መራር ትዝታ ስለ አቶ መለስ አሻንጉሊት ‘ፓርላማ’

ሀብታሙ አሰፋ

ፓርላማ ሲባል ለብዙዎች በአይነ ህሊና የሚታየው በህዝብ የተመረጡ እንደራሴዎች የሚገኙበት፣ የአገሪቱ የበላይ ባለስልጣን አድርገው ይቆጠራሉ። በአንዳንድ አገራት በእርግጥም የፓርላማ ትርጉሙ እንዲያ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን የአንድ ዘረኛና የአፈና ስርዓት መቀለጃ አባላቱ ከሰውነት ክብር ተዋርደው ለገዥው ፓርቲ እንደ እቃ የሚቆጠሩና ያንኑ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።

አንባቢ ስለ አቶ መለስ አሻንጉሊት ፓርላማ ጥቂት ተጨማሪ ግንዛቤ ያገኝ ዘንድ በአገር ቤት በዚህ መቀለጃ ፓርላማ ለሪፖርት በተመላለስኩበት ወቅት ከታዘብኩት ጥቂቶችን ላካፍላችሁ።በኢትዮጵያ ህገ መንግስት የአገሪቱ የበላይ ባለስልጣን አቶ መለስ በጉልበት የሚመሩትን ስራ አስፈፃሚ የሚቆጣጠር፣ ህግ የማውጧት ስልጣን ያለው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሚባለው ነው። ይሄ በወረቀት ላይ የቀረ ተረት ነው።

ማክሰኞና ሀሙስ ማለዳ የአቶ መለስ ፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል። በህጉ መሰረት በዚህ መደበኛ ስብሰባ የሚቀርቡ ጉዳዮች ለአባላቱ ቢያንስ ከ48 ሰዓት በፊት በፁሁፍ እንዲያውቁት ይደረጋል። የህግ ረቂቅ ከሆነ ኮፒውን የማግኘት መብት አላቸው። ብዙ ጊዜ አንዳንድ የተቃዋሚ አባላት ለውጥ ባናመጣም ለምን ህጉ ተከብሮ በሰዓቱ በም/ቤቱ የምንወያይበት ጉዳይ አይሰጠንም ብለው ጠይቀው ደክሟቸው ትተውታል። አባላቱ ከገቡ በሁዋላ በየፊታቸው ይታደረላቸዋል።

ማለዳ ወደ ፓርላማ ለዘገባ ስገባ ከአዳራሽ ውጭ አንዳንዴም አራት እና አምስት የቡድን ስብሰባዎች ይስተዋላል። እነ አቶ መለስ ለህውሃት(ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ)፣ለብሄረ አማራ ዴሞክራሲአዊ ንቅናቄ(ለብአዴን)፣ለኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ለኦህዴድ)፣ለደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ለደህዴግ)፣ ለአጋር ድርጅቶች(የሱማሌ፣አፋር፣ቤንሻንጉል፣ጋምቤላ፣ሐረሪና ለአዲስ አበባ አስተዳደር ተወካይ ተብዬዎች በም/ቤቱ ጠርናፊዎች በኩል በሰጡት ትእዛዝ ሳይስተጓጎል  የሚሰራ ስራ ነው። ጠርናፊው የቡድን አባላቱን ሰብስቦ ወደ ም/ቤቱ ሲገቡ እሱን ተከትለው እጅ እንዲያወጡ የተለመደ ትእዛዙን ያስታውሳል። ብዙ ጊዜ ራሳቸው ጠርናፊዎቹ በእለቱ ስለሚወጣው አዋጅ የሚያውቁት ስለሌለ ብቻ አታውቁም እንዳይባሉ ከበድ ያለ ጉዳይ ስላለ እንወስናለን የሚል ገለፃ ያደርጋሉ።

