ምክር ያልሰማ ንጉስ ፤ አሟሟቱን ሲያረክስ!

ሉሉ ከበደ

ኖቬምበር 5 / 2006 ሳዳም ሁሴን በሞት እንዲቀጣ ሲፈረድበትና ዲሴምበር 30 / 2006 ሲሰቀል  ለስቅላቱ ፍርድ ዋና ወንጀል ሆኖ የቀረበው የክስ ጭብጥ፡ የሚቃወሙት የሺአት ሙስሊሞች በ1982 የመግደል ሙከራ ካደረጉበት በሗላ 148 ቱን ገድሏል ነው። ሚሊዮንም ሰው ይግደሉ፤ አምስት ሰው ይግደሉ፤ የሞት ፍርድ ለመቀበል ሁለትም አስርም በቂ ነው። እንደ አገዳደሉ አይነት። ምርጫ 97 ላይ የኛ ጌታ ንጉስ መለስ ጀግናው ከሁለት መቶ በላይ ግዳይ ጥሏል። ስምንት መቶውን አቁስሏል። ማንም ምንም ያደረገው ነገር አልነበረም በሰላም ለተቃውሞ ሰልፍ ወጣ እንጂ። የሰረቃችሁት ድምጼን መልሱ ብሎ። ይህ ገዳይ ነፍሱ በእስር ላይ መሆንዋን ህሊናው ያለ እረፍት ይነግረዋል:: ይጮህበታል። የፍርዱ ቀን ገና አልታወቀም።

እርግጥ ነው አንባገነኖች እስከቻሉ ድረስ እየገደሉ ስልጣን ላይ ይቆያሉ። በሚሊዮንም በሺዎችም ዜጎች ሊሞቱ ይችላሉ። በመግደል መግዛት የጀመሩ መሪዎች ራሳቸው እስከሚገደሉ ወይም እስከሚያመልጡ መግደልን የሚያቆሙበት ምንም ምክንያት አይኖርም። እኛም ገና እንገደላለን – ኢትዮጵያውያን። መለስም ገና ይገላል -ጀግናው።

ኮሎኔል መንግስቱ እስከ መጨረሻው የስልጣን ዘመኑ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝባችንን ገሏል። የኢራቁ ሳዳም ሁሴን 1979 ወደ ስልጣን ከወጣበት ጊዜ፤ ቲክሪት ጉርጓድ ገብቶ እስከተያዘበት ድረስ ከ 600 ሺህ በላይ ተቃዋሚዎቹን ገድሏል። በካምቦዲያ የከሜልሩሽ አማጽያንን ይመራ የነበረውና ከ 1976-1979 ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ፖል ፖት ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ተቃዋሚዎቹን ገሏል። የሰሜን ኮርያው ኪም ኢል ሱንግ ከ 1948-1987 ከሶስት ሚሊዮን በላይ ተቃዋሚቆቹን ገድሏል። ወደሗላ የሄድን እንደሆነ ደግሞ የቻይናው ማኦ ከ1949-1976 ከአስር ሚሊዮን በላይ ተቃዋሚዎቹን ገድሏል። የጀርመኑ ሂትለር ከ1934-1945 አስራ አምስት ሚሊዮን በላይ ንጹሀን ዜጎችን ገድሏል ። ጆሴፍ እስታሊን ከ1922-1953 ከሀያ ሚሊዮን በላይ ዜጎቹን ገድሏል።

ያሉትንና የነበሩትን አንባገነኖች የግድያ ታሪክ ሁሉ ለመዘርዘር ጊዜውም ገጹም አይበቃምና በዚሁ ምሳሌውን አቁመን ወደ ዋናው ጉዳይ እንመለስ።

