በተጨማሪ ከጭብጥ አንጻር በሪፖርቱ ላይ የቀረቡት ነጥቦች ሳይቀር የተሳሳቱ ናቸው፡፡ አዘጋጆች ይህን ለማረም አለመጨነቃቸው ለሪፖርቱ ከእኛ ይልቅ እነሱ ቁም ነገር እንደማይሰጡት ያሳያል፡፡ ሪፖርቱ የእ.ኤ.አ 2010 ሆኖ እያለ ኢትዮጵያ በቴሌኮሙኒኬሽን ሥርጭት ላይ ያለችበትን ሁኔታ እንኳን በወጉ አላሰፈረውም፡፡
ያቀረበው መረጃ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረ ነው፡፡ የዓለም አቀፉን የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት ጠቅሶ ኢትዮጵያ ውስጥ 43 ሺሕ የኢንተርኔት ደንበኞች እንዳሉ አስፍሯል፡፡ የሪፖርቱ አዘጋጆች ወደ ቴሌ ድረ ገጽ ለመግባት ትንሽ ጥረት ቢያደርጉ፣ ይህ አሃዝ ከአራት እጥፍ በላይ እንደሆነ ይረዱት ነበር፡፡ የሞባይል ደንበኛ ቁጥርም እንዲሁ የተሳሳተ ነው፡፡ ይህ ከሰብዓዊ መብት መከበርና አለመከበር ጋር ያለው ግንኙነትም ግልጽ አይደለም፡፡ ለሪፖርቱ የተጻፈበትን ቀለም ያህል ዋጋ ቢሰጠው ኖሮ ይህ ስህተት ላይፈጸም ይችል ነበር፡፡ ቢሆንም ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ገዢው አይቀበለውም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከለጋሽ አገሮች የሚሰጠውን እርዳታ ለፖለቲካ ደጋፊዎቹ ብቻ በመስጠት የተቃዋሚ አባላትን ያገላል ሲል ይከሳል፡፡ ይህ ክስ በ2002 ምርጫ ወቅት በሂውማን ራይትስ ዎች የተቀዳ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቀድመው ውድቅ ያደረጉት የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ ኬን ኦሃሼ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሂስ በመሰንዘር የሚታወቀው አይሪሽ ኤይድ ሳይቀር ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያደረግነው ምክክር የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርትን አይደግፉም›› ሲል ያቀረበውን ዘገባ ይህ ሪፖርት አያስታውሰውም፡፡ ይህ ድምዳሜ የሂውማን ራይትስ ዎችን ማንነት ለሚያውቅ ሰው ብዙም የሚገርም እንዳልሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች አሳይቷል፡፡ ይህ ሪፖርት የተለያዩ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ ድረ ገጾችን፣ ብሎገሮችን በዋነኛነት እንደምንጭ አድርጐ እንደሚጠቀም ታውቋል፡፡ የመንግሥትን ኦፊሴላዊ መግለጫዎች የመያዝ ብዙም ፍላጐት አይታይበትም፡፡ ለምሳሌ ኦሎምፒያ ኢንተርኔት ቤት ተቀምጦ አንድ ሰው በፖሊስ መታሰሩን ውጭ አገር ባለ ድረ ገጽ ቢጽፉ፣ በ2011 ሪፖርት ሆኖ ይወጣል፡፡ ምንም ዓይነት የማጣራት (Verification) ሥራ አያከናውንም፡፡

ከመሬት መቀራመት ጋር በተያያዘ (Land grabing) በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወረዳዎች 45 ሺሕ ሰዎች በፍቃደኝነት ሰፈራ በሚል ተፈናቅለው መሬቱ ለኢንቨስትመንት እየተሰጠ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ከዚህ የምዕራቡ ዓለም ክስ፣ የወቀሳው አራጋቢ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ምዕራባውያን ሚዲያዎች ጀርባ ስላለው ክስ ለመፈተሽ አንድ ሰዓት አያባክንም፡፡ የሚሰጠው መሬት ከዚህ ቀደም ያልታረሰ፣ በቆላማ አካባቢ ያለና አርሶ አደሩ ያልሰፈረበት እንደሆነ በመጥቀስ ክሱ የእስያ አገሮች በአፍሪካ አገሮች እያሳዩ ያሉትን ፍላጐት የሚቃወም ፖለቲካ አቋም እንደሆነ ለመናገር አይደፍርም፡፡ ሪፖርቱ ፖለቲካዊ የሚባልበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ ኢንቨስተሮቹ አሜሪካውያን ወይም ካናዳዎች ቢሆኑ ይህ ክስ ይቀርባል? አድሏዊ የሚባልበትም ምክንያት ይኸው ነው፡፡