በቡድን ተከፋፍለው በጠርናፊ ትእዛዝ የተሰጣቸው አባላት ወደ ም/ቤቱ ገብተው አንዳንዴ ከፊትአቸው ተቀምጦ አንዳንዴ ከተቀመጡ በሁዋላ የሚታደላቸውን የአዋጅ ጥራዝ አንዳንዶቹ ለይስሙላ ሲያገለባብጡ የቀሩት ከወደቀበት ሳያነሱት እጅ የሚያወጡበትን ደቂቃ እስኪደርስ ወይ የጎንዮሽ ወሬ፣ መጠነኛ ልፊያ ብጤ በማድረግ (እርስ በእርስ የሚቆናጠጡ ሁሉ አሉ) ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።እንዲናገሩ የተፈቀደላቸው ጥቂቶች ብቻ የተለመደ አሰልቺ ገለጻ ያደርጋሉ።ብዙ ጊዜ የዚህ ዕድል ባለቤት ከአቶ መለስ ጀርባ የሚቀመጠው የህወሃት ተወካይ፣የህግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አስመላሽ የሚባለው ነው።የተማረ ያልተማረ ብሎ ነገር የለም ያልተፈቀደለት እጅ ከመስቀል ባለፈ ትንፍሽ የለም።አንዳንዶች ውስጣቸው ያረሩበትን በተለይ በአካባቢያቸው ላይ የሚያውቁትን ጉዳይ እነሱ አፋቸው ስለተለጎመ በጎንዮሽ ለአንዳንድ የተቃዋሚ አባላት እየተለማመጡ ተናገሩልን ይሉ ነበር።አስገራሚው የተነሳው ሀሳብ አጀንዳ ሆኖ ውይይት እንዳይደረግበት እጅ አውጥተው ይቃወማሉ።

አንዳንዴ ከጋዜጠኞች ማማ ላይ ተቀምጠን ቁልቁል እያየን በምልክት <<ተመልከት ያንን!…ያችኛዋን እያት ከጎኑዋ ካለው ጋር እጇን ልካ ስትቆናጠት.. ያኛውን እየው… እነዛውልህ ሲላፉ …ያኛው ተኝቷል ተቀስቅሶ እጅ ሲያወጣ አየኸው?..>> እንላለን። በዚህ ሂደት የሚወጣው አዋጅ ግን በርካታ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት የሚመለከት በመሆኑ ያሳዝናል። ያስቆጫል። በነገራችን ላይ መለስ እንዲህ የሚቀልዱበት ፓርላማ ነው ቅንጅት ካልገባ ሲባል የነበረው።

አንድ ማለደ በነበረ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ከሱማሌ ክልል በግል የመጡ ተወካይ እጃቸውን አውጥተው ቅሬታ ያቀርባሉ። ቅሬታቸው የፓርላማ አባል ሆኜ የመከለከያና የደህንነት ጉዳይ ኮሚቴ ትላንት የደህንነት መ/ቤት ሪፖርት ሲያደምጥ እኔም ሆንኩ ሌሎች አባላት እንዳንገባ ተከልክለናል ለምን ይሄ ይሆናል የሚል ነው። ቋሚ ኮሚቴዎች ለሚባሉት የተለያዩ መ/ቤቶች የስራ ሪፖርታቸውን ለይስሙላ የሚያቀርቡበት ሂደት ነው።  የፓርላማ አባል መሆን ቢያንስ ስብሰባ ለመካፈል መብት የለውም።

በጊዜው የነበሩት አፈ ጉባኤ ዳዊት ዩሐንስ እና ዶ/ር ጴጥሮስ ኦላንጎ ነበሩ። ቋሚ ኮሚቴው ካልፈለገ አለማስገባት መብቱ ነው ተባለና አለፈ። ህጉ ባይልም ህግ ይወጣበታል በሚባለው ፓርላማ እንዲህ ያለው ነገር የተለመደ ነው።

የእለቱ አሰልቺ ስብሰባ እንዳበቃ በዚያው ፓርላማ ውስጥ በሚገኘው የመከላከያና የደህንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጽ/ቤት አመራሁ። የዚያ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዛሬ በሱዳን አምባሳደር የተባሉት የህውሃቱ ሀይሌ ኪሮስ ናቸው። በጊዜውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሰሩ ስለነበር የሉም። የሄድኩት ለምን የፓርላማ አባላቱን ከለከላችሁ ለመሆኑ ምን ሚስጥር ነው ከፓርላማ አባላቱ የሚደበቀው ብዬ ለመጠየቅ ሲሆን እንደተለመደው እምቢ ቢሉም  ባይሆን እድሌን ልሞክር ብዬ ነበር።