የመለስ ዜናዊ አስተዳደግ፤ አነሳስና አሁን ያለበት ደረጃ መድረስ መሰረቱ በሰብእናው ውስጥ ያለው በዓለማችን ያሉት አንባገነኖች የሚጋሩት ልዩ የሆነ ግለሰባዊ ባህሪ ነው። ፍርሀት ፤ ተጠራጣሪነት፤ ጭካኔ ፤ ደባና የፈሩትን በቶሎ የማጥፋት ፍጥነት። ይህን ባህሪ ኮሎኔል መንግሰቱ በቀጥታ ይጋራዋል። እነዚህ ሰዎች መግደል ሲጀምሩ አብረዋቸው ካሉት የትግል ጓዶቻቸው ነው የሚጀምሩት። በውስጣቸው ተደብቆ ያለው በስልጣን የበላይ ሆኖ የመዝለቅ ጉጉትና ፍላጎት እራሳቸውን ላደጋ በማያጋልጥ መልኩ ማናቸውንም እርምጃ እንዲወስዱ ያስገድዳቸዋል። መንግስቱ እነ ተፈሪ ባንቲን እነ ጀነራል አምዶምን እና ሌሎቹንም ይበልጡኛል ወይም ከኔ የበለጠ ድጋፍ ያገኛሉ ብሎ የሚፈራቸውን የጦር አባሎቹን ሲገድል፤ ሳያስቡትና ሳይጠብቁ በድንገትና በፍጥነት ገዳይ ቡድኑን በማሰማራት ነበር ። እናም ያኔ መንግስቱ “ጠላቶቻችን ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረስናቸው” እያለ ባደባባይ ይፎክር ነበር። ልዩነታቸው መለስ ዜናዊ አይተነፍስም። እንዲያውም ገድሎ ያለቅሳል። ለገደላቸውም ሀውልት ያሰራል (ሀየሎም)። እነ እገሌ ገደሉ ብሎ እንደገና ሌላ ሰዎችን ይገላል። የኢትዮሚዲያ ድረገጽ ዋና አዘጋጅ አብርሀ በላይ ምስጋና ይድረሰውና ይህ ብሄራዊ አርበኛ የሆነ ጋዜጠኛ፤ በቅርቡ በተጨባጭ ማስረጃ ይፋ ያደረገው የሀየሎም ግድያ ሴራ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ለትግራይ ህዝብ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ ጥሪ ነው። የትግራይ ህዝብ የራሱን ገዳይ ነው ተሸክሞ ለዚህ ያደረሰው። አሁንም የትግራይ ህዝብ በራሱ ገዳይ  ስልጣን ላይ መቆያ ባላና ካብ እንዲሆን እየተታለለ ነው። በትግሉ ዘመን በህውሀት ውስጥ ሳያስቡት ከሻእቢያ ጋር እያሴረና እየዶለተ የገደላቸውና በህይወት ያመለጡ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ የትግል አጋሮቹ ይቁጠሩለት። እነ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ቋሚ የታሪክ ምስክሮች ሁሉን ነገር መናገር ይችላሉ። ይኸው መሰሪ ሰው ነው እንደግዲህ ይህንኑ መሰሪ ባህሪ ይዞ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የነገሰው። ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በሗላ ኦነግ ነህ ብሎ የፈጀውን ሕዝብ፤ የመላው አማራ ነህ ብሎ የፈጀውን ህዝብ፤ አኙዋክ ሶማሌ ሌላውንም ሁሉ ቤት ይቁጠረው። ተቃዋሚ ብሎ የፈጀውን ወገን ቤት ይቁጠረው።

ያለፉም ሆነ በህይወት ያሉ የዓለማችን አንባገነኖች በተለይም ሀገር በአንድ ሰውና በአንድ ቡድን እስከመጨረሻ መገዛት አለበት ብለው የሚያምኑ፤ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ያሉ ጥንታውያን ሰዎች፤ የሚከፈለው መስዋእትነት ተከፍሎ በቶሎ ከስልጣን ካልተወገዱ ስልጣን ላይ በቆዩ ቁጥር የሚገሉት ህዝብና የሚያጠፉት ጥፋት እየጨመረ፤ እየጨመር፤ አንዴ እጃቸው በደም ከተነከረ ደግሞ ስልጣኑን በምንም መልኩ በፈቃዳቸው ስለማይለቁ ፤ ከለቀቁ ፍርዱን ስለሚያውቁ ፤ ጭካኔው እየባሰባቸው እየባሰባቸው ነው የሚሄደው።

እነርሱ ብቻ በስልጣን ላይ መቆየት እንዳለባቸው ለማሳመን ሲሞክሩ ፤ ከኛ በስተቀር ልማት ማልማት የሚችል ሰው ሊኖር አይችልም ነው የሚሉት። ከኛ በስተቀር ጦር ማዘዝ አገር መጠበቅ የሚችል ሰው አይገኝም ነው የሚሉት። ከኛ በስተቀር ማስተዳደር መምራት የሚችል ሰው የለም ነው የሚሉት ። ሚሊዮኖች በሚኖሩበት አገር ውስጥ ቆመው ነው እነዚህ እብዶች እንዲህ የሚናገሩት ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ፡ ያወቁ፡ የበቁ፡ የተማሩ፡ ዜጎች ያሉበት አገር ውስጥ ቆመው ነው እነዚህ ታማሚዎች ይህን የሚያስቡት፤ የሚለፍፉት። በህይወት ልምድ፤ በስራ ልምድ፤ በትምህርት የበለጸጉ የእድሜ ባለጸጋ ዜጎች የሞሉበት ሀገር ውስጥ ቆመው ነው ይህን የሚናገሩት።

