“ከእያንዳንዱ የህወሀት አመራር ጀርባ ወንጀል አለ”

የአረና ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ

ከፍትሕ ጋዜጣ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ 

አቶ አስራት አብርሃም ይባላል፡፡ የተወለደው በ1970 ዓ.ም በትግራይ ክፍለሀገር፣ ተንቤን አውራጃ ነው፡፡ በተወለደበት ቀዬም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ህፃን የከብት እረኛ ሆኖ ነው ያደገው፡፡ አቶ አሥራት የቄስ ትምህርቱን በተንቤን ተምሮ ኢህአዴግ መላ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በ1984 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ ከዚያም በዲላ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በቋንቋና ሥነ-ፅሁፍ በዲግሪ ተመረቀ፡፡ ከዲላም በቀጥታ ወደ ትግራይ በመሄድ በሽሬ ሁለተኛ ደረጃ ት_ቤት፣ በሽሬ ሚሊንየም ኮሌጅና በአድዋ መምህራን ኮሌጅ በመምህርነትና በሀላፊነት ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ፓርቲ ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ ነው፡፡ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከተመስገን ደሳለኝ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡ 

ፍትህ፤-ወደ ፖለቲካው እንዴት ገባክ?

 

አቶ አስራት ፤– እንደምታወቀው እኛ አካባቢ ደርግም ህወሓትም የነበረበት ነው፡፡ እናም ይሄንን እያየሁ ነው ያደኩት፡፡ ከ1984 ጀምሮ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ ጊዜም የትግራይ ሰው ስለሆንኩ በድፍኑ የህወሓት ደጋፊ ነበርኩ፡፡ እንድያውም በ1989 ዓ/ም በምኖርበት የወረዳ 23 ውስጥ በሚገኘው የወጣቶች ማህበር እንድገባ ጠይቀውኝ አጋጣሚ ሆኖ ወደ ትግራይ ስለተመለስኩ ሳልገባ ቀረው፡፡ እናም ትግራይ ከሄድኩ በኋላ አዲስ አበባ ሲወራ የነበረው እና ትግራይ ያለው በጣም የተለያየ በመሆኑ ለመጀመርያ ስለስርአቱ የተወሰነ ግንዛቤ አገኘሁ፡፡ እዚያም ሌላ ጊዜ  የህወሀት አባል እንድሆን ተጠየኩ እናም አባል የመሆን ፍላጎት እንደሌለኝ ስገልፅላቸው የትግራይ ሰው አይደለህም ወይ ለምንድነው አባል የማትሆነው“ ሲሉኝ የትግራይ ሰው በሙሉ የፓርቲያችሁ ሰው መሆን አለበት ወይ? ብዬ እምቢ አልኩ፡፡ በሂደት የተወሰኑ ወጣቶችም በትግራይ ለሌላ ፓርቲ ያስፈልጋል የሚለው ላይ መነጋገር ጀመርን፡፡

ፍትህ ፤- ይሄ የሆነው ህወሀት ከተከፋፈለ ኋላ ነው ወይስ ከመከፋፈሉ በፊት

 

 አቶ አስራት ፤በተከፋፈለበት አመት ነው፡፡ እዚህ ጋር አንድ ነገር ልንገርክ፡፡ ህወሀት ሲከፈል እኔ ዲላ ዩኒቨርስቲ እማር ነበር፡፡ እናም አንድ ቀን አንድ ልጅ የትግራይ ተወላጆች የሆነውን “ፓርቲያችን ችግር ውስጥ ስለሆነ ተሰባስበን እንነጋገር” አለን፡፡ በዚህም መሰረት ሰበሰበን፡፡ በእርግጥ ስብሰባው ያካሄድነው በመደበኛ ሁኔታ ሳይሆን እንደ ጓደኛ ነው፡፡ እናም በዛ ስብሰባ ላይ የተወሰኑ ተማሪዎች እየተነሱ “ገብሩ አምባገነን ነው“፣ ስዬ ሌባ ነው” እያሉ ሲያወግዙ መላው ተማሪ ደነገጠ፡፡ ምክንያቱም ከዛ በፊት እነዚህ ተማሪዎች ስለስዬም ሆነ ስለ ገብሩ መጥፎ ነገር ተናግረው አያውቁም ነበርና ነው፡፡ ከዛም ”እኛ እንደዚህ አይነቱን ነገር አናውቅም፡፡ ይሄ የሆነ ተንኮል ነገር አለበት “ አለና ተማሪው ከስብስባው ተበተነ፡፡

በእርግጥ ህወሀት ሲከፈል በፓርቲው ውስጥ ከቀሩት አመራሮች ውስጥ የተወሰኑት ከኤርትራ ጋር ንክኪ አላቸው ይባል ስለነበር የኔ ልብ ወደ ወጡት ነበር፡፡ እናም ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ትግራይ እንደተመለስኩ በ1997 ዓ.ም አዲስ ፓርቲ ለማቋቋም መነጋገር ጀመርን ስንቀሳቀስ እነ ገብሩ መረጃው ስለደረሳቸው ፈልገው አገኙንና ተዋወቅን፡፡ ከዚያ ወደ አረና ምስረታ ሄድን ማለት ነው፡፡ የእኔ የፖለቲካ ተሳትፎ ጅማሮ ይህን ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ከፖለቲካው ይልቅ ወደ ስነ ፅሁፍ ነው የማደላው፡፡

ፍትህ ፡- እስከ 1993 ድረስ በትግራይ የነበረው የህወሀት አስተዳደር ዴሞክራሲ ነበር ወይስ አምባገነን? 

