70ኛ ዓመት የድል በዓል ዛሬ ይታሰባል።

“የሀገሬ፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡፡ ዛሬ፡ ኢትዮጵያ፡ እጆቿን፡ ወደ፡ እግዚአብሔር፡ ዘርግታ፡ እልል፡ እያለች፡ ምስጋናዋን፡ የምታቀርብበት፡ ደስታዋን፡ ለልጆቿ የምትገልጽበት ቀን ነው፡፡”

ይህ ቃል ከ70 ዓመት በፊት፣ በዛሬዋ ቀን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም.፣ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት አገዛዝ ባከተመበት የድል ዕለት የቀድሞው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በአዲስ አበባ ከተማ በደረሱ ጊዜ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው።

ከላይ የተጠቀሰው ንግግር ከነሥርዓተ ነጥቡ በአራት ኪሎ በሚገኘውና የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በቆመው የድል ሐውልት ላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ንግግር ሙሉ ቃል ጋር በጉልህ ይነበባል፡፡

ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. አዲስ አበባን የያዘውና ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያልተቆጣጠረው ፋሺስት ኢጣሊያ፣ በእርመኛ አርበኞችና በሕዝቡ ተጋድሎ ከአምስት ዓመታት በኋላ ተጠራርጎ የወጣው በዕለተ ቀኑ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡

የድል ሃውልት በአናቱ ላይ በታላቅ ግርማ ሞገስ የቆመው የዘመኑ ምልክት “የኢትዮጵያ አንበሳ-የይሁዳ አንበሳ”ን የያዘው ትክለ ሐውልት በሥሩ በተለያዩ አቅጣጫዎች በሰው ቁመት ልክ የተቀረጸባቸውን ታሪካውያን ምስል ይዟል፡፡

የሐውልቱ መጠርያ በትክክል ተቀምጧል፡፡ “የድል፡ሐውልት፡Victory Monument” (አንዳንዶች ፖስታ ቤትን ጨምሮ በስህተት እንደጻፉት “የነጻነት ሐውልት” ሳይሆን) የድል ሐውልትነቱ በጉልህም ይነበባል፡፡ በምሥራቅ አቅጣጫ በኩል በሐውልቱ ምሰሶ ላይ “ወልወል ሺ927 ዓ፡ም፡፡ ኅዳር 26፡፡ ይላል፡፡ ኢጣሊያ መዠመርያ ትንኮሳ የከፈተችበት ግንባር መሆኑ ነው፡፡

በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ አንድ ቅርጽ አለ፡፡ ምስሉም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው፣ አንበሳውም ከእግራቸው ሥር ተቀምጦ ይታያል፡፡ ጥቁር አንበሳው ወደ ደቡብ ያማትራል፡፡ ዐፄው ደግሞ ወደ ፀሐይ መውጫ ያተኩራሉ፡፡ ከደንጊያውም ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ፣ በሚያምር የእጅ ጽሕፈት ከነሥርዓተ ነጥቡ ተቀርጾ ይነበባል፡፡

“ከጠላት፡ ጋር፡ ተስማምቶ፡ ከመኖር፡ ሞቱን፡ መርጦ፡ በጦር፡ ሜዳ፡ ላይ፡ የሚገባውን፡ ሠርቶና፡ ደሙን፡ አፍስሶ፡ አምስት፡ ዓመት፡ ሙሉ፡ ሲታገልና፡ ሲሟገት፡ በስደት፡ ላይ፡ ኖሮ፡ እንደገና፡ ከእግዚአብሔር፡ ጋራ፡ በድል፡ አድራጊነት፡ ጠላትን፡ አባርሮ፡ ሰንደቅ፡ ዓላማችንን፡ ለመለሰልን፡ ለቀዳማዊ፡ ኃይለ፡ ሥላሴ፡ የቆመ፡ የዘላለም፡ መታሰቢያ፡፡”