“ ለሐገራችሁ የድርሻችሁን ሰርታችሗል ። እናመሰግናለን ። አሁን ደግሞ ሌላውም ዜጋ የበኩሉን ያድርግ ፤ ተራውን ስጡት። ሀገር የወለደችው እናንተን ብቻ አይደለምና ሌላውም የዜግነት ግዴታውን ይወጣ ተራ ስጡት “ መባሉ አንባገነኖችን እጅግ ነው የሚያስቆጣቸው። ጉዳያቸው ሀገር ማስተዳደሩ ላይ፤ ለሀገር መስራቱ ላይ ሳይሆን፤ ዘረፋውና ስርቆቱ፤ ስልጣን የሚሰጠው ድሎትና ምቾቱ ሙቀቱ ነው። አንባገነንነቱ የሚመጣውም ያን ላለማጣት ከሚጀመር ግብግብ ነው። ስለዚህ አንዴ ለዚያ ከበቁ እየገደሉ መቀጠል ነው ። እየገደሉ መቀጠል እንደጀመሩ ግን ቶሎ ቢቀደሙ ብዙ ህዝብ ከእልቂት ይተርፋል። ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም በመጀመሪያዋ የመግደል ሙከራ ወቅት ቢሞት ኖሮ ያሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት ይተርፍ እንደነበር ዜጎች ይስማማሉ። የጀርመኑ ሂትለር አስራ አምስት ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ጨርሷል ነው የሚባለው ፤ ሰውየው ገና ወደስልጣን መቶ መግደል እንደጀመረ ቢገደል፤ አስራ አምስት ሚሊዮን ህዝብ አይተርፍም ይሆን? መለስ ዜናዊ ከስልጣን ቢወገድ ወይም ደግሞ ቀደም ሲል እሱ ያስገደላቸው የትግል ጓዶቹ ሊገላቸው እንዳቀደ አውቀው ቀድመው ቢገሉት ኖሮ  እስካሁን ያስገደላቸው የገደላቸው ወገኖቻችን ሁሉ አይተርፉ ይሆን?

የሰሜን አፍሪካ አረቦች ቱኒዚያ፤ ግብጾች፤ የመኖች ሌሎቹም አሁን በመነቃነቅ ላይ ያሉት በ አንባገነኖቻቸው ላይ የተነሱባቸው እንደኛ ረሀብና ችግር የለት ተለት ኑሯቸው ሆኖ ተርበው ተጠምተው እርዛትና በሽታ የኑሮ ጉስቁልና አሰቃይቷቸው አይደለም። እርግጥ የብዙዎቹ መነሻ ስራ አጥነቱና እየጀማመራቸው ያለው የኑሮ ውድነት ቢሆንም ከኛ ጋር ካነጻጸርናቸው ሊቢያውያንን ትተን ግብጾችና ቱኒዚያውያን ቢያንስ በቀን ሶስቴ ጠግበው የሚበሉ፤ በማናቸውም የኑሮ መስፈርት ከኛ የተሻለ የሚኖሩ ናቸው። ነገር ግን የተሻለ ህይወት የተሻለ እድገት አለ። ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይኑረንና መሪዎቻችንን እየለዋወጥን ሁሉም የሚችለውን የሚታየውን ጥሩ ነገር ለሀገር እየሰራ የምንደርስበትን የተሻለ ደረጃ እንየው። በሚል ውሳኔ ነው አንባገነኖቻቸውን በቆራጥነት የተጋፈጡት።