 

አቶ አስራት ፤-እንግዲህ ይህንን ለመመለስ ከህወሀት ባህሪ ነው የምትነሳው፡፡ ህወሀት በተፈጥሮው የዴሞክራሲ ባህሪ የነበረው ድርጅት አይደለም፡፡ መጀመርያውኑም በማርክሊዝም-በሌኒኒዝም አስተሳሰብ የሚመራ ነው፡፡ ስለዚህ ጭቆና ነበረ ማለት ነው፡፡ ከ1993 በፊትም ሆነ ከ1993 ኋላ ትግራይ ውስጥ ያለው የህወሓት አስተዳደር ለዴሞክራሲ የሚመች አይደለም፡፡ አዲስ አበባ እንኳ የነበረውን የተወሰነ የመፃፍ መብት በትግራይ ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ከክፍፍሉ በፊት ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ከክፍፍሉም በኋላም የለም፡፡

ልዩነቱ ምንድነው መሰልክ? በዛን ጊዜ ህወሀት ገና አፍላ (አዲስ) ፓርቲ ስለነበርና ገና ከጦርነትም የወጣበት ጊዜ ስለነበር ብዙም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ላይጠበቅ መቻሉ ነው፡፡ በልማቱ ላይ ግን ክልሉን ለማልማት የተወሰነ የመፍጨርጨር ሁኔታ ነበር፡፡ ቢያንስ ህዝቡን አስተባብሮ ድንጋይ መፈንቀል፣ ውሃ መገደብ እና የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ ሳይሆን የህወሀት ንብረት የሆኑት የኢፈርት ድርጅቶች እነ መሰቦ፣ አልመዳ፣ የተተከሉት በዛን ጊዜ ነው፡፡ እናም ከ1993 በፊትም ቢሆን ዴሞክራስያዊ መብቶች አይከበሩም ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ያን ጊዜ የኢዲዩ አባላት ቢሞቱ እንዳይቀበሩ፣ እሳት እንዳይጭሩ ይከለከሉ ሁሉ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከህወሓት ባህሪ ጋር አይሄድም የምልክ፡፡

ፍትህ፡- በአንዳንድ ሰዎች አስተሳሰብ የትግራይ ህዝብ እና ህወሀት የማይነጣጠሉ ተደርጎ የሚቀርቡበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንተስ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ምን ያህል ተጠቅሟል ትላለህ ?

 

አቶ አስራት ፡– እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ወደ 5 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ በህወሀት የሚጠቀመው ስንቱ ይሆናል? የሚለው ነው መታሰብ ያለበት፡፡ የተቀረው የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ያተረፈው ጦርነት ነው፡፡ በደርግ ጊዜም፣ እንደገና ከኤርትራ ጋር በተደረገው ጦርነት፡፡ ሌላው ቀርቶ እዚህ መሀል አገር ያለውን የፈለገውን ፓርቲ የመደገፍ መብት እንኳን አላገኘም፡፡ እናም በአንዳንድ አክራሪዎች እና በህወሀት ሳይቀር የተለየ ጥቅም እንዳገኘ ተደርጎ የሚነገረው ስህተት ነው፡፡

ፍትህ፡- በግልፅ መልስልኝ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት አልተጠቀመም? 

 

 አቶ አስራት ፡- አዎ፡፡ ምንም አላገኘም የተወሰኑ ፋብሪካዎች እዚያ አሉ ተብሎ ይወራል፡፡ ቁም ነገሩ ግን “እነዚህ ፋብሪካዎች የማን ናቸው? “ የሚለው ነው፡፡ ልንገርህ እነዚህ ፋብሪካዎች የህወሓት ናቸው፡፡ ህወሓት እነዚህን ፋብሪካዎች ኦዲት አስደርጎ አያውቁም፡፡ በእነዚህ ፋብሪካዎች ገቢ በትግራይ ውስጥ የተሰራ ትምህርት ቤትም ሆነ ጤና ጣብያ የለም፡፡ ልክ የውጭ አገር ሰው እዚህ መጥፎ ፋብሪካ ቢተከል ያ ፋብሪካ የህዝብ ነው እንደማይባለው ሁሉ እነዚህ ፋብሪካዎች የሚያገለግሉት ለህወሀት እንጂ ለትግራይ ህዝብ አይደለም፡፡ እንዲያውም በአንፃሩ የትግራይ ህዝብ በፊት ወደ ኤርትራ ወደ ሱዳንም እየተመላለሰ ሰርቶ ይበላ ነበር፡፡ አሁን ያ የለም፡፡ ታጥሮ ነው ያለው፡፡ የትግራይ ህዝብ በፊት በቀላሉ በምፅዋ በኩል የውጭ ዕቃ ማስመጣት ይችል ነበር፡፡ አሁን በበርበራ፣ በጅቡቱ፣ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር ዞሮ ነው የሚደርሰው፡፡ እናም በአጭሩ የትግራይ ህዝብ በዚህ ስርዓት መጠቀሚያ ነው የሆነው እንጂ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡

አንዱ ችግር ምን መሰለክ? “የትግራይ ህዝብ ተጠቀመ” የሚሉ የተወሰኑ ሰዎች ምንም አይነት መረጃ የሌላቸው ወይም ሄደው ያላዩ ናቸው፡፡ በሆነ አጋጣሚ ትግራይ የሄዱ ሰዎች ግን ተገርመው ነው የሚመለሱት፡፡ አንዱ ችግራችን እኛ ኢትዮጵያውያኖች ተዛዙረን አገራችንን አለማየታችን ነው፡፡ ነገር ግን በአመት አንድ ክልል የማየት እቅድ ቢኖረን በ12 ዓመት ሁሉንም ክልሎች እናይ ነበር፡፡ እንደ ባህል ግን የተወለድንበት አካባቢ እንሄዳለን እንጂ ሌላው አካባቢ ሄደን “ህብረተሰቡ እንዴት ነው የሚኖረው? የሚለው አናይም፡፡ እናም ይሄ የመረጃ እጥረት ይፈጠራል፡፡ አዲስ አበባ ወይም ውጭ አገር ከህወሀት ተጠግተው የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ብቻ በማየት የትግራይ ህዝብ እንዲህ ነው የሚኖረው ማለት አንችልም፡፡

ፍትህ፡- በዚህ አይነት አስተያየት የሚሰጠው በአገሪቱ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች መከላከያ እና ደህንነትን ጨምሮ የትግራይ ተወላጆች በሀላፊነት በመኖራቸው መሰለኝ?

 

 አቶ አስራት ፡- አንድ ነገር ልንገርህ ፣ ኢህአዴግ የተፈጠረው የህወሀት ታጋዮች ላይ የተወሰኑ ለሌሎች ሰዎች ተጨምረው ነው፡፡ ያ ሁኔታ የፈጠረው ነገር አለ፡፡ ከዛ በተረፈ የትግራይ ሰዎች ወደ ሰራዊቱ የመግባት ፍላጎት የላቸውም፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት ወታደር መሆን የሚፈልግ የትግራይ ሰው ባለመኖሩ ተስፋ ቆርጠው ትተውታል፡፡ ስለዚህም በስልጣን ላይ የተወሰኑ ጄነራሎች እና ኮለኔሎች አሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ከሃምሳ አይበልጡም። እነዚህም ቢሆኑም ለአቶ መለስ በጣም ታማኝ የሆኑ ናቸው፡፡ እንድያውም ከትግራይ አልፈው የአንድ አካባቢ ተወላጆች በመሆናቸው ነው። ሌላው ቀርቶ እራሳቸው አቶ መለስ የትግራይ ህዝብን ይወክላሉ ብዬ አላስብም፡፡ ልክ እንደ አቶ አባዱላ ማለት ነው፡፡ አቶ አባዱላ የኦሮሞን ህዝብ ይወክላሉ እንዴ? እናም ሀምሳ ሰዎች እዛ ውስጥ ስላሉ 5 ሚልዮን ሰዎች ይወክላሉ ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥ ችግር አለው፡፡ ፍትሃዊነት እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ስርዓቱ መጀመሪያ ላይ ስልጣን ላይ ሲደላደል ያደረገው የህወሀት ታጋዮችን ማሰር ነው፡፡ ምክንያቱም በርሃ እያሉ ይሸውድዋቸው ስለነበር ነው፡፡ ይሄ የሚያሳየው ስርዓቱ ለአንድ ህዝብ ሳይሆን ለስልጣን የታገለ መሆኑን ነው፡፡ እናም ስልጣን ያገኙት እነዚህ ሰዎች የትግራይ ተወላጆች ስልሆኑ ሳይሆን፣ ለስርዓቱ ታማኝ ስለሆኑ ነው፡፡ በደርግ ውስጥም እኮ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ፡፡ እነ ፍስሃ ደስታን የመሳሰሉ፡፡ ሌላው መታሰብ ያለበት በሰራዊቱና እና አሉ ያልናቸው ሀላፊዎች የተሾሙት በትግራይ ተወላጆችነታቸው ሳይሆን ስልጣን ላይ ላሉት ሰዎች በተለያዩ መንገድ በጋብቻውም በደምም በመሳሰሉት የተዛመዱ ስለሆኑ ነው፡፡

ፍትህ ፡- አቶ አስራት ከፖለቲካ ይልቅ ወደ ስነ ፅሁፍ አደላለሁ ብለሃል፡፡ ምን ያህል መፅሀፍ ፅፈሃል ? 

 

 አቶ አስራት፡- ሁለት መፅሃፍ! “ጎበዝ ተማሪ የመሆን ምስጥር” የሚልና “ከአገር በስተጀርባ” የሚል መጽሐፍ አሳትሜአለሁ፡፡ ለሌላ ሶስተኛ መጽሐፍ አልቆ ለህትመት እየተዘጋጀ ነው፡፡

ፍትህ፡- “ከአገር በስተጀርባ” የሚለው መፅሐፍ ስለምንድን ነው የሚያወራው? 

