የነ አንዱዓለም አራጌ የሽብርተኛነት ክስ ሙሉ ቃል (17 ገፅ)

እነ አንዱዓለም አራጌ በሽብርተኛነት ተከሰሱ (የአቃቤ ህጉን 17 ገፅ የክስ ቻርጅ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

 ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ጋዜጠኛ ዐብይ ተክለማሪያም፣ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ፣ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም አበበ ገላው በክሱ ውስጥ ይገኙበታል

 እስረኞች ቶርቸር እንደተፈፀመባቸው ገልጸዋል

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት/ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት አላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 24 ሰዎች በዛሬው ቀን ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ የተሰየመው የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛው ወንጀል ችሎት 8 ተከሳሾች ቀርበው የክስ ቻርጅ የተቀበሉ ሲሆን ከተራ ቁጥር 9-24 ያሉት ተከሳሾች በሌሉበት ክሳቸው ተመስርቶአል፡፡

በቁጥር የፍ/ሚ/ፌ/ማ/መ/ቁ 00180/04 ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. በቀረበው የክሰ ቻርጅ ላይ አቶ አንዱዓለም አራጌ ዋለ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን ገ/ኪዳን፣ አቶ ዮሃንስ ተረፈ ከበደ፣ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ በረደድ፣ አቶ ምትኩ ዳምጠው ውርቁ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፈንታ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው ገላው በአካል ፍርድ ቤት ተገኝተው የክስ ቻርጅን የተቀበሉ ሲሆን የቀሩት በሌሉበት ክሱ ቀርቧል፡፡ በአካል ያልቀረቡ ተከሳሾች በጋዜጣ እንዲጠሩ ዐቃቢ ህግ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

በጋዜጣ እንዲጠሩ የተከሰሱት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቦንገር፣ ውቤ ሮቤ፣ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ አቶ መስፍን አማን፣ አቶ ዘለሌ ፀጋ ስላሴ፣ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም፣ አቶ አበበ በለው፣ አቶ አበበ ገላው፣ አቶ ንአምን ዘለቀ፣ አቶ ኤልያስ ሞላ፣ አቶ ደሳለኝ አራጌ ዋለ፣ ኮ/ሌ አለበል አማረ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽና ጋዜጠኛ ዐብይ ተ/ማሪያም ናቸው፡፡

በችሎቱ ላይ አቤቱታ ያቀረቡት ሁለተኛ ተከሳሽ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል መምህር ናትናኤል መኮንን እንዳሉት “በማዕከላዊ እስር ቤት ግፍ ተፈጽሞብኛል፡፡ ከወንጀል ምርመራ ኋላፊ እስከ ታችኛው ወንጀል መርማሪ ሠራተኛ አንድ ላይ ሆነው ልብሴን ሙሉ በሙሉ አስወልቀው ውሃ እየደፉብኝ ለ23 ቀን ሙሉ አሰቃይተውኛል፡፡ እነሱ የሚፈልጉትን እንድናገር ጠይቀውኝ አልናገርም በማለቴ 7 ቀን ምግብ እንዳልበላ፣ እነሱ የሚሉኝን የማልናገር ከሆነ አትቀመጥም አትተኛም ብለው በቁም እንድሰቃይ አድርገውኛል፡፡ እጄን ወደ ኋላ አስረው አሰቃይተውኛል፡፡ የፌድራል ሰባአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር እኔ በስቃይ ላይ ባለሁበት ወቅት ሌሎች ክፍሎች ጎብኝተው እኔን በመዝለል በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በበርካታ ዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ግፍ እንዳልተፈፀም ለመሸፈን በመሞከር ትብብር አድርገዋል፡፡ በጊዜ ቀጠሮ በምቀርብበት ፍርድ ቤት አመልክቼ በዛሬው ዕለት የምርመራ ኋላፊው ቀርበው እንዲያስረዱ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ ቀርበው ከማስረዳት ይልቅ በሌላ በኩል እኔን እዚህ ፍርድ ቤት አቅርበውኛል” በማለት ያመለከቱ ሲሆን ፍርድ ቤቱ “ወደ ፊት በክርክሩ ወቅት እንሰማዋለን” በማለት አልፈውታል፡፡

ተከሳሾች ጠበቃ ማቆም የሚችሉና የማይችሉ መሆኑን ጠይቀው አንችልም ላሉት መንግስት እንዲያቆምላቸው አዟል፡፡ ተከሳሾቹ ከጠበቃቸው ጋር ተመካክረው ለህዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም. እንዲቀርብ ቀነ ቀጠሮ በመያዝ የዕለቱ ችሎት ተጠናቋል፡፡

በተያያዘ ዜና በትላንትናው ዕለት የተሰየመው ፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛው ወንጀል ችሎት “በአሸባሪነት” ክስ የተመሰረተባቸው በእኔ ኤልያስ ክፍሌ ክስ የተከሰሱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዘሪሁን ገ/እግዚሐብሔር፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ርዕዩት ዓለሙ እና ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ የዐቃቢ ህግ ምስክሮች ተሰምቷል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ ከ1-6 የቀረቡት ምስክሮች ሰራተኛ፣ ሊስትሮ የሚሠሩና ዕቃ በማዞር በመሸጥ የሚተዳደሩ መሆናቸውን አድራሻቸውን ሲገልፁ ተደምጠዋል፡፡ አንዱ ምስክር መምህር ሲሆን ሦስቱም ምስክሮች ጋዜጠኛ ውብሸትና ርዕዮት ዓለሙ ከኮንፒተር ጹሑፍ አውጥተው ለፖሊስ ሲሰጡ በታዛቢነት ማየታቸውን፣ ወረቀቶቹን በእንግሊዘኛና በአማርኛ የተፃፉ መሆናቸውን እንጂ ይዘታቸውን እንደማያውቁ ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስተር መለስ ዜናዊ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር የማያወላዳ ማስራጃ በያንዳንዱ ተከሳሽ ላይ ይቀርባል ተብሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው የፍርድ ድራማ ሂደት እንደምንረዳው የፍትሕ ተቋማት ተቃዋሚን የማጥቂያ መሳሪያ ከመሆን ያለፈ ጉዳይ አለመሆኑን ነው፡፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በፖለቲካ ልዩነት ተቻችለው የሚኖሩበት ሃገርና ተባብረው ችጋርና ድህነትን ለማስወገድ የሚሠሩበት ሃገር ለመፍጠር ትግሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ለዴሞክራሲና ለነፃነት ለሚደረገው ትግል በሞራል፣ በሃሳብና በገንዘብ ይርዱ፡፡ የያንዳንዳችን ጥርት ለትግሩ የራሱ ድርሻ አለው፡፡

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close