ለምሳሌ የሊቢያውያንን የኑሮ ድሎት እንመልከት። ጋዳፊ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ጠላት ነው። እሰየሁ መውደቁ መሞቱ። ወያኔንም ሻእቢያንም ገንዘብና ጠመንጃ እየሰጠ ብዙ ብዙ ረድቷል። መለስ በየአረብ አገሩ እየዞረ የተጠጋውን ሁሉ ለመምሰል መልኩን እንደ እስስት እየለዋወጠ ገንዘብ ይለምን የነበር ዘመን፤ ጋዳፊ እንዲረዳው  የመናዊ ነኝ በዘር ብሎት እንደነበረ ጋዳፊ መናገሩ ተዘግቧል። (እዚህ ላይ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ጋዳፊ አለ የተባለውን የሚናገር ሰነድ በአይኔ አንብቤ  ልጻፍኩም። ሁለትም ሶስትም ሰዎች አንብበናል ብለው ስለነገሩኝ እንደ እውነት ወስጀዋለሁ። ልታረም እችላለሁ ) ያ ብቻም አይደለም ኑሮ ካገር አባሯት ከልጁ ቤት ሞግዚትነት ተቀጥራ የምትኖር ኢትዮጵያዊት እንቦቃቅላ በፈላ ውሀ ቀቅለው ስቃይ አይታ እንድትሞት ህክምናም ከልክለዋት በመሰቃየት ላይ እንዳለች ነው ይህ አደጋ የመጣበት። እሰየሁ ነው። ያችን እንቦቃቅላ ብቻ አይደለም በቁም የቀቀሉት። ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን ነው። የጋዳፊ መንግስት አንባገነንነቱና ዓለም አቀፍ ውንብድናው  እንዳለ ሆኖ ምን ነበር ለዜጎቹ የሚያደርገው

ከብዙ በጥቂቱ፤

1ኛ ፤ነጻ ትምህርት ፍጹም ነጻ ህክምና።

2ኛ፤ ማንኛውም ትዳር መስራች 50 ሺህ ዶላር ለቤት መግዣ ይበረከትለታል።

3ኛ፤ ከሀገሪቱ የነዳጅ ሽያጭ ለእያንዳንዱ ዜጋ በየወሩ ባንክ ይገባለታል።

4ኛ፤ መኪና መግዛት የፈለገ ሰው ከመኪናው ዋጋ 50% በመንግስት ይከፈልለታል።

5ኛ፤ የባንክ ብድር የፈለገ ዜጋ ከወለድ ነጻ ይሰጠዋል።

6ኛ፤ እርሻ ማረስ የፈለገ ዜጋ የርሻ መሬትና ዘመናዊ የርሻ መሳሪያ በነጻ ይሰጠዋል፤ ማናቸውም የማበረታቻ ድጋፍ ይደረግለታል።

7ኛ፤ ለመላ የሀገሪቱ ህዝብ ነዳጅ፤ መብራትና፤ ውሀ ከክፍያ ነጻ ይታደላል።

8ኛ፤ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ስራ ያጣ በትምህርት ደረጃው ሊከፈለው የሚችለውን ልክ፤ ስራ እስከሚያገኝ መንግስት ይከፍለዋል። 83 % ህዝቡ መደበኛ ትምህርት የሚያገኝ ነው።

ሌላም፤ ሌላ… በአፍሪካ ምድር አይደለም፤ ሀብታም ነን በሚሉ ምእራባውያን ሀገሮች ዘንድ ሳይቀር የሚያስቀና ኑሮ፤ ማንም ዜጋ የማያገኘውን ጥቅም እያገኙ የሚኖሩ ሰዎች፤ የአንድ ሰው ዘለዓለማዊ የበላይነት፡ የአንድ ቡድን ወይም ያንድ ቤተሰብ ዘለአለማዊ  ‘’ያገሩ ጌታ እኔ ነኝ’’ ሚሊዮን ሰው  በሚኖርበት አገር አንድ ሰው ተነስቶ “እኔን ስሙ” ብሎ ሲያቅራራ “እሺ… እሺ አቤት ወዴት?” እያሉ በጋራ ሀገር መኖር  አንገፍግፎአቸው ፤ እነሱም በሀገራቸው የአስተዳደር ጉዳይ ላይ ድርሻና አስተዋጾ እንዲኖራቸው ተመኝተው፤ ከዚህም የተሻለ ከዚህም የበለጠ ጥቅም ሊኖረን ይችላል ብለው አምነው ፤ በጋራ ሀገር የጋራ መብትና ስልጣን እንዲኖራቸው አንባገነናቸውን አስወገዱ።

እኛ ለራሳቸው ብልጽግናና ታላቅነት ሲሉ፤ ለራሳቸው ዝርፊያና ሌብነት ሲሉ እንደመዥገር ስልጣን ላይ ተጣብቀው፤ አንደ አልቂት ሕዝብ ትከሻ ላይ ተጣብቀው ደም እየጠቡ መኖር ያያዙትን፤ እየገደሉን እድሜልክ ሊገዙን በመዘጋጀት ላይ ያሉትን የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች  ለምን ከላያችን ላይ ወዲያ ወርውረን ሀገራችንን እንደማንረከብ እንቆቅልሽ እየሆነ ነው።