 

አቶ አስራት ፡- ይህ መጽሐፍ የሚያወራው የህወሀት የውስጥ ባህሪን እያንዳንዱ የህወሓት አመራር ስለስራው ሀጢአት ነው፡፡ እያንዳንዱ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የፈለገው ታጋይ ላይ የፈለገውን እርምጃ የመውሰድ ስልጣን ነበረው፡፡ ከዛም ባሻገር ትግራይ ውስጥ ሌላ TLF የሚባል ፓርቲ ነበር፡፡ እሱን እንዋሃድ ብለው ጠርተው ከተዋሀዱ በኋላ ለሊት አመራሩን ገድለው ፓርቲውን የአጠፋበት ሁኔታ አለ፡፡ ይሄ ትልቅ ክህደትም ወንጀልም ነው፡፡ እንዲያውም ህወሀት ሌላ ፓርቲ እንዳይጠጋው ከነበረው አንዱ ችግር ይሄ ነው፡፡ ኢህዴን እስኪፈጠር ህወሀትን አምኖ የሚጠጋ ፓርቲ አልነበረም፡፡ አንድ ስለማፍያዎች የሚነገር አባባል አለ “ከእያንዳንዱ ሀብት በስተጀርባ አንድ ወንጀል አለ“ የሚል! ይህን ወደ ህወሀት ስታመጣው “ከእያንዳንዱ የህወሓት አመራር በስተጀርባ ወንጀል አለ“ ማለት የሚቻልበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ፍትህ፡- በህወሃት ለተሰሩ ወንጀሎች ይበልጥ ተጠያቂው ማን ነው?

 

አቶ ኣስራት ፡-  የህወሀት አመራርን ስታየው እንደ አንድ ቡድን በተለያየ ጥቅም እና ስልጣን ስለተሳሰረ ለክፋቱ እና ለሽሩ መዘህ የምትወጣው ሰው ላይኖር ይችላል፡፡ እናም የህወሓት አምባገነንነት በግሩፕ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን በሂደት አቶ መለስ ብቸኛ አምባገነን ሆነዋል፡፡ መለስ እዚህ ደረጃ እስኪደርሱ ግን የህወሓት አመራር የቡድን አምባገነንነት ነበር እንደ አንድ ሰው ያስባሉ እንደ አንድ ሰው ይናገራሉ፣ ሚስጥር አያወጡም፡፡ እርስ በእርስ የሚያጣላ ነገር እንኳ ቢኖር እዛው ያፍኑታል፡፡ እነ አረጋዊ በርሄ የተወገዱትም በዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም ልዩነት ያላቸው ሰዎች ልዩነቱን ወደ ታች ወደ ታጋዩ ስለማያወርዱት ነው፡፡

 

ፍትህ፡- በመፅሀፍህ ላይ የህወሀትን ታሪክ በአዲስ መልክ ለመፃፍ ለመቀሌ ዩኒቨርስቲ 43 ሚሊዮን ብር እንደተመደበ ገልፀሀል፡፡

ለዚህ ማስረጃ አለክ? 

 

አቶ አስራት ፡- ይሄንን መረጃ የአገኘሁት አቶ አስገደ ገ /ስላሴ “ፅናት” ለተባለው መጽሐፍ በሰጡት መልስ እና በሌላ ሰነድ ላይም ስለአየሁት ነው፡፡

 

ፍትህ፡- አሁን እዛው መጽሀፍክ ላይ ህወሀት በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች ክልሎች የራሱን ሰዎች ያስቀምጥ ነበር ስትል የገለፅከውን አብራራው እስቲ?

 

አቶ አስራት ፡-ይሄ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በኦሮምያ እነ ሰለሞን ጢሞ፡በደቡብ እነ ቢተው በላይ ነበሩ፡፡ እንዲያውም አንድ አጋጣሚ ልንገርህ “አንድ ትግርኛ የሚናገር የአዲስ አበባ ልጅ በአቶ አባተ ኪሾ ጊዜ አዋሳ ሄዶ ከደህንነት መ/ቤት እንደመጣ ሆኖ በመቅረቡ መኪና ተመድቦለት አስተዳደሩን ሲያሽከረክር የነበረበት ነገር ነበር፡፡ ይሄ በራስ መተማመን ያለመኖሩ ያሳያል፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው ያለአንድ ማስረጃ እንዲህ ማድረግ ሲችል ምን ትላለለህ ፡፡ በዛን ወቅት በኦሮምያ በደቡብ የነበሩት አስተዳደሮች ተላላኪዎች ስለነበሩ ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ በሰፊው ይታወቃል፡፡ ከህወሀት ከወጡ አንዳንድ አመራሮችም ሰምቻለው፡፡

