ለወገን ደራሽ ወገን በሚል የተደራጀው የኢትዮጵያኖች የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ውስጥ በርሃብ ለተጠቁ ወገኖች የእርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገለጸ

በዘላለም ገብሬ ቺካጎ

ለወገን ደራሽ ወገን በሚል የተደራጀው የኢትዮጵያኖች የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ውስጥ በርሃብ ለተጠቁ ወገኖች የእርዳታ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ከዝግጅቱ አሰባሳቢ ኮሚቴ ከሆኑት አንዱ የችካጎ ነዋሪ ዶ/ር ይስማ ሸዋ ወልደየስ በትላንትናው እለት በስልክ ባደረግነው ውይይት ገልጸውልኛል ። በቺካጎ የሚገኘው ይህ የመካከለኛው መእራብ የሰሜን አሜሪካ ነዋሪዎች ኮሚቴ በእራስ አነሳሽነት እና የችግሩን የከፋ ሁኔታ በማገናዘብ ወገኖቹን ለመርዳት የተቋቋመ ጊዜአዊ የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም ማናቸውም ግለሰቦች በዚህ የአስቸኳይ እርዳታ ላይ ሊሳተፍ እና የወገኑን ሂዎት ሊታደግ ይገባዋል ሲሉ ጠቁመዋል በዚህም የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን የኪነጥበብ ሰዎች ከሚድ ዌስት (መካከለኛው ምእራብ) ነዋሪዎች ጋር በሙያቸው ተባብረው ህብረተሰባቸውን ለመርዳት የሚያስችላቸውን የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል ። ከእነዚህ ጥሪ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል ታላቁ የሙዚቃ አቀንቃኝ ቴዎድሮስ አፍሮ የሚገኝበት ሲሆን እስካሁን ምላሹን ሙሉ በሙሉ ያላገኙ ቢሆንም በቅርቡ ግን ሊያሳውቃቸው እንደሚችል ተጠቁሞአል በሌላም በኩል ላፎንቴን ፣ ህብስት፡ጥሩነህ ፣ ሄለን በርሄ ፣ ብዙአየሁ ደምሴ ፣ናቲ ሃይሌ እና ሌሎችም ታዋቂ ዘፋኞች በዚህ የተቀደሰ አላማ ላይ ስራቸውን ለህዝባቸው እንዲያቀርቡ ጥሪ እየተደረገላቸው እንደሆነ የገለጹ ሲሆን የህዝብን አለኝታነት በምናደርገው ሙያዊ እና ቁሳቁሳዊ ተሳትፎ እንዲሁም የገንዘብ እርዳታ በምናደርጋቸው ሊለካ ይችላል ብለዋል ። እነዚህም ሰዎች ቀናነታቸው ተሟልቶ የሙዚቃው ኮንሰርት የሚዘጋጅ ከሆነ በአካባቢያችን ያሉትን ህዝቦች እና በጎረቤት አገር ያሉትን ኮሚኒቲዎች ለማነሳሳት ይረዳናል በማለት ዶ/ር ይስማሸዋ ወልደየስ ጠቁመዋል ። በሌላም በኩል በዛሬው እለት ያነጋገርኳቸው የኢትዮጵያን ኮሙኒቲ በቺካጎ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እርቁ ይመር እንደገለጹት ከሆነ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ በቺካጎ ከተቋቋመበት እለት ከ26 አመታት በፊት አንስቶ እሰከ አለፉት ሁለት አመታት ድረስ በኢትዮጵያ ለሚከሰተው ማናቸውም ችግሮች ፈጥኖ ደራሽ እንደነበር እና እስከአሁንም ለሃገሪቱ ያለውን ክብር እና በየጊዜው የሚያደርገውን ታታሪነት ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል ፣እንደ ዶ/ር እርቁ አገላለጽ ኮሚኒቲው