ሩማኒያን ለሀያ አንድ ዓመታት ሲገዛት የነበረው አንባገን ቻውቸስኮ በ1989 ላይ የሩማንያ ህዝብ ቁጣው ገንፍሎ የተነሳበት ጊዜ፤ ከነሚስቱ እጁን ይዞ ለፍረድ አቅርቦ በሞት ሲያስቀጣው በዛን ወቅት የሩማንያ ህዝብ የተማረረበትና በመሪው ላይ እንዲነሳ ምክንያት የሆነውን ድርጊት በሙሉ መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ ከመጣ ጀምሮ አንድ ባንድ እያደረገው ነው።

በዝርዝር እንመልከት፤-

1.   ቻውቸስኮ በዘር ማጽዳት ወንጀል ተከሷል።

መለስ ዜናዊ አኙዋኮች እንዲጨፈጨፉ በሰጠው ትዛዝ መሰረት ተለይተው በመጨፍጨፋቸው ያኙዋክ ጀስቲስ ድርጅት ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ትግል በማድረግ ላይ ነው። በኢትዮጵያውያን ብርቱ ጥረት አንድቀን ፍትህ እንደሚያገኝ ይጠበቃል። ጄኖሳይድ ዋች የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት መስራችና መሪ ዶክተር ግሬጎሪ ስታተን ባረጋገጡት መሰረት መለስ ዜናዊ ያዘዘው ግድያ፡ ጭፍጨፋ የዘር ማጽዳት ተግባርን መስፈርት ያሟላ ነው።ዲሴምበር 13 / 2003 ላይ ጋምቤላ ውስጥ የወያኔ ወታደሮች በሶስት ቀን ውሰጥ 424 አኙዋኮችን ሲገድሉ፡ በዚያም አላቆሙ ተከታታይ ጥቃቶችን በመሰንዘር ከ1500-2500 የሚደርሱ ወገኖቻችንን ገድለው 50 000 የሚሆኑ አገር ጥለው እንዲሰደዱ አደረጉ። ሰበቡ በመሬትና በክልል ይገባኛል በአኙዋኮችና በሌላ አንድ ብሔረሰብ መካከል የተነሳ አነስተኛ ግጭት ነበር። ወያኔ ጸጥታ አደፈረሳችሁ ብሎ ነው የዘመተባቸው።

2.   ቻውቸስኮ በሚያወጣው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሀገሪቱ በውጭ እዳ እንድትዋጥ አድርጓል። የሩማንያን ህዝብ ቀድሞ ባልነበረ መልኩ ለድህነት ዳርጓል። ረሀብን አስፋፍቷል። የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁልቁል እያወረደ ለስቃይ ዳርጓል። የኤሌትሪክ መብራትና የቤት ማሞቂያ ሳይቀር እጥረት በመከሰቱ ዜጎች በተራ እንዲጠቀሙ ተገደዋል። ብዙዎች በብርድ ተሰቃይተው አንዲሞቱ ሆነዋል። ብሎም ህዝቡ ተነስቶበታል።

ባለፉት ሀያ ዓመታት ወያኔ ሲገዛ የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ ከየት ወደ የት ተጓዘ? የመብራቱን ፈረቃ እንተወው ። ከሀያ ዓመት በፊት ደርግ ሊወድቅ አካባቢ አቶ ተመስገን የተባሉ ዜጋ የወር ደሞዛቸው የተጣራ 500 ብር ነበር። ሁለት ልጆች ነበሯቸው ። አራት ቤተሰብ ይህ ጎደለው የማይባል ኑሮ ይመሩ ነበር። እኒሁ ዜጋ ዛሬ ከሀያ አመት በሗላ ደሞዛቸው የተጣራ 1000 ብር ነው። ከሀያ ዓመት በፊት 20 ሳንቲም ትሸጥ የነበረችው አንድ የቁርስ ዳቦ ዛሬ ባንድ ብር በመሸጥ ላይ ነች። ሶስት እጅ ጨምራ። ከሀያ ዓመት በፊት 10 ብር ይገዙት የነበረው አንድ ኪሎ ስጋ ዛሬ ከሰባ ብር ያነሰ አይሸጥም። ካምስት እጅ በላይ ጨምሮ። ከሀያ ዓመት በፊት ሰባት ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ በርበሬ ዛሬ ከሰባት እጅ በላይ ጨምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል። ለአብነት ያህል ይህን ከጠቀስን የቀረውን ውድነት አንባቢ በራሱ ይሙላው ። የአቶ ተመስገን የወር ደሞዝ አንድ እጅ ጨምሮ በመቆሙ ዛሬ ሁለቱ ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ከቤት ወተው ባሉበት ሁኔታ እናትና አባት ለቤት ኪራይ የምንከፍለው እንዳናጣ ብለው በጣም ባነስተኛ በጀት ቁርስና ምሳ ብቻ እየበሉ እራት የሚባል ነገር ከኑሮአቸው ወቶ ከሀያ ዓመት የመለስ አገዛዝ በሗላ እራት ለትዝታ ብቻ የሚነሳ ሆነ። ያቶ ተመስገን ታሪክ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለበትን ስቃይ ይወክላል። በኢትዮጵያ ታሪክ የመንግስት ሰራተኛ የሆነ ሰው የሆቴል ትርፍራፊ እየገዛ ልጆቹን መመገብ የተገደደበት ጊዜ አይታወቅም። በኢትዮጵያ ታሪክ ሰው ጉርሻ በፍራንክ ገዝቶ ረሀቡን አስታግሶ ለመዋል የተገደደበት ጊዜ አይታወቅም። አሁን እዚህ ደረጃ ላይ እንገኛለን።