ድሮ ድሮ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች

“ኃይለ ሥላሴ ሐዋርያ

የሰላም መሪ ባለሙያ

ዕድሜ ለተፈሪ ለታላቁ መሪ

የሚደፍርሽ የለም ኢትዮጵያ ኩሪ፤” እየተባለ ይዘመር ነበር።

በሐውልቱ ዙርያ በአዜብ አቅጣጫ (ደቡባዊ ምዕራብ) ላይ ኢትዮጵያውያቱን እርመኛ አርበኞች የምትወክል እንስት ውበትን ከጀግንነት ጋራ አስተሳስራና ተላብሳ ትታያለች፡፡ በግራ እጇ ጋሻዋን፣ በቀኝዋ ደግሞ ጦሯን አቁማ ይዛ በድል አድራጊ ድባብ አሻግራ ታያለች፡፡ አንድም “ንግሥተ አዜብ” መኾኗንም ታሳያለች፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ክብርና አንድነት ለማስጠበቅ በርካታ ኢትዮጵያውያት፣ ብዙ ሴት አርበኞች በዱር በገደሉ፣ በከተማ ውስጥ አርበኝነትም ታጥቀው፣ ፋሺስትን አንበርክከዋል፡፡ የሚያዝያውን የድል መንፈስ ለመዘከር መሰንበቻውን ሳነበው ከነበረው የመስፍን ኃይሉ “አደራ” መጽሐፍ ስለሴቶቻችን ያዘከረውን ከእዚህ ላይ ማንሣት ይገባል።

“ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ለመጥቀስ ያህልም፣ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ፣ የመንዝና ተጉለት አርበኛ ወ/ሮ ዘውዲቱ ግዛውን፣ በሰላሌ ወ/ሮ ከበደች ስዩምን፣ በዋግ ወ/ሮ ሸዋነሽ አብርሃ፣ በአርሲ ወ/ሮ በላይነሽ፣ እንዲሁም ወ/ሮ ልኬለሽ በያን፣ ወ/ሮ አበበች ቂርቆስና ወ/ሮ አየለች የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በትልቅ አኩሪ አርአያነት ግን የሁለት አርበኛ ሴቶችን የጀግንነት ተግባር እዚህ ላይ መግለጽ አስፈላጊ ነው፡፡

የውጭ አገር ፀሐፊው ውሊያም ማኪን በመጽሐፉ እንደገለጸው፣ “… በዶሎ አካባቢ አበሾች በየተራራው ላይ መሽገው የኢጣሊያን መምጣት ይጠባበቃሉ፤ የዚያች ቦታ ጦር መሪ የሆኑት የደጃዝማች ሀብተ ሚካኤል ሚስት ከተራራ ላይ ሆና ስትመለከት የኢጣሊያ ወታደር ሲመጣ አየች፡፡ የኢጣሊያን ጦር ገፍቶ መምጣት እንዳየች፣ የኢጣሊያ ጦር በመምጣት ላይ ነውና ይመታ ብላ ለባሏ ነገረች፡፡ ባልየው ግን ተጨነቀ፡፡ የተጨነቀበትም ዋናው ምክንያት፣ ጥሩ የመከላከያ ቦታ ስለሌላቸው ከኢጣሊያ ወጥመድ ገብቶ መጋጠሙን ፈራ፡፡

ከዚህ በኋላ ሚስቲቱ ከባሏ ተለይታ ወደ ሌላ ሥፍራ ሄደች፡፡ ከዚያም ልብሷን ለዋውጣ እንደ ወንድ ለበሰች፡፡ ፈቃደኛ የሆኑ 150 ሰዎች አዘጋጅታ ከጨረሰች በኋላ ከበቅሎዋ ላይ ወጥታ ገሰገሰች፡፡ ሰዎቿም የጦርነት ጩኸት እየጮኹ፣ ወደሚመጣው የኢጣሊያ ጦር እየሮጡ ሄዱ፡፡ የኢጣሊያ ወታደሮችም በቅሎ በምትጋልብ ሴት የሚመራ ጦር እንደመጣባቸው ባዩ ጊዜ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ውጊያ ገጠሙ፡፡

