ዶ/ር ነጋሶ ታምራት ላይኔን አደንቃለሁ ሲሉ…?

ዶ/ር ነጋሶ ታምራት ላይኔን አደንቃለሁ ሲሉ…? በሙሉነህ አያሌው በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ህይወት ዙሪያ በቅርቡ ለንባብ በበቃው ..ዳንዲ-የነጋሶ መንገድ.. መጽሐፍ ገፅ 219 ላይ ..ስኳርና ወንጌል.. በሚለው ርዕስ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስለቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ታምራት ላይኔ የሰጡት የራሳቸው ምልከታ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ሆኖኛል፡፡ሁለት ነገሮች ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡ታምራት ላይኔ የብአዴን ሊቀመንበር የነበሩበትን ሂደትና ለእስር የተዳረጉበትን አግባብ፡፡ ..ከታምራት ጋር እንቀራረብ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ከማደንቃቸው ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ ታምራት ንግግርና ግጥም ይችላል፡፡ ኢህዴን መሆኑን እንጂ አማራ ይሁን ምን ይሁን አላወቅም ነበር፡፡ በኋላ ነው ጉራጌ መሆኑን የሰማሁት.. (ገፅ 219) የኢህአዴግ መንግስት ሀገሪቷን ሲቆጣጠር 1983ዓ.ም ታምራት ላይኔ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከአራት አመት በኋላ ደግሞ በምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በኋላም ላይ በውስጥ ሂስና ግለሂስ ተወስዶባቸው ዘብጥያ እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸው በቅርቡ እስራታቸውን አገባደው ..ፖለቲካ በቃኝ.. ብለው አሜሪካ መግባታቸውንም እናስታውሳለን፡፡ አስቀድሞ ዶ/ር ነጋሶ በተናገሩት ውስን አንቀፅ ውስጥ የመጨረሻዋ መስመር ላይ አንድ ቁም ነገር አስተላልፈዋል፡፡ ዶ/ር የተናገሩት በቀጥታ ባይሆንም ያስተላለፉት መልእክት ግን ግልፅ ይመስለኛል፡፡ ..ኢህዴን መሆኑን እንጂ አማራ ይሁን አላውቅም ነበር፡፡ በኋላ ነው ጉራጌ መሆኑን የሰማሁት.. ፖለቲካ የሽሽት ጥበብ ነው ይባላል፡፡ ኢህአዴግ የመንግስትን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በፌዴራል ስርዓት አወቃቀር ዘርን ማዕከል ያደረጉ በጥምር ድርጅቶች ተቋቁሟል፡፡ ከነዚህም መካከል አማራን፣ ኦሮሞን፣ ትግራይን፣ ደቡብንና…የመሳሰሉት ህዝቦች የራሳቸው ድርጅት አቋቁመው ማንኛውንም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ግልጋሎቶችን እንዲያገኙ ማበረታታት ነው የዚህ ሥርአት አላማው፡፡ ከነዚህም ብአዴን አንዱ ድርጅት ነው፡፡ ብአዴን የአማራን ህዝብ ይወክላል የሚባል ድርጅት ነው፡፡ በግንቦት ወር 1981ዓ.ም ከህወሓት ጋር ተጣምሮ ኢህአዴግን መስርቷል፡፡ ይህን ድርጅት በኃላፊነትና በከፍተኛ ደረጃ ከመሩት መካከል የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ አንዱ ናቸው፡፡ የአማራ ህዝብ እንግዲህ በጊዜው ለመብቴና ለጥቅሜ ይታገላል ያላቸው አቶ ታምራት በፍፁም አይወክሉትም ነበር ማለት ነው፡፡ ..