አንድነት የፀረ-ሽብርተኝነት ፅንሰ-ኀሳብን በፕሮግራሙ ውስጥ አካተተ

 የፕሮግራምና የመተዳደሪያ ደንብ ለውጥ አድርጓል

በዘሪሁን ሙሉጌታ

የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) የፀረ-ሽብርተኝነት ፅንሰ-ኀሳብን በፓርቲው ፕሮግራም ውስጥ ማካተቱን አስታወቀ። ፓርቲው ሰሞኑን ባካሄደው የብሔራዊ ም/ቤት ስብሰባ ላይ በፓርቲው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ላይ ለውጥ አድርጓል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ አስራት ጣሴ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ፓርቲው ሽብርተኝነትን በተመለከተ በፕሮግራሙ ማካተት የፈለገው ፓርቲው ሽብርተኝነት በቃል ብቻ ከማውገዝ ባለፈ በፕሮግራም ቀርፀን አጥብቀን የምንታገለው መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል።

ሽብርተኝነት በማንኛውም መልኩ ዓላማውንና የሚያደርሰውን ጉዳት በመገንዘብ ብንታገለውም በጥንቃቄ መታየት ያለበት ግን በሸብርተኝነት ስም የዴሞክራሲ መብቶችን ለመጨፍለቅ የሚጣጣሩ አምባገነኖችንም አምርረን እንደምንታገል የገለፅንበት ነው ሲሉ አቶ አስራት ገልፀዋል።

ሌላው ፓርቲው በፕሮግራሙ ያካተተው አዲስ ነገር የመሬት ወረራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ አስራት፤ በውጪ ሀገር ዜጎች በሰፊው እየተካሄደ ያለውን የመሬት ወረራ የምንቃወምበት ነው ብለዋል። ይህ ማለት ግን ፓርቲው ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ የእርሻ ኢንቨስትመንትን እየተቃወመ አይደለም ብለዋል።

“መሬት አሰጣጡ ሀገርን፣ ሕዝብንና በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችን በማይጎዳና ግልፅነት በተሞላበት አሰራር እንዲሰጥና ቅድሚያም ለኢትዮጵያውያን ባለሐብቶች እንዲሆን እንፈልጋለን። ኢንቨስትመንቱም የኢትዮጵያውያንን የምግብ ዋስትና በሚያረጋግጥ መልኩ መሰጠት አለበት። በኢንቨስትመንቱ ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች መብትና የስራ አያያዝ ሁኔታ በጥንቃቄ መያዝ እና የአካባቢ መራቆት በማያስከትል ሁኔታ መፈፀም ይኖርበታል” ሲሉ አቶ አስራት አስረድተዋል።

በተጨማሪም ፓርቲው ሰሞኑን የወጣውን የሊዝ አዋጅ በፕሮግራሙ ማካተቱንም አቶ አስራት ሳይገልፁ አላለፉም። አዋጁ የግል ይዞታን የሚነካና “በሕገ-መንግስቱ የተቀመጡ መብቶችን የሚጥስ መሆኑን በመገንዘብ በፕሮግራሙ እንዲካተት መደረጉን ገልፀዋል። አዋጁ ሕዝብ ያልመከረበት፣ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አስራት በሕገ-መንግስቱ ማንም ሰው የግል ሐብት የማፍራት መብት ለዜጎች ሰጥቷል። የሐብት ማፍሪያ አንዱ ምንጭ መሬት ሆኖ ሳለ፤ አዋጁ በቀጥታ የዜጎችን መብት የነካ በመሆኑ በፕሮግራሙ አካቶ ለመታገል ወስኗል” ብለዋል።

የመተዳደሪያ ደንብን በተመለከተ አዳዲስ ለውጦች መካሄዳቸውን ከአቶ አስራት መግለጫ መረዳት ተችሏል። በዚህም መሠረት ፓርቲው ቀደም ሲል የነበሩት 60 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላትን ቁጥርን ከ50 እንዳይበልጡ አድርጓል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገውን ውህደት እና ሌሎች ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የፓርቲውን የሥራ አስፈፃሚ ቁጥርን ከ18 ወደ 12ዝቅ እንዲሉ አድርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ የስልጣን መዋቅር በማዘጋጀት ከዚህ ቀደም አራት ምክትል ሊቀመንበር የሆነው አካሄድ በአንድ ሊቀመንበርና በምክትል ሊቀመንበር እንዲወሰን አድርጓል።

በፓርቲ አደረጃጀትም ላይ የተወሰኑ ለውጦች በማድረግ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጉዳይ የኃላፊነት ደረጃዎችን እንደ አዲስ መቋቋሙንም አቶ አስራት አስረድተዋል። ቀደም ሲል የፓርቲው ሊቀመንበር በብሔራዊ ምክር ቤት የመመረጡን አካሄድ በመለወጥ በጠቅላላ ጉባኤው እንዲመረጥ ይደረጋል ብለዋል። በቀጣይ ህዳር 30 እና ታህሳስ 1ቀን 2004 ዓ.ም ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚጠራ ያስታወቁት አቶ አስራት በጠቅላላ ጉባኤውም ከአዲስ አመራር መረጣ በተጨማሪ መድረክን ወደ ግንባር ለማሳደግና ከብርሃን ለአንድነት ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጋር በሚደረገው ውህደት ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ብለዋል።

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close