የኮሚቴው ሰብሳቢ ከሌሉ ምክትላቸውን ላነጋግር ብዬ ጠይቄ ተፈቀደልኝ። አቶ ናምሲ ይባላሉ። ከቤንሻንጉል ኢህአዴግ በአጋር ድርጅት ያመጣቸው ያው የብሔር ብሔረሰብ እኩልነት አለ ለማለት የተሳጉ ናቸው። በጊዜው እሰራበት ከነበረው አዲስ ዜና ጋዜጣ መምጣቴን አስረድቼ ጥያቄየን አቀረብኩ። አቶ ናምሲ በቴፕ እየቀዳሁዋቸው የፓርላማ አባላቱን አላስገባም ያሉት የደህንነት ሚኒስትሩ ጌታቸው አሰፋ ሚስጥር ያሉትን ሪፓርት ያቀርቡ ስለነበር ነው። የሪፖርቱ ይዘት በኢትዮ፡ኤርትራ ጦርነት ሳቢያ ከስራቸው የተፈናቀሉ ኤርትራዊያን በጊዜው አምስት አመት ሞልቷቸው ስለነበር ወደ ስራ የሚመለሱበትን ሁኔታ ውዝፍ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው የሚፈቅድበትን ለደህንነት ስጋት አይደሉም የሚል ነው።እነ መለስ ምስጢር ያደረጉት የኤርትራዊያን ውዝፍ ደሞዝ ከፍሎ ስራ ሲመለሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከየስራቸው ይባረሩ የነበረበት ወቅትም ነው።

ቀኑ ማክሰኞ ስለነበር በማግስቱ ጋዜጣው ገበያ ላይ ይውላል። የፓርላማ አባላቱ በመካከላቸው ቅሬታ ማቅረባቸውን፣ ኮሚቴው በሚስጥር የተወያየው ስለ ኤርትራውያን መሆኑን አቶ ናምሲን የም/ቤቱን ም/የመከላከያና የደህንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ጠቅሼ ፃፍኩ።

ዜናው ከወጣ በሁዋላ አቶ ናምሴ እንደፈለጉኝ ሰማሁ ። የሰራሁት ስህተት ስለሌለ ምን ተፈጠረ ብዬ አገኘሁዋቸው። የኮሚቴው ሰብሳቢ የህውሃቱ አለቃቸው በእለቱ ውጭ ጉዳይ ስለሚሰራ ስብሰባ ያልመጣው ሀይሌ ኪሮስ ተቆጣ አሉኝ። አቶ ናምሲ ደንግጠዋል። ህውሃቶቹ ምስጢር ያደረጉትን ጉዳይ   እንዲናገሩ ሳይፈቀድላቸው አውርተዋል። በነገራችን ላይ አቶ ናምሴ በአለም አቀፍ ህግና በውጭ ግንኙነት የማስተርስ ዲግሪ ሲኖራቸው አቶ ሀይሌ ኪሮስ በጊዜው የሳቸውን ያህል አልተማሩም።ዛሬ እንደቀሩ ጓደኞቻቸው የፈረደበትን ማስትሬት በመንግስት በጀት ተገዝቶላቸው ይሆናል።

በጊዜው ከሌሎች ወገኖች እንዳገኘሁት ተጨማሪ መረጃ በዚያ ቂም የተያዘባቸው አቶ ናምሲ ማስፈራሪያም ማስጠንቀቂያም ተሰጣቸው። ቅንጅት አልገባም ያለበት የተለመደው የነ መለስ መቀለጃ ፓርላማ አዲስ ዙር የስራ ዘመን ሲጀምር የቋሚ ኮሚቴዎች እጩዎች ዝርዝር ቀርቧል። አቶ ናምሲ ቀድሞ ከነበሩበት ከመከላከያና ደህንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትልነት ወደ ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ም/ሊቀመንበር ሆነዋል። የዚህ ኮሚቴ ሊቀመንበር ደግሞ ወ/ሮ አዜብ መስፍን የአቶ መለስ ባለቤት ናቸው።

በፓርላማው እየተገረምን በጊዜው የዘገብናቸው በርካታ አስቂኝና አስገራሚ ጉዳዮች መካከል ሌላ አብነት ልጥቀስላችሁ።

ተሰርቶበት ባያውቅም አንድ የህግ ረቂቅ ለፓርላማው ይቀርባል። የፓርላማው አባላት በረቂቁ ላይ ተወያይተው የማሻሻያ ሀሳብ፣የሚወጣ የሚገባውን ወስነው ይህንኑ እንዲሰራ ለውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራሉ። የውሳኔ ሀሳብ ሲመጣ ተወያይተው ያፀድቃሉ። በዚህ መንገድ የፀደቀ ህግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሲወጣ ስራ ላይ ይውላል።ይህ ሂደት ለይስሙላ ሲፈልጉት ይፈጸማል። ማንም ሀሳብ ሰጠ አልሰጠ የመጣው አዋጅ ይጸድቃል። ይሄ የይስሙላ ስርዓትም  ግን የሚከበረው አቶ መለስ እስከተመቻቸው ብቻ ነው።ካልፈለጉ ሌላ መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ።ለዚህ አብነት ላንሳ።

