የስፖርት ፌዴሬሽኑና ትዝብቶቻችን

ዳዊት ከበደ (አትላንታ)

ሁሉንም ትዝብቶች አልጻፍንም። ሆኖም ለፌዴሬሽኑ ይጠቅማሉ የምንላቸውን መሰረታዊ ስህተቶችን ለማየት ሞክረናል። አላማችንም ፌዴሬሽኑ ስህተቶቹን እንዲያርም ለማድረግ ስለሆነ፤ ችግሮቹንና መፍትሄ ያልናቸውን ሃሳቦች አቅርበናል። አስተያየታችን በግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ባለመሆኑ ስህተት ሰርተዋል ያልናቸውን ሰዎች ስም እዚህ ላይ አልጠቀስንም። በቅን መንፈስ ያዘጋጀነው ሀተታ በመሆኑ፤ እርስዎም ጉዳዩን በቀና ልቦና ያንብቡት።

1- የመክፈቻ ዝግጅት (የመጀመሪያው ቀን)

አትላንታ ላይ የተዘጋጀው የዚህ አመት ጨዋታ የተጠበቀውን ያህል በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል፤ ለማለት አንደፍርም። በ’ርግጥ የመክፈቻውን ዝግጅት የሚያሳምረውና የሚያደምቀው የአዘጋጁ አገር ቅድመ ዝግጅት ነው። በአትላንታ በኩል ብዙ መስራት እየተቻለ ‘ምንም’ ማለት በሚቻል መልኩ ዝግጅቱ የደበዘዘ ነበር። እንዲያውም የአትላንታ መቅድም ወጣቶች የባህል ዝግጅት ባይኖር ኖሮ ዝግጅቱ ይብሱን ሊቀዘቅዝ ይችል እንደነበር ይገመታል። የመቅድም ወጣቶች ዝግጅት እንዳለ ሆኖ የኮንግረስ ማን ጆን ልዊስ በመክፈቻው እለት መገኘታቸው ለዝግጅቱ ድምቀት ሰጥቶታል። በዚህ አጋጣሚ ሚስተር ጆን ልዊስን በግል ጥረታቸው የጋበዙትን ሰዎች ማመስገን አስፈላጊ ነው።

የመፍትሄ ሃሳብ፡ የፌዴሬሽኑ ተከታታይ ቀናት ዝግጅት መሰረታቸው የመክፈቻው ቀን ውበት ነው። የመጀመሪያው ቀን ካላማረ፤ በቀጣዮቹ ቀናት ላይ ጥቁር ጥላ ያጠላበታል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ወደፊት በሚያዘጋጃቸው የመክፈቻ በአላት ላይ የአዘጋጅ አገሩ ሰዎች አይነተኛ ሚና እንዲጫወቱ ቢያደርግ ጥቅሙ ለሁሉም ነው።

2- የክብር እንግዳ አቀባበል፡ (ሁለተኛው ቀን)

የ28ኛው አመት የክብር እንግዳ ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ መሆናቸው ይታወቃል። ለዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ሊሰጣቸው የሚገባውን ክብር ከሁሉም የፌዴሬሽኑ አባላት አልተስተዋለም። መጀመሪያ የመጡ ቀን አብዛኞቹ የፌዴሬሽኑ ሰዎች በስፍራው አልነበሩም፤ ይህም አቀባበሉን አደብዝዞታል። ህዝቡ ያሳየው አቀባበል ግን የሚደነቅ ነበር። በአጠቃላይ ከአንደኛው መድረክ አስተዋዋቂው ጀምሮ አንዳንድ አባላት በበቂ ሁኔታ ስራቸውን የሰሩ አይመስልም። የመድረክ አስተዋዋቂው የዳኛ ብርቱካንን ስም ለመጥራት የፈራ ይመስል ነበር። (ዝርዝር ነገር ውስጥ መግባት አንፈልግም)

ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት፤ በጩኸት ለመረበሽ የተዘጋጁ ሰዎች እንደነበሩ ቀደም ተብሎ ተሰምቶ ነበር። ሆኖም ዳኛ ብርቱካ ሲናገሩ የህዝቡ አቀባበል እና ጩኸት ለረብሻ የተዘጋጁትን ዝም አሰኝቷቸዋል። ከዚያ ይልቅ ግን በጣም የሚያሳዝን ነገር የታየው እዚያው መድረክ አካባቢ ዳኛ ብርቱካን እየተናገሩ ሳለ፤ ሶስተኛው ደቂቃ ላይ አንደኛው የፌዴሬሽን አባል ወደ ህዝብ ግንኙነቱ ዞሮ፤ “አስቁማት” ሲል በሃፍረት ተሸማቀቅን። የህዝብ ግንኙነቱ በመረበሽ ስሜት፤ “በጽሁፍ የተዘጋጀ ንግግር እኮ ነው የምታደርገው… እንዴት ነው የማቋርጠው?” በማለት ከዳኛ ብርቱካን ተቃዋሚዎች ጋር ሲጨቃጨቅ ነበር።

የመፍትሄ ሃሳብ፡ የፌዴሬሽኑ የክብር እንግዳ የሁሉም ህዝብ እንግዳ ማለት ናቸው። ለክብር እንግዳዎች ክብር አለመስጠት ማለት፤ ለህዝቡ ክብር አለመስጠት ማለት ነው። በግል የክብር እንግዳው ላይ ቅሬታ ቢኖርብን እንኳን፤ በስፍራው ለተገኘው ህዝብ ክብር ሲባል ነገሮችን በትዕግስት ማሳለፍ ተገቢ መሆኑን እናስተውል።

3- የበር ላይ ትርምስ (በተለይ ማክሰኞ እና ረቡዕ)

ለተከታታይ ሁለት ቀናት… በተለይ ነጋዴዎች በሚገቡበት በር ላይ ትርምስ ይታይ ነበር። በዚህ በር ጋዜጠኞች እንዳይገቡ የተከለከለበት አጋጣሚም ተስትውሏል። የፌዴሬሽኑ የክብር እንግዳ ዳኛ ብርቱካን በዚህ በር ለመግባት መጥታ ተከክላ ከቆየች በኋላ ገብታለች። ለፌዴሬሽኑ ስራ የመጡ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች ተከልክለዋል። ምግብ ለመብላት በአካባቢው ቆይተው፤ አንድ አፍታ ሲጋራ ለማጨስ ወደ ውጪ ወጥተው የነበሩ ሰዎች እንደገና መግባት አትችሉም ተብለው ሲከለከሉ ታይቷል። በአብዛኛው ከልካዮቹ የፌዴሬሽኑ ጎልድ አባላት ናቸው። ስም መጥቀስ አስፈላጊ አይደለም እንጂ፤ አንደኛው አባል ሴኩሪቲና ፖሊሶቹን “የከፈልናችሁ ለኛ እንድትሰሩ ነው” ብሎ ሲጮህባቸው አይተናል። ፖሊሶቹም የግለሰቦቹን ስም ጠቅሰው በእለቱ መዝገባቸው ላይ ሪፖርት ማድረጋቸውን በቅርብ ያየነው ጉዳይ ነው። ይህ ግን በየቀኑ የሚስተዋል አልነበረም። እዚያ በር ላይ እንደሚቆመው የፌዴሬሽን የወርቅ አባል ሁኔታ ይለያያል። ትሁትና ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ የወርቅ አባላት እንደነበሩ መጥቀስ ያስፈልጋል። ሆኖም አንዳንድ ፖሊስ እና ሴኩሪቲዎች ክፉዎቹን በማየት፤ እነሱ ይበልጥ ክፉ ሲሆኑ ተስተውሏል። ከሃሙስ በኋላ ግን የፌዴሬሽኑም ሆኑ አስቸጋሪዎቹ ሴኩሪቲዎች ከዚያ በር ላይ እየራቁ፤ ጭቅጭቅና ንትርኩም ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል።

የመፍትሄ ሃሳብ፡ ከላይ ያለውን ችግር ያመጣው የህጉ መቀያየር ነው። በመጀመሪያው ቀን በዚያ በር የገባ ሰው በሌላ ቀን፤ “አትገባም” ሲባል ሊፈጥር የሚችለው ደስ የማይል ስሜት አለ። በር ላይ የመግባት እና ያለመግባት ህግ በየጊዜው እየተቀያየረ ሰዎችን ቅር ከማሰኘት ይልቅ፤ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ተመሳሳይ እና አንድ አይነት ህግ ቢኖር፤ ይህም በግልፅ በሚታይ ቦርድ ላይ፤ “ይህ መግቢያ ለነጋዴዎች ብቻ ነው” ተብሎ ቢጻፍ የነበረውን ትርምስ ይቀንሰው ነበር፤ የሚል እምነት አለን።