አቶ ታምራት ጉራጌ ናቸው.. ይህ አባባል ኢትዮጵያዊ ከመሆን ባያግዳቸውም የፈዴራል ስርዓት አወቃቀርን ግን ሙሉ በሙሉ ያወናብደዋል፡፡ አማራን አማራ ይወክል ከተባለ አቶ ታምራት ብአዴን ውስጥ ምን ያደርጉ ነበረ? ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የአቶ ታምራት ላይኔ ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በእጩነት ያቀረቡት አቶ ተፈራ ዋልዋን ነበር፡፡ በጊዜው ጠ/ሚኒስትሩ የተፈራን ስብዕና ለፓርላማው ሲያስተውቁ እንዲህ ብለው ነበር ..በምትካቸው (በታምራት ላይኔ ፈንታ) የኢህአዴግን መልካም ስም እና ስነ-ምግባር ሊያስጠብቁ ይችላሉ፡፡ ብዬ የማምንባቸውና የኢህአዴግም አባላት በተለይም አመራሩ በዚሁ መንፈስ ሙሉ በሙሉ የሚተማመንባቸውን ተተኪ እጩ ለማቅረብ እፈልጋለሁ.. እኚህ አቶ ታምራትን ይተካሉ የተባሉት በመልካም ስነ-ምግባር የተመሰከረላቸው ሰው አቶ ተፈራ ዋልዋ የብአዴን አባል ቢሆኑም ተወልደው ያደጉት ሲዳማ ሲሆን በአንድ ወገናቸውም ከሲዳማ ተወላጅ ነበሩ፡፡ይህ እንግዲህ በራሱ የአማራ ህዝብን ባህል ጠንቅቆ በመረዳት ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ በመጀመሪያው ብቻ ሳይሆን በተካቸውም ሰው ላይ ኢህአዴግ ስህተትን ሰርቷል፡፡ የፖለቲካው ፈላስፋ ዲደሮ እንዲህ ይላል ..በአንድ ጅረት ውስጥ ሁለት ጊዜ አትታጠብም፡፡ የታጠብህበት ውሃ አልፎ ወርዶአል፡፡ እንደገና የምትታጠብበት ውሃ አዲስ ውሃ ነው.. ይላል፡፡ እኛ ግን በታጠብንበት ውሃ ድጋሚ ቆሻሻውን ሳናጠራ ለሁለትኛ ጊዜ እንታጠብበታለን፡፡ ይህንንም ታምራትን አውርደው ተፈራን ሲተኩ አሳይተውናል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በገጽ 176 ላይ ሌላው የብአዴን ተወካይ አቶ በረከት ስምኦንን እንዲህ ያስተዋውቁናል፡፡ ..እነ በረከትም በበዓሉ ላይ ነበሩ (የኤርትራ ነፃነት በሚከበርበት ጊዜ ማለታቸው ነው..፡፡ በረከት ከኤርትራም እንደሚወለድ ያወኩት ያን ጊዜ ነው፡፡ አንዳንዴ ዘመዶቼን ልጠይቅ እያለ ይሄድ ነበር፡፡ በእናቱ ይሁን በአባ.. ረሳሁት እንጂ ኤርትራዊ መሆኑን እሱም ነግሮኛል..፡፡ ይሄ ስህተት ነበር ብሎ ለመናገር አያስችልም፡፡ ድርጊቱ ሆን ተብሎ እንደተፈፀመ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ወጣቶች ከቅርብ ጊዜ በፊት የአቶ አባ ዱላ ገመዳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን በመቃወም ኦሮሞ እንዳልሆኑና ኦሮሚያን መወከል እንደማይገባ ያሰሙ የነበሩትን ተቃውሞ ከግምት ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ..በመልካም ስምና ስነ-ምግባር የተመሰከረላቸው.. የሚለው አረፍተ ነገር በራሱ ምግባራቸውን አይገልፅም፡፡ መልካም ስነ-ምግባር ከእውነት ይጀምራል፡፡ አንዱና ትልቁ የሰው ልጅ የሞራል መለኪያ ለራሱ ያለው ክብር ነው፡፡ አቶ ታምራትም ቢሆኑ አቶ ተፈራ ለዚህ ክብር ሲታጩ ድርጅቱን መወከል እንደማይችሉ ይህም እንደማይገባቸው አስቀድመው ቢቃወሙ መልካም ስምና ስነምግባራቸውን ማሳየት በቻሉ ነበር፡፡ ድርጅቶችን መወከል የማይችሉ ግለሰቦችን እንዴት ልንቀበላቸው እንችላለን? ለማንስ መብት ነው የሚቆሙት?