ከዚህ ጋር የሚነሳው ሌላ ጉዳይ ሪፖርቱ ይህን ፖለቲካዊ አጀንዳ ለመሸፈን ሲል ለአንባቢው ሙሉ ስዕል የሚሰጥ መረጃ አያቀርብም፡፡ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይቅርታ ተደርጐላቸው እንደተፈቱና ለብቻቸው ታስረው እንደነበር ይገልጻል፡፡ ይህ ጉዳይ የተለያዩ አገሮች መንግሥታት ትኩረት ሰጥተውት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ሲሞክሩበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ከአንድ ዓመት በላይ ምን ሠርተው እንደታሰሩ? እንዴት ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ እንዳሉም አንድም ነገር አይገልጽም፡፡ ቢያንስ የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት (Magnanimity and humanity) ቢጠቅስ ለሪፖርቱ ተአማኒነት ይጨምራል፡፡ ወይስ ይሄ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትርጉም የለውም? ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በየደረጃው ውክልና እንዲኖራቸው መንግሥት ያለሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡

ዴቪድ ተርተን የተባሉ ተመራማሪ ‹‹ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ልምድ›› በሚል እንደጻፉት፣ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት አጠቃላይ ሁኔታው ምንም አይወጣለትም ባይባልም እያደር የሚጐለብት ነው፡፡  በያዝነው ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው 5ኛው የዓለም አቀፍ የፌዴራሊዝም ስብሰባ ላይ አቶ መስፍን ገ/ሚካኤል የተባሉ ተመራማሪ ባቀረቡት ጽሑፍ ከመሬትና ድንበር ይገባኛል ጥያቄ ወይም ከማንነት ጋር ከሚያያዙ ግጭቶች በስተቀር የፌዴራል ሥርዓቱ እየጎለበተ ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሪፖርት ይህን የመግለጽ ኃላፊነት እንኳ ባይኖረው እየዳበረ የመጣውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዴት ይክዳል? ለኢትዮጵያውያን የሚወክላቸው መንግሥት (Enclusive and Representative) አላቸው፡፡ ከ1993 እስከ 2003 ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የራሳቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ታሪክ 50 ዓመት ያህል እንዳስቆጠረ ይነገራል፡፡ አቶ ደሳለኝ ራህመቶና ባልደረባቸው ‹‹መያዶች በኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ ባለፈው ዓመት ባሳተሙት ጥናታዊ መጽሐፍ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በንጉሡ ዘመን መንቀሳቀስ የጀመሩት በወሎና በትግራይ ውስጥ ድርቅ ከተከሰተ በኋላ እንደሆነ ጠቁመው፣ ክርስቲያን የአደጋ መከላከል ፈንድ በሚል ስያሜ በ1966 ዓ.ም. የጋራ ማኅበር እንዳቋቋሙ ይጠቅሳሉ፡፡

እነዚህ ማኅበራት ከሚሰጡት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ በተጨማሪ በልማት ሒደት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው እንዳለ ሆኖ የሚቆጣጠራቸው ተቋም ባለመኖሩ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ባለመስፈኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለመነው ገንዘብ የት እንደሚገባ አይታወቅም፡፡ አንዳንዶቹም ቢሮ የሌላቸውና በኃላፊዎቻቸው ቦርሳ (Briefcase NGOs) የሚዞሩ፣ መያዶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርቱ መንግሥት ቀፍዳጅ የበጐ አድራጐት የማኅበራት ሕግ በማውጣቱ ከ10 በመቶ በላይ በጀታቸውን ከውጭ የሚያገኙ በምርጫ ሂደት እንዳይሳተፉ ተደርገዋል ይላል፡፡ ይህ አሠራር አሜሪካ ውስጥም አይፈቀድም፡፡ እነሱ የማያደርጉትን ለሌላው ማዘዝ ምን ይሉታል?