 

4- የኢትዮጵያ ቀን፡ (አርብ 6ኛው ቀን)

ይህ የኢትዮጵያ ቀን በጉጉት ከሚጠበቁት ቀናቶች አንዱ ነው። አንዳንድ ሰዎች በሁሉም ቀናት ወደ ስቴዲየሙ አይመጡም። በ“ኢትዮጵያ ቀን” ዝግጅት ላይ ግን ማንም መቅረት አይፈልግም በመሆኑም ስቴዲየሙ በዚህ እለት ይጨናነቃል። በዚህ አመትም የታየው ይኸው ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ከቀኑ 2፡00 ጀምሮ ይዘው መጥተዋል። ህዝቡ የባህል ጨዋታውን ለማየት ተዘጋጅቶ ሳለ፤ ኳስ ጨዋታው ገና በመካሄድ ላይ ነበር። ጨዋታው ካለቀም በኋላ መድረክ ሲዘጋጅ እና ድምፅ ማጉያው ሲስተካከል ከአንድ ሰአት በላይ ጊዜ ወስዶ ህዝቡ መጮህና ማፏጨት ጀምሮ ነበር። ከጥቂት ሙዚቃዎችና ትውውቆች በኋላ የክብር እንግዶች አጫጭር ንግግር አድርገዋል። የባህል ዝግጅቱ እንደገና ሲቀጥል ጊዜው እየመሸ 11፡00 ፒ.ኤም ሆነ። ህዝቡም ቀስ በቀስ መውጣት ጀመረ… የኢትዮጵያ ቀን ዝግጅትም በዚህ አይነት ሁኔታ በጣምም ሳይደምቅ እጅግም ሳይቀዘቅዝ ተጠናቀቀ።

የመፍትሄ ሃሳብ፡ የብዙ አመት ልምድ ላለው ፌዴሬሽን በዚህ ጉዳይ የመፍትሄ ሃሳብ መስጠት ይከብዳል። ሆኖም ይህ የኢትዮጵያ ቀን በህዝቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ በመሆኑ እግር ኳሱን በጊዜ መጀመር ወይም በዚህ እለት ብዙ ግጥሚያዎችን አለማድረግ ይመረጣል። ሳውንድ ሲስተሙን ቀድሞ መሞከር እና ቢያንስ በዚያ ስቴዲየም ውስጥ ከዚህ በፊት የሰራን የንግድ ድርጅት ማሳተፍ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ያስወግዳል።

5- የምግብ እና መጠጥ መሸጫ ቦታዎች

የምግብ ቦታ

በየአመቱ አቤቱታ ከሚሰማባቸው ቦታዎች አንዱ የምግብ መሸጫ ቦታ ነው። ድንኳን፣ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ፣ መቀመጫዎች እና የቁሻሻ መጣያዎች በበቂ ሁኔታ ከሌሉ እንደጉድለት የሚቆጠር ነው። በዘንድሮው የአትላንታ ዝግጅት ላይ የቀረቡት ድንኳኖች በጥራታቸውም ሆነ በጥንካሬያቸው ጥሩ ነጥብ የሚሰጣቸው ናቸው። ውሃ በጎማ በየድንኳኖቹ ጓሮ ነበር። በድንኳኖቹ ጓሮ በኩል ቁጭ ብለው መብላት ለሚፈልጉ በትንሹም ቢሆን የወንበር እና የጠረጴዛ እጥረት ተስተውሏል፤ የጎላ ችግር ግን አልነበረም።

ዝናብ በዘነበባቸው ቀናት በተለይ በአንደኛው ጎን የነበሩ ድንኳኖች አካባቢ ወለሉን ውሃ ሞልቶት፤ በውሃ መምጠጫ ሲያደርቁላቸው ነበር። የተፈጥሮ ሁኔታ በመሆኑ እንጂ፤ ችግሩ ከ2 ወይም ሶስት ሰዓታት በኋላ ነው የተቀረፈው። ይህም ሆኖ በነጋዴዎች ላይ ሊፈጥር የሚችለው ኪሳራ ቀላል እንደማይሆን ይገመታል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኤሌክትሪኩ በዝናብ እና በመብረቅ ምክንያት አልፎ አልፎ ሲቋረጥ ነበር። ከዚያ በስተቀር ከመቋረጡ በስተቀር በቂ የኤሌክትሪክ ሃይል ነበር። የቁሻሻ መጣያም በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ስለነበር የጎላ ችግር አልታየም።