ጩኹ ሲባሉ የሚጮሁ ፣ ግደሉ ሲባሉ የሚገድሉ ፣ ለፍፁማዊ አምባገነንነት የተመቹ የፖለቲካ መደላደልን ለገዢዎች ከመፍጠር ውጭ ደንታ ቢስ የሚሆኑት ለዚሁ አይደል፡፡ መሪዎችም ቢሆን በራሳቸው ተክለ ሰውነት ዙሪያ ለሚገነቡት አገዛዝ እንዲህ አይነቱን ተውኔት መጫወት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ በዚህ የማስመሰል ፖለቲካ አቶ ታምራትን አላደነኳቸውም፡፡ አላደንቃቸውም፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ስለታምራት የጀመሩት ገለፃ በዚህ ብቻ አይበቃም፡፡ በጊዜው ለእስር ስለተደረጉበት ጉዳይም አጭር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ..አንድ ቀን አስቸኳይ ስብሰባ ተጠራንና መለስ ሪፖርት አቀረበ፡፡ ..የተሰበሰብነው በታምራት ጉዳይ ነው፡፡ ቤተሰቡን ትቶ ከአንዲት ሴት ጋር ግንኙነት መስርቷል.. መከርነው አስመከርነው እምቢ አለ፡፡ ወደ አስራ ሰባት ሚሊዮን ብር ገደማ ገንዘብ በልጁ ስም ስዊዘርላንድ ባንክ አስቀምጧል፡፡.. ገፅ (219) ይህን ዶ/ር ነጋሶ የገለፁትን ጉዳይ ፓርላማው በተከበሩ አፈ ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ ይመራ በነበረበት ወቅት ጥቅምት 1983ዓ.ም አቶ መለስ ዜናዊ በህዝብ ተወካዮች ፊት ቀርበው አቅርበውት ነበር፡፡ ..ከአንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ አባል የማይጠበቅ ተደጋጋሚ የስነ ምግባር ብልሹነት በአለፉት አመታት በድርጅቱ ልምድና ባህል መሰረት በውይይትና በሂስ ለማስተካከል የተደረገው ጥረት ነገሩን ሊያስተካክለው ባለመቻሉ… የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ብሎ አምኖበታል.. ይህንን የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሪፖርት ፓርላማው ካደመጠ በኋላ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ላይ የተወሰደው እርምጃ ተገቢነት ላይ ራሳቸው አቶ ታምራት ላይኔ እንዲናገሩ እድሉን ሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን አቶ ታምራትም በጊዜው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሪፖርት ላይ ምንም አይነት ተቃውሞ እንደሌላቸውና በሰሩት ስራ ተገቢውን እርምጃ ቢወስድባቸው እንደሚቀበሉ እንዲህ ብለው ነበረ የተናገሩት ..የተወሰደውን ውሳኔ እኔ እራሴ በሙሉ ልብ የተቀበልኩትና የደገፍኩት መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ፡፡… ይህ ጉዳይ በድንገት የመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ጀምሮ ከክቡር ጠ/ሚኒስተር ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንነጋገርበት ለእርማትም ብዙ ጊዜ ሙከራ ሲደረግበት የቆየ ነው፡፡ …የሚታየው የስነ ምግባር ችግር እያደር ላለሁበት ኃላፊነትም በስራ ላይ እንድቆይ የማያስችለኝ መሆኑን እኔ ራሴ በመገንዘቤ እንዲሁም ደግሞ ድርጅቱም ሆነ የመንግስት አካል በመገንዘቡ ይህ እርምጃ ሊወስድ ችሏል፡፡.. እነዚህን በወቅቱ የተደረጉትን የሁለትዮሽ ምልልስ ዶ/ር ነጋሶ በጊዜው የተሰማቸውን ስሜት እንዲህ በማለት ይገልፁታል፡፡ ..