የስዬ ህግ የሚባለው አንድ በሙስና የተከሰሰ ሰው የዋስትና መብት የለውም የሚል ረቂቅ ከመለስ ተፅፎ በጊዜው የፍትህ ሚኒስትር በሚባለው ወረደ ወልድ ወልዴ አማካኝነት ለዚህ ፓርላማ ይቀርባል። የሚያስገርመው ወረደ ወልድ ወልዴ ያን ሁሉ የፓርላማ አባላት ሰብስቦ ህጉን እያነበበ ተወያዩ ሲል በጎን አዋጁ አስቀድሞ ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት እነ መለስ ስለላኩት እየታተመ ነበር።

በጊዜው የነበሩት ጥቂት ተቃዋሚዎች በህገ መንግስቱ አንቀፅ19 የዋስትና መብት የተፈቀደ መሆኑን በመጥቀስ በቀላጤ ሙስና በሚል ድፍን ቃል የዜጎችን መብት መገደብ አግባብ አይደለም ሲሉ ተከራከሩ። ሚኒስትሩ የታዘዙትን ስለሚያውቁ ዛሬ መጽደቅ አለበት ሲሉ የአዋጁን ትክክለኛነት ያስረዳሉ። ከዳዊት ዩሃንስ ጋር ሆነው የተቃዋሚዎቹን ሀሳብ አጣጠሉት። መረጃውን የሚያውቁት አቶ በድሩ አደም እጅ ያወጡና እሺ ሁሉን ተቃወማችሁ አዋጁ ሌላው ቀርቶ የፊደል ስህተት አለው ፓርላማው ሳያወጣው ያለ ህጉ በነጋሪት ጋዜጣ እያተማችሁት ነው ሲሉ ይጠይቃሉ። የሚሰማቸው የለም። ድምፅ ይሰጥ ተባለ ጠርናፊን እያየ እጅ ተሰቀለ።ተቃዋሚዎች ተቃወሙት። አዋጁ አለፈ ተባለ። መለስ ባልተሰጣቸው የህግ ስልጣን አስቀድመው አጽድቀው በነጋሪት ጋዜጣ ያሳተሙትን  ፓርላማው አጸደቀ ተባለ።

ተቃዋሚዎቹ በተቃውሞ ድምፃቸውን አስቆጠሩ። መለስ አውጥተው በነጋሪት ጋዜጣ ያሳተሙት አዋጅ ማታ  የውሸት ማሽን በሆነው ቴሌቪዥን ለሙስና ተከሳሽ ዋስትና የሚከለክለውን አዋጅ ም/ቤቱ አወጣ ተባለ። እነ መለስ ህግን እንዲህ በአፍጢሙ ደፍተው የሚቀልዱበት ፓርላማ አባሎቻቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ የግብር ገንዘብ ለሚበሉት ደሞዝ ህሊናቸውን ሸጠው እጅ ሲሰቅሉ የሚውሉ ናቸው።

አንድ ቀን ሁላችንም ያልጠበቅነው አጋጣሚ ተፈጠረ። አንድ አዋጅ ለም/ቤቱ ይመጣል። በእለቱ አብሮ አንድ ሌላ አጀንዳ ነበር። የአሜሪካን አምባሳደርን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገር ሰዎች ከጋዜጠኞች መቀመጫ ማዶ ካለው የእንግዶች ስፍራ ሞልተዋል።

ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን የቦርድ አባላት የሚሾምበት የስም ዝርዝር የያዘ የአዋጅ ረቂቅ ይመጣል። የጊዜው ማስታወቂያ ሚኒስትር በረከት ስምኦን፣ ምክትሉ ወ/ሮ ነፃነት አስፋው እያለ ይቀጥላል። የፓርላማውን የእለት ከእለት የስራ ሂደት ላዬ ሪፖርቱ የተለመደ ነው። ነገር ግን አዲስ ቴአትር ተፈጠረ።

ቀደም ሲል የጠቀስኩላችሁ በአሁኑ ወቅት በሱዳን አምባሳደር የሆነው የህውሃቱ ሀይሌ ኪሮስ ተቃዋሚ ሆኖ ቁጭ አለ። እንዴት የመንግስት ባለስልጣናቱ የህዝብ መገናኛ የሆኑትን ሁሉ በቦርድ ሊቀመንበርነት ይመራሉ አለ። እንኳን እኛ እነዚያ እንደ እቃ ተቆጥረው በወጡ በገቡ ቁጥር ህገ ወጥ የተባለ  አዋጅን ሲቃወሙ የሚሰሟቸው ተቃዋሚዎችን እንጂ ኢህአዴግን ያውም ያለቃቸው የህውሃት አባል በመሆኑ ግራ ሳይጋቡ የሚቀሩ አይመስለንም። ለነሱ ቀላል መንገድ ግን ያው ጠርናፊውን መከተል ነው።