3.   ቻውቸስኮ ከሚስቱ ጋር የሀገሪቱን ሀብትና ገንዘብ እየሰረቁ ለግላቸው በውጭ ባንኮች ሸሽገዋል። እጅግ ብዙ ሀብት አሽሽተዋል። ተብለው በህዝቡ ተወንጅለዋል።

በመለስና በሚስቱ የሚመራው የወያኔ የዘረፋ ቡድን እስካሁን 8.4 ቢሊዮን ያሜሪካን ዶላር በውጭ ባንኮች መደበቃቸውን የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በተጨባጭ ማስረጃ ይፋ አድርጓል። በምን ያህል ፍጥነትና ብዛት እንደሆነ ለጊዜው ባይታወቅም ዘረፋው የሚያቋርጥ እንዳልሆነ መጠራጠር አያሻም። ይህ እስካሁን የተሰረቀው ገንዘብ ሁለት ዓመት ሀገሪቱን የሚያስተዳድር ነው። እንዴት ነው ልናስመልሳቸው የምንችለው? መለስ ዜናዊና ጥቂቱ ታማኞቹ ጀንበር ወታ በጠለቀች ቁጥር ሀብታቸው፤ ንብረታቸው በላይ በላይ እየጨመረ ሲታይ፤ መሬት ላይ ያለው ሰፊ ህዝብ አርሶ አደሩ፤ ተራው የመንግስት ሰራተኛ፤ በአነስተኛ የገቢ ምንጭ የሚተዳደረው ነዋሪ፤ ኑሮ ገሀነም እየሆነችበት ነው። ረሀብን የኢትዮጵያ ሰው በሙሉ አሁን እየተረዳት ነው። የሁሉንም ቤት አንኳኳች። በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂቶች ከሀያ ዓመት ወዲህ የተፈጠሩ እጅግ ሀብታም እየሆኑ እንደ አውሮፓውያን ሀብታሞች የተንደላቀቀ ኑሮ በመምራት ላይ ናቸው። እነዚህ ክፍሎች ከገዢው ወገን የሆኑና እነሱን ተለጥፈው፤ እነሱን ተቀብለው፤ ለነሱ አድረው በመጠቀም ላይ ያሉት ናቸው። እነዚህ ሰዎች ጥቅማቸው አይነካ እንጂ ወያኔ በሐገርና በህዝብ ላይ የፈለገውን ቢያደርግ አልሰሙም አላዩም።

ሕዝብ በኑሮው እንዲዘቅጥ ማድረግም አንዱ ያንባናገነኖች ያገዛዝ ስልት መሆኑን መዘንጋት አያሻም። የራበው ህዝብ የለት ጉሮሮውን ሊዘጋ ይሮጣል እንጂ ስልጣን ላይ የተጠናከረን አረመኔ ሰው ሊያወርድ አምርሮ ለመታገል የሚያስችል አቅም ያንሰዋል። ይህንን መለስ ዜናዊ ጠንቅቆ የተረዳ መሰሪ ነው።

4.   ቻውቸስኮ ጠንካራ የስለላና የመረጃ መረብ በመላ ህዝቡ ውስጥ በመዘርጋት አላፈናፍን ብሏል። በተቃዋሚነት የሚጠረጥራቸውን ሁሉ ገሏል:: ወዴት አንደደረሱ በማይታወቅበት ሁኔታ ሰውሯል:: ቁምስቀል አሳይቷል (ቶርች ) ። ሲልም ያኔ ህዝቡ ወንጅሎታል። የሩማኒያ ህዝብ በቁጣ ገንፍሎ ላስር ቀናት ሀገሪቱን በተቃውሞ ካመሳት በሗላ የህዝቡን ማምረር የተረዱት ቻውቸስኮና ሚስቱ ነፍሳቸውን ይዘው ሊያመልጡ በመኪና ተሳፍረው ካገር ሊወጡ ሲሉ እጃቸውን ተይዘው በሚያስገርም ፍጥነት ወታደራዊ ችሎት ተሰይሞ ፤ በጥይት ተደብድበው እንዲሞቱ ተፈረደባቸው።