ጉዳዩ በሁላችንም ዘንድ ድንጋጤ ፈጥሮብን ነበር፡፡ እኔ እንባ አውጥቼ አልቅሻለሁ፡፡ …መለስ ባለበት ያለመከሰስ መብቱ ተነስቶ ወደ ከርቸሌ ወረደ ከእኔም ጋር ተለያየን.. ገፅ (120) እዚህ ጋር በተሰራው ድራማ ላይ ታምራት ላይኔ በፊልም እንደምናያቸው ..አጋች ታጋች ድራማ.. ላይ የቤቱ አባወራ ለቤተሰቦቹ የሚከፍለውን ዋጋ እናያለን፡፡ ድሮ በፊልም እንደምናየው አባት ወይም የቤተሰቡ ዋነኛ የሆነ ሰው አንድ ግዳጅ ተሰጥቶት የግዳጁ ተቃዋሚ ሆኖ ሲገኝ ከቤተሰቡ አባላት አግተው የአላማው ተፈፃሚ እንደሚያደርጉት የጋንግስተር ቡድን አይነት ነው፡፡ በእውነታው አለም ታምራት ለቤተሰቦቹ ዋጋ የከፈለ ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር ነጋሶም ምን አልባት ያለቀሱት ለዚህ መስዋዕት ሲሆን ተመልክተው ይሆናል፡፡ በእውነትም ሰውየው ለቤተሰባቸው ደህንነት ራሳቸውን ለበርካታ አመታት በእስር ላይ አኑረዋል፡፡ የታገሉላት ፍትህ ዋጋ አስከፍላቸዋለች፡፡ ይህንንም ሆን ብለው እንዳደረጉት ህዳር 1994 ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው በአቶ ስዬ ላይ እንዲመሰክሩ ሲጠየቁ የሰጡትን ቃል ማየት በራሱ በቂ ነው፡፡ ..የዛሬ 5 ዓመት በተመሳሳይ መንገድ የማባበያና የማስፈራሪያ ጫና ተፈጥሮብኝ ያልሰራሁትንና የማላውቀውን ነገር የሰራሁና የማውቅ እስኪመስል ድረስ በምክር ቤቱ ውስጥ እንድናገር ከተገደድኩ በኋላ በፈጠራ ክስ ከህግ ውጭ ተፈርዶብኛል፡፡ ያን ጊዜ ድርጅቴ እያልኩ ለነበረው ለኢህአዴግና ለልጆቼ ደህንነት ስል የደረሰብኝ በደል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ህሊናዬን ለጥቅም በመሸጥ በማላውቀው ነገር በሰው ህይወት ላይ ከመመስከር የራሴን ህይወት አሳልፌ ብሰጥ ይሻለኛል፡፡.. ይሄ ነው ታምራት..፡፡ አሁን ቅድም የነገርኳችሁ የፖለቲካው ምሁር አባባል እዚህ ጋር ትሰራለች ..በአንድ ጅረት ውስጥ ሁለት ጊዜ አትታጠብም፡፡ የታጠብህበት ውሃ አዲስ ውኃ ነው፡፡.. አንዴ ለቤተሰብ ሌላጊዜም ለህሊናቸው ህይወታቸውን ዋጋ ሰጥተዋል፡፡ አሁን ዶ/ር ነጋሶ ባሉት ሃሳብ ላይ ተስማማሁ፡፡ ..ኢህአዴግ ውስጥ ከማደንቃቸው ሰዎች አንዱ ነበር.. ኢህአዴጐች ግን አንድ ጨዋታ ለመጫወት አስበው የነበረ ይመስለኛል፡፡ የታምራትን መታሰር ህግ ከሁሉም የበላይ ነው ለማለት ሳትታቀድ አልቀረችም፡፡ ህግ እንኳን ሌላውን ተራ ሰው ይቅርና የሀገሪቱ ትልቅ ሰው የነበሩትን ታምራትን ሳይቀር መቅጣት እንደሚችል ለማሳየት የደከሙ ይመስለኛል፡፡ የስነ-ምግባር ችግራቸውንም በማንሳት በሞራል ላይ የተመሰረተ መንግስት ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማስገንዘብ ጥረዋል፡፡ ሁሉም ነገር እያደር ቢጋለጥም፡፡ አቶ ታምራትን ዶ/ር አስታውሱኝ፡፡ እኔ ደግሞ አሁንም የሚቀለድብንን ቀልድ አስታወስኩ፡፡ (ጸሐፊው ይህን ጽሑፍ በሃገር ቤት እየታተመ በሚወጣው ፍትሕ ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ አድርገዋል)

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close