በየክልሉ አስተዳደር እንዲሆኑ የተደረጉት ተራ ወታደሮች እና አስር አለቃ የነበሩ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ አንድ አስር አለቃን ከመሬት አንስተህ ሜጀር ጀነራል ብታድርገው የሚኖረው አቅም ያው የአስር አለቃን ነው፡፡ ይሄ እድገት ከአቅም እና ከልምድ ጋር ብቻ ነው መምጣት ያለበት፡፡ ተራ ወታደር የነበርን የአንድ ክልል አስተዳደር የእከሌ ሚኒስተር ብታደርገው፣ ያ ሰው የሚኖረው አቅም ልክ ተኩስ ሲባል እንደሚተኩስበት ጊዜ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጠንካራ ጠንካራ የህወሀት ሰዎች ከኋላ ሆነው እያሽከረከሩ የሚመሩበት ሁኔታን የፈጠሩት፡፡ ይሄንን ልምድ ደግሞ ከሻዕቢያ ነው ያገኙት፡፡ ሻዕቢያ ህወሀትን ብእነ ሙሴ እና ጃማይካ አማካኝነት ለማሽከርከር ያደረገው ሙከራ ህወሀትም መጀመርያ በኢህዴን ላይ ሞከሩት፡፡ አዋጭ ሆነ፡፡ ከዛም ኦህዴድ ላይ አደረጉት፣ በጣም አዋጭ ሆነ-ኦነግን አጠፋበት፡፡ ከዛ ደቡብ ላይም አደረጉት፡፡

ፍትህ ፡- በደቡብ እና በኦሮምያ የነበሩት የህወሀት ሰዎች በአሁኑ ወቅት ከድርጅቱ ከወጡት ሰዎች ጋር ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ተነስተው ይህንን ስራ ይሰራ የነበረው ከህወሀት የወጣው ቡድን ነው ማለት እንችላለን?

አቶ አስራት ፡-  አንድ ነገር ልንገርህ በፓርቲው ውስጥ እስካሉ ድረስ የህወሓት አመራር አፈንጋጩም ሆነ በህወሀት የቀረው አንድ ናቸው፡፡ እንደ ሶስቱ ስላሴዎች አንድም ይሆናሉ ሶስትም ይሆናሉ፡፡ በአካል ሶስት በአስተሳሰብ አንድ እንደማለት ነው፡፡ አስራ ምናምን ቢሆኑም አንድ ናቸው፡፡ ቀረ ወጣ የምትለው የለም፡፡ በጋራ ሲሰሩት የነበረው ነው፡፡ ዋናው ነገር መታየት የአለበት ጉዳይ እነዛ ከወጡ በኋላስ የተሻለ ነገር መጣ ወይ? የሚለው ነው፡፡ የተለየ ነገር የለም፡፡ ልዩነቱ በፊት ህወሓት በአንድ አምባገነን ቡድን ይመራ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት እየተመራ መሆኑ ብቻ ነው ፡፡

ፍትህ፡- አሁን ያለው ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን ከ1993 በፊት ከነበረው የተሻለ መሰለኝ?

 

አቶ አስራት ፡- የተሻለማ ቢሆን ኖሮ “አቶ መለስን አሁን ደግሞ ይብቃዎት እኛ እንተካ ይሉ ነበር፡፡ እንግዲህ 20 ዓመት ሙሉ አንድ ሰው ስልጣን ላይ ሲቀመጥ እነዚህ ፓርቲዎች የመጠየቅ ሞራል እንደሌላቸው ነው የሚያሳየው፡፡ ብእርግጥ በብዛት አባላትን በማሰባሰባቸው የተሻለ አቅም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የአቶ መለስ ስልጣን ከመጠበቅ ውጭ የተሻለ አመራር መስጠት እንችላለን ብለው ሊመጡ አልቻሉም፡፡

ፍትህ፡- ወደ ፓርቲያችሁ አረና እንመለስ አረና ትግራይ ላይ እንዴት እየተንቀሳቀሰ ነ? እንቅፋት አለባችሁ እንዴት?

 

አቶ አስራት፡- ገና ሲቋቋም በእንቅፋት የተሞላ ሁኔታ ነው የገጠመው፡፡ ከተቋቋመ ኋላ እና የምዝገባ ሰርትፍኬት እንደተቀበለ ደግሞ ህወሓት “አረናን እንዴት ነው የምናጠፋው“ የሚል ባለ 18 ገፅ ሰነድ አዘጋጅቶ ለአባላቱ የበተነበት ሁኔታም ነበር፡፡ በተጨማሪም በአባሎቻችን ላይ ተደጋጋሜ እስራት እና ከስራ መፈናቀል ደርሶአል፡፡ እንደምታስተውሰው በ2002 ምርጫ ዋዜማ ተወዳዳሪያችን የነበረው አረጋዊ ገ/ዮሐንስ የተባለ ወንድማችን ህይወቱ አጥተዋል፡፡ አሁንም እንቅፋት አለ፡፡ ፓርቲውን ለመከፋፈል ሴራ እየተጎነጎነ ያለበት ሁኔታም መጠቀስ የሚችል ነው፡፡

ፍትህ፡- በትግራይ ምን ያህል ቢሮዎች አላቸው?