የደረቅ እቃዎች መሸጫ

በስቴዲየሙ ውስጥ በግራ እና በቀኝ በኩል ቦታዎች ተሰናድተው ነበር። ሆኖም ከአንደኛው ጥግ ወደሌላው ለመሄድ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ይህም የደረቅ ነገር መሸጫ ቦታዎችን ፈዛዛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በሽያጭ ረገድ ብዙዎቹ እንዳላተረፉ በምሬት ሲገልጹ ተሰምቷል። በዚያ ላይ ድንኳኖቹ የፊት ለፊት መዝጊያ ወይም መጋረጃ ስላልነበራቸው፤ ማታ ላይ ብዙዎች እቃቸውን እየተሸከሙ ይሄዱ ነበር። በንጋታውም እቃዎቻቸውን መልሰው አምጥተው እንደ አዲስ ሲያደራጁ ይታዩ ነበር። ምናልባት የፊት ለፊት መዝጊያ ወይም መጋረጃ ቢኖራቸው ኖሮ ይህ ችግር ላይኖር ይችል ነበር።

6- የመግቢያ መታወቂያዎች

ከኳስ ተጫዋቾች ጀምሮ ነጋዴዎች እና ሌሎች ሰዎች የነጻ መግቢያ መታወቂያቸው በወቅቱ ስላልደረሰላቸው ምሬታቸውን በንዴት የሚገልጹ ብዙዎች ነበሩ። መታወቂያውን በሃላፊነት የሚያዘጋጀው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዘዳንት ነበር። ችግሩን አስመልክቶ ስንጠይቀው፤ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ የመግቢያ መታወቂያዎችን ማዘጋጀት ነበረብን። ትልቁ ችግር ሊከሰት የቻለው ግን ነጋዴዎችም ሆኑ ተጫዋቾች ቀደም ብለው ስም እና ፎቷቸውን ባለመላካቸው መሆኑን ገልጾልናል።

የመፍትሄ ሃሳብለወደፊቱ ፌዴሬሽኑ የፎቶ እና የስም ዝርዝሮችን የያዘ ዳታ አዘጋጅቶ፤ ቢያንስ በየአመቱ ለሚመጡ ነጋዴዎችና ተሳታፊዎች ያለአንዳች ውጣ ውረድ መታወቂያውን ሊያዘጋጅላቸው ይችላል የሚል እምነት አለን።

7- ስርዓት አልባ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ

ከአስር አመታት በፊት ፌዴሬሽኑ ይወቀስበት የነበረው ጉዳይ ልቅ የሆነ የአልኮል መጠጥ ስርጭት ነበር። እንዲያውም “የፌዴሬሽኑ አመታዊ በአል ከስፖርትና ባህል ወጥቶ፤ የስካርና የጋጠ ወጥነት መድረክ ሆኗል። ወጣቶችንም እያበላሸ ነው” እየተባለ በሰፊው ይወቀስ ነበር። ካለፉት አስር አመታት በኋላ ግን ይህ ወቀሳ እየቀነሰና እየጠፋ መጥቷል። ይህም ፌዴሬሽኑን ሊያስመሰግነው የሚገባ ነው። አሁን አሁን የምናየው ከድንኳኑ ጀርባ በድብቅ፤ ከቢራ ጠርሙስ ወደ ኩባያ እየተገለበጠ የሚደረግ ሽያጭ ሲሆን፤ የፌዴሬሽኑ ሰዎችም፤ “ቢያንስ ከ21 አመት በታች ለሆኑ ወጣቶች አትሽጡ” በሚል አይነት እያዩ እንዳላዩ ሆነው ያልፋሉ። ይህም ነጋዴዎቹን ከመጥቀም አንጻር ያዩት ሊሆን ይችል ይሆናል። ነገር ግን የተፈራው ነገር አልቀረም። በመዝጊያው እለት ሃላፊነት በጎደለው መልኩ በግልፅ የአልኮል መጠጥ ሽያጭ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ይታዩ ጀመር። በአንደኛው ድንኳን ሲጥጡ የነበሩ ወጣቶች በስካር ተጣልተው፤ የነሱ መዘዝ ለሻጮቹም ተርፏል።