መለስ ዜናዊ ምናልባትም ከቻውቸስኮ በከፋ መልኩ ከአንድዘር ከተዋቀረ የስለላና የአፈና ሀይል በፖሊሱም በጦር ሰራዊቱም ሳይቀር እየተጠቀመ በህዝብና በተቃዋሚዎች ላይ እያደረሰ ያለውን አደጋ ፤ ግፍና ወንጀል ህዝቡ በለት ተለት እየኖረው ስለሆነ መደጋገም አያስፈልግም። አዲሱ ነገር ለራሱ በሽብር ተወልዶ በሽብር ያደገ፤ ነፍሱ የተሸበረች ሰው፤ ይህ ቅጥረኛ፤ ውድ የኢትዮጵያን ልጆች “አሸባሪ ናችሁ” እያለ ባወጣው የዲያቢሎስ ህግ ፤ “ህግ አለኝና ኑ ልግደላችሁ” ማለቱ ነው።

ይህ ሰው የአስተዳደሩን ብልሀት ከሁለት ጎራ ያስተዳደር ዘዴዎች ያዋቀረ ነው። አንደኛው ከቅኝ ገዢዎች አሰራር የተወሰደ ሲሆን ይህም ከፋፍሎ የመግዛቱ ስልት፤ ሕዝብ በጥቅማጥቅም እንዲለያይ ማድረግ፤ አንዱን የበለጠ አስጠግቶ ሌላውን ማራቅ፤ ያስጠጉትን ወገን የስልጣንም የሀብትም ተጋሪ እንዲሆን ማድረግና ደጋፊ ወገን ማዘጋጀት ሲሆን፤ ሌላው ከቀድሞው የሶሻሊስት ጎራ የተወሰደ የረቀቀ የስለላና የመረጃ መረብ በህዝብ ውስጥ  በሰራዊቱም ሆነ በሚያዛቸው ባለስልጣናት ውስጥ በመዘርጋት ስጋት የሚሆኑትን ግለሰቦች ማፈን ማስገደልና መሰወር ናቸው። ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ለአምስት ቤተሰብ አንድ ሰላይ በመመደብ ህዝቡን በመቆጣጠር ላይ መሆኑ እንዳይዘነጋ። ሌላው ደግሞ ሕዝብን መንግስት ከሚያቀርበው ወሬና ዜና በስተቀር ሌላ እንዳይሰማ ለማድረግ መጣር ነው። ለዚህም ነው የጀርመን ያሜሪካ ድምጽ ሬዲዮኖች እንዲዘጉለት ያለመታከት በመጠየቅ ላይ ያለው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያን ነጻ ፕሬስ ጋዜጦች ያጠፋው፤ ለዚህም ነው የኢትዮጵያን ሳተላይት ቴሌቪዢን የአገሪቱን ገንዘብ እየከሰከሰ ሲያፍን የሚውለው፤ ለዚህም ነው ኢንተርኔት በሀገሪቱ እንዳይስፋፋ ያገደው።

የቀን ጉዳይ ነው። አፍሪካውያን አንባገነኖች እያገኙት ያለውን ቅጣት መለስ የማይቀበልበት ምክንያት የለም። ችግሩ በሌሎች እየደረሰ ያለውን በማየት መማር አለመቻሉና እንደጋዳፊ የውሻ ሞት ለመሞት መዘጋጀቱ ነው። ከዚያ በፊት ግን ለውጥ ለማምጣት ብዙ አማራጮችና እድል አለው። ኢትዮጵያ ብዙ ያወቁ የበቁ ሐገር ወዳድ ምሁራን አሏት። ምክራቸውን ከሰማ ሊድን ይችላል። እስካሁን እየተመከረ አልሰማም። ምክንያቱም ብዙ ጦር አለው። ብዙ ሰላይ  አሰማርቷል። ብዙ መሳሪያ አለው። የኢትዮጵያን ህዝብ ረገጦ መግዛት መቀጠል ይቻላል። በሺ ኮማንዶዎች እየታጀበ ይኖር የነበረው ጋዳፊ ሬሳው እንደዚያ መሬት ለመሬት ሲጎተት ወዴት ደረሱ እነዚያ አልሞ ተኳሽ ወታደሮቹ? ውድ ጓደኛው መለስ ቢመልሰው መልካም ነበር።