 

አቶ አስራት፡- እንግዲህ ከ2002 ምርጫ በፊት በመቀሌ፣ በዓባዪ ዓዲ፣ እንዳስላሴ ሽሬ፣ አዲግራት፣ አድዋ፣ ማይጨው እና አላማጣ ቢሮዎች ነበሩን፡፡ የአድዋው ስለ ተዘረፈ ተዘግቷል፡፡ በአቅም እጦት የተዘጉም አሉ፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ጽህፈት ቤት ያሉን በመቀሌ፣ በአዲግራት እና በአብይ ዓዲ ብቻ ነው፡፡

ፍትህ፡- እንደሚታወቀው ህወሓት ለትግራይ ህዝብ እንደ ባለውለተኛ ነው የሚታየው ከዚህ አኳያ አረና ሊቋቋመው ይችላል እንዴ?

አቶ አስራት፡- ህወሀት መታየት ያለበት እንደ አንድ ፓርቲ ነው፡፡ይሄ ከሆነ ደግሞ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚደገፈውም የሚቃወመውም ይኖራል ማለት ነው፡፡ ህወሀት ማለት በትጥቅ ትግል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ እና ደርግን የገረሰሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ህወሀት ለትግል የተነሳው አምባገነን ስርዓት አስወግዶ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ለማስፈን ቢሆንም፣ ይህ አልሆንም፡፡ ያን ድል ወደ ህዝብ ጥቅም ለመለወጥ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ህዝቡ በህወሀት ላይ ያለው አመለካከት እየተሸረሸረ ስለሄደ ህዝቡ ሌላ አማራጭ ኃይል እየፈለገ ባለበት ጊዜ ነው አረና የተመሰረተው፡፡ እናም የህወሀት አካሄድ ያልጣመው ህዝብ በብዛት አለ፡፡ በተለይም ከኢትዮጵያ አንድነት አንፃር፣ ከሉአላዊነት አንፃር፣ ከማህበራዊ አንፃር፣ ከኢኮኖሚ አንፃር ጥቅማችንን አጣን የሚል አመለካከት ህዝቡ እየያዘ ነው የመጣው፡፡ ለዚህም ነው በ2002 ምርጫ አረና እንደ ህወሀት ሁሉ በትግራይ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለክልል እና ለፌደራል ም/ቤት እጩ ያቀረበበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ የተፈጠረው አረና ጠንካራ በመሆኑ ነው፡፡

ፍትህ፡-አረና ትግራይ ውስጥ ከአንድ ፓርቲ የሚጠበቀውን ያህል እየሰራ አይደለም የሚባል ነገር አለ?

 

አቶ አስራት፡-እንግዲህ ምንድነው አንድ ፓርቲ የራሱ የሆነ እድገት አለው፡፡ አረና ሲፈጠር የነበረው የፖለቲካ ምህዳር ለተቃዋሚ ፓርቲ ጥሩ አልነበረም፡፡ ሌላው ፓርቲው ከተመሰረተ ገና 3 አመቱ ነው፡፡ እናም በዚህ ውስጥ ሊሰራ የሚገባው ያህል ሰርቶአል፤ እየሰራም ነው ብለው እናስባለን፡፡

ፍትህ፡- በቅርቡ በመቀሌ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከመኖርያቸው እንደተፈናቀሉ ተሰምቶአል፡፡ ፓርቲያችሁ በዚህ ጉዳይ የወሰደው አቋም አለ?

አቶ አስራት፡- በቅርቡ በመቀሌ አካባቢ  ወደ ስድስት ሺ የሚጠጉ ቤቶች ፈርሰዋል ፡፡ እንግዲህ በእያንዳንዱ ቤት 3 እና 4 ሰው ይኖራል ብለን ብንገምት ከ20 ሺ ሰው በላይ ተፈናቅሏል ማለት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አረና መግለጫ ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንዳለ አመራሩ ተነጋግሮ “መግለጫ መውጣት ያለበት በመድረክ በኩል ነው፡ ምክንያቱም አረና የመድረክ አባል ፓርቲ ነውና“ የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ በመድረክ በኩል መግለጫ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በአማረኛ ጀርመን ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ እኔ እና አቶ ገብሩ አስራት ስለሁኔታው መግለጫ የሰጠንበት ሁኔታ አለ፡፡ ዝም አላልንም፡፡ ነገር ግን የፈለግነው ያህል ድምፃችንን ለማሰማት እድል የለም፡፡ ምክንያቱም አካባቢው ከሚዲያ በጣም የራቀ ስለሆነ ነው፡፡

ፍትህ፡- እነዚህ የተፈናቀሉ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በምን ሁኔታ እንዳሉ ልትነግረኝ ትችላለህ?