የተባለው ተባለና ድምፅ ሲባል በማክሰኞው መደበኛ ስብሰባ አዋጅ ሲደግፍ የኖረው እጅ ተቃወመ። ዜናውን ከመፃፍ አልፈን ምን ተፈጠረ እያልን እርስ በእርስ መጠያየቅ ጀመርን።

የሐሙሱ መደበኛ ስብሰባ መጣ። ሌላ ያልተጠበበቀ አስገራሚ ቴአትር ተከሰተ። የሹመቱ አዋጅ ከእንደገና ቀረበ። እናም ፀደቀ። እነ በረከት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የዜና አገልግሎት፣ የፕሬስ መምሪያ የቦርድ ሊቃነመናብርት ሆኑ ።የፓርላማ አባላቱ አውጡ ሲባሉ እጅ ማውጣት በመሆኑ ማክሰኞ የተቃወሙትን  የሹመት አዋጅ አንድ ቃል ሳይለወጥ ሐሙስ ደግፈው አወጡ። እነ መለስ የውጭ ሰዎችን ሲያዩ ሲፈልጉ ቴአትር የሚሰሩበት ፓርላማ ስለሆነ እነዚያ ለደሞዝ ራሳቸውን እቃ ያደረጉ አባላት የመጠየቅ መብት የላቸውም።ይህንንም አዋጅ ተቃዋሚዎች ቢቃወሙም የሰማቸው አልነበረም።

ከፓርላማ አባላቱ እንደ አቶ ናምሲ  የተማሩ አልፎ አልፎ አሉበት። ሆኖም የተማረ ሆነ ያልተማረ የነ መለስ አሽከር ሆኖ እጁን ለመስቀል እስከተስማማ ድረስ እንደ እቃ ይጠቀሙበታል።

ዛሬም የተለወጠ ነገር የለም። በቅርቡ ፓርላማው በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከሚታገሉ መካከል ሶስት ድርጅቶችን መርጦ ከነ አልቃይዳ ጋር የደመረበት ሂደትም ይሄው ነው።

የፓርላማ አባላቱ የሚሰጣቸውን አዋጅ ፣ የአዋጅ ረቂቅ የት እንደሚያደርጉት ላውጋችሁና ላብቃ። ብዙዎቹ አዋጁን አያነቡትም። የወሰዱትን አዋጅ በፕላስቲክ ከረጢት እየሞሉ ገርጅና ቦሌ በመኖሪያቸው አካባቢ ላሉ ሱቆች ለስኳር መጠቅለያነት ይሸጡታል። ዛሬ ስኳር ስለሌለ ባለ ሱቆቹ ለምን መጠቅለያነት እንደሚገዟቸው አላውቅም።

እነ አቶ መለስ በአዲስ አበባ በጠራራ ጸሐይ የገደሏቸወን ንፁሃን ላይ የወሰድነው እርምጃ ትክክል ነው በል ብለው ያንን የወሰነ ፓርላማ ነው። ዳኛ ፍሬህይወት ሳሙኤል እና ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ የአጣሪ ኮሚሽኑን ሪፖርት ይዘው ባይወጡ ኖሮ እንደ አጋዚ በንፁሃን ላይ የሚተኩስ የንፁሃንን ሞት የሚመርቅ ፓርላማ ነው።በጋምቤላ ለተፈጸመው የዘር ማትፋት ወንጀል ጉዳዩ በችኮላ የማምለጫ ሪፖርት እንዲታፈን ያደረገ ፓርላማ ነው።መለስ ፓርላማውን ለህጋዊ ሽፋን ለህገ ወጥ ተግባራቸው ሁሉ ሲያውሉት ኖረዋል።ለአገር ሳይሆን ያንን ግለሰብ ለማትፋት ፣ያኛውን ድርጅት ለማስወገድ እየተባለ በህግ ስም ፍትህ የሚገደልበት ፓርላማ ነው።ለመሆኑ የፓርላማ አባላት ተብዬዎቹ መቼ ነው ራሳቸውን ከአቶ መለስ ጫማ ስር አንስተው የሰውነት ክብራቸውን የሚቀዳጁት?

አቶ መለስ መቀለጃ ስለአደረጉት የመሰላቸውን አዋጅ እየፈጩ የሚያወጡበት  ፓርላማ አስመልክቶ ጥቂት  አብነቶችን ከጠቃቀስኩ ሌሎች ደግሞ የበኩላቸውን እንደሚሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ቸር እንሰንብት።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close