አይነተኛው ያንባገነኖች ባህሪ አንዳቸው ካንዳቸው ገጠመኝ መማር አለመቻላቸው ነው። ምክርን መስማት አለመቻላቸው ነው።

ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማሪያም ነገሮች ከጁ ወተው በራሳቸው መንገድ መሄድ ሲጀምሩ እያያ፤ ተከታታይ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሽንፈት እየተሸነፈ እያየ፤ ያንን ሁሉ የህዝብ ጥላቻና ወታደራዊ ግፊት አልፎ ስልጣን ላይ የሚቆይ እየመሰለው ሐገሪቱንም ለነዚህ አውሬዎች አሳልፎ ሰቶ፤ ሕዝቡንም ዛሬ ላለበት መከራ ዳርጎ ለነፍሱ እድለኛ ነው እንደጋዳፊ እንደሳዳም አሟሟቱን አላከፋም አመለጠ። ነገር ግን ቀደም ሲል በርካታ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሀገር ወዳድ ምሁራን እንደመከሩት፤ ስልጣኑን ለሀገር ሽማግሌዎች የሽግግር መንግስት ሰጥቶ፤ በሚያውቀው ወታደራዊ ተግባር ትግሉን ቢቀጥል ኖሮ ምናልባትም ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት መልኩ አናያትም ነበር።

የአፍሪካ አንባገነኖች ሁሉ መጀመሪያ ሳዳም ሁሴንን ከገጠመው አወዳደቅ አልተማሩም። የህዝብ ጥላቻና ተቃውሞ ይዳፈናል እንጂ አይጠፋም። የቅርብ ጊዜው የሰሜን አፍሪካ ማዕበል በቱኒዚያ ሲጀምር እነ ሆስኒ ሙባረክ እነጋዳፊ እነመለስ ሌሎቹም ተራቸውን በመጠበቅ ላይ ያሉት አንባገነኖች  እንደዋዛ ቤተመንግስታቸው ተቀምጠው በቴሌቪዢን ማየት ቀጠሉ እንጂ፤ ይህ ከመምጣቱ በፊት እኛ ምን ማድረግ አለብን ብለው አልተጨነቁም። ምክንያቱም ህዝቡ እየረገጡት ይወዳቸዋላ! የሴራሊዮኑ ፕሬዚዳንት ባግቦ ከተነሳባቸው የህዝብ ቁጣ ዞር ብለው ባሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች እያስተማሩ በክብር እንዲኖሩ አሜሪካ ጠርታቸው ነበር። አልሰሙም። እውነት ህዝብ የጠላቸው አልመሰላቸውማ! ወይም አሸንፈው በስልጣን ላይ የሚቀጥሉ መሰላቸው ። ማእበሉ ግብጽ መጣ:: ሙባረክም እድለኛ ነው። አሟሟቱ አልረከሰም። በሰላም  ወህኒ ማረፊያ ወረደ። ቢሞትም ቢያንስ ቢያንስ ጠበቃ ቆሞለት በክብር ይሞታል። ጋዳፊ አሁንም አልተማረም:: መለስ አሁንም አልተማረም። ተራው የጋዳፊ ሆነ። እንደመለስ ዜናዊ ህገመንግስት እሱ የማያከብረውን እናንተ ብቻ አክብሩት የሚለውን መተዳደሪያ መጽሀፍ እያነበበ “ወዮ ለናንተ” ሲል “የገባችሁበት ጉድጓድ ገብቼ ነው አይጦች የማድናችሁ ሲል” ጉርጓድ ቱቦ የራሱ መጨረሻ ሆነና እንደሞተች አይጥ እየተጎተተ ወጣ። ርካሽ ሞት ሞተ። አስክሬኑ መኪና ለመኪና እየተጎተተ ተንገላታ። መለስ አሁንም አልተማረም። እየተመከረም አልሰማም። ወዮ መጨረሻዋ ሰዓት ላይ ይህ ህዝብ ትግስቱ አልቆ፤ እንደ ጎርፍ ፈንቅሎ የወጣ ቀን። መትረየስና መድፉ ጋር የተፋጠጠ ቀን፤ ቢገሉትም አያልቅ፤ የሞተው ሞቶ የተረፈው ቤተ መንግት የገባ ቀን ወዴት ይሆን የእባቡ ማምለጫ?…ወዮ መጨረሻዋ ሰዓት ላይ !…መለስ !

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close