የአበሻው ጦር አዛዥ የሚስታቸውን ከጠላት ጋር መዋጋት እንደሰሙ ጦራቸውን ይዘው ለእርዳታ ሄዱ፡፡ ደጃዝማች ከውጊያ ቦታ ሲደርሱ ውጊያው አልቆ ረዳት ከማያስፈልግበት ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ብዙ ኢጣሊያኖች ተገድለዋል፡፡ ብዙዎቹ ቆስለዋል፡፡ ያቺ አገሯን የምትወድ ተዋጊ ሴት ከጠላት ብዙ ጠመንጃና ጥይት ማርካ ተመለሰች፤” በማለት ጽፏል፡፡

የሌላዋ ጀግና ሴት ተግባር ደግሞ ከዚህ የሚከተለው ነው፡፡ “በ1929 ዓ.ም. መረባ በሚባለው ጦርነት ላይ ሲዋጉ ባላቸው ልጅ አንዳርጌ ደስታ ከጠላት በተተኮሰ የእሩምታ ተኩስ ተመትተው ይወድቃሉ፡፡ ሚስትየዋ ወ/ሮ ከበቡሽ ደሴ ተኩስ ሲጀምር ጥሩንባ እየነፉ አይዞህ በለው እያሉ ያደፋፍሩ ነበር፡፡ ወ/ሮ ከበቡሽ ተመትተው የወደቁትን ባላቸውን ወደ ጫካ ወስደው፣ ቅጠል አልብሰው ልጃቸውም ዋኘው አንዳርጌ እንዳያይ አድርገው፣ ጠላት እንዳያመልጥ “አባትህ በዚያ በኩል ጠላትን አስጨንቆታል፤ አንተም በርታና ተዋጋ፤ የሰከረ አሳ እንዳያመልጥህ፡፡” እያሉ ሲያደፋፍሩት፣ በኮረብታ ላይ ለማምለጥ የሚታገለው ጠላት ላይ አነጣጥሮ ቢተኩስ፣ የመቶ እልቅና ባለው ወታደር ላይ በአፉ ከተተበትና ተንከባሎ ሲወድቅ፣ እናቱ ወ/ሮ ከበቡሽም፣

“የዋኘው እናት ያንገት አስደፊ፣

ከአፋፍ ላይ ሆኖ ጥሩንባ ነፊ

የበኸር ልጁ ዋኘው አንዳርጌ

የአባቱን ጠላት ጣለው ከግርጌ” እያሉ በመፎከር የተዋጊዎችን ሞራል አነሣሥተዋል፡፡

በመስዕ (ሰሜናዊ ምሥራቅ) አቅጣጫ ሴቷ አክሊሏን አጥልቃ፣ ሾተል ከዘንባባ አዛምዳ ቆማ ትታያለች፡፡ ከሥሯም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡ “ለሀገራቸው፡ ነፃነት፡ አምስት፡ ዓመት፡ ሙሉ፡ በዱር፡ በገደል፡ እየተንከራተቱ፡ ደማቸውን፡ ላፈሰሱና፡ አጽማቸውን፡ ለከሰከሱ፡ ስመ፡ ጥሩ፡ አርበኞች፡ የቆመ፡ የዘላለም፡ መታሰቢያ፡፡”

ዙርያውን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቀውን የድል ሐውልትና አረንጓዴውን አፀድ ሐውልቱን የሚያስተዳድረው ክፍል በሐውልቱ ዙርያ የተጻፉትን ታሪካዊ መልእክቶች ይከታተላቸዋል ወይ የሚለውን ነው?

በሐውልቱ ላይ የተጻፉት አንዳንድ ሆሄያት መጥፋታቸው፣ ጽሑፍ የሰፈረበትና የተሰነጠቀውን ለማደስም በተደረገ እንቅስቃሴ፣ ልስኑ ጽሑፉን ማጥፋቱ ይታያልና ይታሰብበት።

“የድል በዓል የአርበኞቹ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓል ነው፡፡ አፍሪካውያንም የሚያከብሩት፣ የሚያደንቁትም ነው፡፡”

ምንጭ፦ አድማስ ሬዲዮ – አትላንታ !

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close