“እስክንድር ቢታሰር ሺህ እስክንድሮች ይፈጠራሉ- የእስክድንር ባለቤት ሰርካለም ፋሲል (ግርማ ካሣ)

የአንጋፋዉ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል ፣ በባለቤቷ መታሰር ዙርያ በፓልቶክ ከተሰባሰቡ ኢትዮጵያዉያን ጋር፣ አጭር ቃለ ምልልስ አድርጋለች። ወ/ሮ ሰርካለም ዳግመኛ ወደ እሥር ቤት ከተወሰደዉ ባለቤቷ፣ እስክንድር ነጋ ጋር፣ ከስድስት አመታት በፊት ለሃያ ወራት በቃሊቲ እሥር ቤት ታስራ የነበረ ሲሆን፣ አንድና የመጀመሪያ ልጇን ፣ ናፍቆት እስክንድርን የወለደችዉ በዚያዉ በቃሊት እሥር ቤት ነበር።

“እስክንድር በመታሰሩ ምን ተሰማሽ ? ፈራሽ ወይ ?” የሚል ጥያቄ ነበር መጀመሪያ የቀረበላት። “ፍርሃት አልተሰማኝም። ብንፈራ ኖሮ አገር ዉስጥ አንቀመጥም ነበር። እንደማንኛዉም ጓደኞቻችን፣ ከእሥር እንደተፈቱት፣ ስደትን መርጠን መኖር እንችላለን። ወይንም ደግሞ ሌላ የማያነካካን ሥራ መስራት እንችላለን” ስትል ፣ እርሷም ሆነ ባለቤቷ እስክንድር፣ የፍርሃት እስረኞች እንዳልሆኑ፣ ለሚያምኑበት ነገር የቆሙ ፣ እንደ ባርያ ወይንም እንደ እንስሳ በመንፈስ ያልታሰሩ፣ ነገር ግን ቀና ብለዉ እንደ ሰዉ የሚሄዱ እንደሆኑ ነበር የገለጸችዉ።

ፍርሃትና መረበሽ ባይታይባትም ትልቅ ሐዘን በዉስጧ እንደተሰማት ግን ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል ሳትጠቁም አላለፈችም።

“እኔ ሐዘን ነዉ የተሰማኝ። እስክንድር በመታሰሩ ሳይሆን እርሱን ሲወስዱት፣ ልጃችንን መጀመሪያ ሰጥተዉኝ፣ ከአባቱ አርቄዉ፣ በአባቱ ላይ ያደረጉትን ቢያደርጉ ደስ ይለኝ ነበር። ጨንቆት ፣ እያለቀሰ፣ አባቱን እየቀረጹ፣ አባቱ እጅ ላይ ካቴና ሲያስገቡበት፣ የሚሆነዉን አጥቶ ሶጮህ በቃ ዉስጤ አዘነ። ሃዘኔ በሕጻኑ ነዉ። ሕጻኑ ነዉ ያሳዘነኝ” ስትል፣ የእስክንድር መታሰር በልጃቸዉ በናፍቆት እስክንድር ላይ ያሳደረዉን ትልቅ የስነ-ልቦና ችግር ገልጻለች።

“እስክንድር ያመነበትን፣ የሚያምንበትን ነዉ የሰራዉ። ሌላ አይደለም። በኢትዮጵያ ዉስጥ ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ነዉ ሲሰራ የነበረዉ። አንድ ቀን አንድ ችግር እንዲሚያጋጥመዉ እያወቀ አምኖበት የገባበት ነዉ። “ ስትል የባለቤቷን የመንፈስ ቁርጠኝነትም አብራርታለች።

“ናፍቆት እስክንድር ያኔም በቃሊቲ ሲወለድ ችግር አጋጥሞት አልነበረምን? “ ለሚለዉ ጥያቄ ወ/ት ሰርካለም “ያኔና ዛሬ ይለያያል። ያኔ ምንም አያውቅም ነበር። ቤት ይወለድ፣ መንገድ ይወለድ፣ እሥር ቤት ይወለድ አያውቅም። ያኔ እኔ ነዉ የተሰቃየሁት። አሁን ግን ነፍስ ያወቃል። ይለያል። የሚጮኸዉ፣ እየዘለለ የሚያብደዉ ነፍስ ስላወቀ ነዉ። እቤት ገብቶ እስኪተኛ ድረስ “ፖሊሶች አባባን ወሰዱት ! ለምን ወሰዱት ? በአንበሳ ባስበላቸዉ ….በዉሻ ባስበላቸዉ …እያለ በሕጻን አንደበቱ ሲናገር ነበር። ያ ወቅት ለኔ ነበር ችግሩ። እኔ ነኝ የተሰቃየሁት። አሁን ግን ልጃችን ነፍስ ባወቀበት ሰዓት ላይ፣ በፊት መጥፎ ትርኢት ተከናወነ። ጭራሽም ትምህርት ቤት አልሄድም፤ ነገ አልሄደም እያለኝ ነዉ ያመሸዉ” ስትል ልጇ ያለበትን ሁኔታ ለማሳየት ሞክራለች።

“ባለቤቴ በመታሰሩ አዝኛለሁ። ከእስክንድር ጋር ተነጋግረንበታል። ችግር ሊመጣ እንደሚችል እናውቃለን።ላመነበት ዓላማ ነዉ ዋጋ እየከፈለ ያለዉ። እያንዳንዱን አርቲክል በጻፈ ቁጥር ተሸመቃቄ “እባክህ ተዉ” ልለዉ እችል ነበር። ግን ያመነበት ነዉ። ስለዚህ ሰዉ ባመነበት እስከሞት ድረስ ይሄዳል። እስክንድር ቢሞት ሺህ እስክንድሮች ይፈጠራሉ” ስትል የእስክንድር መታሰር እስክንድር የቆመለትን አላማ የበለጠ የሚያጠናክር እንጂ የሚያሳንስ እንዳልሆነ ወ/ት ሰርካለም በሰጠችው ቃለ ምልልስ ገልጻለች።


Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close