ሐሳብን በነፃነት መግለጽና ለመብት መሟገት በሽብርተኝነት አያስወነጅልም! ዶ/ር ነጋሶ ጊዳ

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ሕገ መንግሥት 
በተለያዩ መንገዶችና ሁኔታዎች እየተጣሱ እያየን 
የምናልፍበት ምክንያት ለምንድ ነው የሚለው ነው፡፡ 
ለኔ የሚመስለኝ ዋናው ምክንያት እነዚህ ግዴታዎችና 
ሃላፊነቶች እንዳሉብን ያለማወቅ ነው፡፡ለማወቅስ 
ፍላጐት አለን ወይ? የሚለው ጥያቄም አብሮ  ሊነሳ 
ይችላል፡፡ ወይም አውቀንም ቢሆን ከግድ የለሽነት 
የተነሳ አይናችንን ጨፍነን እናልፋለን ወይ? የሚል 
ጥያቄም ሊነሳ ይችላል፡፡
ስለ ሕገ-መንግሥት ማወቅን በተመለከተ ይህን 
ካልኩ በቅርቡ የኢህአዴግ መንግሥት እየወሰዳቸው 
ስላሉ ርምጃዎች ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች 
ጋር እንደሚጋጩና ሕገ-መንግሥቱን እንደሚጥሱ 
መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን ለማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ 
ከዚህ አኳያ የሚነሳው ነጥብ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 
29 ላይ ስለተጠቀሰው የአመለካከት እና ሐሳብን በነፃ 
የመያዝና የመግለጽ መብትን በተመለከተ ነው፡፡ በዚህ 
በአንቀጽ 29 ውስጥ የሚከተሉት ተድንግገዋል፡፡
29/1 “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት 
የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡
29/2 “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት 
ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በሀገር    
ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም 
ሆነ በጽሑፍ ወይም በህትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ 
ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ 
ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ 
የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡
እንግዲህ እነዚህ መብቶችና ነፃነቶች በሕገ-
መንግሥቱ አንቀጽ 10/1 እና 10/2 “ሰብአዊ መብቶችና 
ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና 
የማይገፈፉ ናቸው፡፡ የዜጐች እና የሕዝቦች ሰብአዊና 
ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ” ተብለው 
የተጠቀሱትን ጉዳዮች የሚመለከቱ ናቸው፡፡
ፓርቲአችን አንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ 
ለዴሞክራሲያዊና ለሰብአዊ መብቶች መከበርና ፍትህ 
እንዲነግሥ በቆራጥነት የሚታገል ፓርቲ ነው፡፡ ይህን 
ትግሉንም በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት 
በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ሲሆን ለሕግ የበላይነትም 
አበክሮ ይቆማል፡፡ ስለሆነም ሕገ-መንግሥቱን የሚፃረሩ 
ሕጐች ሲወጡና ተግባራዊ ሲሆኑ እንዲሁም የሕገ 
መንግሥቱ ድንጋጌዎችን የሚፃረሩ አካሄዶች ሲታይ 
ዝም ብሎ አያልፍም፡፡ አባሎቻችን ደጋፊዎቻችንና 
አጠቃላይ ዜጐች ሕገ መንግሥቱን እንዲያስከብሩና 
ራሳቸው ለሕገ-መንግሥቱ ተገዥ እንዲሆኑ 
ፓርቲአችን ያለምንም ፍራቻ ይቀሰቅሳል፡፡
በመሆኑም አባሎቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና ሕዝቡ 
ይህን የሕገ-መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ-
መንግሥቱ ተገዥ እንዲሆኑ ለመቀስቀስ የመጀመሪያ 
ኃላፊነቱ ሁሉም የሕገ-መንግሥቱ ምን እንደሚል 
ባግባቡ ማወቅ እንዳለባቸው መጥራትና ማሳሰብ ነው፡፡ 
ዜጐች ግዴታዎቻቸውን ማወቅና መፈፀም አለባቸው፡፡ 
መብቶቻቸውን አውቀው ለምብቶቻቸው መከበርም 
ፀንተው መታገል የሚችሉት ሕገ-መንግሥቱ 
ያስከበረላቸውን መብቶች ማወቅ ሲችሉ ነው፡፡ ሕገ-
መንግሥቱ ምን እንደሚል ዕውቀት ካላቸው ሌሎችንም 
ማስተማር ይችላሉ፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ሲጣስ ሲያዩ 
ጥያቄ ለማንሳት ብቻ ሳይሆን ስህተት እንዲስተካከል 
አስፈላጊውንና ተግቢውን ርምጃ ለመውሰድ ይችላሉ፡፡ 
ይህ ሁሉ እንዲሆን ዜጐች፣ የአንድነት ደጋፊዎችና 
የአንድነት አባላት ሕገ መንግሥቱ ምን እንደሚል 
በትክክል እንዲያውቁ ይቀሰቅሳል፡፡ መላልሶ ጥሪውን 
ያቀርባል፡፡
የሕገ-መንግሥቱን ይዘት አውቆ ተግባራዊ ማድረግ 
ራሱ ሕገ-መንግሥቱ የጣለብን ኃላፊነትና ግዴታ 
ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 9 
ላይ የሚከተለውን ደንግጐአል፡፡
አንቀጽ 9/1፡- “ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ 
ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ 
እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን 
ውሳኔ ከዚህ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ 
ተፈፃሚነት አይኖረውም”
አንቀጽ 9/2፡- “ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት 
አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት 
እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ-መንግሥቱን 
የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት 
አለባቸው”
የቅርብ ሳምንታት ክስተቶች የሚያሳዩን ግን 
የኢህአዴግ መንግሥት እነዚህን መብቶችና ነፃነቶች 
በገሃድ የሚጥሱ ሆነው ይታዩኛል፡፡ ሦስት ምሳሌዎችን 
መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቅርቡ የአውራምባ ታይምስ 
ጋዜጠኛ ዋና አዘጋጅና የፍትሕ ጋዜጣ  አምደኛ 
ርእዮት አለሙ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ መሠረት 
ተይዘው እስካሁን ድረስ በእስር ላይ መገኘታቸው 
ነው፡፡ እግረ መንገዴን ለመጠየቅ የምፈልገው 
የእነዚህ ዜጐች አያያዝ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 19 
እስከ 21 ድረስ በተደነገገው መሠረት መብታቸውን 
ባስጠበቀና ባስከበረ መልኩ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ 
ወደ ዋናው ነጥቤ ልመለስና የነዚህ ሰዎች መታሰር 
ምክንያት የሆነው በኢንተርኔት ከአቶ ኤሊያስ ክፍሌ 
ጋር ግንኙነት ነበራቸው በሚል ነው፡፡ ታዲያ ውጭ 
አገር ካለ ሰው ጋር መገናኘት እንዴት በሽብርተኝነት 
ያስከስሳል? በኢንተርኔት ሰዎችን ማግኘት ምኑ ላይ 
ነው ሽብርተኛ የሚያሰኘው? ኤልያስ ክፍሌስ ማነው? 
ተግባሩስ ምንድን ነው?  
ሁለተኛው ጉዳይ 21 የኦሮሞ የዩኒቨርስቲ 
ተማሪዎች በሽበርተኝነት ተከሰው መታሰራቸው ነው፡፡ 
እንደተገለፀው ከሆነ እነዚህ ተማሪዎች የዓለም አቀፍ 
የኦሮሞ ተማሪዎች ማህበር አባል በመሆናቸውና 
በፌስ ቡክ ርሰበርሳቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር ግንኙነት 
በመፍጠራቸው ነው ተብሎአል፡፡ ከዚያም አልፎ ይህ 
የኦሮሞ ተማሪዎች ማህበር በኦነግ የሚታዘዝና የሱን 
ዓላማ ለማስፈፀም የተደራጀ ነውም ተብሎአል፡፡ 
በመጀመሪያ የሚነሳው ጥያቄ የሕገ-መንግሥቱ 
አንቀጽ 31 ላይ እንደተደነገገው “ማንኛውም ሰው 
ለማንኛውም ዓለማ በማህበር የመደራጀት መብት 
አለው” የሚለውን መብት ሽብርተኛ ያሰኛል ወይ? ይህ 
የተማሪዎቹ ማህበር በኦነግ የሚታዘዝ መሆኑ ምን 
ማስረጃ አለ? ተማሪዎቹ ድንጋይ እንዳይወረወር፣ 
በዘርና በጐሳ ዜጐችን መከፋፈል እንዲቀር ብለው 
ያስቀመጡት ዓላማ የሽብርተኝነትን እንቅስቃሴ 
ያደርገዋል ወይ የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡ በአንቀጽ 
29 ጋር በተያያዘ ግን በፌስ ቡክ ሃሳብን ከሌሎች ጋር 
መለዋወጥ ሽብርተኛ ያሰኛል ወይ የሚለው ጥያቄ 
በአንክሮ መነሳት አለበት፡፡
እነዚህ 21 የዩኒቨርስቲ የኦሮሞ ተማሪዎች የዓለም 
አቀፍ የኦሮሞ ተማሪዎች ማህበር አባል በመሆናቸው 
ሽብርተኞች ተብለው ከተወነጀሉ ኢሕአዴግ ራሱ 
“የሶሻሊስት ኢንተርናሽናል” አባል አይደለም ወይ; 
በዚህም ከቻይና ኮሚንስት ፓርቲና ከተለያዩ ሶሻሊስት 
አገራት ጋር ባለው ግንኙነት መሠረት የሚያገኛቸው 
ጥቅማጥቅሞችና የሞራል ድጋፎች ምን ያህል 
እንደሆኑ የሚያውቀው ራሱ ነው፡፡
ሦስተኛው ምሳሌ በቅርቡ ኢህአዴግ ለVOA በላከው 
ባለ 42 ገጽ ጽሑፍ ውስጥ 34 ኢትዮጵያውያን በVOA 
ፕሮግራሞች እንዳይስተናገዱ መጠየቁ ነው፡፡ ይህም 
በአንቀጽ 29 ላይ የተከበሩትን መብቶች “ማንኛውም 
ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ 
ነፃነት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር 
ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም 
በህትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው 
በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት 
መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት 
ነፃነቶችን ያካትታል” የሚለው የሕገ መንግሥቱ 
ድንጋጌ መጣሱን ያሳያል፡፡
ከዚህም በመነሳት አባላትና ዜጐች ከላይ 
የተጠቀሱትን የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎች በትክክል 
በማወቅ ሁኔታዎችን በመከታተል ሕገ-መንግሥቱን 
የማስከበርና ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ እንዲሆኑ 
ማሳሰብ እወዳለሁ
Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close