የሚመራበት የእራሱ በጀት ባይኖረውም አሁን ከእስከዛሬ ድረስ ያደርገው የነበረው እርዳታ በኮሙኒቲው ውስጥ በተመዘገቡ አባሎቻቸው አማካይነት በሚዋጣ ገንዘብ ወገኖቻቸውን ሲታደጉ መቆየታቸውን ጠቁመው አሁንም እንደዚህ አይነት አስቸኳይ እርዳታ ለማድረግም ሆነ ሌሎችንም ማህበረሰቦች በአደጋ ጊዜ ለመድረስ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ በሆነው ኮሚኒቲ ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ በአባልነት ቢመዘገብ በቀላሉ የሰዎችን ህይወት ሊታደግ በተገባ ነበር በማለት ለቺካጎ ህዝብ ኮሚኒቲው ከህብረተሰቡ ጋር ሊያደርግ የሚገባውን የጠበቀ ግንኙነት ለማስፋት እንዲችል ጥሪ አቅርበዋል በአሁን ሰአትም ከእነዚህ በእርዳታ አሰባብሳቢ ኮሚቴነት ከተዋቀሩት ጋር በመተባበር የአገሩን ህዝቦች ለመርዳት እና አስፈላጊውን መንግስታዊ ድርጅቶች አስቸኳይ እርዳታም ሆነ ሌሎችን ነገሮች ለመጠየቅ ተባብሮ ለመስራት እንደሚችሉ አክለው ገልጸዋል በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ በረሃብ አደጋ የተጠቁት ኬንያኖች የዜጎቻቸውን ህይወት ለመታደግ በአንድ ሳምንት ውስጥ 7.4 ሚሊዮን ዶላር በማሰባሰብ የህዝባቸውን ህይወት ሊታደጉ መነሳታቸው እና የሌሎች ወገኖችን እጅ ላለማየት ያደረጉት ጥረት እኛንም ይበልጥ ሊያበረታታን እና ሊያነሳሳን ይገባል ብለዋል ፣ኬንያኖች በዚህ የገንዘብ ማዋጣት ፕሮግራም ላይ እያንዳንዱ የኬንያ ዜግነት ያለው ሰው የሁለት ወር ሙሉ ደመወዙን በማዋጣት ሃገራዊ ግዴታውን የተወጣ ሲሆን በአሁን ሰአትም በሚድ ዌስት ማለትም ቺካጎ፣ሚንያፖሊስ ፣ሴንትሉዊስ፣ ሴንሴናቲ ፣ኦሃዮ፣ሚሽገን፣ኢንዲያና፣እና ሌሎችም በቅርበት ያሉ ኢትዮጵያኖች በዚህ ስራ ላይ የየእራሳቸውን ግዴታ ሊወጡ ይገባል በማለት ጥሪ አቅርበዋል።በዚህ ከፍተኛ ችግር ምክንያት በምስራቅ አፍሪካ በርሃብ ለተጎዱ ወገኖች ማሰባሰቢያ የሚሆን የሙዚቃ ኮንሰርት በመላው አለም የሚከናወን ዝግጅት በ150 በሚሆኑ ታላላቅ የአለም አቀፍ ዘፋኞች በተሰባሰቡበት ፕሮግራም እየተዘጋጀ መሆኑን እና ይህም ዝግጅት በቅርቡ እንደሚጀመር በህብር ሬድዮ ላይ ባለፈው መግለጻችን የሚታወቅ ነው በዚህም ዝግጅት ላይ ሪሃና፣ጀስቲን ቢበር፣ ዩ ቱ፣ አሊሺያ ኪስ የቦብ ማርሌይ ቤተሰቦች እና ሌሎችም የሚሳተፉበት መሆኑን እና የዚህ ዝግጅት መጠሪያ ስም I am gonna be your friend የሚል ሲሆን Iamgonnabeyourfriend.org የሚባል ተቋም ተቋቁሞ ስራውን በቅልጥፍና ሲያከናወን እ.ኤ.አ በ1973 አመተ ምህረት በወጣው የቦብ ማርሌይ ዘፈን እንደ ፉቴጅነት እየጠጠቀሙበት እና ዘፈኑን የእርዳታ መቀስቀሻ እያደረጉት መሆኑን ባሳለፍነው ሳምንት የታተመው ሬድ አይስ የተሰኘው በቺካጎ ትሪቡኒ የሚታተመው የነጻ ጋዜጣ መጠቆሙን ገልጸን ነበር እነዚህ የውጭ ሃገር ዜጎች ከሚያደርጉልን የርዳታ ማሰባሰብ ፕሮግራም ተላቀን የእራሳችንን ህዝቦች እራሳችን የመመገብ እና ህይወታችንን የመታደግ ትልቅ አጀንዳ ቢኖረን መልካም ነው እንላለን ።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close