ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኽረስት ተሸለሙ

– ቤተመጻሕፍቱም በስማቸው ተሰየመ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በማስገንባት ላይ ያለውን ቤተመጻሕፍት በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኽረስት ስም እንደሰየመ አስታወቀ፡፡

በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ልዩ ልዩ ጥንታዊ ቅርሶች በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር እንዲመለሱ ላደረጉት አስተዋጽኦም ሽልማት አበረከተላቸው፡፡

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኽረስት የ50 ዓመት የወርቃማ የአገልግሎት ዘመን በራስ መኰንን አዳራሽ ጥቅምት 16 ቀን 2004 ዓ.ም. በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የአክሱም ቅርጽ ያለበትን ሽልማት የሰጡት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ምክትል ፕሬዚዳንትና የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ከተቋሙ በስተግራ ባለው ቦታ ላይ እየተገነባ ያለው ይኸው ቤተመጻሕፍት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይታመናል፡፡

ቤተመጻሕፍቱ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀመር በርካታ ስኮላር ተሳታፊ የሚሆኑበት ሲምፖዚየም እንደሚካሄድ፣ ከተሳታፊዎቹም መካከል አመዛኞቹ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኽረስት የቀድሞ ተቋማት እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፐንከርሰት በኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪነትና በመምህርነት ከማገልገላቸውም በላይ የተቋሙና የተቋሙ ወዳጆች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት (ጆርናል) መሥራች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ተቋሙን በዳይሬክተርነት ማኅበሩን ደግሞ በሊቀመንበርነት በመምራት እጅግ ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ሽልማቱን ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ፕሮፌሰር ፓንክኽረስት የኢትዮጵያ ጥናቶችን በማደራጀትና በመምራት ዩኒቨርሲቲውንና የአገሪቱን መልካም ገጽታዎች ለዓለም ኅብረተሰብ በማስተዋወቅ ረገድ የጎላ ሚና መጫወታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ፕሮፌሰር ባዬ ይማም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር ሊቀመንበር ፕሮፌሰሩ ለተቋሙና ለማኅበሩ ያበረከቱትን አገልግሎቶች በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ ከዚሁ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው አፄ ቴዎድሮስ በአንገታቸው ላይ ያንጠለጥሉት የነበረው አሸንክታብ (AMULET) ከ100 ዓመት በኋላ በሪቻርድ ፓንክኸረስት ቆራጥ ተጋድሎ ወደ አገሩ ተመልሶ በእጃቸው በዳሰሱት ጊዜ የአፄ ቴዎድሮስን አካል እንደነካኩ አደርገው መቆጠራቸውን አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ፣ ሪቻርድ ፓንክኸረስት የመቅደላን ቅርሶች ከተወሰደበት ለማስመለስ ያካሔዱትን ጥረትና ተነሣሽነት ምንም ኃይል ሊገታው እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

“ዘ ፕሎት ቱ ኪል ግራዚያኒ” በሚል መጽሐፍ የደረሱት ሚስተር ኢያን ካምንቢስ “የአክሱም ሐውልት መመለስና የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች” በሚል ርእስ በስላይድ አስደግፈው ባደረጉት ገለጻ ሪቻርድ ፓንክኸረስት ለኢትዮጵያ ላበረከቱት አስተዋጽአ ከእንግሊዝዋ ንግሥት ኤልሳቤጥ መሸለማቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙና በቅርስነት መጠበቅ የሚገባቸው ጥንታዊ ሕንፃዎችና ቤቶች እንዳይፈርስ የሚያሳስቡ በርካታ ጽሑፎችን በ1991 ዓ.ም. መጨረሻዎቹ ላይ መጻፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

“እንግሊዝ አፄ ቴዎድሮስ የታገሉበትን ዜጎችን ለማስፈታት፣ እንዲሁም ፋሽስት ኢጣሊያ በየተራ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ዘርፈው የወሰዷቸውን ልዩ ልዩ ዓይነት ቅርሶች ፕሮፌሰሩ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ያደረጉት ልዩ ልዩ ዘዴዎች የተሞላበት እንቅስቃሴን በማከናወን ነው፤” ብለዋል፡፡

ከተጠቀሙባቸው ዘዴዎችም መካከል በቅድሚያ ችግሮችን ለይተው በማውጣት፣ ከሕዝቡ ጋር በመወያየትና በመተማመን፣ ለኅብረተሰቡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካይነት የግንዛቤ ማስጨበጪያ ትምህርት በመስጠት፣ ሕዝቡንና ደጋፊዎቻቸውን በማንቀሳቀስ፣ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራም በማካሔድ፣ የፓርላማውን ድጋፍ በማግኘት የመሳሰሉና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኽረስትም ቤተመጻሕፍቱ በስማቸው እንደሚሰየም ከሰሙና የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከተቀበሉ በኋላ ለተደረገላቸው ነገር ሁሉ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ስም አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምና የተቋሙ ወዳጆች ማኅበር ባዘጋጁት በዚሁ ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የፕሮፌሰሩ አጭር ታሪክ የሚያስረዱ ዝግጅቶች፣ ቪዲዮ ክሊፕ፣ ያሳተሟቸው መጻሕፍትና ጽሑፎች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይም ተካሂዷል፡፡

በጀርመን ሙኒክ ነዋሪና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር አባል የሆኑት አቶ ግርማ ፍሥሐ በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሆነው የቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ በ1927 ዓ.ም. ሲገነባ የሚያሳዩ ሁለት ፎቶግራፎችን ለተቋሙ ዳይሬክተር አስረክበዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close