 

አቶ አስራት፡- እነዚህ ሰዎች ቤታችሁ ይፍረስ ሲባሉ “ለቤቱ ህጋዊነት አስተዳደሩ እውቅና እንደሰጣቸው፣ በምርጫ ወቅትም ለአካባቢው የምርጫ ጣቢያ እንዲቋቋም መደረጉ መንግስት ህጋዊ መሆናችንን ታውቆ በስፋት የተቋቋመበት አካባቢም ነው ስለዚህ ህጋዊ አይደላቹም መባሉ አግባብ አይደለም“ በሚል ህዝቡ ሰልፍ ወጣ፡፡ በዚህ ጊዜም ሰልፈኛው በፌደራል ፖሊስ ተከቦ ተወካዮች የሚሰጠውን መልስ ሲጠበቁ በፌደራል ፖሊሶች እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡ ከዚያም በሀይል ቤቶቹን ለማፍረስ ሲሞክሩ ነዋሪው ተቃውሞውን ሲያሰማ በአስለቃሽ ጭሽ እና በዱላ ተቃዋሚውን አቁመው ቤቱን አፈረሱት፡፡ በአሁኑ ወቅትም እነዚህ ሰዎች በቤታቸው ፍራሽ ላይ ዳስ ሰርተው ተጠልለው ነው ያሉት፡፡ ምክንያቱ እነዚህ ሰዎች ቤት መከራየት እንኳን ቢፈልጉ በመቀሌ በቂ ቤት ሊያገኙ ስለማይችሉ ነው፡፡

ፍትህ፡- ሌላ ጥያቄ ላንሳልህ ፡፡ እንደ ፖለቲከኛነትህ የሰሜን አፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አብዮትን እየተከታተልኩ ነው?

 

አቶ አስራት፡- አዎን፡፡ ይሄ ነገር እንደተፈጠረ በአልጀዚራ፣ በቢቢሲ፣ በጋዜጦች እና ፌስ ቡክን ጨምሮ በተለያዩ ድህረ ገጾች እየተከታተልኩ ነው፡፡ ምክንያቱም እስከዛሬ ድረስ እንደምናውቀው በህዝብ ያልተፈለገ አንድ ስርአት የሚወገደው አንድም በምርጫ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በጠመንጃ ሀይል በማንበርከክ ነው፡፡ አሁን በግብጽና እና በቱኒዚም የሆነው ነገር የተለየ ነው፡፡ አጀማመሩ ብናየው መሀመድ ቦአዚዝ በተባለ አትክልት አዛሪ ነው፡፡ ይሄ ወጣት ዩኒቨርስቲ ድረስ ተምሮ ቢመረቅም ስራ ሊያገኝ አልቻልም፡፡ የዚያ አገር መንግስት ለስራ አጦች የስራ እድል አልፈጠረም፡፡ እናም ይሄ ወጣት ጎዳና ላይ አትክልት ሲቸረችር ፖሊሶች አትክልቱንና ሚዛኑን ከመንጠቃቸውም ባሻገር አንዲት የፖሊስ ሀላፊ በጥፊ መታችው፡፡ ይሄ ወጣት ከዚህ ኋላ ተዋርዶ መኖርን አልፈለገም፡፡ ስለዚህ ራሱን በእሳት አቃጥሎ አጠፋ፡፡ ይህም ህዝባዊ ቁጣ በመቀስቀሱ ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን አበረረ፡፡ በዚህ ሳያቆም ወደ ግብፅ ሄደ፡፡ ለሙባርክም ተረፈ፡፡ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ  አዲስ ክስተት ነው አዲስ ክስተት በመሆኑ በደንብ እከታተለው ነበር፡፡

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ በነዚህ አገራት ተቃውሞ የቀሰቀሱት ችግሮች በእኛም አገር ስላሉ ነው፡፡ አንዱን ቸግር ብናየው ስራ አጥነት ነው፡፡ ስራ አጥነት ደግሞ እኛ አገርም በከፍተኛ ሁኔታ አለ፡፡ ሙስና በሁለተኝነት ይጠቀሳል ፡፡ሙስናም እኛ አገርም በስፋት አለ፡፡ በሶስተኛነትም የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ ይሄም ቢሆን ከዛም በባሰ መልኩ ነው እዚህ ያለው፡፡ የፍትህ አለመኖር፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማፈን የመሳሰሉት እዛም አለ፡፡ እዚህም አለ፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤን አሊም ሆኑ ሁስኒ ሙባርክ የፓርላማው ወንበር ከ90 በመቶ በላይ ፓርቲያቸው እንዲቆጣጠር አድርገዋል፡፡ ተቃዋሚዎች ምንም ድመፅ እንዳያገኙ ያደረጉበት ምርጫ አካሄደዋል፡፡ይሄ ሁኔታ ከዛ ብሶ 99.6 በመቶ ገዥው ፓርቲ የፓርላማው ወንበር የተቆጣጠረበት ሁኔታ እዚህም አለ፡፡ ስለዚህ በግብጽ እና በቱኒዚያ ያለው ሁኔታ በእኛም አገር አለ ካልን ያ ሁኔታ በእነሱ አገር ህዝባዊ ተቃውሞ ካስነሳ በእኛ አገርስ ምን ሊነሳ ይችላል? የሚለው ነገር ማወቅ እፈልግ ስለነበር በተቻለኝ አቅም ሁኔታውን እከታተል ነበር፡፡

ፍትህ፡ የአረብ አገራት ተቃውሞ ዋነኛ ምክንያት ስልጣን በቤተሰብ በመያዙ ነው፡፡ እዚህ አገር ግን በፓርቲ የተያዘበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ታድያ ይህ ልዩነት አይደለም?