የመፍትሄ ሃሳብለዚህ አይነቱ የተለየ የመፍትሄ ሃሳብ ሊመጣ አይችልም። “መጠጥ መሸጥ ክልክል ነው” ከተባለ፤ ለሁሉም በአንድ አይነት ሁኔታ መነገር እና የአልኮም መጠጥ ሽያጩ ለሁልጊዜውም መቆም ይኖርበታል። ችግሩ ያለው አንዱ መሸጥ ሲጀምር… ሌላውም ይከተላል። ገና ከመጀመሪያው ጥብቅ የሆነ እርምጃ ቢወሰድ ሌላውም ተመሳሳይ ጥፋት አይሰራም። ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ ማቆም ባይቻልም እንኳን፤ ከአስር አመት በፊት ወደነበረበት አስከፊ ገጽታ ላለመመለስ ጥረቱ መቀጠል ይኖርበታል።

8- ስርዓት አልባ የምግብ ሽያጮች

እያንዳንዱ ነጋዴ ለምግብ እና ለመጠጥ ሽያጭ ቦታ $2 ሺህ 500 ዶላር ነው የከፈለው። በዚያ ላይ ሌሎች ወጪዎችም ይኖራሉ። የወጪው ብዛት ወይም ብዙ ገንዘብ ለማግኘት ከሚኖር ፍላጎት የተነሳ ህገ-ወጥ ተግባራት ሲከናወኑ ታይቷል። ምግብ መብላት የሚቻለው ወይም የሚስተናገደው በምግብ ድንኳኖች አካባቢ ሆኖ ሳለ፤ እንደኮንትሮባንድ እቃ ሻንጣ ሙሉ ምግብ ይዘው ገብተው ሲያከፋፍሉ የነበሩ ነጋዴዎችን አስተውለናል። የፌዴሬሽኑ ሃላፊዎችን ስንጠይቅ፤ “ምግብ እንዲገባ የተደረገው ሜዳ ውስጥ ሲያጫውቱ ለነበሩ ዳኞች ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። ሆኖም በተከታታይ ቀናት ሌሎችም የምግብ ነጋዴዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በሻንጣ መጠጥና ምግብ ይዘው ስቴዲየሙ ውስጥ መሸጣቸውን ቀጥለው ነበር።

የመፍትሄ ሃሳብአብዛኛው ነጋዴ ህግን አክብሮ ለመስራት የሚጥር ነው። ሆኖም አንደኛው ነጋዴ ከህግ ውጪ ሰርቶ ሲጠቀም ሲመለከቱ ሌሎችም ከህጉ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ይታያል። ሁሉም ህገ ወጥ ከሆነ በኋላ ከመከልከል መጀመሪያውኑ ለሁሉም አንድ አይነት ህግ ማበጀት፤ ህጉንም በሁሉም ላይ እኩል ተግባራዊ ማድረግ ያስመሰግናል እንጂ አያስወቅስም።

9- የመዝጊያው ዝግጅት (ቅዳሜ – የመጨረሻው ቀን)

በመዝጊያው ዝግጅት ላይ የኦሃዮ እና የዲሲ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ግጥሚያ ደማቅ እና ከህሊና የሚጠፋ አይነት አልነበረም። እኩል ለኩል ወጥተው ተጨማሪ ሰአት ተሰጥቶ፤ በፍጹም ቅጣት ምት ነው የተለያዩት። ሁለቱም ቡድኖች በፈረጠመ መንፈስ ነበር የተጋጠሙት። ግፊያና መጎሻሸም ታይቶበታል። ከዳኛ ጋር መጨቃጨቅ እና ሜዳ ውስጥ በንዴት መወራጨት ተስተውሏል። አንዳንዶቹ ተግባራት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ የሚያስወጣቸው ሆኖ ሳለ፤ ዳኛው በቅጣት ምት ነገሩን ሲያልፈው ታይቷል። የህዝቡ ሞራል እና ድጋፍ አሰጣጥ ደግሞ የአውሮፓ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የምናይ አስመስሎት ነበር። ከጨዋታው በኋላም አሸናፊው የኦሃዮ ቡድን የዲሲ አቻቸውን እየጨበጡ እና እየተቃቀፉ ማየት በጨዋ ኢትዮጵያዊ ባህላችን የበለጠ እንድንኮራ አድርጎናል።