የቄሳርን ለቄሳር
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣውን ዓመታዊ የሰብዓዊ መበት ሪፖርት በተመለከተ በርካታ አገሮች የራሳቸውን መልስ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም ቻይና የአሜሪካንን መንግሥት እ.ኤ.አ 2010 የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ወቀሳ ሰንዝራለች፡፡ ሪፖርቱ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት ዋስትናና የመንግሥት ጉዳዮች ሕግ (Homeland Security and Government Affairs Law) መንግሥት ዜጐችን በሽብር ስም ያለ ምንም ማጣራት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲያስር ይፈቅዳል፣ ስልክ ይጠለፋል፣ ኢንተርኔት ይቆርጣል ሲል ይከሳል፡፡ መረጃ ለማግኘት ሲባል በተጠርጣሪዎች ላይ ግርፋት (Torture) በአሜሪካ የሕግ አስከባሪ አካላት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ቺካጐ ትሪቢዩን ግንቦት 2002 ባወጣው ዘገባ፣ የከተማዋ ፖሊስ ያለምንም የእስር ማዘዣ ወረቀት እንደሚይዝ፣ ከግድግዳና ከብረት ወንበሮች ጋር በማሰር ያሰቃያል ሲል ማውጣቱን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ የዚህች ከተማ ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ እንቅልፍ የመንሳት፣ የመፀዳጃ ጊዜ በመከልከል የማሰቃያ መንገዶችን (Soft tortures) ይጠቀማል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የተካተተው ሌላው ጉዳይ የአሜሪካ ፖሊሶች በንፁሐን ዜጐች ላይ ይፈጸማሉ ያለውን ግፍ ነው፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ የኒውዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት (ኤንዋይፒዲ) በፖሊስ ለተፈጸሙ ጥቃቶች 964 ሚሊዮን ዶላር ካሳ መክፈሉን ጠቅሶ ከጥቃቱ ሰለባዎች ውስጥ በሠርጉ ቀን በ50 ጥይት በፖሊሶች የተገደለ አሜሪካዊ አንዱ ነው፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ አልተጠየቁም፡፡ የፖሊሶቹን በነፃ መፍታታ የጠቀሰው የቻይና ሪፖርት ይህ ምን ዓይነት ፍትሕ ነው ሲል ይጠይቃል፡፡

ከዘረኝነት አንጻር ያለው ግፍ ልክ እንደሌላው የቻይና ሪፖርት ሲያስረዳ 61 በመቶ የሚሆኑ ሂስፓኒክስና 52 በመቶ የሆኑ ጥቁሮች ለዘር መድልዎ የተጋለጡ ናቸው፡፡ አሜሪካ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ መብት ፈላጭ ቆራጮች ነጮቹ እንደሆኑ በመጥቀስ ሁሉም መጀመሪያ ቤቱን ያጽዳ ብሏል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት በዜጐቹ ላይ የሚፈጽመውን የሰብዓዊ ጥሰት ያክል በኢራቅ፣ አፍጋኒስታን እንዲሁም በጓንታናሞ የፈጸመቻቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መለኪያ የላቸውም፡፡ እ.ኤ.አ ከ2003-2009 ብቻ 285 ሺሕ ኢራቃውያን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የሟቾቹ ቁጥር 110 ቢደርስም፣ የተጠየቀ ሰው የለም፡፡ አሜሪካ ያልታሰበ ጉዳት (Collateral damage) እና የሰው ሕይወት የቀጠፈውን ጥይትም ወዳጅ አሩር (Friendly fire) ትለዋለች፡፡ እውነትም ወዳጅ፡፡

አዲስ አስተሳሰብ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ላወጣው ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የሚሰጠው መልስ፣ ‹‹የእኔ ጥፋት ከአንተ የባሰ አይደለም›› የሚለው ሙግት ብዙም ውኃ አይቋጥርም፡፡ እንደ ንጉሥ ዶሮ ለምን ተነካሁ የሚል መልስ መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ ተገቢ ወቀሳና ነቀፋን ማዳመጥ ይገባል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት፣ የእ.ኤ.አ የ2010 የሰብዓዊ መብት ሪፖርት 80 በመቶ ከባለፉት ዓመታት የተደገመና እውነትነት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ቀሪው ክርክር የሚካሄደው በ20 በመቶ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ እሱም ቢሆን በሳይንሳዊ መንገድ ያልተሰበሰበ፣ በድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ የታጀለ እንዲሁም ከሁለተኛ (ደካማ) ምንጮች የተሰበሰበ ነው፡፡ ከዚህ ሪፖርት ማንም ወገን ምንም ትምህርት አይቀስምም፡፡