አቶ አስራት፡- እንግዲህ ቤተሰብ ሲባል ምንድን ነው? እነ ሙባርክ የሚመስላቸውን ቤተሰቦቻቸውን እና ጓደኞቻቸውን ነበር የሚሾሙት፡፡ በኢህአዴግስ ምን እየተደረገ ነው? ስልጣን ላይስ ያለው ማነው? ብለን ብንጠይቅ አብዛኛዎች የአቶ መለስ ዜናዊ የአንድ ክልል ሳይሆን እታች ወርዶ የአንድ ሰፈር ሰዎች ናቸው፡፡ አልፎም ተርፎም ባለቤታቸው ወደ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚነት አምጥተዋል፡፡ከዚህ ሁሉ የኢህአዴግ አባላት ከእሳቸው የተሻለ ሴት አመራር ጠፍቶ ነውን? አይደለም፡፡ ልንገርህ ለዚህ ቦታ የያበቃቸው ብቸኛው ምክንያት የአቶ መለስ ባለቤት ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ በቤተሰብ፣በጓደኝነት፣ በወንዘኝነት መሾም ከአረብ አገራት በማይተናነስ መልኩ እዚህም አለ፡፡

ፍትህ፡ ግን እኮ የአረብ አገራት በታቃውሞ እየታመሱ እያለም የኢትዮጵያ መንግስት ግዙፍ ግድብ በአባይ ላይ ለመገንባት ማቀዱን ይፋ በማድረጉ ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገለት ነው፡፡ ይሄ ታድያ መንግስተት ከህዝቡ ድጋፍ እንዳለው አያሳይም እንዴ?

 

አቶ አስራት፡- ይሄ የተለየ ነገር ነው፡፡ አባይን ለመገደብ የሚደረገውን እንቅስቃሴ መደገፍ እና የስርዓቱን ብልሹ አሰራር መቃወም የተለያየ ጉዳይ ነው፡፡ አባይ እንዲገደብ ማንኛውም ዜጋ የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ኢህአዴግ ገደበው፣ ሌላ ፓርቲ ገደበው ማንም ሰው አይቃወምም፡፡ ነገር ግን አባይ ለሌላው ጥያቄ መሸፈኛ መሆን የለበትም፡፡ የዴሞክራሲ ጥያቄ አለ፣ የፍትህ ጥያቄ  አለ ፣ የስርአት ለውጥ ጥያቄ አለ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄ እንደ ጉቦ ሆኖ ማገልገል የለበትም፡፡ ስለዚህ ህዝቡ እየደገፈ ያለው ምንም ይሁን ምን አባይ ተገድቦ መጠቀም አለበን ከሚል ስሜት ነው እንጂ ለስርዓቱ የሰጠው ደገፍ አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ አንድ መንግሥት መንግስት የሚሆነው ቤተ መንግስት ለመቀመጥ ብቻ አይደለም፡፡ ግድብ ለመሥራት፣ ሆስፒታል ለመገንባት፣ መንገድ ለመሥራት፣ ት/ቤት ለመክፈት ነው፡፡ ይሄ ሥራው ነው፡፡ ይሄ ግደብ የሚገድበው ደግሞ አቶ መለስ ከኪሳቸው በሚያወጡት ወጪ አይደለም፡፡

ሌላው ጉዳይ ይሄ ለአባይ ተብሎ የሚሰበስበው ገንዘብ ከሙስና በጠራ ሁኔታ በሥራ ላይ ይወላል አይውልም የሚለውም አሳሳቢ ነው፡፡ የግንባታው ሥራ የተሰጠው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ራሱ መስፈርቱ አይታወቀም የተመረጠበት ማለቴ ነው፡፡ ለህዝቡ ማንም የነገረው የለም፡፡ ብር ግን አዋጡ እየተባለ ነው፡፡ ይሄ ግድብ የሚሠራው በሕዘብ ብር ነው፡፡ በአቶ መለስ ብር አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ አቶ መለስ እስከ አሁን ድረስ ከደመወዛቸው ስንት ፐርሰንቱን እንዳዋጡ አላውቅም፡፡ ደመወዜ 6 ሺ 4 መቶ ነው ብለዋል፡፡ የአንድ ወር ደሞዛቸው ሰጥተው እንደሆነም አልሰማንም፡፡

ፍትህ፡ለፓርትያችሁ አባላት እና ደጋፊዎች የምታስተላልፈው መልእክት ካለ እድሉን ልስጥህ?

 

አቶ አስራት፡- ጥሩ በሰላማዊ ትግል በሚታገለው መድረክ ውስጥ ላሉ አባላትና ደጋፊዎች የማስተላልፈው መልዕክት ትግል ቀጣይነት አለው፡፡ በተለይ ሠላማዊ ትግል በየጊዜው በሚካሄዱ ለውጦች የሚመጣ ስለሆነ ተስፋ ሳንቆርጥ መታገል አለብን እላለሁ፡፡ በተጨማሪም ለመድረክ አመራር አባላት ፓርቲያችንን ወደ ግንባር የምናሸጋግርበት ዕድል በቶሎ እንዲፈጠር በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close