ቅዳሜ ምሽት በነበረው የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ባለመገኘታችን ብዙም የምንለው ነገር የለም። የመግቢያ ዋጋው $40.00 መሆኑን በተመለከተ ግን፤ “ዋጋው በዛ” የሚሉ አስተያየቶችን አድምጠናል።

የመጨረሻው የቅዳሜ ዝግጅት ከመጠናቀቁ በፊት የህዝብ ግንኙነቱን ጨምሮ አንዳንድ የስራ አስፈጻሚ አባላት ስቴዲየሙን ለቀው ሲሄዱ፤ በማታውም ዝግጅት ላይ አለመገኘታቸውን ስንሰማ፤ “ሰላም ነው?” ማለታችን አልቀረም። እንግዲህ ለሚቀጥለው ዝግጅት፤ ስህተቶች ታርመው ዝግጅቱ የበለጠ ልቆና ደምቆ ይከበር ዘንድ ምኞቻችን ነው። እስከዚያው ሰላሙን ያሰማን።

የመፍትሄ ሃሳብ፡ ስፖርት ለሰላም እና ለወዳጅነት የሚደረግ ጨዋታ ነው። ስፖርተኞች በሜዳ ውስጥ በሚያደርጉት ጥፋት በዳኞች ሊቀጡ ይችሉ ይሆናል። የጎላ ችግር ወይም ከስፖርት ዲስፕሊን ውጪ የሚሆኑ ወጣቶችን ፌዴሬሽኑ ከምክር ጀምሮ የራሱን እርምጃ የሚወስድበት መንገድ ቢመቻች ወደፊት ሊመጣ የሚችልን ችግር ሊቀርፍ ይችላል። እናም “ሳይቃጠል በቅጠል” እንደሚባለው ነገሮች መስመራቸውን ከመሳታቸው በፊት የስፖርት ዲስፕሊን አካል ተቋቁሞ፤ ስፖርታዊ ጨዋነት ማለት ምን እንደሆነ፤ ለተጫዋቾች በአማርኛና በእንግሊዘኛ በጽሁፍ ወደ ታች ማውረድ ያስፈልጋል።

10- የአሸኛኘት ፕሮግራም፡

በየአመቱ ፌዴሬሽኑ ዝግጅቱን በጨረሰበት ቀን ማግስት፤ የቦርድ እና የስራ አስፈጻሚ፤ የክብር እንግዶቹን እና ምስጋና የሚገባቸውን ሰዎች ጠርቶ ምሳ ይጋብዝ ነበር። ይህም የተለመደና የፌዴሬሽኑ መልካም ባህሉ ነው። በዚህ አመት ግን ምንም የአሸኛኘት ፕሮግራም አልተደረገም። ሌላው ቀርቶ ሶስት ወይም አራት የሚሆኑት የስራ አስፈጻሚ አባላት ይህ አመት የመጨረሻቸው በመሆኑ በእንዲህ አይነቱ የአሸኛኘት ፕሮግራም ላይ አባላቱ ሌሎችን የሚሰናበቱበትና የሚመሰጋገኑበት መልካም አጋጣሚ ይሆን ነበር። ይህ አልሆነም።

የመፍትሄ ሃሳብ፡ የፌዴሬሽኑ መልካም ባህሎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው እንጂ ፈጽሞ መጥፋት የለባቸውም። በፍቅር የመሰነባበት ባህል ሲኖር ነው፤ አዳዲስ ስራ አስፈጻሚዎችን በጥሩ መንፈስ ፌዴሬሽኑን የሚቀላቀሉት። አሁንም ቢሆን ተሰናባች ስራ አስፈጻሚዎች የሶስት ወራት እድሜ አላቸው። በእነዚህ ወራት ውስጥ በአንዱ ቀን ተሰናባቾችን በክብር ጠርቶ፤ አመስግኖ ማሰናበት ያስፈልጋል።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close