ሌሎች ተንታኞች የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ከጊዜ ጋር ተራማጅ (Progressive) ሆኖ የታዩ ለውጦችን ማሳየት ነበረበት ይላሉ፡፡ በእርግጥ ሪፖርቱ በተዘዋዋሪም ቢሆን መንግሥት ሙስናን ለመከላከል ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን፣ ሥነ ሥርዓት ያጐደሉ የአዲስ አበባ ፖሊሶችን ከሥራ ማስወገዱን ለሌሎቹም የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ እንዲሁም ከአገራቸው የተባረሩ ኤርትራውያን አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የተሟላ ስዕል አይሰጥም፡፡

የአሜሪካ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ጋር በተያያዘ በሁለም መስክ ምንም ችግር የለም ከሚል መነሻ የሚንደረደር ክርክር ሊቀርብ አይችልም፣ አይገባምም፡፡ ዋናው ጥያቄ አገሪቱ ከየት ተነስታ የት ደርሳለች? ምን አዎንታዊ ተግባራትን አከናውናለች የሚለው ነው፡፡ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፣ አደናቃፊ ቢሮክራሲ ወዘተ ዛሬም የኢትዮጵያ ችግሮች ናቸው፡፡ ማንም አልካደም፡፡ አሁን ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተኩራርቶ የሚቀመጥ ባይኖርም፣ ጅምሮቹን በበጐ ዓይን ማየት ግን ጤነኛነት ነው፡፡ ሁለተኛው አሉ የሚባሉት ችግሮች ከመንግሥት የቁርጠኝነት ማነስ ሳይሆን ከዴሞክራሲ ተቋማት የተጠናከረ አለመሆን ይመነጫሉ፡፡ ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ ከትናንት ዛሬ ተሻሽላለች፡፡ መጪውም ጊዜ ብሩህ ነው፡፡ የነፃው ፕሬስ፣ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ሒደቱ፣ የምርጫ ሥርዓቱ ለውጦች ታይተውበታል፡፡ ስለሆነም ሪፖርቱ ከተጻፈበት ቀለም አንጻር ዋጋ አይኖረው ይሆን ማካተት አለበት፡፡ ጉዞው አሁንም ረጅም መሆኑን ግን የአሜሪካም ልምድ ያሳየናል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ለኢትዮጵያ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለማንም ወገን የሕዝብ ግንኙነት ፍጆታም አይውልም፡፡ ስለሆነም 2011 የተሻለ ሪፖርት ይወጣ ይሆናል፡፡

የቪኦኤው ዘጋቢ ፒተር ኢትዮጵያ ሪፖርቱን ቅርጫት ውስጥ ትጥለዋለች ሲል አቶ ኃይለ ማርያምን ቢጠይቅም፣ ሪፖርቱ ያለበቂ ዝግጅት የተከናወነ በመሆኑ በኮንግረስና የሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ አልያም ለሌላ ክስ ማጣቀሻ ከመሆን ውጭ ብዙም ትርጉም እንደሌለው ይነገራል፡፡ ሪፖርቱ በኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት ላይ ምንም አንድምታ የለውም፡፡ ግንኙነቱን ሁለቱም አገሮች ይፈልጉታል፡፡ በፀጥታ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ መስኮች የጋራ አጀንዳዎች አሏቸው፡፡ ሰላም!!!  የሪፖርተር ጋዜጣን  ለሰጠው ማብራሪያ ፖለቲከኞች ማብራሪያ ለመስጠት የሚፈልጉ ካሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ለማነጋገር ዝግጁዎች ነን ስለዚህ ይህንን ሪፖርት አስመልክቶ በዚህ ጉዳይ ላይ የበለጠ መረጃ ወይንም ማብራሪያ መስጠት የሚፈልግ ሁሉ ዝግጅት ክፍላችን ሪፖርቱን ለመቀበል ዝግጁ ነው ። የአሜሪካንም ሪፖርት በተመለከት በቅርቡ ሰዎችን አነጋገረን ለማቅረብ እንሞክራለን  በቀረበው ሪፖርት ላይ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ የሆነ ሪፖርት እንዳልሆነ ስለተረዳን እና አሜሪካም ያወጣችው አቋም በመጠኑም ቢሆን ሚዛናዊ ያደረገ ያልሆነ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሪፖርተር ጋዜጣ የወጣው ግን ከማንኛውም ሃቅ የራቀ እና ይርጋዜጠኞችን ስነምግባር ሸፍኖ ወገንተናዊነት ያደላ አይነት ስሜት ስላለው ሪፖርቱን እንደገና በጥልቀት ማየቱ ተገቢ ነው እንላለን !

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close